Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቹ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቹ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ጀምሯል፡፡ ይሁንና ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው በገቡት ውል መሠረት ወርኃዊ ክፍያ መክፈል እየቻሉ አለመሆኑ፣ በአወዳደሪው አካል የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህን ተከትሎ አንዳንድ የክለብ ተጫዋቾች ክፍያ ካልተፈጸመልን በሚል ልምምድ አንሠራም፣ ወደ ሜዳም አንገባም በማለታቸው፣ አወዳዳሪው አካል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጨዋታውን በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ ውል የገባው ሱፐር ስፖርት እያንዳንዱን ጨዋታ ለማስተላለፍ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ቀደም ብሎ ከመሆኑ አኳያ ችግር እየገጠመው መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ገጽታ ካለ ደግሞ ለድርጅቱ ተጨማሪ ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ በክለቦችና በተጫዋቾች መካከል የሚፈጠሩ በተለይ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ አክሲዮን ማኅበሩ ጠንካራ አቋም ሊኖረው እንደሚገባም ማሳሰቢያ እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ለውድድርና ለቀጥታ ሥርጭት የማያመቹ የስታዲየሞች ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሜዳ መግቢያ ትኬት ሽያጩን በተመለከተ ከአሞሌ ጋር የገባው ውል ተቋርጧል መባሉ፣ እንዲሁም በችግርነት እየተነሳ ይገኛል፡፡ ሌላው ጉዳዩ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ሊግ ካምፓኒው በተለይ በተጫዋቾችና በክለቦች መካከል ከሚደረጉ ስምምነቶች መካከል፣ ውድድሮችን የሚዳኙ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ሊግ ካምፓኒው በባለቤትነት እንዲያስተዳራቸው ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥያቄ ማቅረቡም ተሰምቷል፡፡ ሊግ ካምፓኒው ከኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት ክለቦች በሚያመቻቸው የሕክምና ተቋማትና በአካባቢያቸው ይመርመሩ በሚል ይከተለው የነበረውን የምርመራና የክትትል ሥርዓት በዚህ ዓመት በአንድ ማዕከል እንዲሆን ማድረጉ ጥያቄ የሚያነሱ ክለቦችና ባለድርሻ አካላት መኖራቸው ይደመጣል፡፡ በእነዚህና ክለቦች ከቀጥታ ሥርጭት ስለሚያገኙት ዓመታዊ ክፍያና በሌሎችም ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የሊግ ካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሊግ ካምፓኒው ከዓምናው ተሞክሮ በመነሳት ዘንድሮ ምን ዓይነት አዳዲስ አሠራርን ለመተግበር አስቧል? ምክንያቱም ባለፈው ዓመት ኮቪድ-19ም ስለነበረ፣ አሁንም እንዳለ መሆኑ እንደተጠበቀ በርካታ ክፍተቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ለማሳያ ያህል ተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ አልተከፈለንም በሚል ውድድሮች በፕሮግራማቸው መሠረት የማይከናወኑበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ውድድሮች የሚከናወኑባቸው ሜዳዎች ለቀጥታ ሥርጭት እጅግ አስቸጋሪ የነበሩ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ክፍተቶች በመነሳት በዚህ ዓመት ምን የተሻሻለ ነገር ይኖራል ብለን እንጠብቅ?

አቶ ክፍሌ፡- ሊግ ካምፓኒው የ2013 ዓ.ም. የውድድር ዓመት እንደተጠናቀቀ የነበሩ አጠቃላይ ክፍተቶች ምን ነበሩ፣ እነዚህ ክፍተቶች ወደ ቀጣዩ ዓመት እንዳይሸጋገሩ ምን ዓይነት የመፍትሔ አማራጭ እንውሰድ፣ በሚሉና በሌሎችም ነጥቦች ላይ ቁጭ ብሎ ገምግሟል፡፡ በግምገማው እንደ ክፍተት የተመለከተው አንደኛው በተጫዋቾችና በክለቦች መካከል ከወርኃዊ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አለመግባባት ይጠቀሳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሜዳ ችግር ሲሆን፣ ሦስተኛው በወቅቱ በነበረው የኮቪድ-19 ምርመራና አካሄድ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች የውድድር ዓመቱ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ ሌሎችም ከዳኝነት፣ ከልምምድ ሜዳ፣ ከሆቴሎችና ከሌሎችም ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ችግሮቹ ወደእዚህኛው የውድድር ዓመት እንዳይሸጋገሩ ሊግ ካምፓኒው የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ከተወሰዱ አማራጮች መካከል የውድድር ሜዳን በተመለከተ የ2014 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ከመጀመሩ አስቀድሞ ለ16ቱም ክለቦች መሥፈርት በማዘጋጀት እንዲሰጣቸው ከተደረገ በኋላ፣ ያለምንም ችግር ውድድሩን እንደሚያዘጋጁ መልስ የሰጡት ስድስት ክለቦች ናቸው፡፡ በዚያ መሠረት ከስድስቱ ክለቦች ሐዋሳና አዳማ የመጀመርያውን ውድድር በገቡት ቃል መሠረት እንዲያዘጋጁት ተደርጓል፡፡ እንደ ጅምር እስካሁን መልካም የሚባል አካሄድ ነው ያለው፡፡ ሌሎቹ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳርና አዲስ አበባ ሲሆኑ፣ በሚወጣላቸው የውድድር ፕሮግራም መሠረት የሚያስተናግዱ እንደሚሆን እንጠብቃለን፡፡ ይህ ማለት ግን ክለቦቹ አንድ ጊዜ ዕድሉን አግኝተናል በሚል ባስመዘገቡት መሥፈርት መሠረት የማያከናውኑ ከሆነ ዕድሉን የሚነጠቁ ስለመሆኑ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ በውድድር ዓመቱ ከምርመራና ከውጤት አንፃር ከፍተኛ የሚባል ክፍተት ነበረብን፡፡ አሁን ላይ ያለፈውን ዓመት ላለመድገም የክለብ ተጫዋቾች፣ አመራሮች፣ ዳኞችና ከስፖርቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሁሉ እንዲከተቡ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ውድድር በሚደረጉባቸው ቦታዎች ላይ ባለፈው ዓመት ስናደርግ የነበረው ተጫዋቾችም ሆነ የክለብ አመራሮች ውጤት የሚያቀርቡት በአካባቢያቸው ከሚገኙ የጤና ተቋማት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ሁሉም ክለቦች በተስማሙበት በአንድ ተቋም ብቻ በተደረገ ምርመራ እንዲሆን ነው፡፡ ከተጫዋቾች ወርጋዊ ክፍያ ጋር በተገናኘም፣ ሊግ ካምፓው መፍትሔ ብሎ የወሰደው ጥናት ማድረግ ነው፡፡ የአገሪቱ ክለቦች ከካፍና ከፊፋ መሥፈርት አንፃር ልኬታቸው (ስታንዳርዳቸው) ምን እንደሚመስል፣ በተለይ ውል የገባ ክለብ በውሉ መሠረት ማድረግ ስለሚገባው ሁኔታና መሰል ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ከሁሉም ባለድርሻ አካል የተውጣጡ ሙያተኞች ተካተውበት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ጥናት እንዲደረግ ነው፡፡ ውጤቱም በቅርቡ ይፋ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በጥናቱ በአዲሱ የመንግሥት መዋቅር መሠረት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሙያተኞችም የሚካተቱ ይሆናል፡፡ የባለፈው ዓመት ዓይነት አሠራር ክለብ ውል ለገባለት ተጫዋች ውሉን የማያከብር ከሆነ፣ በተለይ ሊግ ካምፓኒው ከሱፐር ስፖርት ጋር ካደረገው ስምምነት አንፃር የማያስኬድ በመሆኑ፣ ጥናቱ ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት ይፈጠራል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ ይህ ጥናት በዚህ ወር መጨረሻ ተጠናቆ ለውይይት ይቀርባል፡፡ ሌላው ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረን ውል መሠረት ድርጅቱ ብሮድካስት ከሚያደርገው ክፍያ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት ተግባራዊ ባይደረግም፣ በዚህ ዓመት ግን ለአቅም ግንባታ፣ ለአይሲቲ፣ ለክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞችና ለሌሎችም ሙያተኞች ክለብ እንዴት ብራንዲንግ  እንደሚደረግ፣ ለገበያ ጥናትና መሰል የሙያ ድጋፎች ወጪዎች የድርጅቱ በመሆኑ ያንንም መጠቀም ጀምረናል፡፡ ዘገባን በሚመለከት ለስፖርት ጋዜጠኞች እንዲሁም ደጋፊዎች ጭምር ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሌላው ሊግ ካምፓኒው ባለፈው ዓመት ሲተችበት የነበረው የዋንጫ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ችግሩ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ ዋንጫው በእንግሊዝ አገር የኢትዮጵያን እሴቶች በጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ ሊጉ ከመክፈቻ ሙዚቃ ጀምሮ የራሱ ብራንድ እንዲኖረው በዚህ ዓመት ማስተካከያ ከተደረገባቸው አሠራሮች ይጠቀሳል፡፡

ሪፖርተር፡- ሊግ ካምፓኒው ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች በመነሳት በተለይ በክለቦችና ተጫዋቾች መካካል የሚደረግ የውል ስምምነትና የጨዋታ ዳኞችና የታዛቢ ዳኞች ጉዳይ ለውሳኔ አሰጣጥ ያመች ዘንድ ወደ ሊግ ካምፓኒው ቢጠቃለሉ ችግሮቹን በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል በማመን ለፌዴሬሸኑ ጥያቄ ማቅረቡ ይነገራል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ ክፍሌ፡- እውነት ነው፡፡ ሊግ ካምፓኒው ይህን ጥያቄ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አቅርቧል፣ እያቀረበም ይገኛል፡፡ በነበረው አሠራር ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች የአፈጻጸም ክፍተት ቢታይባቸውም፣ ጉዳዩን በሊግ ካምፓኒው በኩል ለመመልከት የሚቻል አልነበረም፡፡ በተመሳሳይ በተጫዋቾችና በክለቦች መካከል ከክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ቢፈጠሩ ፌዴሬሽኑ ካልሆነ የእኛ ድርሻ ምን እንደሆነ አይታወቅም ነበር፡፡ ይህ ውድድሩን በባለቤትነት እመራለሁ ለሚል አካል ችግር ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ መናገር የምችለው ባለፈው ዓመት ከዳኝነት ጋር የተያያዙ ችግሮች በተከሰቱበት ወቅት ሊግ ካምፓኒው የዳኞቹን የውሎ አበልና ሌሎችም ወጪዎችን የሚሸፍን መሆኑን መነሻ በማድረግ ጥፋት በፈጸሙ ዳኞች ላይ የዕርምት ደብዳቤ ሲጽፍ፣ ‹‹ምን አገባችሁ?›› የሚል ነገር ተነስቷል፡፡ እኛም የጉዳዩን አግባብነት በመመልከት ተቃውሞን ተቀብለን ያስተካከልንበት አካሄድ ነው የነበረው፡፡ ዘንድሮ ግን በዚህ ጉዳይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ዋና ጸሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን በተገኙበት ውይይት አድርገናል፡፡ እነሱም ሆነ እኛ ስምምነት ላይ የደረስነው ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመነሳት ጥናት ተደርጎ ውሳኔ እንዲያገኝ በሚል ተስማምተን ነው የተለያየነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይህ ክፍተት በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው ጥናት ውስጥ ተካትቶ የፌዴሬሽኑና የሊግ ካምፓኒው ኃላፊነትና ግዴታ ከውድድር አንፃር ምን መምሰል እንዳለበት አቅጣጫ እንደሚቀመጥለት እንጠብቃለን፡፡ ለጊዜው ግን በአሁኑ ወቅት ፌዴሬሽኑ በሚያዋቅረው የዳኞች ኮሚቴ ጋር ከሊግ ካምፓኒው አንድ ሰው እንዲወከልና ውሳኔዎችን በሚመለከት ሪፖርት እንዲያደርግ በሚል ውድድሩ እንዲቀጥል አድርገናል፡፡ ከተጫዋቾች ጋር ስላለው ጉዳይም ቢሆን ተጫዋቾችን የሚያወዳድራቸው ሊግ ካምፓኒው ነው፡፡ በዚያ ላይ ለሊግ ካምፓኒው አሠራር ከፍተኛ ችግር እየሆነ ያለው በተጫዋቾችና ክለቦች መካከል የሚፈጠረው አለመግባባት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አክሲዮን ማኅበሩ የሚመራውን ፕሪሚየር ሊጉን በራሱ መመርያና ደንብ ችግሮቹን እንዲፈታ ቢደረግ የሚል ጥያቄ አለን፡፡ ይህ ማለት ግን በጉዳዩ የፌዴሬሽኑ ሚና በተለይ ከካፍና ከፊፋ ጋር ያለውን በተመለከተ ሙሉ ኃላፊነት የፌዴሬሽኑ እንደሆነ ለአፍታም መዘንጋት የሌለበት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ይህ ጉዳይም በዚህ በምናስጠናው ጥናት ተካቶ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም በዚህ በኩል ምንም ችግር እንደሌለበት በምናደርጋቸው ተደጋጋሚ ውይይቶች አረጋግጦልናል፡፡ ምክንያቱም በሱፐር ስፖርት ቀጥታ ሥርጭት ያለው ሊግ፣ በተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ተቋረጠ የሚል ነገር ቢሰማ ለፌዴሬሽኑ ሆነ ለሊግ ካምፓኒው ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ከክፍያ ጋር ተያይዞ ከ50 ሺሕ ብር በላይ የሚለው አስገዳጅ ሕግ እንዲነሳ የተደረገው በራሳቸው በክለቦቹ ይሁንታ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው አንድ ክለብ ተነስቶ ውል የገባውን ተፈጻሚ የማያደርገው? በሌላ በኩል ተጫዋቾች ራሳቸው ውል ሲዋዋሉ ጉዳዩን ከሕግ ጋር ለምን እንደማይዙትም አይገባኝም፡፡ ምክንያቱም ስፖርቱ አሁን ላይ ትልቅ የፋይናንስ ተቋም እየሆነ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደ ሱፐር ስፖርት የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ሙዓለ ንዋይ የሚያፈሱት፡፡ ድርጅቱ በዚህ ዓመት ከሚከፍለው 4.25 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ግማሹን ገቢ ሲያደርግልን፣ አንድ በትልቁ ልንወስደው የሚገባው ነገር እንዳለ ይነግረናል፡፡ ይህ ሀብት የሚመጣው ደግሞ በተጫዋቾቹ መሆኑንስ እንዴት መረዳት ያቅተናል? እዚህ ላይ ክለቦች ሊረዱት የሚገባው ከሱፐር ስፖርት የሚከፈላቸው ገንዘብ እንዳለፉት ዓመታት ዝም ተብሎ የሚከፈላቸው አለመሆኑን ነው፡፡ ክፍያው ተፈጻሚ የሚሆነው ክለቦች ሒሳባቸውን በታወቀ የሒሳብ ባለሙያ አሠርተው ትክክለኛውን የፋይናስ ሪፖርት ሲያቀርቡ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሊግ ካምፓኒው የሒሳብ አሠራሩን በየወሩ ለገቢዎች ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ግብር ይከፍላል፡፡ ወጪ ገቢውን የሚያወራርድበት ካሽ ሪጅስተር መጠቀም ጀምሯል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ስፖርቱ ላይ ግልጽ የሆነ አሠራር ሊመጣ የሚችለው፡፡ በነበረው አሠራር አንድ ክለብ በዓመት ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ብር በጀት በአንድና በሁለት ሰው ያንቀሳቅሳል፡፡ ይህ በፍፁም ትክክለኛ አሠራር እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተለምዶአዊ አሠራር እስካልተሻሻለ ድረስ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሰፈነበት እግር ኳስ መፍጠር ከባድ ነው፡፡ የአጭር ጊዜም ቢሆን የምናስጠናው ጥናት ለእነዚህ ችግሮች ጭምር መልስ የሚሰጥ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ችግሩ እንዳለም ቢሆን ሊግ ካምፓኒው ወደፊት ከታች ከሱፐር ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚመጣ ክለብ ሲኖር በቅድሚያ የክለቡ መዋቅራዊ ልኬት (ስትራክቸር) ምን መምሰል እንዳለበት መሥፈርት ወጥቶለት ያንን ማሟላት ከቻለ ብቻ የሚል በሰነዱ ለማካተት ዕቅድ አለው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሊጉን አሁን ከተሸጠበት ሦስትና አራት እጥፍ ከፍ በማድረግ ለመሸጥ የሚያደፋፍረው፡፡ ይህን የምለው በስሜት ሳይሆን ሱፐር ስፖርት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች የሽያጭ አድማሱን እያሰፋ ነው፡፡ በቅርቡ በሐዋሳ ጀምሯል፡፡ ገበያው አዋጪ እንደሆነ ገብቶታል ማለት ነው፡፡ እኛም በዚህ ልክ አስበን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ ድርጅቱ ከእግር ኳሱ በተጨማሪ በፊልም እንዱስትሪው ሳይቀር መግባት ጀምሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ሊግ ካምፓኒው ከስታዲየም መግቢያ ትኬት አሻሻጥ ጋር በተገናኘ ከዚህ በፊት አሞሌ ከሚባል ድርጅት ጋር ውል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ውል ማቋረጣችሁ ተሰምቷል፡፡ ችግሩ ምንድነው?

አቶ ክፍሌ፡- በመሠረታዊነት የሜዳ ገቢ ገንዘብ የሚሰበስበው ባለሜዳ ክለብ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ኃላፊነት አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ክለቦች በጠቅላላ ጉባዔያቸው ላይ ካምፓኒው ነፃ ሆኖ ድርጅት አምጥቶ ገንዘባችን በአንድ ላይ ሰብስቦ ድርሻችንን በአካውንታችን ያስገባልን የሚል አቅጣጫ አስቀመጡ፡፡ በዚያ መሠረት አክሲዮን ማኅበሩ ይህ ሊያከናውን ለሚችል ድርጅት ግልጽ ጨረታ አወጣ፣ ካልተሳሳትኩ ጨረታው ከወጣ በኋላ በጨረታው የተሳተፉ ድርጅቶች 17 ነበሩ፡፡ ድርጅቶቹ በሲስተሙ አማካይነት ከሚሰበስቡት ገንዘብ የሚያገኙትን ኮሚሽን ጭምር እንዲያስቀምጡ ተደርጎ፣ በዚህ ሥሌት መሠረት አሞሌ የተሰኘው ድርጅት አሸነፈ፡፡ ሊግ ካምፓኒው ከድርጅቱ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለው ውል አዘጋጀ፡፡ በውሉ ከተካተቱ ነጥቦች የባንክ ዋስትና (ጋራንቲ) አንድ ሚሊዮን ብር በባንክ እንዲያስቀምጥ የሚለውን ይጠቀሳል፡፡ ይህንን ድርጅቱ አልቀበልም አለ፡፡ ውሉ በዋናነት ያስፈለገው ከተሞክሮ ኔትዎርክ የለም የሚል ምክንያት እንዳይፈጠር በማሰብ ጭምር ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ለድርጅቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግለትም ሊመጣ ባለመቻሉ ውሉ ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ሁለተኛ የወጣው አቢሲኒያ ባንክ ነበር፡፡ እሱም ሙሉ ቁጥጥር አላደርግም በሚል ውሉን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ አሁን ላይ የባለ ሜዳ ክለቡ ተወካዮችን በማሳተፍ የትኬት ሽያጩን በነበረው ዘልማዳዊ አሠራር እየሠራን ነው፡፡ ጎን ለጎን ግን በዚህ ሥራ ለመሰማራት ፍላጎት ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች አንዱ ከሆነው ቴሌ ብር ጋር ድርድር ጀምረናል፡፡ የሚሳካ ከሆነ እሰየው፡፡ ካልተቻለ ግን ሊግ ካምፓኒው በዚህ ሥራ ውስጥ በፍፁም የመቀጠል ፍላጎት የለውም፡፡ ጉዳዩ የክለቦች በመሆኑ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ተበታትኖ የነበረውን የኮቪድ-19 ምርመራ ወደ አንድ ማዕከል ማምጣችሁን ነግረውናል፡፡ ይሁንና ይህ ዓይነቱ አሠራር ‹‹ለሙስና በር ይከፍታል›› በሚል የሚቃወሙት ስለሚኖሩ ምን ይላሉ?

አቶ ክፍሌ፡- አሠራሩን በዚህ አግባብ እንመልከተው ከተባለ አሁን ላይ ከመረጥነው አሠራር በተሻለ ለሙስና ተጋላጭ የነበረው አሠራር ቀደም ሲል የነበረው ነው፡፡ ምክንያቱም የአሁኑ አሠራር የምርመራ ማዕከሉ ናሙና የሚወስደው ውድድሮቹ በሚደረጉባቸው ከተሞች ላይ በአንድ ማዕከል ቁጭ ተብሎ ነው፡፡ ሲስተሙን የሚቆጣጠር ገለልተኛ የሆነ ራሱን የቻለ ሐኪምም በቦታው ይኖራል፡፡ በዚያ ላይ ላቦራቶሪውን የሚቆጣጠረው ከሊግ ካምፓኒው በሚወከል ሐኪም አማካይነት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ግን ማንኛውም ተጨዋችም ሆነ የክለብ አመራር የኮቪድ-19 ውጤት እንዲያመጣ የሚደረገው በአካባቢው ከሚፈልገው የጤና ተቋማት ነበር፡፡ እንዲያውም ትልቅ ሙስና ሊፈጸም የሚችለው በዚህ ዓይነቱ አሠራር እንደሆነ ነው የምናምነው፡፡ ለአሠራርም ቀላል ሆኖ የተገኘው የአሁኑ የናሙና አወሳሰድና አሠራር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሱፐር ስፖርት በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር የገባው የየዓመቱ ክፍያ፣ እንዲሁም ከአቅም ግንባታ ጋር ተያይዞ በዓይነት የሚያወጣቸው ውጪዎችን በተመለከተ ስምምነቱ ምን ይመስላል?

አቶ ክፍሌ፡- ሊግ ካምፓኒው ከሱፐር ስፖርት ጋር ካደረጋቸው ስምምነቶች በአምስት ዓመት ውስጥ የክለቦችን ጨዋታ ብሮድካስት ሲያደርግ፣ በመጀመርያው ዓመት 4.0 ሚሊዮን ዶላር፣ በሁለተኛው ዓመት 4.25 ሚሊዮን ዶላር፣ በሦስተኛው 4.5 ሚሊዮን ዶላር፣ በአራተኛው ዓመት 4.75 ሚሊዮን ዶላርና በመጨረሻው ዓመት 5.0 ሚሊዮን ዶላር፣ በአጠቃላይ 22.5 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ነው፡፡ ድርጅቱ እያንዳንዱን ጨዋታ ብሮድካስት ሲያደርግ ደግሞ ለአየር ሰዓት ግዥ ለአንድ ዓመት 5.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፣ የአምስት ዓመቱ ሲደመር 25 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያወጣም በስምምነቱ ተካቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአቅም ግንባታና ተያያዥ ወጪዎችን በተመለከተ ደግሞ የፕሪሚየር ሊጉን ዌብሳይት ዘመናዊ ከማድረግ ጀምሮ የሊጉን ሎጎና ሙዚቃ ጭምር አገራዊ እሴቶችን ያካተተ እንዲሆን፣ ለአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ጭምር ሙሉ ወጪውን እንደሚሸፍን የስምምነቱ አካል ናቸው፡፡             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...