Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሌብነት ዘውድ!

ሰላም! ሰላም! ማታ ንፋስ ቀን ፀሐይ መኖራችንን የተጸየፉ ይመስል አላስቆም አላስቀምጥ ብለውናል። እንዲህ አልጨበጥ ያለውን የአየር ንብረት ለኃይል ማመንጫነት የሚጠቀምበት ጠፍቶ፣ ከላይ ተፈጥሮ ከሥር ኑሮ ተረባርበው ሲጠብሱን ዝም ባዩ ምነው በዛ? “አይ አንተ! እንኳን ተፈጥሮን እዚህ በምንችለው ነገር ላይ መቼ ለውጥ አመጣን?” ብሎኛል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። አቤት ግን የሚረባረብብን ብዛቱ። እናማ ይኼው እንደምታዩት እኛም አንድ ላይ በመረባረብ ፈንታ ለመገዳደል መበራበር ጀመርንላችሁ። መጨረስ ነው እንጂ ለመጀመርማ ማን ብሎን አትሉም? “እስካሁን ግን ጀምረን ያልጨረስነው ቢቆጠር እንዴት እናፍር ይሆን?” ስል የሰማችኝ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ “ማ እኛ?” ብላ ከት ብላ ሳቀችብኝ። ሳቋ የእጮኝነታችንን ጊዜ ቢያስታውሰኝ ከሳቀች ረጅም ጊዜ ሳይሆናት እንዳልቀረ ገምቼ ዝም አልኩ። ሌላ ነገር ብልማ ደህና የረሳችውን ማስታወስ ነዋ፡፡ ለነገሩ ከአንጀቷ መሳቅ ቀርቶ ማልቀስስ ይጠበቅባታል እንዴ? ለወር የምሰጣት ለሳምንት አልበቃት እያለ፡፡ ጀምሮ መጨረስ አለመቻልን የመሰለ በሽታ አለ? ሌላውን ትታችሁ አጥረው መገንባት ያቃታቸውን ስታዩ፣ ቃል የገቡትን መፈጸም አቅቶአቸው ሲቁለጨለጩ ስትታዘቡ እናንተው መልሳችሁ ታፍራላችሁ፡፡ ይሉኝታ!

ማንጠግቦሽን እንዲያ ከጣራ በላይ ያሳቃትን ነገር ለማወቅ ጓጉቼ “ምነው?” ስላት፣ “ድሮም እኮ ስናፍር የኖርነው ትንሽም ብትሆን ይሉኝታ የሚያውቁ ሰዎች ስላሳደጉን ነው። አሁን ደፋርና አጭበርባሪው ቀን ሲወጣለት እያየን እንዴት ብለን ይመስልሃል ማፈር ትዝ የሚለን?” አለችኝ፡፡ በመቀጠል፣ “አንበርብር ኑሮአችን በሙሉ በማስመሰል ተወሮ መቼ ራሳችንን ሆነን ነው እንዲህ የምታወራው?” ብትለኝ ቅስሜ እንክት ብሎ፣ “ኧረ እውነትሽን ነው፤” አልኳት። በተጨባጭ እናመሳክር ካላችሁ በየጊዜው በዓለም አቀፋዊነት ስም ከየአገሩ የሚኮረጀውን ሕግና ደንብ ምስክር ማቅረብ ይቻላል። የዘንድሮ ሰው በበላበት መጮህ በመጀመሩ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ የተጓደለው አንድም በዚህ ምክንያት አይመስላችሁም? አሁንማ አንዳንዱ ሀቅን ለመዋጥ እንዴት እንደሚተናነቀው ብታዩት? “እንዴ ስለራሳችን እውነተኛውን ነገር መስማትና መዋጥ ቢቻለን ኖሮማ መቼ እንዲህ እንኖር ነበር?” ያለኝ የባሻዬ ልጅ ትዝ አለኝ። “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” ነው የሚባለው መሰል። ሆኖም፣ “እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር” የሚለው ተረታችን ደግሞ ሀቅን መስማት ለማይሆንልን አይዋጥልንም፡፡ ብዙዎቻችን የሰማነውን ሁሉ እውነት ነው ካልን፣ የራሳችንን መናኛ ጉዳይ እውነት አድርገን ካቀረብን ችግር አለ፡፡ አይደል እንዴ!

የጉዟችን ፍጥነት ሲጨምር ዕድገታችን በጣም የዘገየ መስሎ ይታየኝ ጀመር። መዘየድ አልችል እያልን መዘግየት ተግባራችን ሆነ እኮ፡፡ “ምንድነው የምትለው? ገና አሁን አይደል እንዴ ሁሉም ነገር የተጀመረው?” አለኝ ከታዳጊነት ዘመኑ ጀምሮ በድለላ ሙያ ላይ የተሰማራ ጓዴ። “ሁሉም ነገር አሁን አይደል እንዴ የተጀመረው?” የሚለውን ሊሰመርበት የሚገባ ዓረፍተ ነገር እንበለው። “ደግሞ ከዚህ ብሶ አሿፊ ዘመኔ ያስቀኛል ደርሶ” ብለው ባሻዬ የነገሩኝ ግጥም ትዝ አለችኝ። ምሥጋናና ምሬቱ፣ ፀፀትና ተስፋ ከዚህ ከዚህ ነው የሚወለደው ለማለት ፈልጌ ነው። እንዲህ ዙሪያ ጥምጥም እየሄድኩ ነገር የምጠመጥመው ቀጥተኛው መንገድ ስለተረሳ አይመስላችሁም? እውነቴን እኮ ነው። አቋራጭና አማራጭ መንገድ ነው ወሬው ሁላ። “አቋራጭና አማራጭ ስንፈልግ ደግሞ ከብዙ ነገሮች ጋር እንላተማለን፡፡ ለምሳሌ ዕድገትን በአቋራጭ ለማምጣት የሚረዱ መላዎችን ለገዥው ፓርቲ ሰዎች ስንጠቁምና ምክር ቢጤ ስናቀርብ “ይህንን ሙያዊ ጉዳይ ለእኛ ተውልን” ብለው ቆሌያችንን ይገፉናል…” አለኝ የባሻዬ ልጅ፡፡ በአባባሉ እየተገረምኩ የአማራጩ ደግሞ ምን ይሆን ስለው፣ “ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አማራጭ ይዛችሁ ቅረቡ፣ በተሠራ ወይም በታቀደ ላይ ስትዘፍኑ ከምትከርሙ እስቲ የእናንተን አማራጭ አቅርቡልን ብለን ምክር ቢጤ ጣል ስናደርግ “አጨብጫቢ” ብለው ያስደነብሩናል አለኝ፡፡ “መደማመጥ በሌለበት አገር ውስጥ መካሪ ከመሆን ሱባዔ መግባት ይሻላል…” ሲለኝ ተስፋ መቁረጡ ታወቀኝ፡፡ በስንቱ ተስፋ ቆርጠን እንዘልቀው ይሆን!

ማንጠግቦሽ እጇ ይባረክና ምን የመሰለ ምሳ አብልታኝ እንጀራዬን ፍለጋ ዞር ዞር ልል ወጣሁ። ደላላ ከተቀመጠ ሥራ ቆመ ማለት አይደል? እንዳልኳችሁ የቀትሩ ፀሐይ አናቴን ሲፈልጠው የበላሁት ሊተን አማረው። “ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” ብለው ነበር የድሮ ያራዳ ልጆች። ዳሩ፣ “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” ሆኖ የፈለግነውን ሳንመርጥ መብላት የኑሮ ግዴታችን ሆኖብን አረፈው። እንዴ ለዚህ አይመስላችሁም ደህና የሚባል ምሥጉን በየቦታው ጠፍቶ የሌባ ግብረ ኃይል የሚደቁሰን? እውነቴን ነው እኮ፡፡ “ሠርቶ መለወጥ ካስጠላህ ሰርቆ መለወጥን ምረጥ” ተብሎ በቃል ሲነበነብ ካላየን አናምንም ባዮች ማጣራትና መመርመር አልታክተን ብሎ፣ ለስንቱ ዘራፊ ጥሩ የመደለቢያ ጊዜ ሰጠነው መሰላችሁ? ባሻዬ ሲያጫውቱኝ፣ “የድሮ ሰው ሆቴል ገብቶ መብላትን ያወግዝ ነበር። ዛሬ የምግቡን ተወው የሕዝብ ሀብት የሚዘረፈው በሕዝብ ፊት ሆኗል ስልህ…” ያሉኝ ታወሰኝ። ይገርማችኋል አሁን በእኔ አቅም እንኳ ስታዩት አንድ ግለሰብ ከቢጤዎቹ ጋር እየተነጋገረ እንዲህ የነገሮችን ሥረ መሠረት መፈተሽ ከቻለ፣ ሥራቸው የሆኑት ሹማምንትና መንግሥታዊ ተቋማት ምን ዓይነት አዚም ይሆን ፀጥ የሚያሰኛቸው? ዝም ጭጭ ነው!

የበላሁት ምሳ እንዳይተን ዘዴ ሳውጠነጥን እግር ጥሎት አንድ ባለስቴሽነሪ ወዳጄ መንገድ ላይ አጋጠመኝ። ቡና ፉት እንበል ተባብለን አንዱ ካፌ አረፍ አልን። ‹‹ይኼ ፀሐይ እኮ በቃ ራስ ምታት ሆነብን…›› አልኩት የግንባሬን ግለት በመዳፌ እየለካሁ። “አንተ እሱን ትላለህ? የሰላም መጥፋት እኮ ሌላ ራስ ምታት እየሆነብን መስሎኝ?” አለኝ ራሱን ግራ ቀኝ እየነቀነቀ። “ደግሞ ምን ሰማህ?” ብለው፣ “አትሰማም እንዴ ወሎ ምድር ላይ ያለውን ዕልቂት? ኧረ በስንቱ ይሆን ተብሰልስለን የምንችለው?” አለኝ ትክት ብሎት። ኋላ ትንሽ ቆያየና ያናደደውን በደንብ ሳይነግረኝ ይስቅ ጀመር። ‹‹እስኪ እኔም ልስማው…›› ስለው፣ ‹‹እኔ እምልህ ግን የአገር ወቅታዊ ሁኔታ ትክክለኛው መረጃ የሚነገረን መቀመጫቸው ሲያዘነብል ነው እንዴ?›› አለኝ ንዴት ንዴት እያለው። ‹‹አልገባኝም?›› አልኩት ኮስተር እንዳልኩ። ‹‹እኔም አልገባኝም እባክህ፣ ትናንት የጀመርከውን በፍጥነት እንጨርሰዋለን ሲል የነበረ ሁሉ ዛሬ በየፊናው ተኝቶ ሲያንቀላፋ ምኑም አይገባኝም…›› አለኝ ድንገት ደግሞ ፊቱን ቁምጭጭ አድርጎ። እንዲህ ስሜት ሲለዋወጥ እያየሁ ስለችግሮቻችን ሳስብ ቡናዬ በረደ። የዘንድሮ አበሳችን መከራችንን ያባብሰው ይሆን? እንጃ! 

 ቀን ሙቀት፣ ማታ ንፋስና የጦርነት ወሬ እያሳቀቀን ውሎ ማደራችን መቼ ቀረ? ከግሽበቱም ጋር ቢሆን ይኼው ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀን አለን። “መንግሥት ባለበት አገር፣ ፖሊስ ባለበት አገር እንዴት እንዲህ ውሎ መግባት ያሥጋን? እንዴት እርስ በርሳችን ስንጨካከን ገላጋይና አስታራቂ ይጥፋ?” ይላሉ ባሻዬ። በማስከተልም፣ “አቤት የዛሬ ልጆች ዕድላችሁ፣ ይኼም ኑሮ ተብሎ ደግሞ ጥላችሁን ጭምር አለማመን ይምጣባችሁ?” እያሉ ነገሩ እጅግ እንዳብሰለሰላቸው ሰነበቱ። ጎበዝ ተመሥገን ብለን የምንተነፍሳት የሰላም አየራችን ሲወደድ ዝም ብለን እናያት ይሆን? እንጃ፣ ‘አይደረግም!’ ያለው ዘፋኝ ትዝ አለኝ። ሰሞኑን “ባልጠገበ አንጀት ጦርነት?” ብሎ አንዱ በገጠመን ፈተና ላይ ሲያማርር በሩቁ ቁሞ ሲያየው የነበረ አንዱ ሰምቶት ኖሮ፣ “ና እስኪ!” አለው አሉ። እሱም፣ “መቼም እኔን ከሆነ ይገርመኛል፣ እንዲህ ከርቀት ሰምቶ ከጠራኝ ይኼ አንቴና የተገጠመለት ሮቦት ማለት ነው…” እያለ ጉዞውን ሊቀጥል ሲል፣ “አንተን እኮ ነው ና እንጂ…” ብሎ እንደገና ጮኾ ጠራው። መንገደኛውም ማን ይሆን እያለ “አቤት?” አለው ሰማይ ሰማዩን እያየ። “ምን ሰማይ ሰማይ ታያለህ?” ቢለው አቀረቀረና መሬት ላይ ማፍጠጥ ጀመረ። “ምን መሬት መሬት ያሳይሃል?” ሲለው ይኼው ማንነቱና ምንነቱ ያልታወቀ ሰው መልሶ መንገደኛው ስልችት ብሎት ቀና ብሎ እያየው፣ “ወይ አታዘንብ ወይ አታበቅል፣ እና አንተን ላይህ ነው?” ብሎት መጓዙን ቀጠለ ብለው ነገሩኝ። መረጃ አይናቅም!

  ቀኑ ቢገባደድም ትንሽ ሮጥ ሮጥ ማለት አስፈላጊ በመሆኑ ደላሎቹ ድድ የሚያሰጡበት ቦታ ስደርስ እኔም ዕድል ቀናኝ፡፡ አዲስ ኤይት መኪና ውስጥ የተቀመጠ ሰው በዓይኑ ጠቅሶኝ ሲጠራኝ ተንደርድሬ አጠገቡ ደረስኩ፡፡ የማታ እንጀራ ነውና እንደ አሯሯጤ ቢሆን ኖሮ የምላተመው ስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ከሚያወጣው ከዚህ ዘመናዊ መኪና ጋር ነበር፡፡ መስታወቱን ወይም ፍሬቻውን ብሰብር ደግሞ በቀረኝ ዕድሜ በየቀኑ መኪናውን ሳጥብ ብኖር ዋጋውን አልመልስም፡፡ ለማንኛውም ፈጣሪ ተፋኝ፡፡ ተንደርድሬ አጠገቡ የደረስኩት ባለመኪናው በሩን ከፍቶ ግባ አለኝ፡፡ ውስጡ ስገባ ድሪምላይነር የሚባለው አውሮፕላን ውስጥ የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ አቤት ምቾት፡፡ እኛም ኖርን ብለን እናወራ ይሆናል? “ተኖረና ተሞተብለዋል የተባሉት አለቃ ገብረሃና የእኛን አኗኗር ምን ይሉት ነበር? ሰውየው በምቾት የተያዘ ፊቱን በስሱ እየደባበሰ፣የምከራየው ቪላ ቤት ሦስት መኝታ ቤት ያለው ቦሌ አካባቢ በአስቸኳይ እፈልጋለሁ…ሲለኝ ይዤው ወደ ሩዋንዳ በረርኩ፡፡ ለምን እንደሚፈልገው መጠየቅ የለብኝም፡፡ ምን አግብቶኝ!

  ለአንድ ዓመት አሜሪካ ለሕክምና ስለሚሄዱ ባለፈው ሰሞን አከራይልኝ ያሉኝ ባለቤቱ፣ ይኼንን በምቾት የተጥለቀለቀ ደንበኛ ስወስድላቸው እጅ እየነሱ ተቀበሉት፡፡ ዋጋ ተስማምተው ውል ከተፈራረሙ በኋላ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ስሰናበት፣ ደንበኛው በዓይኑ ጠቅሶ ቆይ አለኝ፡፡ ከግቢው ጉዳያችንን ጨራርሰን ስንወጣ፣ታማኝ፣ ተያዥ ያለውና ብርቱ የጥበቃ ሠራተኛ በአስቸኳይ እፈልጋለሁ…ሲለኝ ለዚህ ሥራ የተመቸ ጎረቤቴን አገናኘሁት፡፡ በኋላ ሳጣራ ይኼ ለምቾት የተፈጠረ ሰው አንዲት የኮሌጅ ተማሪ አስረግዞ መውለጃዋ ስለደረሰ ነበር ለካ እንዲህ የሚሯሯጠው፡፡ የባለሥልጣን ልጅ አስረግዞ ጉድ እንዳይፈላበት ቪላ ተከራይቶ ልጅቷን ያርሳል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ምን ይሆን ብዬ ላጣራ ብሞክርም፣ ከዚህ በላይ መጠየቅ ሌላ መዘዝ ያመጣል ተብዬ ለአፌ ገደብ አደረግኩለት፡፡ ማታ ከባሻዬ ልጅ ጋር ወደ ግሮሰሪ ስናመራ የገጠመኝን ብነግረው፣ሌብነት እንደ ሰደድ እሳት አገሩን አዳርሶት ዝም እየተባለ ይኼ ምን ይደንቃል?” ብሎ ውሎዬን አራከሰብኝ፡፡ ሌብነት የትውልዱን ሞራል የሚያዘቅጥ አደገኛ ዕፅ መሆኑ እየተዘነጋ በዝርፊያ የከበሩ እስከ መቼ ይፈንጩ? “ሙስና የዕድገት ፀር ነውእያሉ ማላዘን ሳይሆን ድምጥማጡን ማጥፋት ነው እያልኩ በሐሳብ ብሰጥም፣ የባሻዬ ልጅ ነገረ ዓለሙን ትቶ ይኼን የቀዘቀዘ ቢራ በአንድ ትንፋሽ እያወራረደው ነበር፡፡ እየገረመኝ ያለው ትንሹም ትልቁም ጆሮው ላይ ተቀምጦ ሌብነት አገር ላይ ዘውዱን እየደፋ ነው፡፡ አጃቢዎቹ ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡ የሰማ ላልሰማ ያሰማ፣ ሌብነት አገር ላይ ዘውዱን ደፍቶ ደረቱን አሳብጧል፡፡ መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት