የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ድፍን ሁለት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ወረርሽኙም በከፍተኛ ሁኔታ በመዛመት የብዙ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡
መንግሥትም ወረርሽኙ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመቀነስ በትምህርት ቤቶች፣ በሕዝብ ትራንስፖርትና በሌሎች ነገሮች ላይ ገደቦችን በመጣል የቅድመ መከላከል ሥራዎችን መሥራቱ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ከዓመት በፊት በዩኒቨርሲቲዎችና በትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን መተፋፈግ ለመቀነስ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡
ይሁን እንጂ በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በመሥራት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መንግሥት በመወሰኑ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡
የመማር ማስተማር ሒደትን ከኮቪድ-19 ፕሮቶኮል አንፃር ምን እንደሚመስል ሪፖርተር በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ቅኝት አድርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሳውዝ ዌስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ተሃድሶ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡
የተሃድሶ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ የሺዋስ መለሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በአንድ ወንበር ላይ ሁለት ተማሪዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡
የጤና ሚኒስቴርም በአንድ ክፍል ውስጥ 25 ተማሪዎች ብቻ እንዲማሩ ውሳኔ ማስተላለፉን ያስታወሱት ርዕሰ መምህሩ፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታና የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የታየውን የክፍያ ጭማሪን ምክንያት በማድረግ አብዛኞቹ ወላጆች ልጆቻቸውን በመንግሥት ትምህርት ቤት ለማስተማር በመገደዳቸው የተማሪዎች ቁጥር በፊት ከነበረው ሊጨምር እንደቻለ አብራርተዋል፡፡
በትምህርት ቤቱም 822 ወንዶች፣ 803 ሴት ተማሪዎች፣ በአጠቃላይ 1,625 ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚገኙ፣ ቁጥራቸውም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሆነ አቶ የሺዋስ ገልጸዋል፡፡
በምሳና በዕረፍት ሰዓት ላይ አብዛኞቹ ተማሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ፕሮቶኮልን እንደማይጠብቁ፣ ይኼም ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡
በተለይም በምሳ ሰዓት ምግብ ለመመገብ ረዥም የሆነ ሠልፍ በመኖሩ፣ የመተፋፈግ ሁኔታ እንደሚታይ፣ የሚታየውን ችግር ለመቀልበስ ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አክለዋል፡፡
ተማሪዎች ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲከላከሉ የፊት መሸፈኛና የአፍንጫ ጭንብል (ማስክ) እና ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን፣ ይህም ያለውን ክፍተት በተወሰነ መልኩ ሊቀርፍ እንደሚችል ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል፡፡
በወረዳም ሆነ በትምህርት ቤቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት እንዳለ ያስታወሱት አቶ የሺዋስ፣ ያለውንም ችግር ለመቅረፍ የውኃ ታንከሮች ላይ ውኃ በመቅዳት ቅድመ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ጠዋት ጠዋት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት ሙቀታቸው እንደሚለካና ድንገተኛ የሆነ ሕመም ለተሰማቸው ተማሪዎች ለዚህ ተግባር የሚውል አንድ ማዕከል እንደተዘጋጀ፣ ከአቅም በላይ ከሆነ ግን በአካባቢው ከሚገኘው ጤና ቢሮ ጋር በመሆን አስፈላጊውን የሆነ ክትትል እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡
የምገባ ሥርዓቱን በተመለከተ ለዚሁ ሥራ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ 40 እናቶች መኖራቸውን፣ እነዚህም እናቶች የተማሪዎችን የአመጋገብ ሁኔታና የምግቡን ንፅህና ቁጥጥር የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝንም ለመከላከል ከከተማ አስተዳደሩ በኩል የሚደረገውን ድጋፍ በመጠቀም፣ ለተማሪዎች በየሳምንቱ የፊት መሸፈኛና የአፍንጫ ጭንብል (ማስክ) ግብዓት እንደሚሰጣቸው አስታውሰዋል፡፡
በትምህርት ቤቱም በየቦታው ሳኒታይዘር፣ እንዲሁም ደግሞ ከውኃና ፍሳሽ ልማት ጋር በመነጋገር የማይቋረጥ የውኃ መስመር በማዘጋጀት ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲከላከሉ እየተደረገ መሆኑን የሳውዝ ዌስት አካዴሚ የላፍቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ያሬድ በቀለ ተናግረዋል፡፡
እንደ አጋጣሚ ሆኖ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ቢገኙ የመጀመርያ ዕርዳታ እንዲያገኙ ከግልም ሆነ ከመንግሥት የጤና ተቋማት ጋር ስምምነት መደረጉንና አስፈላጊው የሆነ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን አቶ ያሬድ አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎቹ የትምህርት ገበታቸውን በሚከታተሉበት ጊዜ የፊት መሸፈኛና የአፍንጫ ጭንብል እንዲያደርጉ የሚደረግ መሆኑን፣ ይህንንም ሲተላለፉ የተያዙ ተማሪዎች ላይ አስፈላጊውን የሆነ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ስለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያላቸው ግንዛቤ የጎላ እንዲሆን በራሪ ብሮሸሮችን በማዘጋጀትና መጽሐፎችን በማሳተም ከ8,000 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች እንዲሰጣቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡
ወረርሽኙንም ለመከላከል አብዛኞቹ መምህራንም ክትባት እንዲወስዱ መደረጉን የተናገሩት ርዕሰ መምህሩ፣ ይህም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አክለዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ርብርብ ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ ጤና ሚኒስቴርም በጋራ እየሠሩ ይገኛል፡፡