Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የደኅንነት ተቋምን በመደበኛ ቢሮክራሲ ሥር ማድረግ ውጤታማነቱን ይቀንሳል›› ኮሎኔል አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ መንግሥት የደኅንነት ምክትል ሚኒስትር

በቀድሞው ጎጃም ጠቅላይ ግዛት የተወለዱ የአርበኛ ቤተሰብ ልጅ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ አያታቸው ፊታውራሪ ዓለማየሁ ኦጋዴን መሞታቸውን፣ አባታቸውም በጣሊያን ወረራ ተምጫ ሸለቆ ሦስት ሺሕ ጦር ይዘው ከጠላት ጋር የተዋጉ አርበኛ እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹አባታችን የቤተክህነት ትምህርት ስለነበረው ከገጠር ወደ ከተማ ገብተው በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ማገልገል ሲጀምሩ እኛም ተማርን፡፡ ከስምንት ልጆች አሁን የቀረነው አራት ነን፣ ሆኖም ሁላችንም በትምህርት ብዙ ገፍተናል፡፡ በቤተሰባችን ብዙ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች አሉ፤›› ሲሉም ስለቤተሰባቸው ያወጋሉ፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ማግኘታቸውን፣ ማኔጅመንት ተምረው በዲግሪ መመረቃቸውን፣ ወደ እስራኤል አቅንተው በሪሶርስ አሎኬሽን ዘርፍ ከቤንጎሪዮን ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምረቃ ትምህርት መከታተላቸውንና በኢንተርናሽናል ሎው ሌላ የማስተርስ ዲግሪ መቀበላቸውን ይገልጻሉ፡፡ በሆርቲካልቸር ቢኤስሲ ዲግሪ፣ ከዚያም ወደ ቡልጋሪያ አቅንተው ከካርል ማርክስ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የፖስት ዶክቶራል ፕሮግራም መከታተላቸውን፣ ከቀለም ትምህረቱ እኩል በወታደራዊ ሳይንስ ዘርፍም ብዙ ዓይነት ትምህርቶች መቅሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ በፖሊስ ሳይንስ በአድቫንስድ ዲፕሎማ በመጀመርያ መመረቃቸውንና የፖሊስ መኮንን ለመሆን መብቃታቸውን ያወሳሉ፡፡ በትምህርት ላይ ትምህርት፣ በማዕረግ ላይ ማዕረግ እያከሉ በሒደት እስከ ኮሎኔል ማዕረግ የደረሱት አንጋፋው ምሁር ወደ ደኅንነት ተቋምም ገብተው በብዙ የኃላፊነት ደረጃዎች መሥራታቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የደኅንነቱን ዕቅድ (ፕላኒንግ) ዘርፍ መርቻለሁ፣ የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ተሠማርቻለሁ፣ በምክትል ሚኒስትርነትም አገልግያለሁ፤›› ይላሉ፡፡ ለሦስት ዓመታት በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ፡፡ ስታር አምባሳደር ከመባል ባለፈ በሶማሊያ የተማረኩ የኢትዮጵያ ዜጎችን በልዩ ኦፕሬሽን ለማስለቀቅ የተወጡት የስድስት ወራት ዘመቻ ለብቻው ረጅም ታሪክ ያለው ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡ በሌሎች አገሮችም ልዩ የስለላ ተልዕኮዎችን ሲወጡ መቆየታቸውን፣ በአገር ጉዳይና በመንግሥት አስተዳደር ዘርፍ ያካበቱት ዕውቀት ሰፊ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ በአዲሱ መንግሥት ምሥረታ ማግሥት ከዮናስ አማረ ጋር ረዘም ያለ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ኮሎኔል አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ካሳለፉት፣ ከኖሩበትና ከትምህርታቸው በመነሳት ስለአዲሱ መንግሥት አደረጃጀትና አወቃቀር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ የመንግሥት አወቃቀር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀትና የአስተዳደር ሰዎች ምደባ እንደ አዲስ ተካሂዷል፡፡ በመንግሥታዊ ሥራዎች ምክትል ሚኒስትርነትን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ለረጅም ዘመናት ያገለገሉ በመሆንዎ አዲሱን መዋቅር እንዴት ገመገሙት?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- የመንግሥት የመዋቅር ማሻሻያና የአሠራር ለውጥ የሚደረግባቸው ብዙ አስገዳጅ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በዘመቻና በጦርነት ወቅቶች ሊካሄድ ይችላል፡፡ በሌላም በኩል የተንዛዛ ቢሮክራሲን ወደ ተቀላጠፈ አሠራር ለማምጣት የመዋቅራዊ ለውጥ ሊደረግም ይችላል፡፡ በበጀት አቅርቦት ላይ ለውጥ ሲኖር ወይም በጀት እጥረት ሲከሰት እንዲሁ ቢሮክራሲያዊ ለውጥ ይደረጋል፡፡ አዳዲስ ሁኔታዎች፣ ዕክሎችና ፈተናዎች ሲያጋጥሙ ደግሞ ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል መዋቅር ልትፈጥር ትችላለህ፡፡ በየጊዜው እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ወቅቱ መዋቅርን ማስፋትም ሆነ መቀየር የተለመደ አሠራር ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የአወቃቀር ለውጥ 22 ሚኒስቴሮች፣ ሁለት ኮሚሽኖችና ባልሳሳት ወደ 59 ሚኒስትር ዲኤታዎች ያሉበት መዋቅር መደራጀቱ ነው የተነገረው፡፡ በምንከተለው የፌዴራል አወቃቀር የተነሳ በፌዴራል ደረጃ የሚወጣው የመንግሥት አወቃቀር ማሻሻያ ወደ ክልሎች መውረድ ይጠበቅበታል፡፡ እዚህ ፌዴራል ላይ ስትነካካው እዚያ ክልል ላይም ይነካካል፡፡ እኔ እንደማየው በፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች ባላቸው ሚና ግልጽ የሆነና የጠራ ልዩነት የለም፡፡ በአንዱ ያለው በሌላው ግልባጭ ሆኖ ነው የምናየው፡፡ አሁን የምናየው የአሠራርና የተቋማት ድግግሞሽ የሚያስከትል ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ተዋረድ የበጀት ወጪንም የሚጨምር ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት ውስጥ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ የሚደረገው ቅልጥፍና ያለው ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ነው፡፡ ውጤታማነት የሚለካው ደግሞ በተቋማት ሥራን በመከወን ብቃት ነው፡፡ ከውስብስብ ቢሮክራሲ ወጥቶ ሥራን በቅልጥፍና መከወን ሲቻል ተቋማት ውጤታማ ናቸው ይባላል፡፡

አሁን እንደምናየው ከሆነ በአገራችን ብዙ ችግሮች  አሉ፡፡ የደኅንነት ጉዳይ፣ የጦርነቱ ጉዳይ፣ አለመረጋጋቱ፣ ሰላም መጥፋቱ፣ የኑሮ ውድነቱ ጉዳይ፣ የኢኮኖሚው መዳከም፣ የውጭ ምንዛሪ እንደ ልብ አለመገኘቱ፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አቅርቦቱ በቂ አለመሆኑ በአገራችን ይታያሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ ጫናቸው ብዙ ነው፡፡ ችግሮቻችን እነዚህ ሁሉ ከሆኑ ታዲያ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ፣ አዲሱ የመንግሥት መዋቅርና አደረጃጀት ማሻሻያ ችግሮቹን ለመፍታት በሚያስችል መንገድ ተዋቅሯል ወይ? የሚል ይሆናል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል አደረጃጀት፣ በጀት አመዳደብ፣ አሠራርና ቁጥጥር፣ እንዲሁም የግንኙነት ሰንሰለት አለን ወይ? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ይህን በተመለከተ እኔ እንደማየው ሒደቱ ቅደም ተከተል የሌለው ሆኖ ነው የማገኘው፡፡ በተወሰኑ ነባር መሥሪያ ቤቶች መዋቅሩ በነበረበት ሳይነካ ቢቀጥልም፣ ሌላው ዘንድ ግን የማናውቀው ዓይነት አደረጃጀትና መዋቅር ነው የተፈጠረው፡፡ እነዚህን አዳዲስ ተቋማትና መዋቅሮች በቅጡ ለማደራጀትም ሆነ ወደ መደበኛ ቢሮክራሲው ለማስገባት ብዙ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በግሌ ተቋማቱን ለማደራጀትና ሥራ ለማስጀመር ቢያንስ ወደ ሁለት ዓመት ይፈጅባቸዋል እላለሁ፡፡ የሰው ኃይል ማዘጋጀት፣ የአሠራር መዋቅሩን መልመድና ወደ ሥራ ገብተው ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢያንስ ሁለት ዓመት ይፈጃል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ቀደም ብዬ የዘረዘርኳቸውን አገራዊ ችግሮችን ለመፍታትም ይህ አንዱ ፈተና ነው፡፡   

ሪፖርተር፡– እርስዎ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች በተለያዩ መንግሥታት ሥር ሠርተዋል፡፡ የመዋቅርና አደረጃጀት ለውጥ በመንግሥት ውስጥ ሲደረግ ከጥናት ጀምሮ እስከ ትግበራ የሚገጥሙ እንቅፋቶችን በተጨባጭ ተመልክተዋልና ከዚያ በመነሳት ፈተናዎች የሚሏቸውን ጉዳዮች ቢነግሩን?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች በዋናነት አራት ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ አንደኛው የሥራውን ባህሪ ማወቅና እሱን ተከትሎ መዋቅሩን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መዋቅር ዝምብሎ በሰንጠረዥ/በሳጥን የሚቀመጥ ንድፍ ብቻ አይደለም፡፡ መዋቅሩ ማሠራት የሚችል መሆኑን የማረጋገጥ ሥራም ሌላው ፈተና ነው፡፡ በመዋቅሩ ውስጥ የሚመደበው የሰው ኃይልም ሆነ በጀት በቂና ለሥራው አስፈላጊ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በጀት ወይም የሰው ኃይል እጥረትን መፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ከሠራተኞች የሚነሳውን የሥልጣን፣ የእርከን፣ የደመወዝና ሌላም የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ መዋቅር መሥራት አያስቸግርም፣ ከመዋቅር ለውጡ ጋር የሚመጡ ችግሮችን መፍታት ነው ከባዱ ፈተና፡፡ ለምሳሌ ያህል አዲሱ የመዋቅር ማሻሻያው ሰሞኑን ነው የተካሄደው፡፡ የኢትዮጵያ የ2014 ዓ.ም. በጀት ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው ከወራት በፊት ሰኔ/ሐምሌ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ሁኔታ ከመዋቅር ማሻሻያው ጋር አስታርቆ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ መዋቅር መሥራቱ ሳይሆን ከባዱ መዋቅሩን ለመተግበር የሚጠይቁ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሰባሰብ ነው ችግሩ፡፡ ራዕይ ያላቸው፣ ልምድና ክህሎትን የጨበጡ፣ ታታሪና ትጉህ ሠራተኞች ይገኛሉ ወይ ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎቹ ለአዲሱ ሥራ ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ በያዙት ነገር ላይ ተጨማሪ ሥልጠናዎች መስጠትም እንዲሁ አስፈላጊ ነው፡፡ ከውጭ መጣ ወይም ዲግሪና ዲፕሎማ ደረደረ ብለህ ብቻም በቦታው አትሾመውም፡፡ በአዲሱ መዋቅር ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች፣ የሚገጥሙ ፈተናዎች፣ ተግባቦቱ፣ የሥራ ከባቢው ሁሉ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ መዘጋጀትና ጠቃሚ መንገዶችን ማመቻቸት እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነበሩ በመዋቅር ማሻሻያዎች ወቅት ይገጥሙን የነበሩ ፈተናዎች ናቸው፡፡ መዋቅርን በጥቂት ኤክስፐርቶች ቡድን ማሠራት ቀላል ነው፡፡ ግን ያንን መዋቅር በተጨባጭ መሬት ላይ ለማውረድ ከባድ ነው፣ ብዙ ጥናትም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥናት አለን ወይ? የሚል ነው ጉዳዩ፡፡ በእኛ ጊዜ የተንዛዛ ቢሮክራሲ ስላልነበረ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ቀልጠፍ ያለና ትንሽ ነበር፡፡ ለቢሮክራሲው የሚወጣው የገንዘብ መጠንም ውስን ነው፡፡ እንደ ዛሬው ግማሽ ትሪሊዮን የዓመት በጀት አልነበረም፡፡ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ብር ከተገኘም ትልቅ ነገር ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ነው ወይስ አጠቃላይ ለመንግሥት የሚያዝ በጀት?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- በዚያን ጊዜ አጠቃላይ ለመንግሥት ይያዝ የነበረው ዓመታዊ በጀት እኮ ከ200 ሚሊዮን ብር የማይዘል ቢሆን ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅርም ሆነ ገንዘቡ ውስን ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ነው አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ ያደገው፡፡ በተለይ የጦር ሠራዊቱ ቁጥር ወደ 500 ሺሕ ማሻቀቡ የጦሩንና በዙሪያው ያለውን የመንግሥት በጀት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮታል፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ደመወዝ የሚቆረጥለት ሳይሆን፣ ሚሊሻውንም ሌላውንም በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ኃይል ያካተተ ስለነበር ብዙ ወጪ ቀንሶለታል፡፡ በተረፈ ግን ተቋሙን አደራጅቶ ለመምራት የነበረው ጠንካራ መዋቅር የመፍጠር ፈተና እንደተጠበቀ ነበር፡፡ በእኛ ጊዜ ለመዋቅር መዘርጋት ትልቅ እሴት ከነበራቸው ጉዳዮች አንዱ ሌብነትና ዝርፊያ አለመኖሩ ነው፡፡ በአንፃራዊነት ሲታይ በኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመን ሙስና እጅግ ዝቅተኛ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑም የተመደበችዋ በጀት ከሞላ ጎደል በቀጥታ ለተመደበችበት ዓላማ ትውላለች፡፡ ሌላው የመዋቅርን ስኬት ከሚወስኑ ጉዳዮች አንዱ የአገር ፍቅርና ለአገር መስዋዕትነት የመክፈል ዝግጁነት ሳይጠቀስ መታለፍ አይኖርበትም፡፡ በእኛ ጊዜ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በፖለቲካ፣ በቋንቋ፣ በቀበሌ፣ በጎሳ ወይም በጎጥ ፍትጊያ አልነበረም፡፡ ሁሉም ለአገሬ ነው የምሠራው ብሎ ያስብ ነበር፡፡ ለመንግሥታዊ አሠራሮች ተፈጻሚነትና ስኬት ይህ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ዛሬ ግን እንደምናየው የማንነቶች ፍትጊያ ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ ያኔ ሰዎች የመንግሥት መዋቅርን ለግላቸውና ለቡድናቸው መጠቀሚያ አያደርጉም ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ጠፍቶ መገፋፋት ተበራክቷል፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች በብሔርም ሆነ በእምነትና በፖለቲካ የመጓተት ነገር አለመኖሩ ጠቅሞናል፡፡ የጥቅም ግጭቶችን የሚፈጥረው ፍትሕን የሚያዛባው እኮ ዘረኝነትና በማንነት መጓተት ነው፡፡ በአገር ፍቅር ስሜት ለአገር በጋራ የመቆም ዝንባሌ የዳበረበት ጊዜ ነበር፡፡ የብሔር ድርጅት፣ የዘር ፖሊስ፣ ወይም የአንድ ወገን ጥቅም ማስጠበቂያ ተቋም መፍጠር በበዛበት በዚህ ዘመን ግን ይህንን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ለሁሉም ማኅበረሰብ አገልግሎት ለመስጠትን ባማከለ መንገድ የተመሠረተ ተቋምና የተደራጀ መዋቅር ፍትሕ አያዛባም፡፡ ቅልጥፍና ያለው ሀቀኛ አሠራር ለመተግበርም ያስችላል፡፡ በእኛ ጊዜ ቀላል፣ አነስተኛና ቀልጣፋ ቢሮክራሲ ነበር፡፡ በብሔርና በዘር መጓተት አለመኖሩ፣ ሙስናና ሌብነት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ያለችዋን አሠራር አደራጅቶና አዘምኖ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ነበር፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር ያኔ ከነበረው በአሁኑ ወቅት ብሶበታል፡፡ አሁን ብዙ ጊዜ እንደማየው ወረቀት ነው የሚቆጠረው፡፡ ይህን ያህል ፒኤችዲ፣ ዲፕሎማና ዲግሪ እየተባለ ይነገራል፡፡ ይህ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ይህ የሥራ ቅልጥፍናም ሆነ የክህሎት መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ ማስተርስና ዲግሪ ሳይሆን ክህሎት የጨበጠ ባለሙያ አፍርተናል ወይ? የሚለው ቁምነገር ነው ለመዋቅር ለውጥ ስኬት አስፈላጊው፡፡ የማስፈጸም/የመፈጸም ብቃት ነው ወሳኙ ነገር፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በኖሩበትና በደረሱበት የትኛው መንግሥታዊ አደረጃጀት ውጤታማ ነበር ብለው ይገልጻሉ? ከተሞክሮ በመነሳት ቢያነፃፅሩልን?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- ወደኋላ ተመልሰን ያለፈውን በምናይበት ጊዜ ከኢሕአዴግም ሆነ ከደርግ ጊዜ ይልቅ በጃንሆይ ጊዜ የነበረው ቢሮክራሲ የተመጠነ ነበር፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረው ቢሮክራሲ ውስን ቢሆንም እጅግ ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ተደራሽነት ያለው አሠራር ነበረው፡፡ ፍርድ ቤት እኮ በየመንገዱ ነበር፡፡ አቤት ብትል ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱም ጉዳይህን ያዩልሀል፡፡ ፍርድ ለኅብረተሰቡ ምን ያህል ተደራሽ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ በደርግ ጊዜ አብዛኛው መዋቅር በዘመቻ ነበር፡፡ የአብዮታዊ ዘመቻ፣ የዕድገት ዘመቻ፣ የትምህርት ዘመቻ፣ የጦር ዘመቻ፣ የፊደል ሠራዊት ዘመቻ፣ ወዘተ እየተባለ ሁሉ ነገር በጥድፊያና በዘመቻ ነበር የሚካሄደው፡፡ በጊዜው ያልነበረ የኮሚቴ ዓይነት የለም፡፡ መደበኛና ሕጋዊ መዋቅርም ሆነ የአስተዳደር ሥርዓት ተዘርግቶ አልነበረም በዚያን ጊዜ ሁሉ ነገር የሚሠራው፡፡ በዘመቻ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት አስመዘግባለሁ በሚል ምኞት ነበር ሥርዓቱ የሚመራው፡፡ ወደ ኢሕአዴግ ዘመን ስንመጣ ደግሞ ሥልጣን በተቆጣጠሩባቸው 27 ዓመታት ውስጥ ወደ ስድስት ጊዜ የመዋቅር ለውጥ አድርገዋል፡፡ ቢፒአር የሚባልና ሌሎችም የመዋቅር ለውጦች አድርገዋል፡፡ ሆኖም የኢሕአዴግ ዘመን የመዋቅር ማሻሻያም ሆነ ለውጦች ነባሩን የቢሮክራሲ ሥርዓት ማሻሻል በሚል፣ ሰዎችን ለማስወጣትና ለማግለል ጥቅም ላይ የዋለ ነበር፡፡ በሌላ በኩል የራሳቸውን ሰዎች ለማስገባትና ለማሠልጠንም ማሻሻያዎቹን ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ኢሕአዴግ የእኔ የሚላቸውን በተለይ የአንድ ብሔርና የፖለቲካ ቡድን ሰዎችን ለመጥቀምና ለማሠልጠን የመዋቅር ለውጦችን አድርጓል፡፡ ውጭ ተምረው ወይም ተመርቀው የሚመጡና ጀማሪ ካድሬዎቹን ወደ ቢሮክራሲው እያስገባና እየሾመ አሠልጥኖበታል፡፡ ነባሩን የቢሮክራሲ ሥርዓት ለማሻሻል በሚል እንደዚህ ዓይነት ነገር ይፈጥሩ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የንጉሡም ሆነ የደርግ አስተዳደር ምን ያህል ጊዜ የመዋቅር ለውጦችን ወይም ክለሳዎችን እንዳደረጉ ያስታውሳሉ?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- በደርግ የ17 ዓመታት ሥልጣን ዘመን ሁለት ጊዜ ነው የመዋቅር ለውጦችን ያደረግነው፡፡ ንጉሡን በተመለከተ እሳቸው ለ50 ዓመታት የዘለቀ በመሆኑ እኔ ያልደረስኩባቸው ብዙ ዓመታት አሉ፡፡ በንጉሣዊ ሥርዓት ሰዎቹ በሞት እስካልተለዩ ድረስ ብዙም የሚለወጥ ነገር ሊጠበቅ አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ንጉሡ ሕገ መንግሥት አስረቅቀው በሥራ ላይ ያዋሉበትን ወቅት እንደ አንድ የመዋቅር ለውጥ የመጣበት ጊዜ ማየት ይቻል ይሆን?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- የሕገ መንግሥት መረቀቅና መተግበር አዎን ለውጥ ሊባል ይችላል፡፡ ከ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ወዲህም ለውጥ ተደርጓል፡፡ ሆኖም በዘውዳዊ ሥርዓቱ ሥር የነበረው የለውጥ ዑደት እጅግ አዝጋሚና በየጊዜው መዋቅራዊ ለውጦች የታየበት ሥርዓት ነው ልንለው አንችልም፡፡ ሥልጣን ላይ የሚወጡት ሰዎች ብዙ ዘመን ቆይተው ነው በሕመምና በሞት የሚሰናበቱት፡፡ ለውጡም ቢሆን ከሰዎቹ የዕድሜ ዘመን መርዘምና ማጠር ጋር የተቆራኘ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ መንግሥታዊ መዋቅሮች የዘረጋች አገር ነች፡፡ ባለው አሠራርም ሆነ በነበረው አወቃቀር ላይ እሴት እየጨመሩና ማሻሻያ እያደረጉ ወጥነት ያለው የተቋማት ግንባታን መፍጠር ያልተቻለው ለምን ይመስልዎታል?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- አዲስ መንግሥት ሲመጣ ሁሌም ከዜሮ ነው የሚጀምረው፡፡ የዜሮ ድምር አሠራር ነው የምንከተለው፡፡ ይህ የሚፈጥረውን ጉዳት መገምገም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓትም ሆነ ዘለቄታዊነት ያለው የመንግሥት አገነባብ የለንም፡፡ መንግሥት በሦስት ዓይነት መንገዶች ነው የሚገነባው፡፡ አንዱ በዘር ውርስ ወይም በሮያሊቲ ተመርጠህ ትመጣለህ፡፡ ሁለተኛው በአብዮት ወይም በመንግሥት ግልበጣ ሲሆን፣ ሦስተኛው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠህ የምትመጣበት ሒደት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ብሎ የነበረው በዘር የሚዋረስ የዘውድ ሥልጣን ሲሆን፣ ከዚያም በመፈንቅለ መንግሥት ነበር ሥልጣን መፈራረቅ የተካሄደው፡፡ በዚህ ሒደት የሥልጣን መፈራረቅ ሲከሰት ሁል ጊዜ ከዜሮ መጀመርና የነበረውን አፍርሶ ከአዲስ መሥራት እየተለማመድን ነው የመጣነው፡፡ የነበረውን አፍርሰንና እንዳልነበረ አድርገን ነው የምንመጣው፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ መንገዶች ሲጎዳን ቆይቷል፡፡ እንኳን የመንግሥት መዋቅሮችንና አሠራሮችን ለማስቀጠል ቀርቶ የአገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትም እያፈረስን ነው የተጓዝነው፡፡ ይህ አካሄዳችን የተቋማት ባህል እንዳይኖረን አድርጓል፡፡ የተቋሞቻችን የአሠራር ባህል ቀጣይነት የሌለው ሆኗል፡፡ አመራርነት በቅብብሎሽ ሳይሆን በመጠፋፋት ላይ የተመሠረተ ሆኗል፡፡ ይህ አገሪቱን በእጅጉ የጎዳት ሲሆን፣ ጠንካራ ተቋም የሌለው አገር ያደረገን ዋና ምክንያትም ነው፡፡

ተቋሞቻችን ወጥነት ያለው ጠንካራ የሥራ ባህል እንዳይገነቡ የሚያደርገውም ይህ ነው፡፡ በአንድ ሥራ ላይ ዕውቀትን፣ ክህሎትን፣ ቴክኖሎጂንና ቅልጥፍና ያለው አሠራርን እያዳበሩ ለመሄድም ቅብብሎሽ ያለው የአሠራር ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ የሥራ አፈጻጸም ብቃትም ሆነ ውጤታማነት ከዚህ ዓይነቱ የሥራ ባህል ግንባታ ነው የሚጀምረው፡፡ በሦስተኛ ደረጃም ተቋማትንና የአሠራር ሥርዓትን እያጠፉ ከአዲስ የመገንባት ሒደት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ ወጪው ኢኮኖሚን የሚያቃውስ ነው፡፡ በአራተኝነት ደግሞ የወደፊቱን አቅጣጫ ለመቀየስም መንገዱ ይጠፋብሀል፡፡ የነበረውን ታጠፋለህ፣ መሠረትም ሆነ እርሾ ስለሌለህ ቀጣይነቱ ይጠፋብሀል፡፡ ሁሉንም ከአዲስ ስለምትጀምር ያቆምክበት ይጠፋብሀል፡፡ አምስተኛ ላይ ልናስቀምጠው የሚገባው ደግሞ ተዓማኒነት ለመገንባት መቸገርን ነው፡፡ ያለፈውን ነገር ማጥፋት ለወደፊቱ ወዴት፣ እንዴትና በምን አቅጣጫ ነው የምንቀጥለው የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አፍርሶ መገንባት ሒደት ለውጡ ለምንድነው ያስፈለገው ለሚለው ጉዳይም ጭምር መልስ ማግኘት ከባድ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የነበረውን ዑደት እንደመታዘብዎ መጠን፣ ተቋማዊ ማንነቱንና ቅርፁን ይዞ መዝለቅ የቻለ ተቋም በኢትዮጵያ አለ ብለው ያምናሉ? ማንነቱን ሳይለቅ እስካሁን መቀጠል የቻለ ተቋም አለ ይላሉ?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ ማንነታቸውን ይዘው ከቀጠሉ ተቋማት መካከል ሦስት መጥቀስ እችላለሁ፡፡ አንደኛው የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡ የማዕረግ አሰጣጡ፣ አመራሩም ሆነ የምልመላ ሒደቱና ተቋማዊ አሠራሩ ሁሉ ብዙም አልተለወጠም፡፡ በወታደራዊው አስተዳደር ዘመን ተቋሙ ማንነቱን ሊለቅ ቀርቶ የበለጠ ተጠናከረ፡፡ ተቋሙ ፈረሰ ወይም ትኩረት አጣ በተባለበት የኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን፣ መከላከያ ተቋማዊ ይዞታውና ቅርፁ ሁሉ አልተቀየረም ነበር፡፡ ሁለተኛው ፖሊስ ነው፡፡ የፖሊስ ተቋም በኢሕአዴግ ዘመን አደረጃጀቱን ወደ ፌዴራል ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልና ክልል ፖሊሶች እያሰፋ ቢሄድም በተቋማዊ ማንነቱ ላይ ግን ብዙም ለውጥ የለም፡፡ በኢትዮጵያ የፖሊስ ተቋማዊ ይዞታና ቅርፅ አንፃራዊ ከሆኑ ለውጦች ውጪ፣ ምንም የተለየ ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦችን አላይበትም፡፡ ሌላው በሦስተኛ ደረጃ የማስቀምጠው ይዞታውን ጠብቆ መዝለቅ የቻለ ተቋም ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ፖሊሲው በየጊዜው ቢቀያየርም የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት አተገባበር ግን ባለበት ነው የቀጠለው፡፡ አንደኛ ደረጃ አለ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አለ፣ መምህራንም ሆነ ካሪኩለሙ አለ፡፡ ዋናው ደግሞ ካሪኩለሙ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ተቋሙ ላይ በየጊዜው ትንንሽ ለውጦች ብናይ እንጂ፣ መሠረታዊ የተቋሙ ማንነት አልተለወጠም፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርንስ እንዴት ይገመግሙታል?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- እሱም ቢሆን በአራተኝነት ሊካተት የሚችል ተቋም ነው፡፡ ከአንፃራዊ መርዘምና ለውጥ ካልሆነ በስተቀር ራሱን ማስቀጠል ችሏል፡፡ የውጭ ጉዳይን በተመለከተ ፖሊሲው እንጂ የውጭ ግንኙነት ጉዳዩ አይደለም የሚቀያየረው፡፡ የውጭ ጉዳይ ተልዕኮው፣ አሠራሩም ሆነ ይዞታው አንድ ዓይነት ነው፡፡ የፈለገው መንግሥት ቢመጣ የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን ወይም የተቋሙን ተልዕኮ ሳይሆን ፖሊሲውን ነው ሊለዋውጥ የሚችለው፡፡ ከየትኛው አገር ጋር ልቀራረብ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮች፣ ከጎረቤት አገሮች ወይስ ከማን ልጣበቅ የሚለው በየወቅቱ ይለያያል፡፡ ለየትኛው አገር ወይም ጉዳይ ቅድሚያ ልስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛው አገር በአገራችን የበዛ ተፅዕኖ ይኑረው ወይ አይኑረው የሚለውም በየወቅቱ ይቀያየራል፡፡ ከምዕራቡ፣ ከቻይና፣ ከሩሲያ ጋር ልቀራረብ፣ እንዲሁም ወሳኝ ጥቅሞቼና ፍላጎቶቼን ለማስጠበቅ የምችለው ከማን ጋር ስቀራረብ ነው ተብሎ ነው የተቋሙ አቅጣጫ የሚወሰነው፡፡

የኢትዮጵያ ወሳኝ ጥቅሞች ለምሳሌ በቀዳሚነት ከጂቡቲ ጋር እንጂ፣ ከኬንያም ሆነ ከደቡብ ሱዳን ወይም ከሶማሊያ አይደለም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ባለው እርከን ደግሞ ኢትዮጵያ አንድ ላይ ከኖረቻት፣ በባህል፣ በቋንቋና በብዙ ነገሮች ከምትቆራኛት ኤርትራ ጋር መቀራረቧ መሠረታዊ ጥቅሟን ያስጠብቅላታል ሊባል ይችላል፡፡ በቀይ ባህር ባለን ፍላጎትም ሆነ ሊኖረን ከምንፈልገው የፖለቲካ ኃይልና የኢኮኖሚ ጥንካሬ ከኤርትራ ጋር የበለጠ መቆራኘት ለኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ቅደም ተከተሎችንና ፍላጎቶችን ተንተርሶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የፖሊሲ ለውጦች ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ በተረፈ ግን የተቋሙ ተልዕኮም ሆነ አሠራር በየወቅቱ የሚቀያየር ሊሆን አይችልም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማንነቱንና ይዞታውን ይዞ መዝለቅ የቻለውም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እነ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ መብራት ኃይል የመሳሰሉ ተቋማትንስ ከእነዚህ ጋር ማካተት እንችል ይሆን?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- እነዚህ ቴክኒካዊ መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ልለውጥ ብትልም አሠራራቸውም ሆነ ይዞታቸው አይለወጥም፡፡ የቴክኒክ ሥራን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እነዚህን ተቋማት የረዳቸው ሌላው ነገር ደግሞ በከፊል ራሳቸውን እያስተዳደሩ መዝለቅ መቻላቸው ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖለቲካ አይፈልጉም፡፡ መንግሥት ልነካካቸው ወይም ልቀይራቸው ቢል መንግሥት ራሱ እንጂ ሌላ ማንም አይጎዳም፡፡ ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ አመራሮችን ከመለዋወጥ በስተቀር አልነካኩትም፡፡ ፖለቲካ እነዚህን መሰል ተቋማት ሊመራ አይችልም፡፡ ፖለቲካው ልምራ ካለ ግን ወዳቂ ናቸው፡፡ የቴክኒክ ዕውቀት ያለው አመራርን ይጠይቃሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ይጠቅሙሀል እንጂ ካንተ የሚወስዱት የለም፣ አትራፊዎች ናቸው፡፡ መንግሥት በዋናነት የመዋቅር ለውጦችን በተቋማት ላይ የሚያደርገው የሥልጣን የስበት ማዕከልን ለመሰብሰብ ወይ ለመበተን እንዲጠቅመው በማሰብ ነው፡፡ በአንድ ተቋም ላይ ሥልጣኔን ላጠናክር ወይም እንዲላላ ላድርግ ብሎ ሲያስብ ነው የመዋቅር ለውጥ የሚያደርገው፡፡ እነዚህን የቴክኒክ ዕውቀት የሚጠይቁ ተቋማትን መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አሠራራቸውን በራሴ መንገድ ልቆጣጠር፣ ወይም ላፍርስ ካለ ተቋማቱ ወደ ኪሳራና መፍረስ ነው የሚገቡት፡፡ ለዚህ ነው እነ አየር መንገድ፣ መብራት ኃይልና ቴሌ ከአንፃራዊ ለውጥ በስተቀር ብዙ የማይነኩ የሆኑት፡፡       

ሪፖርተር፡- አንድ ተቋም ወይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በሥሩ ብዙ ንዑስ ተቋማትን አካቶ እንዲደራጅ የማድረጉ አሠራር አዲስ አልሆነብዎትም ወይ? የሰላም ሚኒስቴርን ለምሳሌ ብንወስድ ብዙ መሥሪያ ቤቶች በሥሩ ያጨቀ ትልቅ አደረጃጀት ያለው ግዙፍ ተቋም ሆኗል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተቋማትን በአንድ አደረጃጀት የመሰብሰብ አሠራር በፊትም ነበረ? ወይስ አሁን እንደ አዲስ የመጣ አካሄድ ነው?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- አዲስ አካሄድ አልነበረም፡፡ ሆኖም የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ የማምጣት አሠራር ሁለት ነገሮችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ አንዱ የበጀት አጠቃቀም ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ መሥሪያ ቤቶችን ወደ አንድ ስታመጣ በጀት ትቆጥባለህ፡፡ አራት ሚኒስትሮች ያሏቸውን አራት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንድ ተቋም አድርጎ በአንድ ሚኒስትር መምራት ቢያንስ የሦስት ሚኒስትሮችን ደመወዝ ስለሚቆጥብ አዋጪ ይሆናል፡፡ ለአራት ሚኒስትሮች መኪና፣ ደመወዝ፣ ፕሮቶኮል፣ የበታች ሠራተኛ ቅጥር እያልክ በጀት ስትመድብ ወጪው ከባድ ይሆናል፡፡ ይህን ዓይነት የበጀት ወጪ ለመቆጠብ ስትል ብዙ መሥሪያ ቤቶችን አጥፈህ ወደ አንድ ታመጣለህ፡፡ ሁለተኛው ታሳቢ ጉዳይ ደግሞ የሥራ አፈጻጸም ብቃትን ለማሳደግ በሚል ነው ተቋማት የሚጠቀለሉት፡፡ በተዝረከረከ፣ መደጋገም በሚታይበትና በተበታተነ መንገድ የሚካሄድ አገልግሎት አሰጣጥ አንዳንዴ ቀልጣፋ ላይሆን ይችላል፡፡ የተቋማት መብዛትና መበታተን ቁጥጥርን የላላ ያደርጋል፡፡ ቁጥጥር በማጠናከር የሥራ ክንውንን ለማቀላጠፍ ሲባል ነው ተቋማትን ወደ አንድ አደረጃጀት የምታመጣው፡፡

ስለዚህ ተቋማትን የመሰብሰቡ ሥራ ይህን ታሳቢ አድርጎ ከተሠራ አዋጪ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የበጀት ቁጠባንም፣ የሥራ ቅልጥፍናንም ሆነ የአገልግሎት ጥራትን ካላመጣ ግን አደረጃጀቱ ለቁጥጥር ብቻ የተደረገ የተለየ ጥቅም የማያመጣ የመዋቅር ለውጥ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ካነሳኸው አይቀር በሰላም ሚኒስቴር ሥር ያለውን አወቃቀር በደንብ መመልከት ይኖርብናል፡፡ በሰላም ሚኒስቴር ሥር ድሮ ራሳቸውን የቻሉ ትልልቅ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የነበሩ ተቋማት ገብተዋል፡፡ ፖሊስ አንዱ ሲሆን ድሮ ራሱን ችሎ በኮሚሽን የተደራጀ ከ50 እስከ 60 ሺሕ ሰዎች ያሠማራ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ሁለተኛው የደኅንነት ተቋሙ ሲሆን የመረጃ፣ የክትትል፣ የኦፕሬሽን፣ የምርመራና ሌሎች ሥራዎችን የሚሠሩ አደረጃጀቶችን ያቀፈ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ በእኛ ጊዜ (በደርግ) እኔ የነበርኩበት የደኅንነት ተቋም ወደ 25 ሺሕ ሰዎች አካባቢ ነበሩት፡፡ በሰላም ሚኒስቴር ሥር ልዩ ተልዕኮ ያለውን ኢንሳ የሚባለውን (ስፔሻላይዝድ ኦርጋናይዜሽን) የመረጃ መረብ ደኅንነት ተቋምንም ታገኛለህ፡፡ ይህ ተቋም በመደበኛ ቢሮክራሲ ሊመራ የማይችል የረቀቀና የዘመነ አሠራርን የሚከተል ልዩ የደኅንነት መዋቅር ነው፡፡ ይህን መሰሉ የሰላም ሚኒስቴር አወቃቀር ደግሞ ለደኅንነት ሥራው ምን ያህል አመቺ ይሆናል የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡

በሌሎች አገሮች እኔ እንዳየሁት የደኅንነት መዋቅር ለብቻው ነው የሚደራጀው፡፡ እኔ ብዙ የሶሻሊስት አገሮችን አደረጃጀት ዓይቻለሁ፡፡ ሩሲያ ሄጄ ዓይቻለሁ፣ ምሥራቅ ጀርመንን ዓይቻለሁ፣ የኩባንም እንዲሁ ዓይቼዋለሁ፣ የእስራኤልንም አውቀዋለሁ፡፡ የደኅንነት ተቋማት አደረጃጀት በእነዚህ አገሮች ለብቻው ነው፡፡ እኔ የተማርኩበት እስራኤል ነውና የስለላ ድርጅቱ ሞሳድን አደረጃጀት በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ሞሳድ ማለት በእስራኤል ራሱን የቻለ ሁለተኛ መንግሥት በለው፡፡ የእስራኤል መንግሥት ወይም የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማለት በተግባር ሞሳድ ማለት ነው፡፡ ሞሳድ እጅግ ውጤታማ ሥራዎችን የሚሠራ እጅግ ሰፊ ተቋም ነው፡፡ ከዚያ አንፃር ሳይ የእኛ የደኅንነት ተቋማት እንዴት ነው የሚሠሩት የሚለው ጥያቄ ይሆንብኛል፡፡ የደኅንነት ተቋምን በመደበኛ ቢሮክራሲ ሥር ማድረግ ውጤታማነቱን ይቀንሳል፡፡ የደኅንነት ሥራ “ፍሪላንስ” አሠራሮችን የሚጠይቅ ነው፡፡ የደኅንነት ሥራ ሚስጥራዊነት ይጠይቃል፡፡ በመደበኛ ቢሮክራሲ ደብዳቤ በመጻጻፍ የሚሠራ አይደለም፡፡ መረጃ አሰባሰቡ፣ ተልዕኮ አፈጻጸሙና አሠራሩ ሁሉ በሚስጥር ነው፡፡ የደኅንነት ሰዎችም ዝም ብለው የፖለቲካ ካድሬን ሥራ የሚሠሩ ሳይሆኑ፣ እጅግ ከፍተኛ ሙያዊ ክህሎትን የጨበጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ቢሮክራት ተቀምጦ የሚያዘውና የሚመራው አይደለም፡፡ የሥራ ባህሪው የተለየ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከሌላው የቢሮክራሲ ሥራ ጋር መደባለቅ የለበትም፡፡ ይህ ዓይነቱ አደረጃጀት ደግሞ ፖሊስንም የሚጨምር መሆን መቻል አለበት፡፡ ደረቅ ወንጀል የሚከታተል ፖሊስ አለ፣ የመረጃ ሥራ የሚሠራ አለ፣ የወታደራዊ ተልዕኮዎችን የሚወጣ የፖሊስ ክፍል አለ፣ የመገናኛና የኮሙዩኒኬሽንም ራሱን የቻለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለፖሊስ ተቋማትም ልዩ አደረጃጀት መከተልን የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል ካየን የደኅንነት ተቋማቱ የሚደራጁበት መንገድ ባላቸው የተለያየ የሠራተኛ ቅጥር አሠራር መቀመጥም ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ፖሊስና አንድ የደኅንነት ሰው እኩል ሊከፈላቸው አይችልም፡፡ የደኅንነት ሰዎች ክፍያቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በሌላ አገር እንዳይጠለፉ፣ በውጭ ጠላት እንዳይሰለሉ፣ በገንዘብ እንዳይታለሉና በሌሎችም ምክንያቶች ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ምልመላቸውና አቀጣጠራቸው ራሱ የተለየ መሆን አለበት፡፡ ይህን ዓይነት አሠራር የሚጠይቁ የደኅንነት ተቋማትን ወደ ቢሮክራሲው ስታስገባ ግን አሠራሩ ይቀየርና የፖለቲካ ሰዎች ውሳኔ ሰጪ ይሆናሉ፡፡ በተቋሙ ላይ የሚያዙት ሚኒስትሩ ወይም ሚኒስትር ደኤታው ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ በፖሊስ ተቋማት በፊት በነበረው አሠራር በየእርከኑ የፖሊስ ሙያን ተላብሰው የመጡ ኮሚሽነሮች ነበሩ ፖሊስ ኮሚሽንን የሚመሩት፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ግን ይህ ተለውጦ ሲቪል ሆኑ ኮሚሽነሮቻችን፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ወደ ፖለቲካው ያጋደለ እንዲሆን ተቋሙን ያስገድዳል፡፡ በሌላም በኩል በቀደመው ዘመን የደኅንነት ተቋማት በጀት ኦዲት አይደረግም ነበር፡፡ ኦዲት ስታደርግ እኮ ገንዘቡ ለምን ዋለ? የሚል ጥያቄ ታነሳለህ፡፡ እሱ ደግሞ የደኅንነት ተቋማቱን ሚስጥር የሚያጋልጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በአሁኑ የመዋቅር አደረጃጀት ብዙ ተቋማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተጠሪ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡ ይህ አደረጃጀት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ሥልጣን በእጃቸው እንዲገባ ያደረገ ይመስል ይሆን?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ፣ ወደ 12 የሚሆኑ በሚኒስትርና በሚኒስትር ደኤታዎች የሚመሩ ተቋማትን በሥሩ አስገብቷል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ መዋቅር እንዴት እንደሚመራ ግር የሚል ነገር አለው፡፡ ከዚህ አደረጃጀት መታዘብ የምችለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ኃይል በተጨባጭ መጎልበቱን ወይም መጨመሩን ነው፡፡ ይህ በመዋቅር ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ጭምር ነው፡፡ ይህ እንዴት ሆነ የሚለውን ስጠይቅ እኔ በሦስት ምክንያቶች የመጣ ነው የሚመስለኝ፡፡ አንዱ በጦርነት ጊዜ ሥልጣን ወደአንድ ማዕከል ለመሰብሰብ ይገደዳል፡፡ በጦርነትና በቀውስ ወቅት ያለው አሠራር በሰላም ጊዜ ካለው እጅግ የተለየ ነው፡፡ አሁን የምንገኘው ግጭትና ጦርነት ባለበት ወቅት በመሆኑ ሥልጣንን በአንድ መዋቅር በመሰብሰብ ቁጥጥርን በማጠናከር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሰውየው ስብዕና ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዓብይ አህመድ ተቀባይነት እጅግ ሰፊና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው፡፡ የሰውየውን ተፅዕኖ ከማንም ጋር የምታወዳድረው አይደለም፡፡ የእሳቸው ቅቡልነትና ተፅዕኖ ብዙ መዋቅሮችን በእሳቸው ሥር እንዲወድቁ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ዓብይ ባይኖሩ ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ይሳካለት ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ ዓብይ ባይኖሩ በእኔ እምነት ተቃዋሚዎች የተለየ የምርጫ ውጤት  ያገኙ ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ኢዜማና ሌሎች ፓርቲዎች የተሻለ ዕድል ሊኖራቸው ይችል ነበር፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የምንገኝበት የእርስ በርስ መጓተት፣ መገፋፋትና መሻኮትም ብዙ ሥልጣን ወደ አንድ ለመሰብሰብ ያስገደደ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ የብሔር፣ የሥልጣን፣ የማንነትና ሌላም ግጭት ቀውስ ፈጥሮ አደጋ ከሚያስከትል በአንድ የሁሉንም ቅቡልነት ባማከለ ሰው ሥር ብዙ ሥልጣን ቢወድቅ የተሻለ ይሆናል በሚል እምነት የተደረገም ይመስላል፡፡ ምናልባትም አራተኛ ብዬ የምወስደው ምክንያት ደግሞ የፖለቲካ ባህላችን ይመስለኛል፡፡ ድሮ ሁሉም ነገር በንጉሡ ሥር ነበር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ሁሉም በወታደራዊው ዕዝ ሥር ወደቀ፡፡ ከዚያ ሁሉንም ነገር ኢሕአዴግ ጠቅልሎት ኖረ፡፡ ኢሕአዴግ ሄዶ ዓብይ ከመጡ በኋላ ይህን ዓይነቱ ሥልጣን የመጠቅለል ባህል ላልቶ መታየት ጀመረ፡፡ ነገር ግን ትንሽ ለቀቅ ሲደረግ በሁሉም አቅጣጫ ግጭትና ጦርነት ሥርዓተ አልባ ሆነ፡፡ ትንሽ ለቀቅ ሲል የተፈጠረውን ችግር ለማረም ሥልጣኑን መልሶ መጠቅለል አስፈላጊ የሆነ ይመስለኛል፡፡ የተበታተነውን መሰብሰብ አስፈለገ፡፡ በፖለቲካ ባህላችንም ሥልጣንን በአንድ ጠቅሎ መምራት እንጂ፣ ከፋፍሎና አጋርቶ መምራት ባለመኖሩ የጠበቀው ጥቂት ሲላላ ግጭት ማስከተሉ ተሞክሮ የሰጣቸው ይመስለኛል፡፡ የቀደመውን ነገር ነው መልሰው የተገበሩት፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ቦታዎችንና አገሮችን ያውቃሉ፡፡ በሥራ ልምድም ሆነ በአካዴሚክና በምርምር ብዙ ለማወቅ ችለዋል፡፡ ከዚህ ተነስተው ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባ ወይም ብትቀስመው የተሻለ ነው የሚሉት ጥሩ ተሞክሮ ያለው አደረጃጀትም ሆነ አሠራር የማነው ይላሉ?

ኮሎኔል አስማማው (ዶ/ር)፡- ኩባን ለሦስት ወራት ተቀምጬ ዓይቼዋለሁ፡፡ የአሜሪካና የሩሲያን ደግሞ ሄዶ ከማየት ባለፈ የፈለገ ሰው በየመጽሐፉ እንደ ልብ ያገኘዋል፡፡ ሆኖም ጥሩ የሥራ አደረጃጀትም ሆነ መዋቅር ያለው ማነው ብለህ ከጠየቅከኝ የእስራኤል ነው እላለሁ፡፡ እስራኤል ዙሪያዋን በጠላት የተከበበች ናት፡፡ ሆኖም ለጠላት ተጋላጭ ላለመሆን በፖሊሱ፣ በስለላው፣ በሚሊታሪውም ሆነ በሁሉም ረገድ ራሷን በሚገባ ዝግጁ ያደረገች አገር ናት፡፡ እኛንም ብትወስድ ዙሪያችንን በጠላት የተከበብን አገር ነን፡፡ ያን የእስራኤል ዓይነት ዝግጅት ለእኛም ማምጣት ይጠቅመናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እስራኤሎቹ ያላቸው የኢኮኖሚ ውጤታማነትና ምርታማነት ለእኛ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የመስኖ ልማት ውጤታማነታቸው ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በቴክኖሎጂና በፈጠራ ሥራቸው ከጃፓኖች ጋር መቀራረብ የቻሉ ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ በአገር ቤት ብቻ ሳይሆን በውጭም ሆኖ ለአገሩ ለእስራኤል ራሱን አደራጅቶ የየራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ መቻላቸውም ለዚህ ጥንካሬ አብቅቷቸዋል፡፡

እዚህ ኢትዮጵያም እኮ ለአገሩ የሚሞትና አገሩን የሚወድ ብዙ ነው፡፡ ልክ እንደ እስራኤሎቹ አስተባብሮ በጋራ ማሠራት ከተቻለ ለአገር ጠቃሚ ውጤት ያመጣል፡፡ የእነሱ የትምህርት ሥርዓታቸውም ቢሆን ልንቀስመው የሚገባ ነው፡፡ እስራኤል ጥብቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓትን የሚከተል ማኅበረሰብ ያቀፈች አገር ናት፡፡ ነገር ግን እንደ እኛ ሳይቸገሩ ነው ባህሉንና እምነቱን ከዘመናዊነት ጋር አስተሳስረው ማደግ የቻሉት፡፡ እኛ ለምን ይህን ማድረግ አንችልም? እጅግ ቀላልና ዝባዝንኬ የሌለው በጣም ውጤታማ ነው የእስራኤሎቹ አሠራርና አደረጃጀት፡፡ እነሱ የሚሠሩትን የመስኖ ቴክኖሎጂ አምጥተን ሰፊውን መልማት የሚችል እርሻችንን ማልማት እንችላለን፡፡ የእነሱ ተሞክሮና ቴክኖሎጂ ቀላል ሲሆን ነገር ግን እጅግ ውጤታማ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ስኬታቸው የመጣው ደግሞ በዘየዱት ውጤታማ አወቃቀርና አደረጃጀት ነው፡፡ እኛም የእነሱን ውጤታማ መዋቅሮችና አሠራሮች መኮረጅና መጠቀም እንችላለን፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...