Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከአዲሱ ክልል የሚቀዳው ባህላዊ ዕርቅ

ከአዲሱ ክልል የሚቀዳው ባህላዊ ዕርቅ

ቀን:

ለሦስት አሠርታት ያህል ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር የነበሩት የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በአንድነት ሆነው የራሳቸውን ክልል ዕውን ያደረጉት ነዋሪዎቹ መስከረም 20 ቀን 2014 .. በተካሄደው ውሳኔ ሕዝብ (ሪፈረንደም) ነው፡፡ የክልሉም መጠርያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሆኖ የሪፐብሊኩ 11ኛ ክልል ሆኖ መቋቋሙም ይፋ ሆኗል፡፡

አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳን አቅፎ በአዲስ ክልልነት እንዲደራጅ የተደረገውና በየምክር ቤቱ ይበልታን የተጎናፀፈው፣ የአካባቢዎቹ ኅብረተሰብባህላዊ እሴቶች ትስስር፣ በሥነ ልቦናዊ አንድነት፣ በቋንቋ ተዘምዶ፣ በታሪክና በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ መቀራረቡ ነው፡፡

በሰሜን ከኦሮሚያ ክልል፣ በምሥራቅ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በምዕራብ ከጋምቤላ ክልል፣ እንዲሁምደቡብ ሱዳን የሚዋሰነው አዲሱ ክልል፣ ካሉት መስህቦች መካከል ጨበራ ጩርጩራ እና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች፣ የንጉሥ ሃላላ የድንጋይ ካብ  ይገኙበታል፡፡ በገበታ ለአገር ከሚለሙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውኮይሻ ፕሮጀክት የሚገኘውም በዚሁ ክልል ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሐውርታዊ (ባለብዙ ብሔረሰብ) እንደመሆኑ በብዝኃ ባህል የበለፀገ ነው፡፡ በክልሉ ካሉት ባህላዊ መገለጫዎች መካከል ባህላዊ የግጭት አፈታት፣ ባህላዊ ዳኝነትና የዕርቅ ሥርዓት ይገኙበታል፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከዓመታት በፊት በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ብሔረሰቦች ባህላዊ ቅርሶች ላይ ምዝገባና ቆጠራ (ኢንቨንቶሪ) አካሂዶ ነበር፡፡ የአንትሮፖሎጂና የፎክሎር ባለሙያዎቹ እነ ኤፍሬም አማረና አበበ ኃይሉ ባዘጋጁት ጥራዝ ላይ ከዳሰሷቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ከባህላዊ የግጭት አፈታት አንፃር ከተመለከቷቸው ብሔረሰቦች ውስጥ የቤንች፣ሸኮ፣ የካፋ፣ የሸካና የኮንታ ይገኙባቸዋል፡፡ የተወሰኑትን እዚህ ላይ አቅርበናቸዋል፡፡

ባህላዊ ግጭት አፈታት በቤንች

በቤንች ቋንቋ ‹‹ኬርግ› ማለት ሽማግሌ ማለት ሲሆን በብሔረሰቡ የሚከሰቱ የእርስ በርስ አለመግባባቶችን ወንጀሎችንና የሞት አደጋዎችን ጭምር ሽማግሌዎች በመመርመር የማስታረቅ ባህላዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ የችግሩን ክብደትና ቅለት ታይቶ ከአካባቢ ሽማግሌዎች እስከ ጎሳ መሪዎች ያሉ አዛውንቶች የዕርቅ ሥርዓት ያከናውናሉ፡፡ ከበድ ያለ ጥፋት ሲፈጸም ጉዳዩ ለጎሳ መሪው ከቀረበ በኋላ የጎሳ መሪው ጉዳዩን እንዲያጣሩ ራሱ የወከላቸውን ሽማግሌዎች ይልካል፡፡ የተላኩት ሽማግሌዎች ጉዳዩን አጣርተው የተበደለውን አስክሰው ያስታርቃሉ፡፡

በሥውር የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚዳኘው በአብዛኛው የጎሳ መሪው ሲሆን፣ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ከካደ ከጎሳ መሪው ጋር አብሮ በሚሠራው ባለውቃቢ/ካሀ አማካይነት መሃላ እንዲፈጽም ይደረጋል፡፡ በሐሰት መሃላ ከፈጸመ በራሱ በቤተሰቡ እንዲሁም በጎሳው ላይ ጥፋት ያመጣል ስለሚባል እውነቱን እንደሚናገር ይታመናል፡፡

‹‹ተም›› በቤንች ባህል ከሕይወት መጥፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ቅራኔን ለማስታረቅ የሚከናወን ሥርዓት ነው፡፡ በባህሉ በድንገተኛ ጠብ አንድ ሰው የሌላውን ሰው ሕይወት ቢያጠፋ በሕግ መጠየቁ የማይቀር ቢሆንም በቤተ ዘመድ መካከል ከበቀል በተጨማሪ አደጋን ለማስቆም ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ሁለቱንም የገዳይና የሟች ዘመዶችን ያቀራርባሉ ለዕርቅ ካስማሙ በኋላ ወራጅ ውኃ አጠገብ ይዘዋቸው ይሄዳሉ፡፡ የገዳይ ወገኖች ከወንዝ ማዶ እንዲቆሙ ከተደረገ በኋላ አንድ ላም ታርዳና አንጀቷ ከወጣ በኋላ፣ ማዶ ለማዶ የሚተያዩት ባለጋራዎች የአንጀቱን ጫፍና ጫፍ እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ‹‹በሁለታችሁ መካከል ቂምና በቀል ይጥፋ›› ተብሎ አንጀቱ ከተበጠሰ በኋላ ሁለቱ በዝምድና እንዲተሳሰሩ፣ ከገዳይ ወገን ልጃገረድ ከሟች ወገን ከሆነ ሰው ጋብቻ እንዲፈጽሙ ከተስማ በኋላ ዕርቁ ይጠናቀቃል፡፡ የባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቱ አሁንም ከመንግሥት የፍትሕ አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን መረጃ ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

ባህላዊ ዕርቅ በሸኮ

ሸኮዎች የእርስ በርስ አለመግባባቶችንና ማኅበራዊ ግጭቶችን የሚፈቱባቸው በየደረጃው ያሉ የሽምግልናና የዕርቅ መዋቅሮች አሏቸው፡፡ በየጎሳው ያሉ የጎሳ መሪዎች/ኪያዞች በሕዝቡ መካከል ከፍተኛ አክብሮትና ተሰሚነት አላቸው ከዚህ አንፃር የደም መፋሰስ፣ ቂም በቀልና የንብረት ውድመት ወንጀሎችን በሽምግልና ያያሉ፡፡ ውሳኔም ይሰጣሉ፡፡

በድንገት በመጠጥ ወይም በሌላ አጋጣሚ ድንገተኛ ጠብ ተከስቶ ሰዎች ቢጎዳዱ ድንገታዊ ጠብ ወይም ጊብዙቢጫ ስለሚባል ያካባቢ ሽማግሌዎች ወዲያውኑ ያስታርቃሉ፡፡ ደግሞ ላመጣላት በጎሳ መሪው ፊት ቃል እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ለመታረቃቸው ማረጋገጫ አንድ ቅል/ቲያራ አፋቸውን አጋጥመው ይጠጣሉ፡፡

በአጋጣሚ በተከሰተ ጠብ የሰው ሕይወት ድንገት ቢጠፋ፣ የጎሳ መሪዎችና ሃይማኖታዊ መሪዎች/ቡርዣቦች ወዲያውኑ በጉዳዩ በመግባት ካላስታረቁ በስተቀር፣ ምንም እንኳን ገዳይ የሚዳኝበት የአስተዳደር ሥርዓት ቢኖርም፣ በቤተ ዘመድና በጎሳ መካከል መበቃቀል መከሰቱ አይቀርም፡፡ ይህን ለማስቆም ድርጊቱ በተፈጸመበት አካባቢ ያሉ የጎሳ መሪዎች የወንጀሉን አፈጻጸም ያጣራሉ፤ የገዳይ ቤተሰቦች ለሟች ወገኖች ካሳ እንዲከፍሉ ያደርጋሉ፡፡ ለወደፊቱም ጠቡ እንዳያገረሽ ከገዳይ ወገኖች አንድ ልጃገረድ ከሟች ወገኖች ጋር በጋብቻ እንድትተሳሰር ይደረጋል፡፡

ይህ ከተከናወነ በኋላ የአገር ሽማግሌዎች ሁለቱንም ባለጋራዎች ፈሳሽ ወንዝ ዳር በመውሰድ ቡርዥቡ/የባህላዊ ሃይማኖት መሪው አንድ በግ አርዶ በወራጅ ወንዙ ላይ ደሙን ያፈሳል፤ ይህም የተፈጸመውን የደም ኃጢዓትና በቀል ለማንፃት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከሟችና ገዳይ ወገኖች ሁለቱም ፊታቸውን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ አዙረው በጀርባቸው ብቻ ተነካክተው፣ ሁለቱም ከሐረግ የተሠራ ጋሻ ወይም በብሔረሰቡ አጠራር በሸጊያሱ በመያዝ እንደሚዋጋ ሰው ለጥቂት ሰከንዶች ከተወኑ በኋላ ጋሻውን በየፊታቸው ባለ ነገር ላይ ይወረውራሉ፡፡ ይህ የመጨረሻ የዕርቅ ሥርዓት በሸኮ ‹‹ውርቢቁፃ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ባህላዊ ዳኝነት በካፊቾ

በካፊቾ ብሔረሰብ የተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ በድብቅ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አጋልጦ አጥፊን ለመቅጣት ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በሰፊው የሚሠራበት ባህል ነው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ‹‹ሾዬ ካቤገሮ›› በብሔረሰቡ የተከበሩና የዕርቅ ጥያቄያቸውን ማንም ሰው እስከመጨረሻው የማይገፋው ነው፡፡ አለመግባባቶች የሚፈቱት ከቀላል የግለሰቦች ጠብ እስከ ነፍስ መጥፋት ድረስ ያሉት ናቸው፡፡ ሁለት ሰዎች በጊዜያዊ ጠብ ቢቀያየሙ ወይም አንዱ ሌላውን ቢበድል ቢደበድብ፣ ሁለቱም ተጠርተው በሽማግሌዎች ፊት ችግራቸውን ገልጸው እንዲያስረዱ ይጠየቃል፡፡ የችግሩን ሥረ መሠረት በጥንቃቄ ከለዩ በኋላ ያጠፋውን ለይተው ይቅርታ እንዲጠይቅ የበደለውን እንዲክስ ካደረጉ በኋላ በገበቴ ውኃ በማስመጣትና ሣር ነጭተው ውኃ ውስጥ በማድረግ ይቅር በመባባል ቃለ መሃላ/ወጎ ካስፈጸሙ በኋላ ሣሩ በተነጨበት ቦታ ላይ ውኃው ይደፋል፡፡

በአካባቢው በድብቅ ወንጀል ከተፈጸመ ንብረት ከተሰረቀ አውጫጭኝ ወይም በካፊኖ ቋንቋ ‹‹አቶ›› ይደረጋል፡፡ በአውጫጭኙ ላይ ወንጀሉ በማን እንደተፈጸመ ጥርጣሬው ይኖራል፤ ወይም ለሕግ ምስክርነት በቂ ያልሆነ አንድ ሰው ብቻ ዓይቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ የአገር ሽማግሌዎች ሕዝቡ እንዲሰበሰብ ካደረጉ በኋላ የተፈጸመው ወንጀል በማን እንደተፈጸመ እንዲያጋልጥ ሕዝቡን ያሳስባሉ፡፡ በብዙ ውይይት ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ሁሉም ዋስ ጠርተው እንዲሄዱና በነጋታው እንዲመጡ ዋስ ያላገኘ ከዕድር እንደሚወጣ ይወሰናል፡፡ አንዱ ላንዱ ዋስ ከሆነ በኋላ በመጨረሻ ተጠርጣሪው ዋስ እንዲጠራ ይጠየቃል፡፡ ሁሉም ሰው በዋስትና በመተሳሰሩ ብቻውን ይቀራል፡፡ ተጠርጣሪው በነጋታው ዋስ እንዲያመጣ ካለበለዚያ ከዕድር እንደሚወጣ ይነገረዋል፡፡ በማግሥቱም ዋስ እንደማያገኝ የሚታወቅ ሲሆን፣ በሚደርስበት ሥነ ልቦናዊ ጫና ወንጀሉን መፈጸሙንና አፈጻጸሙን ያስረዳል ነገር ግን ሁለተኛ እንደማይፈጸም ቃል ገብቶ ምሕረት ይደረግለታል፡፡

በብሔረሰቡ አልፎ አልፎ በጠብ መካከል የሰው ሕይወት ቢያልፍ፣ አጥፊው በሕግ ቀርቦ መቀጣቱ ባይቀርም በዘመዶቹና በሟች ወገኖች መበቃቀል እንዳይኖር ገዳይም ቅጣቱን ጨርሶ ሲመለስ ከወገኖቹ እንዲላቀል ሽማግሌዎቹ ሁለቱን ወገኖች አሰባስበው ያስታርቃሉ፡፡ በባህሉ ጠላ ይጠመቃል፣ በሬ ይታረድና ደሙን በመቅበር በትልቅ ገበቴ ውኃና ሣር ቀርቦ ሁለቱም ባለጋራዎች እጃቸውን ገበቴ ውስጥ በመጨመር ቃለ መሃላ ‹‹ወጎ›› ይገባሉ፡፡

ባህላዊ ዕርቅ በኮንታ

ኮንታዎችም ግጭቶች የሚያስወግዱበት የቆየ ባህላዊ ደንብ አላቸው፡፡ አንድ ሰው በደል ሲደርስበት እንደወንጀሉ ሁኔታ በቅርብ ባሉ ሽማግሌዎች እስከ ቃልቻዎች/አላሞዎች በመሄድ ፍትሕ ያገኛል፡፡ ሽማግሌዎች በዳይና ተበዳይን በማቀራረብ የተጣሉትን ሰዎች ዋስ በማስጠራት ጉዳዩን በመመርመርና በማጣራት የተበደለውን ካሳ/አጫ ካስከፈሉ በኋላ ደግሞ በቂም በቀል እንዳይፈላለጉ በገበቴ ውኃ ላይ ሣር ከተጨመረ በኋላ ሁለቱም እጃቸውን ባንድ ላይ ነክረው ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ፡፡

በኮንታ ባለው ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት ባጋጣሚ የሚከሰቱትንና እስከ ሕይወት መጥፋት ያሉትን ወንጀሎች በተለይ ቀደም ባለው ጊዜ ቃልቻዎች/አላሞዎች በማስታረቅ ይፈቱ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በድንገት በተከሰተ ግጭት አንድ ሰው ሕይወቱ ቢያልፍ የአካባቢው መንፈሳዊ መሪ/አላሞ ሁለቱንም ወገኖች በማቀራረብ የዕቅር መንገድ ይፈላልጋል ጉዳዩን በቀጥታ የፈጸመው በወንጀል የመጠየቅ ቢሆንም፣ ቀሪው ቤተሰብ እንዳይበቃቀል ያስታርቃሉ፡፡

በዕርቅ ሥርዓቱ መጀመርያ ሁለቱ ቤተሰቦች ይታረቃሉ፡፡ ዕርቁን የበለጠ በዝምድና ለማስተሳሰር አንድ የገዳይ ቤተሰብ ልጃገረድ ከሟች ቤተሰብ ከሆነ ሰው ጋር በጋብቻ እንዲተሳሰሩ ቅድመ ቃል ኪዳን ከተገባቡ በኋላ፣ የመጨረሻው ሥርዓት ይከናወናል፡፡ በዚህ የመጨረሻ ሥርዓት ከሦስት ጎሳ የወጡ ሦስት ሰዎች ሥርዓቱን ይመራሉ፡፡

 ማካ ከሚባል ጎሳ የመጣ አንድ ሰው ፀበል ይረጫል፤ ፀበል እየረጨ ሁለቱ ባለጋራዎች ራቁታቸውን በረዥሙ በተቆፈረ ጉድጓድ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፣ ፉጋ ከሚባለው ወገን የመጣ ሰው እምቢልታ እየነፋ ያጅባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከጉድጓዱ ሲወጡ ከሚኒ ከሚባለው ጎሳ የመጣ ሰው አዲስ ልብስ ያለብሳቸዋል፤ ከብት ታርዶ በደሙ ይቀባቸዋል፡፡ ዕርቁ ይጠናቀቃል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የዕርቅ ሥርዓቱ በተለይም በድንገትና በአደጋ ለሚደርሱ የሕይወት መጥፋቶች እየሠራ ያለ ሲሆን፣ ከላይ የተዘረዘሩት ሥርዓቶች በሙሉ እየተተገበሩ ባይሆንም የሽማግሌዎች የአስታራቂነት ሚና ግን አልቀነሰም፡፡

  • ቅንብር በሔኖክ ያሬድ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...