Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፍትሕ ሚኒስቴር በሕወሓት ታጣቂዎች ተፈጽመዋል ያላቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ያካተተ የምርመራ ሪፖርት ይፋ...

ፍትሕ ሚኒስቴር በሕወሓት ታጣቂዎች ተፈጽመዋል ያላቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ያካተተ የምርመራ ሪፖርት ይፋ አደረገ

ቀን:

በአዲሱ መዋቅር በፍትሕ ሚኒስቴር የተተካው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፖሊስና  ከክልል አካላት ጋር በመሆን፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች በንፁኃን ዜጎች ላይ በሕወሓት ታጣቂዎች ተፈጸመ የተባለው ኢሰብዓዊ ወንጀል ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ተደረገ፡፡

ዓርብ ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ለተመረጡ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች በፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ፈቃዱ ፀጋና የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በጋራ የቀረበው የምርመራ ሪፖርት የሚሸፍነው፣ በሕወሓት ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩና ቆይተው በሕግ ማስከበር ዘመቻው ነፃ የወጡ አካባቢዎችን እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ፣ የንፋስ መውጪያ ከተማ አስተዳደር፣ የጉና በጌምድር ወረዳ፣ የፋርጣ ወረዳ፣ እስቴ ወረዳ (በከፊል)ደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር (በከፊል)በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ ዳባት፣ ደባርቅና ዛሪማ ንዑስ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያና በፈንቲረሱ ዞን ሥር በሚገኙ እዋ፣ አውራና ጉሊና ወረዳዎች አካባቢዎች ተካሄደ የተባለው ምርመራ በሕወሓት ታጣቂዎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ብቻ ሪፖርቱ ማካተቱን አመላቷክል፡፡

ወንጀሉ ተፈጸመ የተባለው ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አካባቢዎቹ በፌዴራልና በክልል የፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር ተመልሰው እስከ ገቡበት ጊዜ ድረስ ባሉት ጊዜያት እንደሆነ የምርመራ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በምርመራው የተጎጂዎችና የቤተሰቦቻቸው ቀጥታ ምስክሮች፣ ወንጀሎቹን ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ማስረጃዎች፣ ገላጭ ማስረጃዎች፣ ኤግዚቢቶች፣ እንዲሁም የቴክኒክ ማስረጃዎች ማሰባሰቡ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን ለጊዜው በዝርዝር ማስረጃ የተለዩ የ96 ሰዎች ሞት፣ 53 የአካል ጉዳት፣ 29 አስገድዶ መደፈር፣ 11 ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ ስድስት ዕገታ፣ እንዲሁም የመንግሥት፣ የግልና የሃይማኖት ተቋማት ንብረቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውድመት መፈጸሙን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች ደግሞ በአጠቃላይ የ129 ሰዎች ሞት፣ የ54 ሰዎች የአካል ጉዳት፣ በንፋስ መውጪያ ከተማ ብቻ በ73 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል፣ እንዲሁም በርካታ ግለሰቦች ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል በአፋር ክልል ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋሊኮማ ቀበሌ መጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 240 ሰዎች ሲሞቱ፣ 42 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና በቀሪዎቹ ሦስት ወረዳዎች ደግሞ 17 ሰዎች ተገድለው፣ ለ17 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ እንዲሁም ሰባት ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ታጣቂዎቹ በተጠቀሱት አካባቢዎች ከሰላማዊ ዜጎች ንብረት በተጨማሪ በመንግሥትና በግል ተቋማት ላይ ማለትም ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ኬላዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶችና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ዘረፋና ውድመት በስፋት መፈጸማቸው መረጋገጡ ተገልጿል፡፡

የምርመራ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የሕወሓት ታጣቂዎች ይህንን መጠነ ሰፊ ጥቃት የፈጸሙበት ዋነኛ ዓላማ፣ በአሸባሪው ድርጅት የበላይ አመራሮች ውሳኔና ትዕዛዝ በብሔር ላይ የተመሠረተ የጥላቻና የበቀል ዕርምጃ ለመውሰድ፣ የተወሰነ ብሔርን እንደ ማኅበረሰብ በኢኮኖሚና በሞራል ለመጉዳት የታሰበ ነው፡፡

በተጨማሪም ፀያፍ የሆኑ ስድቦችን በመጠቀምና በመፈረጅ፣ የፌዴራል መንግሥት ተረጋግቶ አገር እንዳይመራ ለማድረግ፣ ሕወሓት ከሌለ አገር አትመራም በማለት የተዳከመ የፌዴራል መንግሥት እንዲኖር ለማድረግ፣ የሚጠቅው ማኅበረሰብ ባህሉ፣ እሴቱና መሠረታዊ ስሪቱ እንዲጠፋ ዓላማ አድርጎ የተነሳ መሆኑን በምርመራው ሒደት የታዩ እውነታዎች ያስረዳሉ ሲል ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በምርመራው ተገኙ ከተባሉት ዘግናኝና ኢሰብዓዊ የምርመራ ጭብጦች መካከል አንድን ሴት እስከ አሥራ አምስት በመሆን እየተፈራረቁ መድፈር፣ እናትና ልጅን በአንድ ላይ መድፈር፣ ከተፈጥሮተቃራኒ የወሲብ ጥቃቶችን መፈጸም፣ ልጆችን በእናቶቻቸው ፊት መድፈር፣ እንዲሁም አንዲትን ሴት ከደፈሩ በኋላ በጠመንጃ አፈሙዝ ብልቷን በመውጋት የፌስቱላ ተጠቂ እንድትሆን ማድረግ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የስምንት ወር እመጫትን ጨቅላ ልጇን በፈላ ውኃ ውስጥ እንጨምራለን በማለት እናትዋን በማስፈራራት መድፈር፣ አንዲት የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሴትን ለሦስት አስገድዶ መድፈርና ባህላዊ እሴቶች የሆኑትን የካህናት ሚስቶችንና ቆራቢ መነኮሳትን ለይቶ አስገድዶ መድፈር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል ከ30 ቀን ጨቅላ ሕፃ እስከ 70 ዓመት ሽማግሌ ድረስ ተጠቂ የሆኑባቸው ግድያዎች፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ስድስት ሰዎችን በጅምላ መግደል፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በመስጊዶች ውስጥ የነበሩ የሃይማኖት አገልጋዮች እንደተገደሉ ተገልጿል፡፡

 በዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ሟች ጥላሁን ንጉሤ የተባሉ 68 ዓመት አዛውንትን ጭንቅላታቸውን በጥይት በመምታት ገድለው ለአምስት ቀናት በቤት ውስጥ ሳይቀበሩ ሚስታቸውን ከአስክሬኑ ጋር በዚያው ቤት በማቆየት ለገዳዮች ምግብ እንዲያዘጋጁ እንዳስገደዷቸው፣ ደባርቅ ወረዳ አብርሃም ቀበሌ ሟች ዘለቀ አስመራ የተባሉ አባትን ከሕፃን ልጃቸው ፊት አንገታቸውን በማረድ ሦስት ልጆቻቸው እግራቸውንና እጁን እንዲይዙ በማድረግ፣ ከአንገታቸው እስከ ሆዳቸው በልጆቻቸው ፊት በሳንጃ አካላቸውን እንደሰነጠቁት የምርመራ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

የማኅበረሰቡ መኖሪያ ቤቶችን የሞቱ የሽብር ቡድኑ አባላትን ለመቅበሪያነትና ለመፀዳጃ ቤት ለምግብ ማብሰያነት እንደተጠቀሙበት፣ እንዲሁም ሰዎችን በማገት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደፈጸሙባቸውና በዚህም ብዙ ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በአፋር ክልል የስድስት ወር ሕፃን የእናቱን ጡት እንደያዘ በከባድ መሣሪያ ከእነ እናቱ ተመትቶ ስለመገደሉ፣ በክልሉ የስደተኛ ጣቢያ የተጠለሉ ስደተኞች በሙሉ በተኙበት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የጅምላ ከባድ ተኩስ በመክፈት እንዲያልቁ እንደተደረገ ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል አብያተ ክርስቲያናትንና መስጊዶችን ለወታደራዊ ዓላማ ከመጠቀም በተጨማሪ ማቃጠልና ማውደም፣ ለአብነትም በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኙ 22 አብያተ ክርስቲያናትና አንድ መስጊድ የሕወሓት ታጣቂዎች በከባድ መሣሪያ በመምታት እንዳወደሟቸውና ንብረቶቹንም እንደዘረፏቸው በሪፖርቱ ተብራርቷል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...