Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንሳ ፌስቡክ ሆን ተብሎ ለጥላቻ ንግግሮች እንደሚውል ማረጋገጡን አስታወቀ

ኢንሳ ፌስቡክ ሆን ተብሎ ለጥላቻ ንግግሮች እንደሚውል ማረጋገጡን አስታወቀ

ቀን:

በዮናስ አማረ

የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ፌስቡክ ሆን ተብሎ ለጥላቻ ንግግሮች እንደሚውል ማረጋገጡን አስታወቀ፡፡

የፌስቡክን ሚስጥር በቅርቡ ያጋለጡት የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሆገን፣ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴው ሆን ተብሎ ለጥላቻ ንግግሮችና ለግጭት ማባባስ ይውል እንደነበር ለአሜሪካ ኮንግረስ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ በተለይ በማይናማርና በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያበጣብጡ ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችን ሲያሠራጭ መቆየቱንም፣ የቀድሞ ሠራተኛዋ ፍራንሲስ ሆገን ማጋለጣቸው አይዘነጋም፡፡

ይህን በተመለከተ የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ ተልዕኮ የተሰጠው ኢንሳ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ የሆኑት አቶ መልካሙ የሱፍ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ፌስቡክ ሆን ተብሎ ለጥላቻ ንግግሮችና ለግጭት ማባባሻ ቅስቀሳዎች ውሏል ብለዋል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ወይም ለአገርና ለሕዝብ ደኅንነት መጠበቅ በጎ መረጃዎችን የሚያሠራጩ አገር ወዳድና አፍቃሪ ኢትዮጵያ ወገኖች፣ የፌስቡክ አካውንታቸው ተደጋግሞ ይዘጋ እንደበር አረጋግጠናል፤›› በማለት አቶ መልካሙ አስረድተዋል፡፡ እንደ ሳይበር ባለሙያው ከሆነ የእነዚህ ወገኖች የፌስቡክ አካውንት የሚዘጋው፣ የፌስቡክን ሕግና ደንቦች አክብረው በመጠቀም ላይ እያሉ ነው፡፡ ከዚህ ተቃራኒ ደግሞ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ዘር፣ ሃይማኖት ወይም ፖለቲካን መነሻ በማድረግ መከፋፈል፣ ጥላቻና ግጭት የሚሰብኩ ሰዎች የፌስቡክ አካውንታቸው ያለ ዕገዳ እንዲገለገሉበት ይደረጋል፤›› ሲሉ ነው ባለሙያው ያስረዱት፡፡

ኢንሳ በፌስቡክ ላይ የቀድሞ ሠራተኞቹ ሚስጥር ሳያወጡ አሠራሩን ሲገመግም መቆየቱን አቶ መልካሙ ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተቋማቸው ግምገማም ማኅበራዊ ሚዲያው በኢትዮጵያ ላይ አፍራሽ መረጃዎችን ለማሠራጨት መዋሉን፣ ተጨባጭ መረጃዎች መገኘታቸውን ያስረዳሉ፡፡

‹‹የተቋሙ የምሥራቅ አፍሪካ ተወካዮች ተብለው በኦሮሚኛ፣ አማርኛና በትግርኛ ቋንቋዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚሠራጩ መረጃዎችን የሚከታተሉ ሰዎችን ፌስቡክ መድቧል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፉና የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎች ሲሠራጩ ዕርምጃ አይወስዱም፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ መልካሙ፣ ይህ ደግሞ ጉዳዩ በተቋሙ ወይም ተቋሙ በመደባቸው ሰዎች ሆን ተብሎ የሚደረግ አፍራሽ ሥራ ሊሆን እንደሚችል ኢንሳ እንደሚጠረጥር አስረድተዋል፡፡

ለአሜሪካ ኮንግረስ ጭምር ቀርበው የፌስቡክን አሻጥር ያጋለጡት የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሆገን፣ ‹‹በኢትዮጵያና በማይናማር ላይ ተቋሙ ያደረገው አሻጥር ገና የመጀመርያው እንጂ፣ መጪውንም ሆነ የችግሩን ግዝፈት እንደማያሳይ›› ተናግረው ነበር፡፡ በሴትየዋ እምነት ፌስቡክ ገጹ በተገለጠ ቁጥር አዳዲስ አደጋዎችን ይዞ የሚመጣ፣ ለአሜሪካ ለራሷ ጭምር ችግር የሚደቅን ተቋም እየሆነ ነው፡፡

የቀድሞ ሠራተኛዋ በፌስቡክ ላይ ምስክር ሆነው ከመምጣታቸው በፊትም ቢሆን፣ ፌስቡክ በደንበኞች ሚስጥር ጥበቃና የምርጫ ፖለቲካን በማዛባት ክሶች በተደጋጋሚ ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ በጥላቻ ንግግርና ግጭት ቅስቀሳዎች ስሙ ቀድሞ የሚጠራው የፌስቡክ መሥራች ማርክ ዙከርበርግ፣ ሐሙስ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት በሰጠው መግለጫ ድርጅቱን ‹‹ሜታ›› በሚል ስያሜ መቀየሩን ይፋ አድርጓል፡፡

በፌስቡክ በሚሠራጩ የሐሰት መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች ፈተና እየገጠማት የምትገኘው ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ምን እንደሚሆን ለኢንሳ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ይህ በሚመለከተው የመንግሥት አካል የሚኬድበት መሆኑን ያስረዱት አቶ መልካሙ፣ በፌስቡክ ላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚኖረውን ጥቅምና ጉዳት ማገናዘብ እንደሚጠይቅና ጉዳዩን በጥሞና መከታተል እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ ይልቅ ማኅበረሰቡ በፌስቡክ ለሚፈጸሙ አፍራሽ ተግባራት አውቆም ይሁን ሳያውቅ መገልገያ እንዳይሆን፣ የሳይበር ግንዛቤ መፍጠር ላይ ሊተኮር እንደሚገባ አቶ መልካሙ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ማኅበረሰቡ ጥላቻ ቀስቃሽ፣ ሐሰተኛና ግጭት አባባሽ መረጃዎችን በፌስቡክ ሲመለከት ላይክና ኮሜንት ከማድረግ ይልቅ በቀጥታ ለተቋሙ ሪፖርት ያድርግ፤›› ሲሉ ባለሙያው አስትውቀዋል፡፡ በፌስቡክ ለሚለቀቁ አፍራሽና አገር አውዳሚ መረጃዎች ሥርጭት መጨመር ሰዎች ተባባሪ መሆን እንደማይኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከሰሞኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የሳይበር ግንዛቤ መፍጠሪያ ወር ማክበር የጀመረው ኢንሳ፣ በተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ስለሳይበር ደኅንነት ከፍተኛ ቅስቀሳ እያካሄደ ነው፡፡ ከአንድ ሳምንት አስቀድሞ የሳይበር ደኅንነት ወር መከበር ሲጀምር የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፣ ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ከ2,800 ያላነሱ የሳይበር ጥቃቶችን ማምከኑን አረጋጋጠዋል፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ተቋማትና ጥቅሞች ላይ የተነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸውን ነው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በይፋ የተናገሩት፡፡

ስሙን ‹‹ሜታ›› ብሎ የቀየረው ፌስቡክ የሚሰማበት ቅሬታና ውንጀላ በተበራከተበት በዚህ ወቅት ድርጅቱ ጫና ውስጥ መውደቁ ከሰሞኑ እየተዘገበ ነው፡፡ ራሱን የጥላቻና የግጭት መገልገያ ከመሆን መታደግ ያልቻለው ፌስቡክ፣ ስሙን በመቀየር ብቻ ከገባበት አጣብቂኝ መውጣቱ ሲበዛ እንደሚያጠራጥር የዓለም ሚዲያዎች እየዘገቡበት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...