Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የድንጋይ ከሰልን ከውጭ ማስገባት እንዲቆም ውሳኔ ማሳለፉ ታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርት መሸጫ ዋጋ ሊወጣ ነው

በአሸናፊ እንዳለ

የማዕድን ሚኒስቴር የድንጋይ ከሰል ከውጭ ማስገባት እንዲቆም ውሳኔ ማሳለፉ ታወቀ፡፡ በአገር ውስጥ ለሚመረቱ የተለያዩ ዓይነት የድንጋይ ከሰል ምርቶች፣ እንደ ጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የመሸጫ መነሻ ዋጋ ትመና ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

‹‹አሁን ያለው የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል ዋጋ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ያልተቀየረና እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እሱም በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ፍላጎት ብቻ እየተወሰነ በመሆኑ አምራቾችን እየጎዳ ነው፤›› ሲሉ የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ መገርሳ በተለይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ተመን ለአምራቾች እንዲሁም ለድንጋይ ከሰል ተጠቃሚ ፋብሪካዎች የትርፍ ህዳግ የሚወስን ሲሆን፣ ነባሩን ዋጋ ከፍ እንደሚያደርግ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአገር ውስጥ ድንጋይ ከሰል በማውጫ ቦታዎች (Quarry) በቶን በ1,665 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ በመሀል በደላሎች ሰንሰለት ዋጋው እንዲንር ተደርጎ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋ ሲደርስ ግን በቶን ከ3,500 ብር እስከ 5,000 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከውጭ ከሚገዛው በሦስት እጥፍ ያነሰ ነው ተብሏል፡፡ በሎጂስቲክስ ምክንያት ከውጭ የሚገባው የአንድ ቶን ድንጋይ ከሰል ዋጋ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ12,000 ብር ወደ 17,000 ብር ማሻቀቡ ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የደንጋይ ከሰል ከጭልጋ ጀምሮ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከምዕራብ ኦሮሚያ እስከ ደቡብ ክልሎች ይገኛል፡፡ እንደ ቦታው የጥራት ደረጃው የሚለያይ ሲሆን፣ በአንድ ቦታ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ የካርቦን መጠን ልዩነት አለው፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሥልጣን የጥራት ደረጃዎችን ለእያንዳንዱ አካባቢ እያወጣ ሲሆን፣ በወጣው ደረጃ መሠረት ማዕድን ሚኒስቴር መነሻ ዋጋዎቹን በጥቂት ወራት ውስጥ ለመተመን ጥናት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ነገር ግን የድንጋይ ከሰል አምራቾች ማኅበር በበኩሉ ዋጋውን መተመን ያለበት ራሱ መሆኑን፣ በዚህም ላይ እየሠራ እንደሆነ የማኅበሩ አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዋጋውን የአምራቾችን ጥቅም በማስጠበቅ ለመወሰን ጥናት እያረግን ነው ሲሉ የማኅበሩ አባላት ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ማዕድን ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት ከአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል አውጪዎች ጋር ባደረጉት ምክክር፣ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ለመተካት ውሳኔ መተላለፉን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በዓመት የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት 280 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ጥረት የጀመረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከ500 ሺሕ ቶን በላይ ከአገር ውስጥ ቀርቦ 56 በመቶ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ሸፍኗል፡፡ እስካሁን በጥናት የተረጋገጠው ኢትዮጵያ ከ250 ሚሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ዕምቅ ሀብት ቢኖራትም፣ ፋብሪካዎች ‹‹ሙቀት የማመንጨት ጥራቱ ከደቡብ አፍሪካ ከሚገባው በታች ስለሆነ ማሽን ያበላሽብናል›› በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በማዕድን ሚኒስቴር ለአሥር ድርጅቶች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን አስገብተው፣ የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ከሚገባው ጋር እኩል እንዲያደርጉ በልዩ ትዕዛዝ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መከፈቱን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም መሠረት ኢስት አፍሪካ ትሬዲንግ፣ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን፣ ቱሬ ትሬዲንግ፣ ካፒታል ሲሚንቶ፣ ናሽናል ማይኒንግ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው ኦሮሚያ ማይኒንግ፣ ሪል ማይኒንግ እንዲያስገቡ ልዩ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ ማጠቢያዎቹን ለማቋቋም ዲልቢ ሞዬ፣ ጦላይ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ያዩና ካማሺ የተመረጡ ሲሆን እነዚህ ቦታዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ቀለበት ውስጥ የሚያርፉ ናቸው፡፡

‹‹ማሽኖቹን ከውጭ አዘናል፣ በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ወደ ተመረጠው ቦታ ቢደርስልን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተክለን ሥራ መጀመር እንችላለን፡፡ ነገሮች በጣም ቢጓተቱ እንኳ ግፋ ቢል በስድስት ወራት ውስጥ ከውጭ የሚገባውን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ይቻላል፤›› ሲሉ የሪል ማይኒንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋጋሪ ተመስገን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አንዱ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን 300 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ውስጥ የሚገኘውን እንደ አፈር፣ ሰልፈርና ሌሎች ጥራቱን የሚያወርዱ ይዘቶችን ለይቶ በማውጣት ለሌላ ምርት ግብዓት እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የታጠበው የድንጋይ ከሰል የካርቦን መጠኑ ከፍ ሲል በኪሎ ግራም 6,000 ኪሎ ካሎሪ ማመንጨት ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከቦታ ቦታ ቢለያይም የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ከ2,500 ኪሎ ካሎሪ እስከ 5,500 ኪሎ ካሎሪ ብቻ እንደሚያመነጭ ይነገራል፡፡

ሪል ማይኒንግ ከጅማ 70 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የድንጋይ ከሰል እያወጣ ለሐበሻ፣ ለዳንጎቴና ለደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲያቀርብ የነበረ ሲሆን፣ ለማጠቢያ ማሽኑ በአካባቢው ሁለት ሔክታር መሬት ተሰጥቶታል፡፡ ማጠቢያው ሲተከል በዓመት ከ200 ሺሕ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል በማጠብ፣ የሁለት ሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል አቶ ዋጋሪ ገልጸዋል፡፡

‹‹80 በመቶ የማሽኑን ወጪ ከባንክ አግኝተናል፡፡ ከጠቅላላ ዋጋው 60 ሚሊዮን ብር ከራሳችን እንሸፍናለን፡፡ አሁን ናሙናውን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አስጠንተንና ማሽኑን ዲዛይን አስደርገን ግዥውን አዘን እስኪለቀቅ እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች