Thursday, May 30, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ሚና

(ክፍል ሁለት)

በበቀለ ፀጋዬ

በአዲሱ መንግሥት ምሥረታ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ትገኛለች፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረው የፖለቲካ ሥራን ይበልጡን ዋነኛ ያደረገውና አገር የማስቀጠል የቀውስ ማኔጅመንት ሒደት በአንፃራዊነቱ አሁን ወደተረጋጋ የመንግሥት አመራር የምንገባ ይመስላል፡፡ ወደዚህ ከገባን ደግሞ የበለጠ ወደ ኢኮኖሚው ግንባታ ማተኮሩ ግዴታ መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን ቆልፎ የያዘው የኑሮ ውድነቱም ሆነ የሥራ አጥ ቁጥር ከፍተኛነትና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነቱ ያደረሰውን ጉዳት መልሶ መገንባትን ጨምሮ፣ የኢኮኖሚ ግንባታው ላይ መረባረቡ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ በዚህ መሠረተ ሐሳብ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባታ ለዚህ ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታና ዕድሉን የበለጠ ለመጠቀም መሻሻል በሚገቡ ጉዳዮች ላይ በክፍል አንድ የተጀመረው ጽሑፍ ሁለተኛው ክፍል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባታው ላይ ኢትዮጵያውያንን በስፋት ስለማሳተፍ

የኢንቨስትመንት አንቀሳቃሽ ኃይሎችን የመለየትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በኢንቨስትመንት በተለይ በአምራች ኢንዲስትሪ ዘርፍ ታሳቢ የተደረጉት አንቀሳቃሾች ይበልጡኑ የግሉ ባለሀብት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀቶችና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንደሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ እንደተጠበቁ ሆነው ዜጎችን በአክሲዮን በማደራጀት ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ሊሠራ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ግንባታ ጥቃቅንና አነስተኛዎችን ወደ መካከለኛና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ማሳደጉ ግብ ቢኖርም፣ ዜጎች በስፋት የመንግሥት ሠራተኞችንም ይጨምራል ልዩ ድጋፍ ተደርጎላቸው በአክሲዮን ቢደራጁና አክሲዮኖች በመንግሥት የቅርብ ክትትልና ዕገዛ ቢስፋፉ፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍሉም ሆነ ለድህነት መቀረፍና ለሥራ ዕድል ማስፋፊያ ትልቅ ጠቀሜታ የሚኖረው ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት በዚህ ረገድ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግና የአክሲዮን ሕጎችን በመፈተሽና በማሻሻል፣ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የኢትዮጵያን ዜጎች በስፋት በኢኮኖሚው ግንባታ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን በበለጠ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡

በተለየ የገንዘብ ድጋፍ ጭምር/ብድር መውሰድ ሊሆን ይችላል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በአክሲዮኖች ግዥ ተሳትፈው በሀብት ክፍፍሉ ባለድርሻ የሚሆኑበትን ሁኔታዎችን መፍጠር ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚለውን ማስፈን ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸውንም ድርሻ ያሉባቸው የንግድ ተቋማትን በቅንነት ለማገልገል የሚያዘጋጃቸውና የሥራ ቅልጥፍናን የሚጨምርም ይሆናል፡፡ አክሲዮኖቹ የተበታተኑ አነስተኛ የሆኑትን የኢትዮጵያን ሀብቶች በአንድነት በማሰባሰብ ትልቅ የገንዘብ አቅም ለመፍጠር ያግዛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በግል ባለሀብቶችና በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ከሚደረጉት ኢንቨስትመንቶች በበለጠ ወደ ትልልቅና አዋጭ ኢንቨስትመንቶች እንዲተኮር ይረዳል፡፡ ይህም የዕድገት ጊዜን ያፋጥናል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በኅብረተሰቡ እንዲካሄድ ያግዛል ማለት ብዙ የኅብረተሰብ አካላት ኢንቨስተሮችና ባለሀብት እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያውያንንም ክብር ይጠብቃል፡፡ የአገር ፍቅርና መውደድንም ያጠናክራል፡፡ ሙስናንም ይቀንሳል፡፡ በሌላ መልኩ በቴክኖሎጂና በማኔጅመንት ማነስ ምክንያት በኢትዮጵያውያን በአምራች ኢንዲስትሪ ተሳትፎ የሚታዩትን ክፍተቶች በዚህ በተደራጀና በባለሙያዎች በሚሠራ መልኩ ተሳትፎ ማድረጉም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለይ የውጭ ባለሀብቶች የሚታሙበት ሌላው ከውጭ በሚገዙ ግብዓቶች ከዋጋ በላይ (Over Invoice) በማድረግ ትርፉን በዚያ መልክ ስለሚወስዱ ፋብሪካዎቹ ኪሳራ በማስመዝገብ ለአገር የሚፈለገውን ጥቅም እየሰጡ አይደለም የሚሉትንም ቅሬታዎች የአገር ዜጎች ያስቀራሉ፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች መንግሥት የአክሲዮኖቹ በጀማሪነት ከባለቤቶቹ አንዱ ሆኖ ድርሻውን ሸጦ የሚወጣበትና ዳግም ሌላ አዲስ አክሲዮን ማቋቋሙ ላይ በሚሳተፍበት መልኩ ድጋፍ እያደረገ ዜጎችን በስፋት በማሳተፍ ኢንቨስትመንቱ ቢስፋፋ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የምናለቅስበት ሁኔታ እንዲቀንስ ይረዳል፡፡ በዚህ መሠረተ ሐሳብ ትልልቅ አክሲዮኖችን በአገር ውስጥ የሚኖሩና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ቢያተኩሩባቸው ይመረጣሉ፡፡ ለአገርም ትልቅ ጠቀሜታ ይሰጣሉ ተብሎ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የቀረቡት የፕሮጀክት አቅጣጫ የሚያመላክቱ ጥቅል ሐሳቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

አንፃራዊ ጠቀሜታ ያላቸውና ሊተኮርባቸው የሚገቡ የፕሮጀክት ሐሳቦች

በዚህ በየግሉናመንግሥት የጋራ ጥምረት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች በሌሎች ከሚሠሩት ለየት የሚሉና ስትራቴጂያዊ ሆነው ለሌሎች በርካታ ኢንዱስትሪዎች የወደፊትና ወደኋላ ትስስር መሠረት የሆኑ፣ ብዙ የሰው ኃይል ለመቅጠር የሚያስችሉ፣ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን በብዛት የሚጠቀሙና ጉልህ የውጭ ምንዛሪ የሚያድኑ ወይም የሚያመጡ፣ ለአንፃራዊ ጠቀሜታ በተለየ የኤሌክትሪክ ኃይል ግብዓታቸው ከፍተኛ ሊሆኑ የሚችሉ ትልልቅ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ የተመሠረቱ ቢሆኑ ይመረጣል በሚል ዕሳቤ ላይ የተመረኮዘ የተመረጡ አምስት የፕሮጀክት ሐሳቦችን ቀጥሎ እናያለን፡፡ እነዚህም አንደ የእንስሳት መኖና አልኮል፣ ሁለተኛ ፐልፕ፣ ወረቀትና የማሸጊያ ዕቃዎች ምርቶች፣ ሦስተኛ ብረትን ከአፈር ለይቶ ማምረት፣ አራተብረት ባልሆኑ ማዕድናት ወይም ኢንኦርጋኒክ ኬሚካል ኢንዱስትሪ በሚባሉትና አምስተኛ በፔትሮ ኬሚካል ላይ የተመሠረቱ ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡

የእንስሳት መኖና አልኮል

ይህን ፕሮጀክት የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሚመራው የግል ድርጅት በአነስተኛ መጠን ለማምረት ጥናት አጥንቶ በኋላ በትልቅ መጠን ቢመረት ይሻላል በሚል እንደገና ከበቆሎ አልኮል ማምረትን ጨምሮ በማጥናት ከዛሬ ሦስት ዓመት ተኩል በፊት ‹‹የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት›› በሚል በኦሮሚያ ለተጀመረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደ አንድ ፕሮጀክት እንዲወሰድ ለክልሉ መንግሥት ጥናቱን በስጦታ አበርክቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ በተፈጠረው የሕግ ማስከበር ምክንያት ፕሮጀክቱ ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

ይህ የመጀመርያው ፕሮጀክት የእንስሳት መኖና አልኮል የቅባት ሰብሎች ላይ ከተመሠረተ የምግብ ዘይት ምርት ከሚገኙ የፋጎሎ ተረፈ ምርትን ከበቆሎ አልኮል /ኢታኖል/ በማምረት የሚቀረውን ወይም ተረፈ ምርትና ከሌሎች ጋር በማዋሀድ ለእንስሳትናዶሮ መኖ ለማዘጋጀት እንዲቻል ነው፡፡ አገራችን እንስሳትን በጥራት ማምረት ያለመቻልና ለወተት እጥረት፣ ለዶሮ ምርትና የዕንቁላል ምርት አለማደግ ማነቆ የሆነው የመኖ እጥረት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም ከበቆሎ አልኮልንማምረቱ ዋና ዓላማ የእንስሳት መኖን ለማምረት ሆኖ፣ በቆሎን እንዳለ ለመኖ መጠቀሙ ለእንስሳት ጤንነትም ተመራጭ ባለመሆኑ አልኮሉን በማምረት ተረፈ ምርቱን ለመኖ ለመጠቀም ነው፡፡ አልኮሉ ደግሞ ከቤንዚን ጋር ተዋህዶ ለተሽከርካሪ ነዳጅ ይውላል፡፡ ካስፈለገም በኬሚካል ኢንዱስትሪ ለተለያዩ የኬሚካል ምርቶች ማምረቻ በጥሬ ዕቃነት ያገለግላል፡፡ ከዚህ በፊት የተጠናው ፕሮጀክት የአገሪቱን የዘይት ፍላጎት አርባ ከመቶ እንደሚሸፍን ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የመኖ ፍላጎትን የማሟላት ረገድ 10 ከመቶ በላይ የሚሸፍን አልነበረም፡፡ ይህ የሚያሳየው የመኖ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በቀላሉ ሊሸፈን የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በዘይት ግብዓቶችና በበቆሎ የእርሻ ምርት ጀምሮ እስከ የከብቶችና የዶሮ ዕርባታና የማሸጊያ ምርቶችን ማምረትንና ማከፋፈልን ጨምሮ የሚኖረው በእሴቱ ሰንሰለት 3.5 ሚሊዮን ላላነሰ ዜጎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ነበር፡፡ በእርግጥ አሁን በቂ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች ለጊዜው በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የምግብ ዘይት ፋብሪካው በፕሮጀክቱ አይኖርም፡፡ የዘይቱን ተረፈ ምርት ከእነዚህ ፋብሪካዎች ለመቀበል ከሌሎቹ ጥሬ ዕቃዎች ጋር በመጠቀም መኖዎቹን ማምረት ላይ የተሞረኮዘ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ የዚህ ዓይነት ሦስት ፕሮጀክቶች ቢተገበሩ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የኢትዮጵያ ዜጎች የሥራ ዕድልን መፍጠር ይቻላል ተብሎ ይገመታል፡፡ በዚህ ዓይነት ፕሮጀክትመንግሥት ተሳትፎ ኖሮት የተለያዩ ክልል ሕዝቦችን በሚያስተሳስር ጭምር በአክሲዮን መልክ ቢኬድበት ለአገራችን ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡

የፐልፕ ወረቀትና የማሸጊያ ዕቃዎች

ፐልፕና ወረቀትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፍጆታ ወደ 4,000 ቶን ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ በዓመት የሚወጣው ከ400 ሚሊዮን  ዶላር በላይ እንደሆነም ይገለጻል፡፡ ፐልፕ የሚባለው ለተለያዩ ወረቀቶች በትምህርት ላይ ለሚገኙ 30 ሚሊዮን ዜጎች ደብተርን ጨምሮ ለመጻፊያና ለኅትመት ወረቀቶች፣ እንዲሁም ለካርቶኖች፣ ፓኬቶች፣ ወዘተ ማሸጊያዎች መነሻ ጥሬ ዕቃ ነው፡፡ ለዚህ ምርት በዋና ግብዓትነት የሚያገለግለው እንጨት፣ ቀርከሃና የስኳር ምርት ተረፈ ምርት የሆነው የሽንኮራ ምጣጭ በተለምዶባጋስ› ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ በስኳር ፋብሪካ ባጋሱ ለኃይል ማመንጫ እንደ ማገዶ ነው እያገለገለ ያለው፡፡ ይህም ከማገዶውም በትርፍነት ይመረታል ይባላል፡፡ እንጨትን በተመለከተ በፍጥነት የሚያድገውና ታዳሽ የሆነው ቀርከሃ በተጨማሪ የባህር ዛፍ ለዚህ በጥሬ ዕቃነት የሚውል ነው፡፡ ለአብነት ደቡብ አፍሪካ በባህር ዛፍ ላይ በተመሠረተ የፐልፕ ምርት ታዋቂ አገር ነች፡፡ ሆኖም ባህር ዛፍና ባጋስ አጭር ጭረት (Fiber) ያላቸው በመሆኑ ከሌሎች የጥድ ዓይነት ዛፎች ጋር መቀላቀል ያስፈልጋል የሚባልም በመሆኑ ለጊዜው ቀርከሃ አሁን ከሁሉ ተመራጭ ነው፡፡ በምርት ሰንሰለቱ የፐልፕና የወረቀት ምርት በርካታ ኬሚካሎችን የሚጠቀም በመሆኑ ለሌሎች የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ስትራቴጅክ ከሆኑት ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፣ ለወደፊት ሰንሰለቱ እያደገ ለሚመጣው የጽሕፈት ወረቀት፣ ለጋዜጦችና የመጻሕፍት ኅትመትና ለማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም ለኤክስፖርት የውጭ ምንዛሪን በማፍራት የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይሆንም፡፡ በፕላስቲኮችና በወረቀት ላይ የተመሠረቱ በተለይ በንፁህ አመራረት ለመድኃኒቶች፣ የምግብና ኮስሞቲክ ምርቶች የሚያገለግሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ማሸጊያዎች በኢትዮጵያ አይመረቱም፡፡ ስለሆነም ለአትክልትና ፍራፍሬ አሽጎ ወደ ውጭ ለመላክ ጭምር ካርቶን ከውጭ አገር ይገባል፡፡ ስለዚህ በአክሲዮን መልክ እነዚህንም ማምረት ቢቻል ለአገር ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ብረትን ከአፈር በመለየት ማምረት

ብረትን በተመለከተ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለግዥ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ ከቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ የብረት ጠቀሜታን በተመለከተ የእሴት ሰንሰለቱ በጣም ሰፊና ረዥም ነው፡፡ ለኮንስትራክሽ ሥራዎች፣ ለባቡርዲዱ፣ ለተሽከርካሪዎችና የማሽኖች ማምረት ጋር ተያይዞ የስፋቱን መጠን ከፍተኛነትን መረዳት ይቻላል፡፡ የብረት አፈሩ በተለያየ የአገራችን ክልሎች የሚገኝ በመሆኑ ይህን ወደ ምርት ማሸጋገር ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው መገመት አያዳግትም፡፡

ኢንኦርጋኒክ ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ብረት ባልሆኑ የማዕድናት ጥሬ ዕቃዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የማዕድናቱም ጥሬ ዕቃዎች የምግብ ጨው፣ የኖራ ድንጋይ፣ ጂብሰም፣ ድኝ፣ ዚንክ፣ ክሮሚየም፣ ፖታሽ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ የተለያዩ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለቆዳ፣ ለፅዳት መጠበቂያ የዲተርጀንት ምርቶች የኬሚካል ምርቶችን፣ የፖታሽና የፎስፌት የአፈር ማዳበሪያዎችንና ለግርግዳና ብረት ቀለሞች መሥሪያ ጥሬ ዕቃዎች የሆኑትን የመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑም ናቸው፡፡ እነዚህን በአገር ውስጥ በሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች የማምረት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ ብረትን ከአፈር በመለየት በዚያው አፈር ውስጥ የቀለም ዋና ጥሬ ዕቃ የሆነው ቲታኒየም ይመረታል፡፡ ከዚህ ከቀረው ተረፈ ምርት ደግሞ ለማዳበሪያና ሌሎች ምርት የሚውል ፎስፌት ይገኛል፡፡

በፔትሮ ኬሚካል ላይ የተመሠረቱ ኢንዱስትሪዎች

በእነዚህ ላይ የተመሠረቱ ፕሮጀክቶች ነዳጆችን ጨምሮ ዩሪያ ማዳበሪያ የመሳሰሉትና የፕላስቲክ፣ የጎማ፣ ጥሬ ዕቃዎች፣ የሞተር ዘይቶችና ቅባቶች፣ የሳሙና ወይም ዲተርጀንት፣ የቀለም ጥሬ ዕቃዎች ማጣበቂያዎችና የውበት መጠበቂያ፣ ወዘተ ምርቶች ጥሬ ዕቃዎች መነሻ የሆኑ መሠረታዊ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ናቸው፡፡ የእነዚህ ግብዓቶች የሚሆኑት ፎሲል ፊዩል (Fossil Fuel) የሚባሉ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ፔትሮሊየምና ድንጋይ፣ ከሰል በኢትዮጵያ መገኘታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ እነዚህ በቴክኖሎጂ አቅምም ሆነ በካፒታል ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልጉ በመሆናቸው ጊዜ ተወስዶ አቅምን አጠናክሮ የሚኬድበት ቢሆንም ከአሁኑ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ላይ የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ሲል በውጭ አማካሪዎች የመጀመርያ ደረጃ ጥናት አስጠንቷል፡፡ ይህንኑ ኢትዮጵያውያን አማካሪዎችን ባሳተፈ መልኩ ዝርዝር ጥናቶች ተካሂደው ቅደም ተከተልም ተዘጋጅቶ ቢሠራበት የሚለውን ሐሳብ ለማንሸራሸር ነው፡፡ የኬሚካሎች ማምረቻ ፓርኮችን በየአካባቢዎቹ በጥናት ላይ በመመሥረት በማቋቋም በትልልቅ አክሲዮኖች ወደ ሥራዎቹ መግባትም ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ጽሑፍ የቀረቡትንም ሆነ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የአገራችን ሕዝብ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ትልልቅ አክሲዮኖችን በማቋቋም የውጭ ምንዛሪውን እጥረት በውጭ በሚኖሩት ወገኖች እንዲሸፈን በማድረግ በመንግሥትም ልዩ ትኩረት፣ ክትትልና ዕገዛ የተሳኩ ሥራዎችን መሥራት ቢቻል ለአገር ትልቅ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩትም ሥራቸውን ትተው በመምጣት በግል ፕሮጀክቶችን እዚህ ለመተግበር የነበረውን ችግር በዚህ መልኩ ገንዘባቸውን ብቻ በመላክ አክሲዮኖችን በመግዛትና አገርን በመጥቀም የመንፈስ ዕርካታ ያገኛሉ፡፡ ለራሳቸውም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሐሴ አጋማሽ 2013 ዓ.ም. የአሜሪካ ቆይታ ባደረገበት ወቅት በአሜሪካ በተወሰኑ ግዛቶች ከሚኖሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ ጋር ጉዳዩን አስመልክቶ ላደረገው ውይይት የሚሰጠው ግብረ መልስም በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ አደረጃጀቱና ሕጋዊነቱ አስተማማኝ ከሆነ በአክሲዮን በሚቋቋሙት ፕሮጀክቶች ለመሳተፍ ፈቃደኛ እንደሚሆኑና ሐሳቡም የተቀደሰ ስለመሆኑ ነው ሲገልጹ የነበረው፡፡ ስለሆነም ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀሱ ጊዜ የሚሰጠው አይሆንም፡፡ በእርግጥ ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ከአክሲዮን ሕግ መፈተሽ ጀምሮ የፕሮጀክቶቹን ዝርዝር ጥናቶችን የሚመለከቱና ተቆጣጣሪ አካል እስከ ማቋቋም ድረስ ያሉት ሥራዎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በመተግበር ረገድ የመንግሥትን ትልቅ ትኩረትን ይጠይቃል፡፡

ጠንካራ የመንግሥት ትኩረትና የማስተባበር ኃላፊነት ካለ እነዚህን ፕሮጀክቶች መተግበር ይቻላል፡፡ በዓለም ዙሪያ በውጭ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ 100,000 ሰዎች የ2,000 ዶላር የሚያወጣ ባለድርሻ በየዓመቱ ቢገዙ $200 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ማግኘት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህ በውጭ ምንዛሪ ለሚገዙ ፕሮጀክት ማሽኖች ይውላል ማለት ነው፡፡ ለአገር ውስጥ የፕሮጀክት ወጪ ይህን ያህል መጠን በብር ሌሎች ኢትዮጵያኖች በአገር ውስጥ ሼሩን ሊገዙ ይችላሉ፡፡ ይህ መጠን ለአምስቱም ዓይነት ፕሮጀክቶች በየዓመቱ ሼሩ ቢገዛ በአምስት ዓመት ሁሉንም ፕሮጀክቶች ለመተግበር በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የሚቻል ነው፡፡ ተግባራዊነቱ ግን በሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ አገርን ለመርዳት ከፍተኛ መነሳሳት ያላቸው በመሆኑ፣ በዚህ አገራቸውን ጠቅመው ራሳቸውን የሚጠቅሙበትን ዕድል ማመቻቸት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ፔትሮ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ የህዳሴ ግድብ ሥራ ሲጠናቀቅ ሙሉ ኃይሉን በማሳተፍ መተግበር ቢቻል ለአገራችን ህልውና ማረጋገጥም ሆነ በአፍሪካ በኢንዱስትሪ የመሪነት ሚናን በመጫወት፣ እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እየሰጡን የሚገኘውን የኢትዮጵያን የአፍሪካ እናትነትን በአስተማማኝ ማረጋገጥ ያስችላል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ድጋፍ ሰጪ የሆኑትን ኢንስቲትዩቶችን ስለማጠናከር

ሌላው ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑት የንዑስ ዘርፍ ተቋማት ተግባር ነው፡፡ እነዚህ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳ፣ የኬሚካል፣ የምግብ፣ የመጠጥና ፋርማሲዩቲካል፣ ወዘተ የሚባሉ ተቋማት ናቸው፡፡ ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ስለማከናወናቸው የመገምገሚያ መድረክም እምብዛም አይታይም፡፡ በሁሉም ተቋማት ላይ ያሉትን ሁኔታዎች ለመገምገም ጥናት የሚሻ በመሆኑ ሁሉንም በአንድነት መፈረጅ ባይቻልም አንዳንዶች የራሳቸውን ቡድን በመፍጠር ተቋሙን እንደ የግል ኩባንያቸው የሚያሽከረክሩ ሥልጣኑን በርስትነት የያዙ የእከሌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ናቸው ተብለው የሚቀለዱባቸው  አሉ፡፡ ተጠሪ ለሆኑትም ፋብሪካዎች አገልግሎት በመስጠት የፋብሪካዎቹን ችግሮች ከመፍታት ይልቅ፣ የችግሩ አካል የሆኑ የመንግሥት የተቋም መሪ ሹመኞች መኖራቸውም ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ እነዚህ ችግሮች መኖራቸው እየታወቀ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት የለውጥ መንግሥቱ ያለበትን ውስጣዊና ውጫያዊ የፖለቲካ ችግሮችን ከግንዛቤ በመውሰድ በመንግሥት ላይ ሌላ ተጨማሪ ጫና ላለመፍጠር ሁኔታዎች ተዳፍነው እንዲቆዩ ተደርጓል የሚል እምነት አለ፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ወደ ኢኮኖሚው ግንባታ ለመግባት እነዚህን የመሳሰሉትን መሰናክሎች መፍታት የግድ ይሆናል፡፡ ተቋማቱም  የአምራች ኢንዱስትሪውን ፍላጎት በማድመጥና በመረዳት ጥርስ አበጅተው አምራች ኢንዱስትሪውን በአግባቡ ማገልገል እንዲችሉ ሊደረጉ ይገባል፡፡ እንዲያውም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተወካዮች በአማካሪ ቦርድም ይሁን በአመራር ቦርድ ተሳትፈው የጋራ ሥራ በሀቅነት እንዲሠራ ቢደረግ መልካም ይሆናል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማኅበራትን ስለማጠናከርና የመንግሥት በቅርበት አብሮ የመሥራት አስፈላጊነት

አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚወክሉ የዘርፉ ማኅበራት በሚል የሚታወቁ የተበታተኑ አንዳንዶች ቢሮም የሌላቸው ማኅበራት አሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት ለምሳሌ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳ፣ የኬሚካል ውጤቶች፣ ወዘተ የሚባሉ በአዋጅ ቁጥር 341/95 የተቋቋሙ ማኅበራት ናቸው፡፡ እነዚህን ግን በጋራ የሚያሰባስብ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በሙሉ የሚወክል፣ የአምራች ኢንዱስትሪው የፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን ዓይነት የወል ማኅበር ቢኖር ይመረጥ ነበር፡፡ በዚህ ምትክ በወቅቱ የተደረገው የተወሰኑት ትልልቅ የሚባሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ፣ የጫማና የቆዳ ውጤቶች የስኳር፣ ጣፋጭና ሌሎችም ሦስት የሚሆኑ ማኅበራት በቀጥታ የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት እንዲሆኑ በማድረግና አምራች ኢንዱስትሪዎቹ እንዲከፋፈሉ ነው የተደረገው፡፡ ሌሎቹን ከጥቃቅንና አነስተኛ የዘርፉ ማኅበራት ሊሟላላቸው በሚፈልጉት ዓላማ ከማይገናኙ ጋር በማደባለቅ አገር አቀፍ የኢትዮጵያ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተብሎ የተቋቋመ ሲሆን፣ በተግባር ይህ ማኅበር የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ምክር ቤት ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ሌሎቹ የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበራት በዚህ ተሳትፎ አላደረጉም፡፡ እያደረጉም አይደሉም፡፡ በእርግጥ አዋጅ 341/95 የሚተካ በቅርቡ ተረቅቆ ለውይይት የቀረበው የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይህም ረቂቅ የዚህን ዓይነት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን በጋራ የሚያሰባስብ አደረጃጀትን አያሳይም፡፡ ሁሉንም በንግድና በኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ውስጥ ይከታል፡፡ በረቂቁ ላይ በተደረገውም ውይይት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማኅበራት እንዲሳተፉም አልተደረገም፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ጥያቄ በአብዛኛው ከ80 ከመቶ በላይ ማለት ይቻላል ተመሳሳይ ወይም የጋራ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ሁሉንም አምራች ኢንዱስትሪ የሚወክል አንድ ጠንካራ የጋራ ማኅበር ቢኖር የጋራ የሆኑትን ጉዳዮች በአንድ ማዕከል ለመፍታት ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አሥር ወይም ከዚያ በላይ የዘርፉ ማኅበራት የመንግሥት ኃላፊዎች ሲያነጋግሩ ከሚውሉ የተጠቃለለ አንድ ወጥ ጥያቄን ከአንድ አካል ብቻ ለማግኘት ስለሚያደርግ የመንግሥት ኃላፊዎችንም ጊዜ ይቆጥባል፡፡ ለመንግሥትም የተጠናከረ፣ የተቀናጀ ሐሳቦችንም ለማግኘት ይጠቅማል፡፡ ማኅበራቱም ተበታትነው ተመሳሳይ ሥራ በየማኅበራቸው ሲሠሩ የሚውሉትንና የጉልበት ወይም አቅም ማዳከምን ችግር አስወግዶ ጠንካራ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚወክል ማኅበር እንዲፈጠር ይረዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለእርስ በርስ የኢንዱስትሪዎች ትውውቅና የሥራዎች ትስስርም የበለጠ ይጠቅማል፡፡

የንግድና የዘርፉ ምክር ቤት አለ አይደለም ወይ? ይህ ሥራ ለምን በዚህ አይሠራም የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ግን የአምራች ኢንዱስትሪዎችና የሌሎች የንግድ ተቋማት ጥያቄዎች የሚለያዩባቸው እንዲያውም አንዳንዴ እርስ በርስ ሊቃረኑ የሚችሉ የጥቅም ግጭቶችን የሚያስከትሉ ስለሚኖሩ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማጠናከር ከተፈለገ የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበራት ለብቻቸው ጎልተው የሚወጡበት አደረጃጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ አደረጃጀት የንግድ ምክር ቤቱን አያደክምም ወይ ለሚሉ ወገኖች በግል የአምራች ኢንዱስትሪዎቹ አባል የሆኑት ድርጅቶች በነጋዴነታቸው በተጨማሪ የንግድ ምክር ቤቱ አባልም መሆን ስለሚችሉና ሁለቱም ተደጋግፈው የሚሠሩ ስለሚሆን የሚያመጣው ምንም ጉዳት አይኖርም፡፡ የአምራች ዘርፉ በቴክኒክ ነክ ጉዳዮች ማለትም በምርቶች ጥራት፣ በምርምርና ሥርፀት፣ በየዩንቨርሲቲና በኢንዱስትሪ ትስስር በመሳሰሉትና በሌሎች የኢንዱስትሪ ማናቆዎችን ላይ የሚመሠረት ሆኖ፣ የንግድ ምክር ቤቱ በንግዱ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎች፣ በአካባቢያዊ የቢዝነስ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር በመሳሰሉት ላይ ሊያተኩር የሚችል ይሆናል፡፡ በተለይ የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮችን በአንድነት ማዋሀድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን በጣም ጎድቶት ነበር፡፡ አሁን ይህ ተወግዶ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለብቻ መደራጀቱ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የሚኖረውን ትኩረት ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪውን በተመለከተ እስካሁን ባለው ሒደት የለውጥ ኃይሉ መንግሥታችን ለንዑስ ዘርፉ በቂ ትኩረት አልሰጠም ማለትም ይቻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በቱሪዝም ዙሪያ በተለይ አዲስ አበባን በማስዋብ፣ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ያደረጉትን የማሻሻያ ሥራዎች ዓይነት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ላይ አልሠሩም ማለት ይቻላል፡፡ ከንዑስ ዘርፉ ትልቅነት ጠቀሜታ አንፃር ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች አመዳደብ ጀምሮ በዚህ በሦስቱ ዓመት ዓብይ (ዶ/ር) ለዚህ ዘርፍ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነበር፡፡ በወቅቱ ለፖለቲካው የበለጠ ትኩረት የሚጠይቅ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማወያየትና ለማነጋገር ከሰጡት ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ለባለኢንዱስትሪዎችና ለአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ አልሰጡም፡፡ ወደ መጀመርያ አንድ ጊዜ የንግድ ማኅበረሰቡን ተወካዮች አነጋገሩ፡፡ ከዚያ በኋላ አልተደገመም፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን በያዙ በጥቂት ወራት ነበር የንግዱን ማኅበረሰብ ተወካዮች ያነጋገሩት፡፡ ከዚያ በኋላም በየዓመቱ የመወያያ መድረክ በመፍጠር ከአምራች ኢንዱስትሪው ማኅበራትና ከሌሎች ከንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ይወያዩ ነበር፡፡ ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ሥልጣን በያዙ በዓመታቸው አካባቢ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማጠናከር ትክክለኛ ስያሜውን የዘነጋሁት ግን መንፈሱ፣ ‹‹የአምራቾችን ምርታማነት ማሻሻያ የመወያያ መድረክ›› አቋቁመው ነበር፡፡ በዚያ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤቶች አምራች ዘርፍ ማኅበርን በመወከል የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የስብሰባ አዳራሽ በመስከረም ወር 2006 ዓ.ም. በተካሄደው የመጀመርያ የምክክር ስብሰባ ተከፋይ ነበር፡፡ በዚያ ስብሰባ ከመንግሥት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የፓርቲና የመንግሥት መሪዎች ተሳትፈው ነበር፡፡ ተሳታፊ የነበርን የማኅበራት ተወካዮች ለኢንዱስትሪው ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ሐሳቦችን አንስተን አርኪ ውይይትም ተካሂዶ ነበር፡፡ ይህ ውይይት ግን ሁለተኛ አልተደገመም፡፡ ክቡር አቶ ኃይለማርያም ለወደፊት ምናልባት መጽሐፍ ከጻፉ ስለሁኔታው ሊገልጹልን ይችሉ ይሆናል፡፡ ግን በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ግምት የተንሸራሸሩት ሐሳቦች ወደ ግልጽነትና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የሚወስዱ ስለነበር፣ ሌሎቹ የኢሕአዴግ ፓርቲ መሪዎች በሁኔታው ባለመደሰታቸው ያስቆሙ ይመስላል፡፡ በተለያዩ መድረክ ይህ ጉዳይ ለምን ቆመ ተብሎ በተደጋጋሚ ተጠይቆ ምላሽ ሳይገኝ ነው ተዳፍኖ የቀረው፡፡ ይህን መድረክ እንደገና  ዓብይ (ዶ/ር) ቢያስጀምሩት ለኢንቨስትመንት ዕድገትና ለኢንዱስትሪዎቹ ምርታማነትና ትርፋማነት ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡

የዚህን ዓይነት መድረክ አስፈላጊነትን አንገብጋቢ የሚያደርገው ዋነኛው ምክንያት yማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የንዑስ ዘርፉ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የባለ ኢንዱስትሪውን ወይም የሌሎች የንግዱ ማኅበረሰብ ጥያቄዎች በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻውን የሚፈታ ባለመሆኑም ነው፡፡

የንዑስ ዘርፉ ጥያቄዎቹ የበርካታ መሥሪያ ቤቶችንና ሌሎችንም የሚመለከት ለምሳሌ ገቢዎች ሚኒስቴርን፣ ጉምሩክ ኮሚሽንን፣ ገንዘብ ሚኒስቴርን፣ ብሔራዊ ባንክን፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣንን፣ የመርከብ ድርጅቶችን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ የመድኃኒት፣ የምግብና የጤና ቁጥጥር ባለሥልጣንን፣ የደረጃዎች ኤጀንሲ፣ ወዘተ መሥሪያ ቤቶችን የሚመለከት በመሆኑና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከእነዚህ ሚኒስቴሮች በተመሳሳይ የሥልጣን ዕርከን ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ እነዚህን በበላይነት የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በተገኙበት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የጋራ የውይይት መድረክ ቢፈጠር በርካታ መሰናክሎች ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጉምሩክ ኮሚሽን አማካይነት በአምራች ኢንዱስትሪው የተጋረጡትና የለውጥ መንግሥቱን ቁመናን የማይመጥኑ በዚህ መሥሪያ ቤት እየደረሱ ያሉ ችግሮች የዚህ ዓይነት መድረክ ቢኖር ቀደም ብለው መፍትሔ ባገኙ ነበር፡፡ ይህ መድረክ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥራ አብዛኛውን የሚሸፍኑ ሥራዎች የሚካሄድበት፣ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ከዘርፉ ተዋናዮች፣ የኢንተርፕረነር ተወካዮችና በግልም ከታዋቂ የኢንዱስትሪዎቹ መሪዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኝና የመንግሥት ኃላፊዎችን ፊት ለፊት እነዚህን መሪዎች በቀጥታ የሚያገኙበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን በተሳካ ሁኔታ የሚሠሩበትና ሥልጣናቸውን የሚተገብሩበት ጥሩ ዕድል የሚሰጣቸው ነው፡፡ ሒደቱ በአጠቃላይ ለመልካም አስተዳደር መሻሻልና ለሙስና መከላከል ጭምር ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡

በዚህ ረገድ የሚታዩት ክፍተቶች የፖሊሲ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን፣ በአፈጻጸም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ዕድሎችን አሟጠን ለመጠቀምና እንዲሁም ዘርፉን ለመምራት የሚያስችል የአመራር ወይም የቁጥጥር ሥርዓት ብቃት አለማዳበራችንም በመሆኑ የጋራና የተቀናጀ ሥራ በዚህ መልኩ መሥራት ከተቻለ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነት የጋራ ሥራ የመረጃና የልምድ ልውውጦች ይካሄዳሉ፡፡ በርካታ ለአገር የሚጠቅሙ የግንኙነት (ኔትወርክ) ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ መግባባት፣ መተሳሰብና መተማመን ይፈጠራል፡፡ ክንውኑ የሁሉንም ሞራል ያነሳሳል፡፡ ለበለጠ ዕድገት ያዘጋጃል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው እንግዲህ በእውነት፣ በዕውቀትና በችሎታ ላይ ወደተመሠረተ አሠራር በመግባት ራሳችንን በሁሉም እንድንችል በማድረግ ወደሚታሰበው ታላቅነትም የሚወስደን፡፡ በዚህ ረገድ የሲንጋፑር ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ሚስተር ሊ ክዋንዩ (Lee kuan yew) እና የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዚዳንት ጄኔራል ፓርክ ቱንግ በግንባር ቀደም የልማት ተሳታፊነት አገራቸውን እንደቀየሩት ሁሉ፣  ዓብይም (ዶ/ር) ይህንን ፈለግ ተከትለው ብልፅግናን ለኢትዮጵያ ባጠረ ጊዜ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዕውን እንደሚያስደርጉ በተስፋ እንጠብቃለን፡፡ ለዚህ ብቃቱም ሆነ ዕድሉ አላቸው፡፡

ማጠቃለያ

ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን በሁለት በተከፈሉ ጽሑፎቼ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሲጠናከር የእርሻውም ሆነ የማዕድኑ ክፍለ ኢኮኖሚዎች እንደሚያድጉም ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ከሚፈለገው በላይ ቁጥጥር የሚያበዛ ቢሮክራሲ የንዑሱን ክፍለ ኢኮኖሚ ከማሳደግ ይልቅ ያቀጨጨ መሆኑም ተወስቷል፡፡ በተለይ ሥራ ጀማሪ ወጣቶችን ለማበረታታት የግብር ዕፎይታ ቢደረግላቸው የተሻለ መሆኑም ተብራርቷል፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን በግብርና በታክስ መልክ ብዙ ገንዘብ በሚያስፈልጋት ወቅት ስለግብር መቀነስ እንዴት ይነሳል የሚል ሐሳብ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ሲደረግ የመንግሥት ገቢ የሚቀንስ ሆኖ ከተገኘ እንኳን ሌሎች በሁለት እግራቸው የቆሙ ትልልቅ ድርጅቶች አሁን ከሚከፍሉት ዓመታዊ ግብር ላይ አምስት ከመቶ ተጨማሪ እንዲከፍሉ ቢደረግ ይመረጣል፡፡ በትልልቆቹ ድርጅቶች ላይ ሊፈጥር የሚችለው ጉዳት በዚያን ልክ ለኢንቨስትመንት የሚውለው ገንዘብ መቀነስ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ለእነዚህ ግብሩና ታክሱ የቀነሰላቸው ኢንቨስትመንቱ ስለሚጨምር በአገር ላይ የሚቀንሰው ኢንቨስትመንት አይኖርም፡፡ እንዲያውም የተሻለ የሥራ ሁኔታ ስለሚፈጠርላቸው የትንንሾቹ ሥራ ፈጣሪዎች ገቢ ይጨምራል፡፡ ይህን ተጨማሪ ክፍያ ትልልቆቹ በመፈጸማቸውና የተሻለ ከባቢያዊ የሥራ ሁኔታ በመፈጠሩ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡ ቆጥረው ዕርካታ ሊያገኙ የሚችሉ ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል የሌሎቹ ገቢ መጨመር የመግዛት ኃይል እንዲጨምር ስለሚሆን ከዚህ የትልልቆቹ የሽያጭ ገቢም ይጨምራል፡፡ ይህ ደግሞ በዚያ የቀነሰውን ገቢ ሊተካ ይችላል፡፡ ከዚህ በላይ ጠቀሜታው ድህነትን ለመታደግ ባደረጉት ድጋፍ ከሚኖረው ሰላምና ፀጥታ መከበር ትልልቆቹ ድርጅቶች የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸውም ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ በሚኖረው የተመቻቸ ሁኔታ ማለትም በሚቀንሰው ቢሮክራሲያዊ አሠራር ወይም የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሻሻል ከሚገኘው ጥቅምም ሁሉም ተጋሪ ስለሚሆን የወጣው ተጨማሪ ወጪ በዚህም ሊካካስ ይችላል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በቅርቡ ያደጉት አገሮች የተከተሉት ፖሊሲ ከአገር ወደ አገር የተወሰነ ልዩነት ይኑራቸው እንጂ፣ አብዛኞቹ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ዋንኛ የዕድገታቸው ምንጭ አላደረጉም፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ቀድሞውኑ ጃፓን እንዳደረገችው በመጀመርያው የዕድገት ጊዜያት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን በትንሹ ነው የተጠቀመችው፡፡ ይልቅ የውጭ ሰዎችን ቴክኖሎጂውን በንግድ፣ በቴክኖሎጂ ግልበጣ (ሪቨርስ ኢንጂነሪንግ) በሚባለው፣ በቴክኖሎጂ ፈቃድ ግዢ (ላይሰንሲንግ) ነበር የተጠቀመችው፡፡ በኋላ ግን ሌሎቹን መወዳደር ስትጀምር ቴክኖሎጂውን በቀድሞ መልክ ማስተላለፉን የበለፀጉት አገሮች ሲከላከሉ የራሳቸውን ቴክኖሎጂ በምርምርና ሥርፀት ወደ ማበልፀግ ነው የገባችው፡፡ በእርግጥ መሠረታዊ ቴክኖሎጂዎችን (Cutting Edgi Technologies) ለመጠቀም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተወሰኑ መስኮች ለመሳብ ሞክራለች፡፡ በመንግሥት በተለየ የሚደገፉት ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን በመንከባከብ ነው አሁን ለደረሰችበት ዕድገት ደቡብ ኮሪያ የበቃችው፡፡ የጃፓንም ዕድገት ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ እንደነበር ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቻይናና ህንድም ቢሆኑ ቆይተው ነው ለውጭ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪዎቻቸውን ክፍት ያደረጉት፡፡ በእርግጥ ሲንጋፖርና ሆንግ ኮንግ ከመጀመርያውኑ ነው በራቸውን ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የከፈቱት፡፡ እነዚህ ትንንሽ አገሮች ከመሆናቸውም ወደ ትልቁ የጎረቤታቸው የቻይና መግቢያነት ተገልግለውበታል፡፡ ሌላው በተለይ የሲንጋፑር መሪ የተጫወቱት የተለየ ሚና ሲንጋፖርን ተጠቃሚ ማድረግ ማስቻሉ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ያላደረገችውና ለኢትዮጵያውያን የተከለሉ የኢንቨስትመንት መስኮች ነበሩ፡፡ ይህ ግን በቅርብ ዓመታት እየተሸረሸረ የመጣ ስለሚመስል አሁንም እንደገና ታይቶ ኢትዮጵያኖችን ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የማያስወጣ ፖሊሲ ሊበለፅግ ይገባል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ላይ ያላቸውን መተማመን ለማይሸረሽርና የዜግነት ክብር በማይነካ መልኩ ሆኖ፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብ ከሀብት ባለቤትነት አርቆ ተስፋ ቆራጭና ድንጋይ ወርዋሪ እንዳያደርገን በጥንቃቄ መጓዝ ይመረጣል፡፡ አንዱ ዶላር ይዞ ስለመጣና የዶላር ፍላጎት ስላለን ብቻ ሁለመናችንን በዶላር መሸጥ የለብንም፡፡ በሌላ በኩል የተነሳው ጉዳይ የኢኮኖሚ ትስስርን መሠረት ባደረገ መልኩ ለመጓዝ በዕውቀትና መረጃ ላይ የተመረኮዘ የዝርዝር ፕሮጀክቶች ዕቅድ አስፈላጊነት ነው፡፡ የአገሪቱን ሀብት በቁጠባ በአግባቡ ለመጠቀምም ሆነ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ፕሮጀክቶች ገንዘቡንና ጊዜውን ለማዋል በጥናት ላይ የተመሠረተ በተለይ በባለሙያዎች ተተችተው ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ የአገር መሪዎችም ቢሆኑ የሚታያቸውን ራዕይ ሥልጣን ስላላቸው ብቻ እንዲተገበር ፕሮጀክቶችን በራሳቸው ብቻ የሚወስኑት ሊሆን አይገባም፡፡ እነርሱም ቢሆኑ እንደማንኛውም ዜጋ የፕሮጀክት ሐሳባቸውን አቅርበው፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሐሳብ ለማቅረብ ለሚቋቋም የቴክኒክ ቡድን ወይም ሌላ ለሚመለከታቸው ሐሳባቸውን ገልጸው፣ ተጠንቶና ተተችቶ ሐሳቡ ተቀባይነት ካገኘ የሚተገበር ካልሆነ ግን ሊዘገይ ወይም ሊሰረዝ በሚችል መልኩ መስተናገድ ይኖርበታል፡፡ ይህ ነፍሳቸውን ይማርና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ 10 የስኳር ፋብሪካዎች እንዲቋቋሙ ትዕዛዝ ሰጥተው፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ የህዳሴ ግድቡንም የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራ ለሜቴክ ሰጥተው በጉዳዮቹ ላይ ዝርዝር የአዋጪነት ጥናት ሳይካሄድ ወደ ትግበራው በመገባቱ በአገር ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ ዓብይም (ዶ/ር) ብዙ ሐሳብ ወይም ራዕይ ያላቸው ናቸው፡፡ ግን ሐሳቦቻቸውን ከማስተግበራቸው በፊት እንደ ማንኛውም ዜጋ በሐሳቦቹ ላይ በቂ ክርክርና የአዋጪነት ጥናት መካሄድ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ዓይነት መሪዎቻችንን መከራከር ከስህተትም ማዳን ስለሚሆን በሌሎች፣ በተለይ አብረው በሚሠሩት ሚኒስትሮቻችን ሊለመድ ይገባል፡፡ መሪዎቻችንም እነዚህን ለቀና መንፈስ ሐሳባቸውን የሚሞግቱትን ማድነቅና ማክበር እንጂ እንደተቃዋሚ እንደማያዩት ይታመናል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስቴሮች ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መጠናከርና ማደግ የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ እንጠብቃለን፡፡ በተለይ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን የገቢ ኮታን ለማሟላት ብቻ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ችግር በማባባስ በንዑስ ዘርፉ ላይ ዱላ በማሳረፍ ከማቀጨጭ በመታቀብ ለወደፊቱ ሁለንተናዊ ዕድገት እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ በየንዑስ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ በጡረታ የተገለሉ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን፣ እንዲሁም የሙያ ማኅበራትን ጭምር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማሰባሰብና ዕውቅና ሰጥቶ በማሳተፍ ትልልቅ ሥራዎች ይሠራሉ የሚል እምነት አለው የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ፡፡ ሚኒስቴሩ የዩኒቨርሲቲ – ኢንዱስትሪ ትስስርንም እንዲጠናከር የበኩሉን ሚና በመጫወት በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን ዕውቀት ለኢንዱስትሪዎቹ ዕድገት በማዋል የተሻለ ይሠራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ይህ መንግሥት ሐሳብ ለሚያቀርቡ ወገኖች በሩን ክፍት አድርጎ ሐሳቦች ለጋራ የአገር ልማት ለማዋል መትጋት ይኖርበታል ተብሎም ስለሚገመት የተሻለ ሐሳብ ያላቸው ወገኖች በዚህ ውይይት እንደሚሳተፉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቤካስ ኬሚካልስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤት አምራቾች የዘርፍ ማኅበር ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles