በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 14ሚሊዮን ደርሷል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የብሄራዊ ባንክ የክፍያ ስርዓት ክትትልና ልማት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳምጠው እንደተናገሩት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ 3.5 ሚሊየን የነበረው የሞባይል ባምኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 14 ሚሊየን ከፍ ብሏል።
ዘጠኝ ቢሊየን ብር የነበረው የሞባይል ባንኪንክ የገንዘብ ልውውጥ ደግሞ ወደ 326 ቢሊየን ብር ከፍ ማለቱን አብራርተዋል።
ዜጎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የቴክኖሎጂ አማራጮችን ማየታቸውንና የዲጂታል ክፍያን ማመን መጀመራቸው ለቁጥሩ መጨመር አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የዜጎች የዲጂታል ክፍያ አማራጭ ፍላጎት እንዲጨምርና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ጠንካራ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አክለዋል።
በኢኖቬሽናን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ኤክስቴንሽያ ትብብር በተዘጋጀው 18ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ስብሰባ ላይ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራት እየተሳተፉ ነው።