Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዋጋን ማረጋጋት ያለሙ የእሑድ ገበያዎች

ዋጋን ማረጋጋት ያለሙ የእሑድ ገበያዎች

ቀን:

የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ብቻ ሳይሆን መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ፈትኗል፡፡ መቆጣጠር ያልተቻለው የሸቀጦች ጭማሪም የሕዝቡ ሮሮ ከሆነ ሰንብቷል፡፡

አገራዊ ሰላም ማጣትና ሌሎች ችግሮች ለኑሮ ውድነቱ የሚጠቀሱ ምክንያቶች ቢሆኑም፣ እንደ ሰንሰለት የተጠላለፈ ሕገወጥ አሠራር የሚያራምዱ ነጋዴዎች፣ ባለሥልጣናትና ደላሎች ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

መንግሥት መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋቸው እንዳይጨምሩ ለማድረግም ፖሊሲ ከማሻሻል ጀምሮ እስከ አቅርቦት ድረስ ዕርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡

ሆኖም በገበያው ያለው ዋጋ፣ ዋጋን ለማረጋጋት ተሠርቷል ከተባለው ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ እንዳልታየ ሸማቾች በምሬት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ዕርምጃዎችን ጀምሯል፡፡

 አስተዳደሩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ውጤቶችን የሚያቀርቡ አምራቾችን ከሸማቹ ጋር ለማገናኘት ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የእሑድ ገበያዎችን ማስጀመሩ ዋጋን ለማረጋጋት ከተጀመሩ ሥራዎች ይጠቀሳል፡፡

አቶ ክቡር ገና፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

በመገናኛ ቦሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ፣ ሜክሲኮ አደባባይ ፊት ለፊት፣ ፒያሳ ሸዋ ዳቦ አጠገብ፣ ቃሊቲ መናኸሪያ ፊት ለፊት፣ ጀሞ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ለእሑድ ገበያ ክፍት ሆነዋል፡፡

አምራቹንና ሸማቹን በአጭር የገበያ ሰንሰለት በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እንዲሁም የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ያለመውን የእሑድ ገበያ ማስጀመሪያ ሪፖርተር በተለያዩ ቦታዎች ተገኝቶ ገዥዎችንና አቅራቢዎችን አነጋግሯል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ የኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫላ ተገኝ እንደተናገሩት፣ ክፍለ ከተማው በተለያየ ጊዜ ገበያ ለማረጋጋት ሠርቷል፡፡ የክልል ዩኒየኖች፣ አርሶ አደሮችና የተለያዩ ፋብሪካዎች በባዛሩ በማሳተፍ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እንዲሠሩም ተመቻችቷል፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት ዘይት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝና ሌሎችንም ሸቀጦች በስፋት የቀረቡ መሆኑን፣ ዋጋቸው ከመደበኛው ገበያ ጋር ሲነፃፀር ልዩነት እንዳለው አረጋግጧል፡፡

አምስት ሊትር ዘይት 540 ብር፣ የሽሮ አተር በኪሎ 58 ብር፣ ምስር ክክ 95 ብር፣ ጨው 15 ብር እየተሸጠ ነበር፡፡ በገበያው ያሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተለያየ ዋጋ ያቀረቡ መሆኑን ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡

ለምሳሌ፣ ጨው አንዳንድ ቦታዎች 14 ብር ከ50 ሳንቲም የሚሸጡ መኖራቸውን ሌላዎቹ ደግሞ 15 ብር እየሸጡ እንደነበር አይተናል፡፡

በቀጣይ የተሻለ ግብይት እንዲኖር ይደረጋል ያሉት ኃላፊው፣ ቦታው ትራንስፖርት የሚጨናነቅበትና ሕዝብ የሚበዛበት በመሆኑ በቀጣይ እንደሚያስተካክሉ ተናግረዋል፡፡

በቦሌ ክፍል ከተማ 20 ሸማቾች እንዳሉ፣ በጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የተሳተፉት ሁሉም አለመሆናቸውን፣ በቀጣይ ሁሉም ማኅበራት ለማሳተፍና ከክልል ዩኒየኖች ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

መደበኛ ገበያ ያለው ዋጋና የሸማቾች ማኅበራት ዋጋ መጣራታቸውን የገለጹት አቶ ጫላ፣ በነጋዴውና በሸማቾች ውስጥ የፉክክር ነገር የሚታይ መሆኑን፣ ኅብረት ማኅበራቱ ዋና ዓላማ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት በመሆኑ ከመደበኛ ዋጋ ባነሰ እንዲሸጡ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ቦታዎች በተለይ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ እኩል የሚሆኑበት ሁኔታዎች መኖራቸውን፣ እሱንም ተገምግሞ በቀጣይ ለማስተካከል እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ጤፍ በመደበኛ ገበያ 53 ብር የሚሸጥ መሆኑን፣ በሸማች ደግሞ እስከ 44 ብር እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ ከክልል ዩኒየኖች ጋር በመሆን፣ አርሶ አደሩን በቀጥታ ከገዥዎች (ሸማቾች) የማገናኘት ሥራ መሥራቱም ተጠቁሟል፡፡

የካ ወረዳ አራት ኮሪያ ሠፈር ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር እንደመጡ የተናገሩት አንድ አባት የጤፍ ዓይነቶች በጥሬውና የተፈጨ ለናሙና የሚሸጡ፣ ምስር ክክ፣ አተር ክክና የፋብሪካ ምርቶችንም ለገበያ ማቅረባቸው ተመልክተናል፡፡

የሰዎች የመግዛት ፍላጎትና የገበያው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን፣ ዋጋቸው ከመደበኛ ገበያ የቀነሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጀማል አደም ከምዕራብ አርሲ ዞን ጨፌ ገበያ ማኅበር ወክለው፣ በቦሌ ክፍለ ከተማው ዩኒየን በኩል እንደመጡ ይናገራሉ፡፡

በእሑድ ገበያ ላይ 60 ኩንታል ድንች ለገበያ ያቀረቡ መሆናቸውንና አንድ ኪሎ በአሥር ብር ሲሸጡ አይተናል፡፡

ለትራንስፖርት ዘጠኝ ሺሕ ብር እንዳወጡ፣ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንጂ ብዙም ትርፍ እንደሌለው አቶ ጀማል ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የሚገኙ 50 ገበሬዎች በመደራጀት ምርቱን በቀጥታ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ማቅረብ የመጀመርያቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ገበያ ድንች ብቻ የቀረበ ቢሆንም፣ በቀጣይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ካሮት ጎመንና ሌሎች ምርቶችም ለገበያ ይዘው እንደሚቀርቡም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ቀይ ሽንኩርት በኪሎ እስከ 10 ብር፣ ጥቅል ጎመን በኪሎ ሰባት ብር ለቀጣይ ገበያ እንደሚያቀርቡም ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ ሕይወት ወርቁ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቂሊንጦ አካባቢ የተለያዩ ምርትን ለመግዛት እንደመጡና ከአንድ ዕቃ ከአሥር እስከ ሃያ ብር ከመደበኛ ገበያ ያነሰ መሆኑን ነግረውናል፡፡ በአቅራቢያቸው የእሑድ ገበያ ቢኖር ያተረፉትን ገንዘብ ለትራንስፖርት እንዳያወጡ ያግዝ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በነበረው የእሑድ ገበያ ሽንኩርት በ16 ብር ከ50 ሳንቲም እንዲሁም ሌሎች አትክልትና ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበው አይተናል፡፡

የተፈጨና ጥሬ ጤፍ ከገበያው ዋጋ እስከ 200 ብር ቅናሽ ቀርቦ ነበር፡፡ በሥፍራው ያገኘናቸው ሸማቾች እንዳሉት ገበያን ለማረጋጋት የተሰየመው የእሑድ ገበያ የአንድ ሰሞን ሆኖ እንዳይቀር ነው፡፡ በሌላ በኩል በሥፍራው መፀዳጃና ሸማቾች መኪና የሚያቆሙበት ሥፍራ አለመኖሩ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡

እሑድ ገበያው የሚካሄድባቸው ሥፍራዎች በመደበኛ ቀናት ለተሽከርካሪ ለማቆም የማይፈቀድ ከሆነ፣ በገበያ ቀን እንዲፈቀድ፣ የአካባቢ ፅዳት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው፣ የሚቀርቡ ምርቶች ተለያይነት ቢኖራቸው መልካም መሆኑን አስተያየት የሰጡን ነግረውናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ