- ሚኒስቴሩ የአደረጃጀትና የባለሙያዎች ምደባ እንደተጠናቀቀ አገልግሎቱን እንደሚጀምር አስታውቋል
ቀደም ሲል የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተብሎ የሚጠራው መሥሪያ ቤት ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመዋሀዱ ምክንያት፣ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ላልታወቀ ጊዜ መቋረጣቸው እንግልት መፍጠሩ ተገለጸ፡፡
ቅሬታቸውን ለሪፖርተር የገለጹ የፍጥነት መገደቢያ አስመጪና ገጣሚ ድርጀት ባለንብረቶች እንዳስታወቁት፣ የትራፊክ አደጋ መቆጣጠሪያዎችን ለመግጠም ለተዋዋሏቸው ደንበኞች መሣሪያውን ቢገጥሙምም ሰሌዳ ለማግኘት የሚያስችለውን ደብዳቤ ባለሥልጣኑ በአዲስ መዋቅር ሥር በመጠቃለሉ ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ አገልግሎቱ ተቋርጧል፡፡
ባለሥልጣኑ አገልግሎቱን በማቋረጡ ደንበኞቻቸው ሰሌዳና ሊብሬ ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የተቋሙ አደረጃጀት ባለመጠናቀቁ አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልተቻሉ ተናግረዋል፡፡
አንድ ድርጀት የፍጥነት መገደቢያ ከገጠመ በኋላ በትራንስፖርት ባለሥልጣን ሲስተም ላይ ታይቶ ተሽከርካሪው ሰሌዳና ቦሎ ቢያገኝ አንቃወምም የሚል ቅጽ 3 የሚባል ደብዳቤ እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ደብዳቤ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ከባለሥልጣኑ ባለማግኘታቸው ቅሬታቸውን በእነሱ ላይ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ደብዳቤውን ለማግኘት ሲኬድ ባለሥልጣኑ መዋቅር እየተሠራለት ስለሆነ አገልግሎቱን ማግኘት እንደማይችሉ እንደሚገለጽላቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ መቼ አደረጃጀቱ ተሠርቶ እንደሚያልቅ በትክክል የሚመልስ አካል እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ወደ ባለሥልጣኑ ቢሮ ሲኬድም ከሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ አገልግሎት ሰጪዎችን ለማግኘት እንደማይቻል ተገልጿል፡፡
በባለሥልጣን ደረጃ የተዋቀረ አንድ መሥሪያ ቤት ለአንድ ወርና ከዚያም ለበለጠ ጊዜ ሲዘጋ መንግሥት ከአገልግሎቱ ከሚያጣው ገቢ ባሻገር በዜጎች ላይ ቅሬታዎችን እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎችም የኦንላይን ሲስተሙ በመቋረጡ ምክንያት ሰሌዳ መስጠት እንዳልቻሉና ችግሩ ውስብስብ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ሌላ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ቅሬታ አቅራቢ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ አዲስ ተሸከርካሪ ላይ የፍጥነት መገደቢያ ገጥመው ታርጋ ለማግኘት የሚሰጠውን ደብዳቤ ለማግኘትና ለደንበኞች መስጠት አልተቻለም፡፡ ይህም በዋናነት የሆነው በአዲሱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አወቃቀር እንዲቀየር የተደረገው ባለሥልጣን የማኅተምና ተያያዥ ጉዳዮችን ለውጥ አድርጎ አገልግሎቱን መስጠት እስኪችል ድረስ፣ በተፈጠረ ሰፊ የጊዜ ክፍተት መሆኑ እንደተገለጸላቸው ገልጸዋል፡፡
በትራንስፖርት ባለሥልጣን ቢሮዎች ስለጉዳዩ ለማወቅ ተደጋጋሚ ጥረቶችን እንዳደረጉ የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ አገልግሎቱ እስከሚጀመር ጠብቁ ከማለት ውጪ የሚሰጣቸው ምላሽ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
ከፍጥነት መገደቢያው ጋር ብቻም ሳይሆን ከፌዴራል መንጃ ፈቃድ ጋር ተያይዞ ያሉ አገልግሎቶች፣ ከውጭ የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ያሉ አገልግሎቶች እየተሰጡ ስላልሆነ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴርና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ወደ አንድ መዋቅር ሥር እንዲጠቃለሉ በመወሰኑ፣ ሚኒስቴሩም ሆነ ባለሥልጣኑ የድሮው አደረጃጀታቸው ፈርሶ አዲስ በተሰየመው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አደረጃጀት ሥር እንደሆን ተደርጓል፡፡
ይህንን አዲስ አደረጃጀት በማስተካከል በሽግግር ሒደት ላይ የሚያጋጥሙ መስተጓጎሎች እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ እንዳልካቸው፣ አንዳንድ አንገብጋቢ አገልግሎቶችን አሁን ባለው ሁኔታም መልስ እንዲያገኙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም መካከል ለድንበር ተሻጋሪ የጭነት አሽከርካሪዎች ሲሰጥ የነበረውን የይለፍ ፈቃድ አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡
ሌሎቹን አገልግሎቶች ደግሞ በአደረጃጀቱ ወይም ባለቤት ባለው የዲፓርትመንት ዳይሬክተር ወይም ባለሙያ ታይቶ ምላሽ የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች የባለሙያዎች ምደባና የአደረጃጀት ሥራዎች ተጠንተው ስለተጠናቀቁ፣ በቀጣይ ቀናት ውስጥ አገልግሎቶቹ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ብቻ ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ብቻ በመሰጠታቸው አላስፈላጊ ወጪ፣ መጉላላቶችና የዕዝ ሰንሰለቶች አገልግሎቶችን ሲያንዛንዙ እንደቆዩ የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ እነዚህ አገልግሎቶች በክልልና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች እንዲሰጡ የተለዩ ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ አገልግሎቶች በዝርዝር የትኞቹ ናቸው የሚለው በቀጣይ እንደሚገለጽ፣ ለአብነትም የፌዴራል ወይም የአገር አቋራጭ መንጃ ፈቃድ አገልግሎት ቀደም ሲል ሲሰጥ የነበረው በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በኩል እንደነበረና አሁን ግን ክልሎች መስጠት እንዲችሉ መፈቀዱ ተጠቃሹ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እያንዳንዱን የሥራ ክፍል የሚመራ አመራርንና ባለሙያን በአጠረ ጊዜ መድቦ በማጠናቀቅ አገልግሎቶችን ጥራታቸውን ጠብቆ ለመስጠት ዝግጅቶች እንደተደረጉ ያስታወቁት አቶ እንዳልካቸው፣ በዚህ ቀን እነዚህ አገልግሎቶች መሰጠት ይጀምራሉ የሚለውን ግን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡