Thursday, March 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ ከነባር አባላት በተጨማሪ ሰላሣ አዳዲስ ወንበሮችን ሊሸጥ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጨረታው የፊታችን ዓርብ እንደሚከፈት ተጠቁሟል

በአሸናፊ እንዳለ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ወንበር ይሸጥ የነበረው ነባር አባላት፣ አባልነታቸውን ትተው ሲወጡ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን 30 አዳዲስ የአባልነት ወንበሮችን ለመሸጥ ጨረታ ማውጣቱ ታወቀ፡፡ ቀደም ብሎ ለአንድ ወንበር እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር ድረስ ዋጋ ይሰጥ ስለነበር፣ የፊታችን ዓርብ ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚከፈተው ጨረታ ላይ  ከፍተኛ ዋጋዎች እንደሚቀርቡ ተገምቷል፡፡

በወንበሮቹ ላይ እየተጫረቱ ያሉት አብዛኛዎቹ ተጫራቾች የቡናና ሰሊጥ ላኪዎች ሲሆኑ፣ እነሱም ከምርት ገበያው በቀጥታ የመግዛት መብት ብቻ ሳይሆን በምርት ገበያው ውስጥ እስከ ቦርድ ሊቀመንበርነት ድረስ መብት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡

ምርት ገበያ ውስጥ 347 ወንበሮች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ወንበር የሚሸጠው ባለቤቱ አባልነቱን ትቶ ሲወጣ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ባለፈው ዓመት አንድ ወንበር ብቻ የተለቀቀ ሲሆን፣ እሱም በሰባት ሚሊዮን ብር ተሸጧል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ምርት ገበያው አሥር ወንበሮችን ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ብቻ በትንንሽ ዋጋዎች ማቅረቡም ይታወቃል፡፡

‹‹አሁን ላይ 30 አዳዲስ ወንበሮችን ለግል ተጫራቾች ያቀረብንበት ምክንያት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ECX ውስጥ የሚሸጡ ምርቶች በዓይነትና በቁጥር እየበዙ ስለሆነ፣ የወንበሮችን ቁጥር ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ፣ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ወንበሮቹ ምርቶችን ቀጥታ ገዝቶ ወደውጭ ለመላክ ወይም ለሌሎች ላኪዎች ተወካይ ሆኖ ለመግዛት መብት እንደሚሰጡ ጠቁመው፣ ለአገር ውስጥ ገበያና ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች ከ ECX የመግዛት ፍላጎትም ከፍ ማለቱን አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና የቡና ምርት ከ ECX ይልቅ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አዲስ በፈጠረው ‹‹የቀጥታ ትስስር›› (Direct Marketing) በኩል መሸጥ መጀመሩ፣ የECXን ተፈላጊነትን በከፊል ቀንሶታል፡፡ በቀጥታ ትስስር ውስጥ የውጭ ገዢዎች ቀጥታ ከኢትዮጵያ የቡና አምራቾች ጋር የሚገበያዩ ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት ወዲህ 65 በመቶ የቡና ኤክስፖርት የተደረገው ከECX ውጪ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹ያንን ለማስተካከል አዳዲስ ዕቅዶችን አውጥተናል፡፡ ቡና ከ ECX  ውጪ ቢላክም እኛ ደግሞ ኮንትራት አስተዳደር (Contract Management) የጥራት ሰርቲፍኬሽን (Quality Certification) እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች እናቀርብላቸዋለን፡፡ ቅመማ ቅመምና ጓያን ጨምሮ አምስት አዳዲስ ምርቶችንም በዚህ ዓመት እንጀምራለን፤›› ሲሉ አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች