በአማኑኤል ይልቃል
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የኮቪድ-19 ፋይዘር ክትባት ኢትዮጵያ መድረሳቸውን አስታወቀ፡፡ አሜሪካ እነዚህን ክትባቶች ለኢትዮጵያ የሰጠችው፣ የኮቪድ-19 ክትባት በደሃ አገሮች በፍትሐዊነት እንዲዳረስ በተመሠረተው ኮቫክስ ዓለም አቀፋዊ ጥምረት ሥር ነው፡፡
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የሰጠችው ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ክትባት ከዚህ በፊት ከሰጠችው ጋር ሲደመር፣ የለገሰችው የክትባት መጠን ወደ አራት ሚሊዮን ደርሷል፡፡ አሜሪካ አሁን ለኢትዮጵያ የሰጠችው የክትባት መጠን ለኢትዮጵያ ከተበረከቱት ውስጥ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ለኢትዮጵያ የተለገሰው የፋይዘር ክትባት ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ መድረሱን ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አሜሪካ የኮሮና ክትባት ለኢትዮጵያ የለገሰችው ከፖለቲካ ነፃና ሕይወትን ማዳን ብቸኛ ግብ በማድረግ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ ኢትዮጵያ የአሜሪካ የቅርብ አጋር መሆኗን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመጋፈጥ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትሆን ተናግረዋል፡፡
ኮቫክስ የተሰኘው ዓለም አቀፋዊ ጥምረት በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች የኮቪድ-19 ክትባት በፍትሐዊነት የማዳረስ ዕቅድ አለው፡፡ በዚህ ጥምረት አማካይነትም ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከ5.2 ሚሊዮን በላይ የአስትራዜኒካና የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶችን መቀበሏ ይታወሳል፡፡