የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላ አገሪቱ፣ በአገር ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከልና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ በሚል፣ ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለስደስት ወራት ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡
ለአዋጁ መውጣት በተለይም የሕወሓት ታጣቂ ቡድንና ግብረ አበሮቹ እንቅስቃሴ በአገር ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ ጉልህና አደጋ የደቀነ በመሆኑ፣ እነዚህ አካላት ለእኩይ ዓላማቸው መሳካት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በንፁኃን ዜጎች ላይ እየፈጸሙት ያሉት ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎችም ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢሰብዓዊ ጥቃቶች እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ከቀጥተኛና መደበኛ የውጊያ ዓውድ በተጨማሪም ሕወሓትና ግብረ አበሮቹን ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች፣ ከሰላማዊ ዜጎች ጋር በመመሳሰል በሕዝብና በአገር ላይ የደቀኑትን ከፍተኛና ተጨባጭ የደኅንነት ሥጋት በመኖሩና ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ ምኞት ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እየሠራ መሆኑን አንስቷል፡፡
በመሆኑም የተገለጹት በአገር ህልውና ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግና ተግባራዊ ማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት አዋጁ መውጣቱን አመላክቷል፡፡
የአገር ህልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው አዋጅ፣ በመላ አገሪቱ የሚተገበር ሆኖ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በክልል ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት አማካይነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በበላይነት ይመራዋል ተብሏል፡፡
በዚህ መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የፀጥታ አካል በማሰማራት፣ ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል፣ ዕድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱና የጦር መሣሪያ የታጠቁ ዜጎች ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲቀበሉ፣ ወይም ይህን ማድረግ የማይችሉ ሲሆን በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ሊያዝ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡
‹‹የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን ይችላል፣ ማናቸውም የሕዝብ የመገናኛና የሕዝብ መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል፡፡ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል›› ተብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚችል አዋጁ ይገልጻል፡፡
ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማናውንም ቤት፣ ሕንፃ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፡፡ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሣሪያዎችን መውረስ ይችላል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቀቁ ለማዘዝ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡
በተመሳሳይ ከፍተኛ የፀጥታ ችግርና ሥጋት በተፈጠረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የአካባቢ አመራር መዋቅርን በከፊልም ሆነ በሙሉ፣ ማገድ፣ መለወጥና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት ይችላል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራልም ሆነ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚጠረጥረውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት እንቅስቃሴ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራል ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚያምነውን የመገናኛ ብዙኃንን ወይም ጋዜጠኛ በሚመለከተው ባለሥልጣን በኩል እንዲታገድ ወይም ፍቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል፡፡ ተመጣጣኝ ኃይል ስለመጠቀምና የማይታገዱ መብቶች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በዚህ አዋጅ የተመለከቱ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎችን ለማስፈጸም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሕግ አስከባሪ አካላት ተመጣጣኝ ኃይል እንዲጠቀሙ መመሪያ ለመስጠት ይችላል ይላል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በአዋጁ መሠረት የሚያወጣቸውን መመሪያዎችና የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች የመቀበል ግዴታ እንዳለበት አስቀምጧል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዓላማ የሚቃረን፣ የሚቃወምና ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሠራጭት ይከለክላል፡፡
እንዲሁም በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የገንዝብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ስለመሆኑ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ መከልከሉንና ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወይም ሌሎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው የፀጥታ አካላት ወይም ከነዚህ አካላት ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደተከለከለ አስቀምጧል፡፡
በተጨማሪም በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ የመንጃ ፈቃድ፣ የሠራተኛ መታወቂያ፣ ፓስርፖርት ወይም ከነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስን ይከለክላል፡፡ ከነዚህ የመታወቂያ ሰነዶች መካከል የትኛውም የሌለው ሰው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ ዝርዝር የአፈጻጸም መመርያ ባወጣ በሁለት ሳምንት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የቀበሌ፣ የወረዳ የፀጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ በመመዝገብ ጊዜያዊ የመታወቂያ ወረቀት የመያዝ ግዴታ አንዳለበትና ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሒደት ላይ የሥራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈጸም የተከለከለ ስለመሆኑ አዋጁ ያብራራል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማገዦር ሹም የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ስለመቋቋሙ የገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ ለመጭዎቹ ስድስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡
የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎችና በአዋጁ መሠረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደጥፋቱ ክብደት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል፡፡