Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትኩረት የሚሻው የተማሪዎች ምገባና የግብዓት አቅርቦት

ትኩረት የሚሻው የተማሪዎች ምገባና የግብዓት አቅርቦት

ቀን:

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍላተ ከተማ ከ400 በላይ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል በሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በግለሰቦችና በትምህርት ቢሮ ትብብር በምግብ ዕጦት ለሚቸገሩ ተማሪዎች የምግብ አቅርቦት ይሰጥ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የምግብ ችግር የአብዛኛው ተማሪው በመሆኑ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የምግብ አቅርቦት ከስምንተኛ ክፍል በታች ላሉ፣ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) እና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶች ደግሞ ለሁሉም ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ በመንግሥት በኩል እንዲሸፈን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ይኼም የብዙ አቅመ ደካማ ወላጆችን ሸክም አቃሏል፡፡ አሁንም እያቃለለ ይገኛል፡፡ ጅምሩ ቀጣይነት ኖሮት እየተተገበረ ቢሆንም፣ የተወሰኑ ጉድለቶች ግን መታየታቸው አልቀረም፡፡

ሪፖርተር በቃሊቲ አፀደ ሕፃናትና የመጀመርያ ደረጃ፣ በመጋቢት 28 እና ተሃድሶ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ቅኝት አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም በቃሊቲ አፀደ ሕፃናትና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ልጃቸውን  የሚያስተምሩት ወ/ሮ ወይንሸት ጌታቸው እንደገለጹት፣ ልጃቸውን እስከ ሰባት ዓመቷ ድረስ ያስተማሯት በግል ትምህርት ቤት ነው፡፡

z

ዘንድሮ ለአካባቢያቸው ቅርብ በሆነው የቃሊቲ አፀደ ሕፃናትና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል አስገብተዋታል፡፡ ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ልጃቸውን በግል ትምህርት ቤት ለማስተማር እንደከበዳቸው ይናገራሉ፡፡ እንደ ወ/ሮ ወይንሸት፣ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ተማሪዎች በምሳ ሰዓት ረዥም ጊዜ ቆመው መጠበቅ አሰልቺ ስለሆነባቸው ቅሬታ ያሰማሉ፡፡

አንዳንድ ወላጆችም የልጆቻቸውን ችግር በመረዳት በትምህርት ቤቱ ከሚቀርበው ምግብ እንግልት እንዲላቀቁ ምግብ ከቤታቸው ተቋጥሮላቸው እንዲሄዱ መደረጉን ወ/ሮ ወይንሸት ገልጸዋል፡፡ 

ዩኒፎርም፣ ደብተር፣ እስኪርቢቶና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን መንግሥት ማቅረቡ መልካም ቢሆንም፣ በትምህርት ቤቱ ላይ አንዳንድ ክፍተቶች መኖራቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሁለት ልጆቻቸውን በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ወ/ሮ ብዙነሽ ደስታ እንደተናገሩት፣ ከዚህ በፊት የግል ትምህርት ቤት ቢያስተምሯቸውም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚደረገው  የክፍያ ጭማሪ ልጆቻቸውን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ለማስገባት አስገድዷቸዋል፡፡

ወ/ሮ ብዙነሽ፣ ልጆቻቸውን ለማስተማርና ለቁም ነገር ለማብቃት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሠሩ፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ልጅን ማስተማር ከባድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለተማሪዎች እያደረገ ያለው ድጋፍ በኑሯቸው ላይ ያለውን ጫና በተወሰነ መልኩ እንደቀረፈ፣ በተለይም የተማሪዎች ደብተር፣ እስክርቢቶና ሌሎች ግብዓቶች ድጋፍ ማድረጉን አወድሰዋል፡፡

በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ብዙነሽ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የመተፋፈግ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ልጆቻቸው ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡

የቃሊቲ አፀደ ሕፃናትና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አንዋር ሀቢብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከ2,700 በላይ ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ በአንድ ክፍል ውስጥም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ተመድበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡

በትምህርት ቤቱም ሆነ በአካባቢው የውኃ እጥረት እንዳለ የሚናገሩት አቶ አንዋር፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም መፍትሔ ለመፍጠር ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርበው መልስ እየተጠባበቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ በፊት የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ የማስተካከልና ለተማሪዎች እንዲያመች አድርጎ የተሠራ መሆኑን በአሁኑ ወቅትም የሙዓለ ሕፃናት ተማሪዎች ዩኒፎርም መዳረሱን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ከተጀመረ ወዲህ ከወላጆች የተለያዩ ቅሬታዎች እየቀረበ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አንዋር፣ የተከሰቱትን ችግሮች ለመቅረፍ ከወላጅ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት መደረጉንና ለችግሩም ዕልባት ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ያልደረሳቸው ሲሆን፣ ይህንንም በተያዘው ሳምንት ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ በተማሪዎች እንዲረከቡ ይደረጋል፡፡

የምገባ ሥርዓቱንም በተመለከተ የመጣ ቅሬታ እንዳለ ይኼም ቅሬታ ለአንድ ምግብ ዋጋ 16 ብር ሲሆን፣ ይህም የማያዋጣ መሆኑን ይህንንም መሠረት በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ 20 ብር እንዲከፈል ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተመለከተ ምን ዓይነት ይዘት ላይ እንዳሉና ምንስ ዓይነት ችግር ገጥሟቸዋል? የሚለውን ለማረጋገጥ ኮሚቴ መዋቀሩን ርዕሰ መምህሩ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የአፀደ ሕፃናት ተማሪዎች የደንብ ልብስ በሚከፍልበት ጊዜ ዩኒፎርሙ ያጠራቸውና የረዘመባቸው እንደነበሩና በዚህ የተነሳ በወላጆች ዘንድ ቅሬታ እንደተነሳ አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በከተማ ለሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እንዲውል 1.9 ቢሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

ሪፖርተር በሦስት ትምህርት ቤቶች ላይ ተዘዋውሮ እንዳየው፣ የምግብ ሥርዓቱ ሆነ ለትምህርት የሚሆኑ ግብዓቶች አሰጣጥ የተሻለ ቢሆንም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገው ርብርብ ግን እንደገና መጤን ያለበትና በመንግሥት በኩልም ክትትልን የሚፈልግ ነው፡፡

ጉዳዩንም በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነትን በስልክ ለማናገር ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...