Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበተማሪዎች ብዛት ምክንያት እያሠለሰ የሚያስተምረው ትምህርት ቤት

በተማሪዎች ብዛት ምክንያት እያሠለሰ የሚያስተምረው ትምህርት ቤት

ቀን:

በወረዳው ያሉ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ቆጣሪ ከሚባለው የመንግሥት ትምህርት ቤት ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት ከምሽቱ 3፡00 ጀምሮ ለምዝገባ ተሠልፈዋል፡፡ ምሽቱ ለማለዳ ፀሐይ ቦታውን ሲለቅ እነሱ እዚያው እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡

የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምዝገባ እስከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም ተከናውኗል፡፡ በአካባቢው የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ብቻ በመሆኑ በተለይም የቅድመ መደበኛ የተመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት ትምህርት ቤቱ መቀበል ከሚችለው በላይ ነበር፡፡ ይህም ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡

አቶ መሐመድ አሊ (ስማቸው ተቀይሯል) የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ለማስገባት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ‹‹የኬጂ ዋን››  ትምህርቱን ሳይማር የቀረው የአቶ መሐመድ ልጅ፣ አሁን ላይ ‹‹ኬጂ ቱ›› በቆጣሪ ትምህርት ቤት በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ እየተማረ ይገኛል፡፡

አቶ መሐመድ እንደሚሉት ሌላ ትምህርት ቤት በወላጆች መዋጮ ይገነባል ተብሎ 1,000 ብር መሰብሰቡ እሳቸውም በማዋጣታቸው የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት የክፍለ ከተማ ቦታ አግኝቶ ያለውን ችግር ይቀርፋል ብለው ጠብቀው ነበር፡፡

ነገር ግን ከጊዜያት በኋላ ትምህርት ቤት ለመገንባት የታሰበበት ቦታ ለሌላ ዓላማ የሚውል በመሆኑ፣ ግንባታው ሊቋረጥ እንደቻለ እንደተነገራቸው አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ገንዘባቸው እንዳልተመለሰ፣ ቆጣሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ለሁለት በመክፈል አዲስ ገቢዎች በሳምንት ሁለቴና ነባሮችን ደግሞ በሳምንት ሦስቴ እያስተማረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በወረዳ 11 ብቸኛው የመንግሥት ትምህርት ቤት ‹‹ቆጣሪ›› ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን፣ በየዓመቱ በወረዳው ከፍተኛ የሕዝብ ፍልሰት በመኖሩ ተማሪዎችም በዚያ መልክ ቁጥራቸው ከፍ እንዳለም ሰምተናል፡፡

የቆጣሪ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወ/ሮ ሀገሬ ታሪኩ እንደሚናገሩት፣ በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቱ ዕቅድ መሠረት ምዝገባ አከናውነዋል፡፡ ነገር ግን በወረዳው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ፍልሰት በመኖሩ፣ የተማሪዎች ቁጥር በየዓመቱ ይጨምራል፡፡

እንደ መንግሥት በወረዳው ያለው ትምህርት ቤት ‹‹ቆጣሪ›› ብቻ በመሆኑ፣ ያለው የሕዝብ ቁጥርና የትምህርት ቤት ቁጥር ሊመጣጠን እንዳልቻለ ርዕሰ መምህሯ ይናገራሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ ባለው አቅም ማኅበረሰቡን ማገልገል የግድ በመሆኑ መያዝ ከሚገባው በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ሀገሬ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አማራጭ ያደረገው ተማሪዎች መመዝገብና ከዚያም ሌላ ትምህርት ቤት ለመገንባት ማቀዱን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ምዝገባው የተከናወነው ለቆጣሪ ትምህርት ቤት ሳይሆን፣ አዲስ ይገነባል ለተባለው ትምህርት ቤት መሆኑን ወ/ሮ ሀገሬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይህንን የተደረገውም ሕዝቡን በማወያየት ለግንባታው 1,000 ብር ወላጆች እንደሚችሉ፣  በመንግሥት በኩል ደግሞ መምህርና የተማሪዎች ቁሳቁሶች እንደሚቻልላቸው በመንገር መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ምዝገባ እንዲያከናውን በተነገረው መሠረት ማከናወኑን የገለጹት ወ/ሮ ሀገሬ፣ ከዚያ በኋላ ወላጆች በነፍስ ወከፍ ያዋጡት 1,000 ብርና ሌሎችም ውስጥ የለሁበትም ብለዋል፡፡

አዲስ የተመዘገቡት ተማሪዎች 926 መሆናቸው፣ ኬጂ ዋን፣ ኬጂ ቱና ኬጂስሪ የተመዘገቡ መሆናቸውን፣ ከምዝገባው በኋላ ክፍለ ከተማውና ወረዳው መሬት መረከባቸውን ሆኖም ቦታው ለሌላ አገለግሎት የተሰጠ በመሆኑ ግንባታው ቀርቷል መባሉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሠረት የተመዘገቡት ሕፃናት ሳይማሩ እንዳይቀሩ በማለት እንደገና ምዝገባ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ አማራጭ የተወሰደው ግማሹ ለሁለት ቀናትና የተቀሩት ደግሞ ለሦስት ቀናት እንዲማሩ ነው፡፡

በቅድመ መደበኛ 1,800 ተማሪዎችን በአንድ ፈረቃ ላይ ለማስተማር ያሉት ክፍሎች አነስተኛ በመሆናቸው፣ ተማሪዎች በሳምንት ሁለቴና ሦስቴ ተከፍለው እየተማሩ እንደሆነ ወ/ሮ ሀገሬ አብራርተዋል፡፡

የነበሩትን ተማሪዎች በሳምንት ሦስት ቀናት እንዲማሩ፣ አዲስ የተመዘገቡትን ደግሞ ሁለት ቀናት እንዲማሩና በየወሩ ደግሞ ፈረቃውን እየቀየሩ አገልግሎቱን ለመስጠት መታሰቡን አብራርተዋል፡፡

ትምህርት ቤት ይገነባል ተብሎ ከ926 የተማሪዎች ወላጆች የተሰበሰበው ብር ጉዳይ የወላጆች ተማሪዎችና መምህር ማኅበር እንደሚመለከተውም ጠቁመዋል፡፡

የቆጣሪ ትምህርት ቤትን ችግር ወረዳው፣ ክፍለ ከተማውና ከተማው ትምህርት ቢሮ እንደሚያውቁ፣ ነገር ግን ወርዶ ችግሩን ያየ አካል እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡

ከሳምንት አምስት ቀን እንዲማሩ ተጨማሪ አሥር የመማርያ ክፍሎችና መምህር፣ ሞግዚት እንደሚያስፈልጉ፣ በአሁኑ ጊዜ በአንድ የመማርያ ክፍል ውስጥ 60 እና ከዚያ በላይ ተማሪዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

በ2005 ዓ.ም. እንደተመሠረተ የሚነገረው የቆጣሪ ትምህርት ቤት ምንም እንኳን ከአቅሙ በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ ቢሆንም፣ በክፍለ ከተማ ሞዴል ትምህርት ቤት መሆኑን ርዕሰ መምህሯ ገልጸዋል፡፡

በቅድመ መደበኛው ትምህርት ቤት 37 መምህራን፣ 11 ሞግዚት፣ አራት ፅዳትና አራት  ጥበቃዎች ያሉት መሆኑን፣ ትምህርት ቤቱ በግብረ ሰናይ ድርጅት አማካይነት በ2005 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ መንግሥት ተረክቦት እያስተዳደረ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

 በክፍል ቁጥር ልክ ሞግዚት መቀጠር የነበረበት ቢሆንም በ2014 ዓ.ም. ቅጥር ስለቆመ አንድ ሞግዚት ለሁለት ክፍሎች ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ስድስት የፅዳት ሠራተኞች የሚያስፈልጉ ቢሆንም፣ አራት ብቻ መሆናቸውን፣ በወረዳው ከትምህርት ቤት በተጨማሪ ከፍተኛ  የውኃ አቅርቦት ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ ሕፃናት እጃቸውን የሚታጠቡበትና ሌሎችም ተግባሮች ለማከናወን ከፍተኛ የውኃ አቅርቦት ችግር ቢኖርም፣ ከወላጆች ጋር በመነጋገር ተማሪዎች ውኃ ይዘው እንዲመጡ፣ የእጅ ሳኒታይዘር መንግሥት ባለማቅረቡ፣ ወላጆች እንዲያመጡ እየተደረገ መሆኑን ወ/ሮ ሀገሬ ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎች ወላጆች መምህራን ማኅበር አባል የሆኑት አቶ ግርማ ተኩ እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ ልጆች በተሻለ አካባቢ እንዲማሩ ለማድረግ ከግቢ ማስዋብ ጀምሮ ከትምህርት ቤቱ ጋር በጥምረት እየሠራ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የተማሪዎች ቁጥር በመኖሩ፣ የመማር የምገባና ሌሎችም ላይ ጫና ማሳደሩንና በሳምንት አምስት ቀን መማር ሲገባቸው ሦስትና ሁለት ቀን በመሆኑ፣ የተማሩትን እየረሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

አቶ መላኩ አበበ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ ለሕፃናት በተከታታይ አምስት ቀን እንዲማሩ፣ ተጨማሪ ትምህርት ቤት እንደሚያስፈልግና ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎች ለማፍራት ፍትሐዊ የትምህርት ሥርዓት ለወረዳው አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፋንታሁን ተካልኝ እንደተናገሩት፣ ችግሩ ውስብስብ መሆኑን፣ ትምህርት ቤቱና በአካባቢው የሚኖረው የሕዝብ ብዛትና ሊማሩ የሚገባቸው ልጆች ቁጥር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡

በአካባቢው ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ትምህርት ቤት ለመገንባት ለተነሺዎች ካሳ ተከፍሎና የአፈር ጥናት ተከናውኖ ያለቀ ቢሆንም፣ ከአገራዊ ለውጥ በኋላ የትምህርት ቤቱ ጉዳይ ደብዛው እንዲጠፋ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በወረዳው ከ50,000 በላይ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ የሚገመት ቢሆንም፣ በአካባቢው የሚገኘው የመንግሥት ትምህርት ቤት ግን ቆጣሪ ብቻ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ካሳ የተከፈለበት የአርሶ አደር መሬት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን እዚህ ላይ መሥራት አልተቻለም፡፡

ከወላጆች በተሰበሰበው ገንዘብ በክፍለ ከተማው በተሰጠው ቦታ ላይ 25 ክፍሎች ለመገንባት መታሰቡን፣ ነገር ግን እንዲቆም ከክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አቅጣጫ እንደተሰጣቸው አቶ ፋንታሁን ተናግረዋል፡፡ የወረዳውና የክፍለ ከተማው የትምህርት ጽሕፈት ቤት በወረዳው ያለውን የትምህርት ተደራሽነት ችግር ለመፍታት ብዙ ርቀት መጓዙን የጠቆሙት አቶ ፋንታሁን፣ የመሬት ጉዳይ ውስብስብ በመሆኑና ሌሎች ፍላጎቶችም በመኖራቸው ትልቅ ማነቆ ሆኗል ብለዋል፡፡

በወረዳውና በክፍለ ከተማው ሦስት አማራጮች እንደተወሰዱ፣ ትምህርት ቤት በተለምዶ ናሆም አደባባይ አካባቢ፣ ቴሌ አካባቢ የሚባለውና ፍኖተ ሎዛ ትምህርት ቤት አካባቢ ለመገንባት አቅደው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ክፍለ ከተማው የሰጠው አቅጣጫም 17 የይዞታ ካርታዎች እንዲመክኑና ለትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሰጥ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እስከዚያው ተማሪዎች ባለቡትና በየርቀታቸው ከቀለበት መንገድ፣ በላይ ያሉት ወደ ሐና ትምህርት ቤት፣ ከቀለበት በታች ያሉት ደግሞ ቆጣሪ ትምህርት ቤት እንዲማሩና ቀጣና ስድስትና ፀበል የሚባሉ አካባቢዎች ደግሞ መጋቢት 26 ከሚባለው ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

በወረዳው እንደዚህ ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫ ተደርጎም ተማሪዎች ብዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አዲስ ትምህርት ቤት ለመገንባት የተሰበሰበው መዋጮ የከፈሉና ልጆቻቸውን ሌሎች ትምህርት ቤቶች ስለገቡ ተማሪዎች ወላጆች ገንዘባቸው ተመላሽ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ኃላፊ ወ/ሮ ነፃነት ዳባ በበኩላቸው በወረዳው ከአቅም በላይ ተማሪዎች አሉ ብለዋል፡፡

አካባቢው ላይ ሰዎች ከተለያየ ቦታ መጥተው የሚኖሩበት መሆኑን፣ ለዚህም የረዥም ጊዜ ፕሮጀክት ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ ትምህርት ቤት ለመገንባት ሒደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ከክፍለ ከተማው የሚጠበቀው ተጨማሪ ትምህርት ቤት መገንባት መሆኑንና በዕቅድ ከተያዙ ዜጎች በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በመብዛታቸው ችግሩ መፈጠሩን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ትምህርት ሥርዓት ላይ ያለው ጫናም በአንድ ጊዜ የሚፈታ ችግር አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...