ወጣት ኤሞን ብርሃኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የስድስተኛ ዓመት ተማሪና የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ነው፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴና ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበርን አመሠራረትና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ኤሞን፡- የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበር የተቋቋመው ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ሲሆን በየክልሎቹም 25 ቅርንጫፍ ማኅበራት አሉት፡፡ ማኅበሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ እናት ማኅበር አለው፡፡ እናት ማኅበሩም ‹‹ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ኦፍ ሜዲካል ስቱደንት አሶሴሽን›› ይባላል፡፡ ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ142 አገሮች የሚገኙ የሕክምና ተማሪዎች ማኅበራትን ያቀፈና በየማኅበራቱ የታቀፉ 1.2 ሚሊዮን የሕክምና ተማሪዎችን ያገለግላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበር አባላት የሆኑ ሁለት ተማሪዎች ፌዴሬሽኑ ባካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ተሳትፈው ጥሩ ተሞክሮና ልምድ ለመቅሰም ችለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ በጤና ክብካቤ ላይ ምን እየሠራ ነው?
ኤሞን፡- ማኅበሩ በዘርፉ በርካታ ቁምነገሮችን እየሠራ እንደሚገኝ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ይህንንም ሥራ በጥራትና በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን እንዲቻለው ስድስት ቋሚ ኮሚቴዎችን አዋቅሯል፡፡ እያንዳንዱም ቋሚ ኮሚቴ የሚያከናውነው የሥራ ደረጃ ተለይቶ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መልኩ ከተዋቀሩት ስድስት ኮሚቴዎች መካከል አንደኛው አዲስ አበባ ውስጥ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኙ ሦስት የመንግሥት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች በሥነ ተዋልዶ ጤናና በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ያስተምራል፡፡ ትምህርቱ ያተኮረው በወር አበባ ጊዜ መወሰድ ስላለበት ንጽሕና አጠባበቅ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ሊተላለፉ ከሚችሉ ልዩ ልዩ ዓይነት በሽታዎች እንዴት መከላከልና መጠበቅ እንደሚቻልና የጡት ካንሰርን አስመልክቶ መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ ወዘተ ናቸው፡፡ ኮሚቴው ትምህርቱን ለመስጠት ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱና ዋነኛው አሥር ተማሪዎችን ያቀፈ ቡድን በመመሥረት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ ትምህርት በሦስት የትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ለምን አተኮረ?
ኤሞን፡- የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንዱ ምክንያት ማኅበሩ የዚህን ዓይነት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የመጀመርያው መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የማኅበሩ አባላት ደመወዝተኛ ስላልሆኑ ራቅ ወዳለ አካባቢ በሚገኙት ትምህርት ቤቶች ለመሄድ አስቸጋሪ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ አስቸጋሪነቱም የማኅበሩ አባላት በትምህርት ላይ ያሉ ስለሆነ ከትምህርታቸው ሊስተጓጎሉ አይገባም፡፡ የኢኮኖሚ አቅሙም አይፈቅድላቸውም፡፡ በሦስቱም ትምህርት ቤቶች በመካሄድ ላይ ያለው የማስተማሩ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ሌላ ፕሮጀክት በሚቀረፅበትና ለዚህም ተገቢ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ከተገኘ ራቅ ወዳሉ የትምህርት ቤቶች ለማዳረስ እንችላለን የሚል ሐሳብ አለን፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በሦስቱ የትምህርት ተቋማት በመካሄድ ላይ ያለው ፕሮጀክት ተሳክቷል? ወይም ግቡን መትቷል ወይ? የሚለውን መገምገም በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
በሌላ በኩል ሌላኛው ኮሚቴ ትኩረቱ በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ላይ ያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ፣ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፉ ያሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (ስትሮክ፣ ስኳር በሽታ፣ ደም ግፊት፣ ልብ ድካም) እንዴት መቆጣጠርና መከታተል እንደሚቻል ያስተምራል፣ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡ ሆስፒታላችን ጥቁር አንበሳ እንደመሆኑ መጠን በቀኑ እስከ 400 የሚጠጉ ተመላላሽ ታካሚዎች አሉ፡፡ ታካሚዎቹ ቁጭ ብለው ወረፋቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሌ እንደሚደረገው የጤና ትምህርት ይሰጣል፡፡ ይህንን የሚያስተምሩት መደበኛ ሐኪሞች ሳይሆኑ የሕክምና ትምህርት የሚከታተሉና የማኅበሩ አባላት የሆኑ ተማሪዎች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከሰኞ እስከ ዓርብ ሁለት፣ ሁለት ተማሪዎች እየተመደቡ እንዲያስተምሩ እየተደረገ ነው፡፡ ሦስተኛው ቋሚ ኮሚቴ ደግሞ በሕክምና ትምህርት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ይህም ኮሚቴ የሕክምና ትምህርት በሚሰጥባቸው 25 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ የሕክምና ትምህርቶች ካሪኩለም አቀራረፅን፣ ከዚህም ሌላ ምን ዓይነት ቴክኒካል ትምህርቶች ያስፈልጋቸዋል? በሚሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት ያደረገ እንቅስቃሴ ያከናውናል፡፡ በውጭ አገር በሚገኙ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን በተለያዩ ዘዴ በመቅሰም በአገሮች ውስጥ እንዲተገበሩ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ በአሁኑ ጊዜ በዋናነት እየሠራ ያለው መንግሥት በመደበው አሠራር መሠረት አምስት ለአንድ፣ በእኛ በኩል ደግሞ ‹‹ፒር አሲስታንስ›› እያልን በምንጠራው አደረጃጀት ወይም የቡድን አፈጣጠር በመጠቀም ነው፡፡ በዚህም እርስ በርስ የምንማማርበት፣ ልምድና ተሞክሮ የምንለዋወጥበት አካሄድ ፈጥረናል፡፡ አወቃቀሩ ወይም አደረጃጀቱ የተመሠረተው አምስት የመጀመርያ ዓመት ተማሪዎች በአንድ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ መሪነት የሚንቀሳቀሱበት አካሄድ ሲሆን፣ ስድስቱንም ዓመት በዚህ መልኩ አዋቅረነዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተደራጁት ተማሪዎች በሳምንት አንዴና ሁለቴ እየተገናኙ የትምሀርት፣ የአሠራር፣ የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ያደርጋሉ፡፡ ይህም ትልቅ ለውጥና ውጤት አፍርቷል፡፡ ከተጠቀሰው ልውውጥ ባሻገር የጊዜና የሰዓት አጠቃቀማቸውን እንዴት ማካሄድ እንደሚችሉ፣ ወደ ትምህርት ቤት ሲመጣ ሊያጋጥም የሚችለውን ፍርኃት እንዴት ሊቋቋሙና ለውጤትም የሚበቁበትን አቅጣጫ የቡድን አወቃቀሩ ሊያስጨብጣቸው ችሏል፡፡ በትምህርታቸውም ላይ ጥሩ ውጤት እያገኙ እንደመጡም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ አራተኛው ቋሚ ኮሚቴ ‹‹የሪሰርች ኤክስቼንጅ›› (የምርምር ልውውጥ) ይባላል፡፡ በሕክምና ትምህርቶች ላይ ብዙ ምርምሮች ሊሠሩ እንደሚችሉ ቢታወቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሕክምና ተማሪዎች በምርምር ላይ አልበረቱም፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ አኳያ የምርምር ልውውጥ ቋሚ ኮሚቴ ተግባሩ ምንድነው?
ኤሞን፡- ዋና ተግባሩ ተማሪዎቹ በምርምር ዙሪያ በርትተው እንዲንቀሳቀሱ መገፋፋትና ማበረታታት ነው፡፡ የማበረታታቱም ሥራ የሚከናወነው የምርምር ክህሎትን ማዳበር ላይ ትኩረት በማድረግ ነው፡፡ ይህም ከሆነ በኋላ ታላላቅ ከተባሉ ተመራማሪዎችና ሐኪሞች ልምድና ትምህርት እንዲሁም የአቻ ለአቻ የሆነ ትምህርት እንዲከታተሉ ቋሚ ኮሚቴው ጥረት ያደርጋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ምርምር ግኝቶች በዓለም አቀፍ መጽሔት ታትመው እንዲወጡና የውጭ አገር ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የአገሪቱን ምርምሮች እንዲቃኙ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ነገር ግን እዚህ ደረጃ ላይ ስላልደረስን በአሁኑ ጊዜ ያለው ትልቁ ሥራ ክህሎት ማስጨበጥ ነው፡፡
የፕሮፌሽናል ኤክስቼንጅ ሥራ ላይም ፌዴሬሽናችን ዓለምን በአንድ ላይ ለማስተሳሰር እያካሄደ ያለውን ተግባር የመከተልና ብሎም የማጠናከር ሥራም የሚያካሂድ ኮሚቴ አለን፡፡ ይህም ማለት በተለያዩ የውጭ አገሮች የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ለአንድና ለሁለት ወራት ያህል ይመጡና ያለውን ተሞክሮና ልምድ ቀስመው እንዲመለሱ ማድረግ የኮሚቴው የሥራ ድርሻ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጡት ተማሪዎች ደስ የሚላቸው ነገር ቢኖር ሌላ አገር የሌለ በእኛ አገር ብቻ የሚታዩ ልዩ ልዩ ዓይነት ተላላፊ በሽታዎች መኖራቸው ነው፡፡ በእነዚህ በሽታዎች ላይ የየራሳቸውን የምርምር ሥራ ሊተገብሩ ይችላሉ፡፡ እኛ ደግሞ እነሱ አገር ሄደን ብዙ ቴክኖሎጂዎችን፣ የሕክምና ትምህርት አሰጣጥ ክህሎቶችን የምንቀስምበትና የምናይበት መንገድን ይፈጥራል፡፡ ይህ ዓይነቱም እንቅስቃሴ ዓለምን በአንድ የማዋቀር ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ከዚህም ሌላ አገሬን እንዴት ላሳድግ የሚለውንም ፍላጎት በተግባር ለመለወጥ የሚረዳ አቅጣጫ ያስይዛል፡፡ የሰብዓዊ መብትና ሰላም (የሒውማን ራይት ኤንድ ፒስ) ቋሚ ኮሚቴም በሕክምና አሰጣጥ ረገድ ያለውን ፍትሐዊነት ይከታተላል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው አዲስ እንደመሆኑ መጠን ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
ሪፖርተር፡- በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ማኅበሩ ያለው ተሳትፎ እስከምን ድረስ ነው?
ኤሞን፡- በተለያዩ ምክንያት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ምግብ ነክና የተለያዩ አልባሳትን በመስጠት የበኩሉን ዕገዛ ከማድረግ ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ለዚህም የሚያግዙን ስፖንሰሮች አሉን፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋናነት የሚጠቀሰውና ከጎናችን ሁልጊዜ የማይለየው ጤና ሚኒስቴር ይገኝበታል፡፡ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ሴንተርም ሌላው አጋዣችንና ተባባሪያችን ነው፡፡ በአጠቃላይ ብቻችንን ሆነን የምንሠራው ነገር የለም፡፡ ሁልጊዜ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየተጣመርን እንሠራለን፡፡ አባሎቻችንም አክብሮትና ርህራሄነት የተሞላባቸው ስለሆኑ አገልግሎት የሚሰጡት በፍቅር፣ በሙሉ ልባቸውና ኃይላቸው ነው፡፡ በዚህ በቂ የሆነ የሰው ሀብትና ዕውቀት አለን ብለን እናምናለን፡፡ ማኅበራችን የተለያዩ የሕክምና ቀናትን፣ ለምሳሌ ያህልም የዓለም ስትሮክ ቀን፣ የሥነ አዕምሮ ቀን፣ ወዘተ በመሳሰሉት እንቅስቃሴ ላይም ያተኮረ ሥራ ያከናውናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ሐኪሞች ቀደም ሲል መንግሥት ነበር በየጤና ተቋማቱ የሚመድባቸው አሁን ግን ራሳቸው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ነው የተደረገው፡፡ በዚህ ላይ ያለህን አስተያየት ብታካፍለን?
ኤሞን፡- ዋናው ችግር የአገራችን ዕድገት ከሕዝቡ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ነው፡፡ እስካሁን እየተተኮረ ያለው አካሄድ ብዙ ሐኪሞችን ማፍራት ላይ ያለመ ነው፡፡ ለዚህም ብዙ የሕክምና ኮሌጆች ተቋቋሙ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከጥራት አንፃር ተመሳሳይ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሐኪሞች ያንሳሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ኮሌጆችን የማቋቋም ሥራ በችኮላ ወይም በፍጥነት የተከናወነ ነው፡፡ አርቀን ያላሰብነው፣ ግን በሁሉም የጤና ኮሌጆች ተመርቀው የሚወጡት ሐኪሞች የት ነው የሚሠሩት የሚለውን አለማየታችን ነው፡፡ ያሉት የጤና ተቋማት ድሮ የተቋቋሙ እንደመሆናቸው መጠን ከያዙት ሌላ አዳዲስ ተመራቂ ሐኪሞችን የመያዝ ወይም የመቅጠር አቅምና ቦታ የላቸውም፡፡ ከዚህም ሌላ በአገሪቱ በየዓመቱ ቢያንስ ከሁለት ሺሕ በላይ ሐኪሞች ይመረቃሉ፡፡ ሥራ ግን አያገኙም፡፡ ለዚህ ብቸኛው መፍትሔ ተጨማሪ የጤና ተቋማትን ማቋቋም ወይም ደግሞ በጤና ትምህርት ላይ ወደ ቀድሞው መለስ ብለን ብዛት ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወደፊት ብዙ ሥራ አጥ ሐኪሞች ይኖራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በመጪው አምስትና አሥር ዓመታት ሊቀየር የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊያድግ አይችልም፡፡ በመቀጠል ደግሞ ትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች ደግሞ በየዓመቱ ከመመረቅ የሚገታቸው ወይም የሚያቆማቸው የለም፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ያለን አስተያየት ጥራት ላይ ብዙ ትኩረት ቢደረግበት የሚል ነው፡፡ ወይም አሁን ባለው ሲስተም መቀጠል አይገባም፡፡ በአጠቃላይ በሕክምና ትምህርት ላይ ቁጥር ከማብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ቢተኮር ይሻላል የሚል ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት አንድ ሐኪም ለአምስት ሺሕ ሕዝብ ነው የሚለውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አንድ ሐኪም ከሃያ ሺሕ በላይ ነው እያከመ ያለው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የመገልገያ ቁሳቁሶች እጥረት ሲጨመርበት አሠራሩን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሐኪም ሆኖ ለመመረቅ ለሰባት ዓመታት የሕክምና ትምህርትን መከታተል ግድ ይላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሰባተኛ ዓመት ላይ በምን መልኩ ነው ትምህርቱን የምትከታተሉት?
ኤሞን፡- ሰባተኛ ዓመት ላይ ስንደርስ በየጤና ተቋማቱ ተመድበን አፓረንትሺፕ እንከታተላለን፡፡ ለዚህም የደመወዛችንን ግማሹን እየተከፈለን ነው አፓረንትሺፕ የምንከታተለው፡፡ ይህንን በጥሩ ሁኔታ ካጠናቀቅን በኋላ ዲግሪያችንን በመቀበል የምንመረቀው፡፡