Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አርሶ አደሩን ከሸማቹ ለማገናኘት የተጀመረው ሥራ የአንድ ሰሞን እንዳይሆን በጥናት ይደገፍ

ባለፈው ሰሞን በአዲስ አበባ ገበያዎች የአንድ ኪሎ ሽንኩርት የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ 50 ብር ደረሰ ሲባል አጀብ ተብሎ ነበር፡፡ አንድ ኪሎ ሽንኩርት በዚህን ያህል ዋጋ መሸጡ በምንም ሁኔታ አግባብ አልነበረምና ‹‹ኧረ ወዴት እየሄድን ነው?›› ብሎ ሸማቹ በምሬት ጮኋል፡፡ በሸቀጦች ላይ የተጫነው የዋጋ ንረት ሳያንስ ሽንኩርትም እንዲህ ዋጋው መወደዱ ያበሳጫል፣ ያናድደል፡፡

የበለጠ ነገሩን እንድንማረርበት የሚያደርገው ደግሞ ማንም እየተነሳ ገበያውን ሲያተረማምሰው ለምን ይህ ሆነ ብሎ የጠየቀ፣ ጠይቆም ያሳወቀ፣ አሳውቆም ቀጣይነት ያለው በቂ ሕጋዊ ዕርምጃ የወሰደ አለመታየቱ ነው፡፡

አንድ ኪሎ ሽንኩርት 50.00 ብር የገባው በሸፍጥ ነው፡፡ ይህንንም መንግሥት ራሱ ነግሮናል፡፡ ሰው ሠራሽ ድርጊት ነው፡፡ ምርቱ ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከአሥር ብር በታች፣ ስድስትና ሰባት ብር ጭምር እየተሸጠም ነበር ተብሏል፡፡

እንዲህ ያለው ባልተገባ ሁኔታ ዋጋን በማናር የሚደረግ ሸፍጥ አድራጊ ወይም አድራጊዎች አሉት፡፡ ግን እንደሚገባው አይያዙም፣ አይገሰፁም፡፡ ድርጊታቸው የአንድ ሰሞን ወሬ ሆኖ የመቅረቱ ነገርም ተለምዷል፡፡

በዚህ ሳምንት ደግሞ የሽንኩርት ዋጋ እየወረደ መጥቷል፡፡ አሁን የጅምላ መሸጫ ዋጋው ቀንሷል፡፡ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋው ወይም በገበያው ያለውን ሰሞናዊ ዋጋ ስንቃኝ ደግሞ በብዙ ገበያዎች ከ16 ብር እስከ 20 ብር መሸጥ ተጀምሯል፡፡ ይህም ወትሮም ቢሆን ዋጋው 50 ብር መግባት ያልነበረበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሽንኩር 50 ብር ገባ የመባሉ ዜና ሁሉንም ያነጋገረ ነበርና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ በቅርቡ ለጉብኝት መስክ በወጡበት ጊዜ የሽንኩርት ዋጋን ተንተርሰው አንድ ኪሎ ሽንኩርት እዚህ ሰባት ብር ይሸጣል አዲስ አበባ ግን 50 ብር ነው ብለው ችግሩ በአምራችና በሸማቾች መካከል ያለው ረዥም የግብይት ሰንሰለት ስለመሆኑ መጠቆማቸው አንድ ማሳያ ነው፡፡

በዚሁ ሐሳብ መነሻነት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤም ለዋጋ ንረቱ ምክንያት የሆኑ ደላሎችና ረዥሙን የግብይት ሰንሰለት በመቁረጥ ሽንኩርት አምራቾች ሸማች ድረስ የሚደርሱበትን አሠራር እንደሚተገብሩ ባስታወቁት መሠረት አታክልት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ሱቆች መሸጥ ጀምሯል፡፡ አርሶ አደርና ሸማች በቀጥታ የሚገናኙበት የእሑድ ገበያ ደግሞ እሑድ ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በተለያዩ የአዲስ አበባ ቦታዎች ለማስጀመር ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

አስተዳደሩም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶችን ከአምራቹ በቀጥታ ሸማቹ ጋር ለማድረስ ከአምራቾች ጋር ተዋውሎ ለአዲስ አበባ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡ 50 ብር የነበረው የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ ከግማሽ በላይ ቀንሶ ከ20 ብር በታች እየተሸጠ ለመሆኑ አንዱ  ምክንያት ይኼው የአስተዳደሩ  ሰሞናዊ ዕርምጃ ብቻ ነው ተብሎ ባይታሰብም የራሱ አስተዋጽኦ ግን እንዳለው ይታመናል፡፡  

ለማንኛውም የሽንኩርትን ዋጋ ላይ ሰቅሎ በዚያው ለማስቀጠል የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ አንድን ምርት ከአምራች በቀጥታ ሸማች ጋር የማድረስ ሥራ ገበያን በማረጋጋቱ ረገድ ያለው አስተዋጽኦም ታይቷል፡፡

ደላሎችን ቆርጦ ምርትን በቀጥታ ከሸማቾች ጋር የሚያገናኝ አሠራር ካለ ብዙ ነገሮች ሊለወጡ የሚችሉ ስለመሆኑም ከሰሞኑ ዕርምጃ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቁርጥ ዕርምጃ ተወስዶ ከልብ ከተሠራ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡

 የአስተዳደሩ ሴክሬታሪያት ቢሮ ያመለከተውም በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት በግብርና ኢንዱትሪ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ችግር ከደላላ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም የደላላ ሰንሰለት በመበጣጠስ እነዚህን ምርቶች ኅብረተሰቡ በቀጥታ እንዲያገኝ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራዊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑና ይህንንም መተግበሩ ያሳየን ነገር ቢኖር የተለጠጠ የትርፍ ህዳግ ይሠራ እንደነበር ጭምር ነው፡፡

በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ችግር ለመቅረፍና ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን ለማግኘት እንዲያስችል አስተዳደሩ ከኦሮሚያና ከሌሎች የክልል አርሶ አደሮች ጋር ውል በመግባት በቀጥታ ኅብረተሰቡ ጋር እንዲደርስ ማድረጉም ቢሆን ሌሎች ምርቶችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ማገበያየት የሚችልበት ዕድል እንዳለ ያሳያል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አሠራር መተግበር በጀመረበት በዚህ ሳምንት ውስጥ የተለያዩ መጠን ያላቸው ምርቶች በተለይ ሽንኩርት በተመረጡ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና በተመረጡ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሥርጭት እየተደረገ መሆኑንም ዓይተናል፡፡

ይህ የአስተዳደሩ ወቅታዊ ዕርምጃ አሁን ካለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አንፃር አግባብ የሚባል ዕርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ፣ እንደተባለውም የዋጋ ለውጥ እንዲታይ አስችሏል ማለት ቢቻልም አሁን በከተማዋ እየገባ ነው የተባለው የምርት መጠን ከፍላጎቱ አንፃር ሲታይ ኢምንት የሚባል ነው፡፡ በእርግጥ የገበያ ትስስሩ አሁን የተጀመረ ቢሆንም በቀጥታ አምራች ወደ ኅብረተሰቡ የሚደርሰው የምርት መጠን ፍላጎቱን ያገናዘበ ካልሆነ አሁንም ከአዙሪቱ መውጣት አይቻልም፡፡

ስለዚህ ሐሳቡን በተግባር ለመለወጥ ትልቁ ነገር ከፍላጎቱ ጋር ተመጣጣኝ የሚሆን ምርት እንዲመረትና  እንዲቀርብ ማድረግ ነው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ወደ ገበያ የሚገባው ምርት መጠን እየጨመረ ከሄደ ገበያውም እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ አስተዳደሩ በገባው ውለታ መሠረት ከሚገቡ ምርቶች ውጪ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ገበያ የሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶችም ዋጋቸው እንዲቀንስ ያልተገባ የትርፍ ህዳግ እንዳይፈጠር ያስችላል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአስተዳደሩ ወቅታዊ ዕርምጃ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ግን ይህንን አሠራር በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል የተደራጀ አሠራር ሲኖረውና ያለማቋረጥ ሲያስኬደው ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማለት የምንወደው የሰሞኑ ዕርምጃ ድንገት የተወሰነና በጥናትና በተደራጀ ሁኔታ ወደ ሥራ የገባበት ነው ተብሎ ስለማይታመን ነው፡፡

ሐሳቡ እጅግ ግሩም ሆኖ የአተገባር ሥልቱ ግን በጥናት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ውጤትም ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ይህንን አዲስ የግብይት ሒደት በዕውቀት የሚመራ ራሱን የቻለ የሚያስተዳድረው ተቋም ሊኖረው ይገባል፡፡

አሠራሩ ሕግና ደንብም ኖሮት የሚሠራበት ከሆነ ውጤቱ ያምራል፡፡ በትክክል ከአምራች ሸማች ድረስ ያለውን ሰንሰለት በመቁረጥ ደላሎችን በማስቀረት እየተሠራ ነው የተባለው ሥራ በእርግጥም ለውጥ ማምጣት መቻሉን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡

ሌላው እነዚህ በውለታ ጭምር ከአምራቹ የሚመጡ ምርቶች ራሱን የቻለ ማከፋፈያ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ነው፡፡

ከአስተዳደሩ ሴክሬታሪያት መረጃ ከሸማቾች ማኅበራት ሌላ በተመረጡ ጎዳናዎች ላይ ምርት እየቀረበ ነው ከመባሉ ጋር ተያይዞ ብዙ ጥያቄ ሊነሳ ስለሚችልም ምርቱ በቀጥታ ሸማቹ ጋር ስለመድረሱ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እንዲህ ባለ ውለታ ይቀርባል የሚባለው ምርት ወቅታዊውን ንረት ለማረጋጋት ታሳቢ ያደረገ ነውና የመሸጫ ዋጋውንም መወሰን ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

ስለዚህ ዕርምጃው ተገቢ የመሆኑን ያህል እያስገኘ ያለውንም ለውጥ በመገምገም አሠራሩን ማሻሻል ይቻላል፡፡ ደላላና የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለትን መቁረጥ ከተቻለ ለውጥ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ዋናው ነገር ነገራችንን የአንድ ሰሞን አለማድረግና ቁርጠኛ ሆኖ መሥራት ብቻ ነው፡፡

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት