የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በወንጀል ድርጊት መጠርጠራቸውን አስታውቆ፣ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳባቸው ሁለት ዳኞች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው በተጠረሩበት የ267 ሚሊዮን ብር የሙስና ወንጀል ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች አቶ አዱኛ ነጋሳና አቶ አክሊሉ ዘሪሁን የሚባሉ ሲሆኑ፣ ‹‹በከባድ የሙስና ወንጀል ጠርጥርያቸዋለሁ›› በማለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረባቸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ነው፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በጥቅም በመመሳጠር ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተዋል፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ ያዘጋጁት ቱሉ ጣፋ በዳዳ የሚባል ግለሰብን የፍርድ ባለመብትና ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር የሚባል ግለሰብን ደግሞ የፍርድ ባለዕዳ መሆናቸውን የሚያሳይና የሚያስረዳ አድርገው ነው ብሏል፡፡
በተዘጋጀው ሐሰተኛ ሰነድ የፍርድ ባለዕዳ መሆኑ የተገለጸው ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሒሳብ ቁጥር (ተጠቅሷል) ላይ 267 ሚሊዮን ብር ተቀንሶ፣ የፍርድ ባለመብት ተደርጎ በሐሰት ለተገለጸው ቱሉ ጣፋ፣ በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር (ተጠቅሷል) ገቢ ሆኖ እንዲከፈለው ትዕዛዝ ለመስጠት መደራደራቸውን መርማሪ ቡድኑ ጠቁሟል፡፡
የአፈጻጸም ትዕዛዙን ለማሰጠት ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ዳኛ አቶ አዱኛ ጋር ከተደራደሩ በኋላ፣ በተጠርጣሪ ዳኛ አቶ አክሊሉ አማካይነት ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ቦሌ አንድነት ሆቴል በመገናኘት፣ አሥር ሚሊዮን ብር በሦስት የቼክ ቁጥሮችና (ተጠቅሰዋል)በጥሬ ገንዘብ 400,000 ብር እንዲተላለፍላቸው ትዕዛዝ መሰጠቱን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎች በተጠርጠሩበት ጉዳይ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን፣ የግለሰቦችን ቤት በርብሮ ማስረጃ ማግኘቱንና ግብረ አበሮችን መያዙን አስረድቶ፣ የምስክሮች ቃል ለመቀበል ከግልና ከመንግሥት ተቋማት ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ፣ ተጠርጣሪዎቹ በሕገወጥ መንገድ ኅብረት አፍርተዋል የሚል መረጃ ስለደረሰው ለማሳገድ በሒደት ላይ መሆኑንና ሌሎች የሚቀሩትን ማስረጃዎች ለመሰብሰብና ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ ሒደት ካዳመጠ በኋላ አሥር ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ፣ ለጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡