Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር“ዳያሌሲስ” - ለሕዝበ ኢትዮጵያውያን!

“ዳያሌሲስ” – ለሕዝበ ኢትዮጵያውያን!

ቀን:

በብርሃነ ዓለሙ ገሳ

አስፈላጊ ባይሆንም የምጽፍበትን ርዕሰ ጉዳይ ለማፍታታት ያመቸኝ ዘንድ ከራሴ ታሪክ እጀምራለሁ፡፡ እኔ የዚህ መጣጥፍ ባለቤት ትውልዴ ከጉራጌ ብሔረሰብ ሲሆን፣ የተወለድኩበት ቦታ ጎማረ ደወሼ ይባላል፡፡ በታዳጊነት የዕድሜ ዘመኔ የቀዬአችን ልጆች፣ “ደወሼ ተጉማ ነሼ” ይሉኝ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ወደዚህኛው ዓለም የተፈናጠርኩት ወይም ተገፍቼ የወደቅኩት በ1950ዎቹ ግድም መሆኑን ከወላጆቼ ዘገባ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ አባቴ አባ ዝናብ ዓለሙ ገሳ በጎማረ ከይነቋምት፣ እናቴ ወ/ሮ ብዙነሽ hብቴ ደግሞ ሞህር ቅራረ ከተባለ ጎሣ ተገኝታ ጥምረት ፈጥረው ከዓለም ምዕመናን ጋራ እንድቀላቀል ምክንያት ሆኑኝ፡፡ አብዛኛውን ሥራ ፈጣሪዬ አቀነባብሮት እነሆ ሰው ሆኜ ከሰው ጋር ተቀላቀልኩ፡፡

በልጅነቴ “በጣም ሞኝ” ከሚባሉት ተርታ ስለነበርኩ ሞኝነቴ ብዙ ዋጋ አስከፍሎኛል፡፡ በጉራግኛ ቁልምጫ፣

“ብርኼ!” ሲሉኝ

“ዮ” አቤት እንደማለት እመልሳለሁ፡፡

“ሟን የሙት?” (በምድር ላይ ቀድሞ ማን ቢሞት ደስ ይልሃል?)

“የሞህር አዲ”፣ የሞህር እናት (የሞህር እናት፣ የእናቴ እናት አያቴን ማለቴ ነው)፡፡

አያቴ እንዲሞቱ እመኝ የነበረው ከሞህር ሊጠይቁን ጎማረ ድረስ ሲመጡ ከእናቴ ጋር በመተባበር እግሬንና እጄን ጥፍር አድርገው ይዘው ባህላዊውን ኮሶ ያጠጡኝ ስለነበር ጥላቻዬ ወደር አልነበረውም፡፡ የአካባቢው ሰውም ይህን ደካማ ጎኔን ስለሚያውቅ ሁሌም ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ተመሳሳይ መልስ ነበር የምሰጠው፡፡

“ብርኼ ሟን ትረምድ?” (ብርሃን ማንን ትወዳለህ?)

“ኮንቴ አባ!” (በአካባቢያችን በየሳምንቱ ዓርብ የሚቆመው ገበያ ደርሰው ሲመለሱ ከያዙት ባለ አሥር ሳንቲም ወንጂ ስኳር መዳፌ ላይ በማፍሰስ ያስልሱኝ ስለነበር ለእሳቸው የነበረኝ ፍቅር ከፍ ያለ ነበር፡፡ እኔ በሕፃንነት ዕድሜ ላይ እያለሁ የእኔ ወላጆች በአካባቢው በሀብትም ሆነ በዝና ደህና ከሚባሉት ተርታ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እኛ ቤት ብዙ ጊዜ የወተት ላም ስለማይኖር ወተት አገኝ የነበረው ከመንደሩ ነዋሪዎች በመዋጮ ነበር፡፡ በመሆኑም በአካባቢው ኅብረተሰብና በወላጆቼ ያላሰለሰ ጥረት ዓይኔን መግለጥ ቻልኩ፡፡ ሲርበኝ ያበሉኝ፣ ሲጠማኝ ያጠጡኝ፣ ስታረዝ ያለበሱኝና አንሸራቶኝ ልወድቅ ስል ምርኩዝ ሆነው ያዳኑኝ የትየለሌዎች ናቸው፡፡

ዕድሜዬ ለመጠነ አስኳላ ሲደርስ የኔታ ቴኒ ንዳ (ታዮ) ቀለም አስቆጥሮኝ ጉመር አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼ ተደመርኩ፣ መዓልትን አስቆጥሬ ተባዛሁ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ፍቅር ተካፈልኩ፡፡ ከብዙዎቹ የቤተ ጉራጌዎች ጋር ተቀላቅዬ የማይምነት ሰንኮፌን ነቅዬ ጣልኩ፡፡ እዚህ ትምህርት ቤት በወቅቱ የሕይወት ፍኖቴ ፈር እንዳይለቅ ያደረጉት የአሁኑ የዘር አቆጣጠር ቀመር ከተጠቀምን የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብና ሌሎች ተወላጆች ነበሩ፡፡

ዕውቀት የሸመትኩበት አስኳላ የስዊድን መንግሥትና ሕዝብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በዕርዳታ ያሠሩት ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት የደወሼ ቀበሌና አካባቢው ሕዝብ የጎን ውጋት ሆኖ የቆየው የውኃ ችግር የተፈታው በአየርላንድ መንግሥትና ሕዝብ ድጋፍ ነው፡፡ ለእኔ ውልደት ዕድገትና ውጤት የወላጆቼና የቄዬ ማኅበረሰብ ድጋፍ በቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ታላቅ ነው፡፡ የሁለተኛና የሦስተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለመማር ያደረግኩት ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ከትውልድ አካባቢዬ እስከ ድፍን ኢትዮጵያ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ሲልም የዓለም ሕዝብ ያደረገልኝ ዕገዛ የትየለሌ ነው፡፡

እኔ የብዙዎች ድምር ውጤት ነኝ፡፡ ሰው ሆኜ ተፈጥሬ፣ ሰው ሆኜ እንዳድግ፣ ስኬታማ ሆኜ ዕሴት እንድጨምር ያበረታቱኝ፣ አቅፈው ደግፈው እንድዘልቅ ያደረጉኝ ዘራቸውም ሆነ ጎሣቸው ለይቼ ያላወቅኳቸው የሰው ዘሮች ናቸው፡፡ የማይምነትን ጨለማ የገፈፍኩበት ትምህርት ቤት፣ ታምሜ የታከምኩበት ሐኪም ቤት፣ ኢትዮጵያውያንና የዓለም ሕዝብ ተባብረው ያሠሩት ነው፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ የተጓጓዝኩት፣ የወጣሁትና የወረድኩት፣ በሁለት እግሬ እንድቆም የተገለገልኩባቸው መሠረተ ልማቶች የኢትዮጵያ ከፍ ብሎም የዓለም ሕዝብ እጅ አለባቸው፡፡

በእያንዳንዱ የየዕለት እንቅስቃሴዬ ውስጥ የሰዎች ብርቱ ድጋፍና ዕገዛ አለ፡፡  በተማርኩባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ ዘራቸውን ያላስመዘገቡኝ ጓደኞች አሉኝ እስከ ዛሬም ድረስ፡፡ እነዚህ ጓደኞቼ በትምህርቴ ውጤታማ እንድሆን ያደረጉልኝ ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ በብዕር መንጉዬ ወይም ዘርዝሬ ስለማልጨርሰው ምን ለማለት እንደፈለግኩ አንባቢ እንደሚረዳኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በእኔ ውጤታማነት (ስክሰስ) ውስጥ እጅግ በርካታ የሰው ዘሮች ተሳትፈዋል፡፡  እኔን ሰው ለማድረግ ዕልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ አገሮች ወዳጆች ከፍ ሲልም ሕዝብ ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡ በመሆኑም እኔ ባለ ዕዳቸው ነኝ፡፡ የእኔ ዕዳ መጥፎነቱ በየዕለቱ ወለዱ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚጨምር እንዲህ በቀላሉ የሚከፈል አለመሆኑ ነው፡፡ 

በተለያዩ ቦታዎች ለእኔ መኖር ጠጠር ለወረወሩ ሁሉ ባለ ዕዳቸው ነኝ፡፡ የእኔ ድጋፍ የሚወራ እንጂ የሚከፈል ስላልሆነ “ለሽ” ብዬ ተኝቻለሁ፡፡ ኮልፌ አጣና ተራ የሚገኝ አንድ ካፍቴሪያ አዘወትራለሁ፡፡ ለሻይ ቡና ብቻ ሳይሆን፣ ለውይይትና ለክርክርም ይመቻል፡፡ ከብዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እማራለሁ፡፡ ከእነርሱ ጋር ስሆን በቀላሉ የማስተርስና የፒኤችዲ ዲግሪ የምሠራ ያህል ይሰማኛል፡፡ ጥበብ ይስሳል፣ ጥበብ ይቀዳል፡፡ ዕውቀት ከአንዱ ወደ አንዱ በቀላሉ ይተላለፋል፡፡ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ እንዲሉ፡፡ ከእነዚህ ወዳጆቼ ጊዜዬን ሳሳልፍ በአስተውሎት ተሞርጄ በዕውቀት ተሞልቼ ከዓለም ምዕመናን ጋር ለመቀላቀል ሞራሌ ይገነባል፡፡ ‹‹ሐሳብና ሐሳብ ይፋጩ ይጋጩ፣ በዕውን በቁም ነገር በጋራ እስኪቋጩ፤›› እንዲል መጽሐፉ፣ ሐሳብ ከሐሳብ አፋጭተን ሕይወት ላይ ነፍስ እንዘራለን፡፡ እንዲህ ሲሆን ልቤ እጅግ ይሻቅላል፡፡ አንዱ በዓይን ስለሚያውቀኝ ከየት መሆኔን ማወቅ ፈለገ፡፡ ቀረበኝ፣ ቀረብኩት፡፡ አንድ ጠረጴዛ ተጋርተን ወግ ጀመርን፡፡

“ዘርህ ምንድነው?”

“ዘር ማለት?”

“አማራ ነህ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ…?”

“ዘር ምን ያደርግልሃል?”

“ለመቀራረብም ለመራራቅም ከዘር መነሳት ስላለብን ነው”፡፡

“ዘር የእህል ዓይነት ለመለየት እንጂ ሰውማ በሰውነቱ እንጂ እንደምን በዘሩ ሊመዘን ይገባል?”

መልስ ከመስጠቴ በፊት ሰው መሆኔን ለማሳየት መረቤን ዘረጋሁ፡፡ መጀመርያ በፍቅር ሚሳይል የተመረጡ የሰውዬው ዒላማዎችን መደብደብ፡፡ ሰብዓዊነትን መስበክ ሳይሆን ሆኖ መገኘት፡፡ ከዚያ “ዋንጫችን ይሞላ ድካማችን ይቅለጥ፣ ሞት እንኳ ቢመጣ በደስታችን ይዋጥ”፡፡

ስለዘርና ዘረኝነት ብዙ ጊዜና ብዙ ሰዓት አወራን፡፡ ስለዘሬ ከመንገሬ በፊት የሚሰማኝንና የማምንበትን ገለጽኩለት፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተናገሯቸው ተብለው ከሚጠቀሱላቸው አባባሎች መካከል፣ “ከትልቅ ወይም ከትንሽ መወለድ ሳይሆን ራስን ለታላቅ ሙያና ክብር መውለድ ነው”፡፡ ውስጤን እኔ “የእገሌ ዘር ነኝ” ብዬ ከማወጄ በፊት መጀመርያ ዕዳዬን መክፈል እንዳለብኝ ነገርኩት፡፡ ከተወለድኩበት አካባቢ ጀምሮ የአገሬ የኢትዮጵያ እንዲሁም የዓለም ሕዝብ ያደረገልኝ ድጋፍ በገንዘብ ቢሰላ አይደለም እኔ ወደፊት የሚመጡ ዘመዶቼ ከፍለው የሚጨርሱት አይደለም፡፡

ተወልጄ ባደግኩበት ዳውሺ/ቦሌ ገበያ የነበረው የዘመናት የቦታ ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ትግል ውስጥ የአየርላንድ መንግሥትና ሕዝብ ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡  የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩበት ትምህርት ቤት ዕውን ለማድረግ የሲዊድን መንግሥትና ሕዝብ፣ የታከምኩበት የአጣጥ ሆስፒታል በዚያ ክፉ ጊዜ ለውጤት ለማብቃት በተደረገው ያላሰለሰ ተጋድሎ የጣሊያን መንግሥትና ሕዝብ የተጫወቱት ሚና እጅግ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ እኔ የኢትዮጵያና የዓለም ሕዝብ ድምር ውጤት ነኝና በመሆኑም ፀንቶ የሚወራ እንጂ የሚከፈል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በገንዘብ የሚሰላ አይደለምና! የርዕሳችን ጭብጥ ለማምጣት ይህን ያህል ከተንደረደርን ራሳችንን ለመጠየቅ ያመቸን ዘንድ ጥቂት ነጥቦችን እናንጥብ፡፡

እኔ ብርሃነ ዓለሙ፣ ዘር የሚባለው ውጥንቅጥ ውስጥ ከመግባቴ በፊት የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ፣ የደቡብ፣ የሲዳማ፣ የቤንሻንጉል፣ የሶማሌ (የመላው ኢትዮጵያውያን)፣ የአፍሪካ፣ ብሎም የዓለም ሕዝብ ዕዳ መክፈል ይኖርብኛል፡፡ ይህች አገር ወዴት እንደምትሄድ፣ በማን እንደምትመራ ግራ ይገባል፡፡ የእኛ ነገር ለንግግርም ሆነ ለአስተያየት አይመችም፡፡ በዓለም ላይ በድህነቷ ተጠቃሽ የሆነች ኢትዮጵያ እንዲህ መከራዋ ይብዛ! አዬ የእኛ ነገር አለች አሉ ቀበሮ፡፡ “ኢትዮጵያ” በምትባል በገዛ የአገሩ ስም፣ በባንዲራው፣ በታሪኩና በቋንቋው… የማይስማማ፣ ዘር እየቆጠረ የሚዋጋ፣ የሚጋደልና የሚጫረስ ሕዝብ ያለባት አገር ኢትዮጵያ፡፡ 

በኢትዮጵያ ያልተፈጸመ የግፍ ዓይነትም ሆነ ወንጀል ምን አለ? እኛ ደማችን መመርመር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ከተፀናወተን ክፉ ደዌ ለመፈወስ አሁን ያለው ደማችን በዳያሌሲስ ሙልጭ ተደርጎ ወጥቶ በአዲስ ደም መተካት ይኖርበታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥር ነቀል ዕርምጃ ካልተወሰደ ልንፈወስ አንችልም፡፡ ኤሎሄ ኤሎሄ ደማችን ይመርመር ደያሌሲስ ለመጀመር፡፡

ሰው ተገድሎ አስክሬን የሚዘቀዘቅበት፣ በጅምላ ሰው የሚፈጅበት፣ የአስከሬን ክምር በኤክስካቫተር ታፍሶ የሚቀበርበት አገር ኢትዮጵያ፡፡ ዕዳዬን ስጨርስ ብወስን ደስ ይለኛል፡፡ የብዙዎች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተጋመደ መሆኑን ለመረዳት የጋብቻ፣ የትምህርቱን፣ የማኅበራዊ ሕይወቱን፣ የሐዘን የደስታውን መስተጋብር መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ካጋጠሙኝ ሥፍር ቁጥር ከሌላቸው ሁኔታዎች አንዱን ብቻ አንስቼ መጣጥፌን ልቋጨው፡፡ እኔ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ሦስት መጻሕፍት ለፍሬ አብቅቻለሁ፡፡ ለፍሬ በማብቃቱ ሒደት የመጀመርያ መጽሐፌን ለማሳተም ብዙዎች ተረባርበዋል፡፡ ሁለተኛውን መጽሐፌን ሙሉ ወጪውን የሸፈነው እዚህ ስሙን የማልጠቅሰው አንድ የትግራይ ተወላጅ ሲሆን፣ ሦስተኛው መጽሐፌን ደግሞ አብዛኛው ወጪውን የሸፈነው የስልጤ ብሔረሰብ ተወላጅ ነው፡፡ እንደምን የዚህ ብሔረሰብ ጠበቃ ነኝ ብዬ ለማለት ሞራሉ ይኖረኛል?

ስለሆነም እኔ ባለ ዕዳ ነኝ፡፡ ያውም ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ፡፡  በሙስሊሙ እምነት ታላቅ አስተምህሮ ያሌላቸው ነብዩ መሐመድ (ሶለላ አለይወሰለም) ዘረኝነትን ሲገልጹት ምን ነበር ያሉት? “ዘረኝነት ጥንብ ነው!” አይደል? ደህና ሁኑልኝ፣ ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...