Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ኢንሹራንስ የዓረቦን ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደጉን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 290.3 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉንና አጠቃላይ የዓረቦን ገቢውን በ44 በመቶ በማሳደግ 1.28 ቢሊዮን ብር ማድረሱን አስታወቀ፡፡

ኩባንያው ቅዳሜ ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ ዘንድሮ ያስመዘገበው ትርፍ የ31 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ኩባንያው በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶት የነበረው የትርፍ መጠን 221.1 ማሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ይህም የ2013 የሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠኑ ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ያሳያል፡፡

ኩባንያው የዓረቦን ገቢውን በተመለከተ በሪፖርቱ እንደገለጸው፣ ከጠቅላላ ወይም ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ከ952.2 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ያሰባሰበ ሲሆን፣ ከሕይወት የኢንሹራንስ ዘርፍ ደግሞ 332.6 ሚሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ አግኝቷል፡፡

ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 1.28 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ ያስመዘገበው የዓረቦን መጠንም በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛው ሆኖ የሚመዘገብ መሆኑን የኩባንያው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የ2013 የሒሳብ ዓመት የዓረቦን መጠን በግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ባገኘው የዓረቦን መጠን ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 332.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የዓረቦን መጠን ደግሞ ከቀዳሚው ዓመት ሲነፃፀር የ181 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ኩባንያው ከሕይወት ኢንሹራንስ የዚህን ያህል ደረጃ ዕድገት ሲያሳይ የመጀመርያው ነው ተብሏል፡፡

የኩባንያው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ሕይወት ነክ ላልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የቀረበበት የካሳ ጥያቄ መጠን 450.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ይህም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ ከዋለው ገንዘብ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የተሽከርካሪ ወይም የሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ ነው፡፡ በመረጃው መሠረት በ2013 የሒሳብ ዓመት ለሞተር ኢንሹራንስ የተከፈለው 339.0 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ሲነፃፀር ለሞተር ኢንሹራንስ የተከፈለው ካሳ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ኩባንያው ከሞተር ኢንሹራንስ ቀጥሎ ከፍተኛ የካሳ ክፍያ የተጠየቀበት ዘርፍ የማሪን ኢንሹራንስ ነው፡፡ ለማሪን የተከፈለው የጉዳት ካሳ 31 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደግሞ የኢንስታሪንግ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ ለዚህ ዘርፍ የተከፈለው የጉዳት ካሳ 24 ሚሊዮን ብር መሆኑን ዓመታዊ ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ ይህ የካሳ ክፍያ ምጣኔ ለሞተር ኢንሹራንስና ለሌሎች የመድን ሽፋኖች የሚከፈለውን ከፍተኛ ልዩነት የሚያመለክት ነው፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ መስከረም 1987 ዓ.ም. በ456 ባለአክሲዮኖች ተመሥርቶ ታኅሳስ 1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የባአክሲዮኖችን ቁጥር ከ1670 በላይ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታል መጠኑም 754.8 ማሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ከ600 በላይ ሠራተኞች ያሉት ኩባንያው በመላ አገሪቱ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቅርንጫፎች ቁጥር 60 አድርሷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች