Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይህም ያልፋል!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ከረማችሁ ብዬ ሰላምታ ባቀርብላችሁ፣ ‹አከራረማችን እንዴት እንደሆነ አታውቅምና ነው የምትጠይቀን…› ብላችሁ ሆድ እንደሚብሳችሁ ስለማውቅ ትቼዋለሁ፡፡ እንዲያው በደፈናው ሰላም ማለቱ ይቀላል፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ ግን ሰሞኑን በፆማቸው ላይ ፆም፣ በፀሎታቸው ላይ ፀሎትን አብዝተው ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከፀሎቶቻቸው ርዕሶች መካከል ዋነኛው ይህ ጦርነት አልቆ ሰላም እንዲሰፍን ነው፡፡ ፈጣሪ እንደሚሰማቸው ምንም ጥርጥር የላቸውም፡፡ ‹‹ሰው ነው እንጂ ፈጣሪን አልሰማ ያለው፣ ፈጣሪማ ከልብ የሚለምኑትን ለመስማት ጆሮዎቹ ሁልጊዜ የተከፈቱ ናቸው…›› ሲሉም ፈጣሪ እንደሚሰማቸው በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡ መናገር የሚፈልጉትንም ሁሉ ሰው ሊሰማው በማይችለው ንግግር ከንፈራቸው ብቻ እየተንቀሳቀሰ ይናገራሉ፡፡ ከፈጣሪ ጋር በለሆሳስ የሚነጋገሩ ይመስላሉ፡፡ ‹‹እንደ ሀብቶች የምንቋቋምበት አቅምም ኅብረትም ስለሌለን አገራችንን ጠብቃት…›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ የአዛውንት ፀሎትና ምርቃት ለአገር ትሩፋት ነውና እኔም አብሬያቸው ‹‹አሜን… አሜን…›› ስል ሰነበትኩ፡፡ አሜን በሉ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹መሪዎች የመረረ ችግር ሲገጥማቸው ወይ ሥልጣናቸውን ወይ ደግሞ ሕይወታቸውን ለአገራቸው መስጠታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው…›› እያለ አዲስ አጀንዳ ይከፍታል፡፡ ሕዝባችን አንድ ላይ ከቆመ የኢትዮጵያ ትንሳዔ በደጅ ነው ባይ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ከማናቸውም ጥቃት ለመጠበቅ የአዛውንቶች ፀሎትና ምልጃ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ልጆቿ ደግሞ በአንድነት ተሠልፈው ሊከላከሏት አደራና ኃላፊነት አለባቸው…›› ይላል፡፡ ‹‹መንግሥት እንደ ግለሰብ ለራሱ ጥቅም ብቻ ማሰብ ሲጀምር ነገር ይበላሻል፣ ተዓማኒነትን ያጣል፡፡ የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነት ከሕዝብ በፊት ቀድሞ ለአገር ህልውና የሚጠቅሙ ዝግጅቶች ላይ ማተኮር ነው፡፡ መዘናጋትና ክፍተት እያሉ ሕዝብን ግራ ማጋባት ጠቃሚ አይደለም…›› ሲል እኔኑ መልሶ ግራ ያጋባኛል፡፡ ‹‹እስቲ ይህንን ጉዳይ አብራራው…›› ስለው፣ ‹‹ምን ማብራሪያ ያስፈልገዋል፣ ያለንበትን ሁኔታ አትረዳም እንዴ…›› ብሎ ሲያፈጥብኝ ድንብርብሬ ይወጣል፡፡ ወይ መደናበር!

እስቲ ወደ ሌላ ጉዳይ እንለፍ፡፡ ሴትዬዋ አርግዛ ያማሯትን ነገሮች ዝርዝር ለባለቤቷ እየተናገረች ነው አሉ፡፡ ባለቤትዋ የአምሮት ዓይነቶችን ይመዘግባል፡፡ ‹‹ሥጋ›› ስትለው፣ ‹‹ምንም ችግር የለም አገሩ ሁሉ ሥጋ ነው፣ ደግሞ ኪሎው አንድ ሺሕ ብር ለገባ ሥጋ፣ እንኳን ዛሬ ያኔም ቢሆን ያለ ምንም ችግር ገዝቼ አመጣልሽ ነበር፣ ሥጋ እንደ ጉድ ይመጣል…›› አላት ምንም እንዳልተገረመ ሆኖ፡፡ ሚስት ቀጠለች፣ ‹‹ብርቅዬ›› የሚባሉ የምግብና የቁሳቁስ ዝርዝሮችን ጠርታ ስታበቃ ባለቤቷን ያስደነገጠ አንድ ጥያቄ ጠየቀች፡፡ ምን ብላ? ‹‹ስኳር አማረኝ…›› ብላ፡፡ ሰውዬው እንደ ቀላል ነገር ስኳር በመፈለግ አዲስ አበባን አካሎ ከጨረሰ በኋላ ወደ አዳማ ናዝሬት ገሰገሰ አሉ፡፡ ምናልባት ለወንጂ ቀረብ ይላል ብሎ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድ መደብር ገብቶ፣ ‹‹ማነህ ስኳር አለ?›› ጠየቀ ሰውዬው፡፡ ባለ ሱቁ በፍጥነት፣ ‹‹አለ…›› ሲለው ሰውዬው ማመን አልቻለም፡፡ ‹‹በፈጠረህ እውነትህን ነው?›› በደስታ እየተርገበገበ መልሶ ጠየቀው፡፡ ባለ ሱቁ የሰውዬው ሁኔታ ገርሞት ስኳሩ ያለበትን ጆንያ አሳየው፡፡ ዓይኑ ሥር ያለውን ስኳር እያየ በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ የሚስቱ እርግዝና አምሮት መልስ አገኘ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ በተወደደ ሥጋ ያልተገረመው ሰውዬ አገር ለቆ ሄደ በስኳር መገኘት ሲደሰት ግራ አይገባም? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ምን እንደምንፈልግ ስለማናውቅ እኮ ነው በስሜት የምንናውዘው…›› ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ ወይ ስሜታዊነት!

ባሻዬ በስኳር እጥረት ምክንያት፣ ‹‹እነ እንትና ቤት ሻይ እየተጠጣ ነው…›› የሚባልበት ዘመን ሳይመጣ አይቀርም ይላሉ፡፡ ማንጠግቦሽ በከፍተኛ ድካም ያመጣሁትን ስኳር በቡና በሻይ እያለች አባክና ልትጨርሰው አልፈለገችም፡፡ እንዲያውም የምትወደውን ቡና ሳይቀር በጨው መጠጣት ጀምራለች፡፡ ሌላው ማንጠግቦሽ የዘየደችው መላ፣ ‹‹ቡና ሊጠጡ ሲመጡ ስኳር ይዘው ይምጡ…›› ነው፡፡ ይህንን አዲሱን መፈክር የሰሙት ባሻዬ በማንጠግቦሽ ፈጠራ ተደንቀዋል፡፡ ባሻዬ ቡና በጨው ከሚጠጡ ባዶውን ቢጠጡ ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ትንሽዬ የስኳር ዕቃ በካፖርት ኪሳቸው ውስጥ ይዘው መዞር ጀምረዋል፡፡ ማንጠግቦሽ ባዶውን ቡና ስትቀዳላቸው እሳቸው ደግሞ ስኳራቸውን አውጥተው ይጨምራሉ፡፡ በቃ ይህ አዲሱ የስኳር አጠቃቀም መመርያ መሆኑ ነው፡፡ አንዱ ከስኳር መጥፋት ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት በሬዲዮ የሰማውን አስታወሰ፡፡ ‹‹በስኳር መጥፋት ምክንያቱ ገበሬው ስኳር መጠቀም በመጀመሩ ነው…›› የሚል ዓይነት አስተያየት መስማቱን ካስታወሰ በኋላ በሐሳቡ በጣም ተደሰተ፡፡ የአንዳንዱ ደስታ ምንጭ ይገርማል!

ሰውዬው ወደ ገበሬ አባቱ ዘንድም ደወለ፡፡ ‹‹ሃሎ አባዬ?›› አባቱ በገመድ አልባ ስልካቸው ማውራት ጀመሩ፣ ‹‹ሃሎ ልጄ ከየት ተገኘህ?›› አሉ፡፡ ገበሬ አባቱን ካያቸው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሰላምታቸውን ከተለዋወጡ በኋላ ዋናውን ቁም ነገር ጠየቃቸው፣ ‹‹ለካስ እኛ በስኳር እጦት የምንገላታው እናንተ ስኳሩን ሁላ ሰብስባችሁ ገዝታችሁት ነው?›› ሲል፣ በስልክ እያነጋገሩ ያሉት አባት ግራ ተጋቡ፡፡ የአገሪቱ ስኳር እናንተ ዘንድ ነው የሚለው የልጃቸው ንግግር የሚሉትን አሳጣቸው፡፡ ግራ ቢገባቸው፣ ‹‹ልክ ነህ እውነት ብለሃል፣ በእርግጥ ለውጥ አለ፡፡ ድሮ በሁለት በሬ ነበር የማርሰው አሁን ግን በማኅበር ታቅፌ…›› እሳቸው ግን እውነቱን ያውቁት ነበር፡፡ ሻይ የሚጠጡት ሌላኛው ልጃቸው ለበዓል ሲጠይቃቸው ስኳር ካመጣላቸው ብቻ ነው፡፡ ያኔ ገበሬው ተጠቃሚ በመሆኑ ነው ተባለ፣ እሺ አልን፡፡ በመቀጠል ነጋዴው አፍኖት ነው ተባልን እሺ ከማለት ውጪ አማራጭ አልነበረም፡፡ ነገ ደግሞ ሌላም ሊባል ይችላል፡፡ የሆነስ ሆነና ስኳር ሲያምረን እንዴት ያደርገናል? ‹‹ከስኳርና ከሰላም የቱ ይቀድማል? ስንዴ እየተመፀወትን ስኳር ቅንጦት ቢሆንብን ምን ይገርምሃል?›› የሚለኝ ምሁሩ ወዳጄ ነው፡፡ እውነት ነው እኮ!

ባሻዬ የዱሮ ታሪክ ሲያወሩ ሰምቶ የማይመሰጥ የለም፡፡ አንዴ ምን አሉ፣ ‹‹ግስላን ለመግደል ስታስብ በተለይ በወጥመድ ተይዞ ከሆነ ቀላሉ መንገድ በሆነ ነገር እየነካኩ እንዲበሳጭ ብቻ ማድረግ ነው፡፡ በጣም ሲናደድ ራሱን ለማጥፋት ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ወዲያው በስለታም ጥፍሮቹ ጉሮሮውን ሲጥ አድርጎ ይገድላል…›› ነበር ያሉት፡፡ ስለዚህ፣ ‹‹ማነው የገደለው?›› ብለው የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች ቢጠይቁ እንኳን መልሱ፣ ‹‹ራሱን በራሱ አጥፍቶ ነው…›› በማለት ከተጠያቂነት ማምለጥ ይቻላል ይላሉ፡፡ ከግስላው ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ስላለው ጊንጥም የተናገሩትን እኔ አንበርብር ምንተስኖት አልረሳውም፡፡ በምሳሌያዊ ንግግር ማን ያክላቸዋል? ማንም ማለቱ ይቀላል፡፡  አንዳንዴ እኮ ነገራችን ሁሉ ግራ ሲያጋባ ብዙ ያስቀባጥረኛል፡፡ እኔ ደግሞ ከግራም ከቀኝም የምሰማው ጭንቅላቴን ሲበጠብጠኝ አፌን ምን እንደሚያቅለበልበው ይገርመኛል፡፡ ምሁሩ ወዳጄም ጭንቀት ነው ይለኛል፡፡ ጭንቅ ጥብብ!

እንዴት ነው አየሩ? መንደሩ? የሚታየው፣ የሚሰማው፣ የሚደረገውና የሚባለው እኮ አልጨበጥ አለን፡፡ ‹‹የእኛ ነገር መያዣና መጨበጫ አጥቷል…›› የምትለው ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ናት፡፡ ሰሞኑን ፍራሽ አውርዳ መሬት በመተኛት ከመጋረጃው በስተጀርባ ላሉት ዝብርቅርቅ ነገሮች መስተካከልን ትማፀናለች፡፡ ቆይ እኔ የምለው የምቾት ወንበር ላይ ተቀምጦ በጉቦ ሕዝብ ከሚያምስ ጀምሮ፣ ሰላም አደፍራሽ በበዛበት በዚህ ዘመን ማንጠግቦሽ ብቻዋን ተማፅና ትችለዋለች ትላላችሁ? እንጃ ብቻ። እኔም የጥሞና ጊዜዋን ትጨርስ ብዬ ስሜቴን ገድቤ ሰንብቻለሁ፡፡ ይኼኔ እኮ ምድረ ዘራፊ አሰፍስፎ ያለው እንደ ባለቤቴ ለፀሎትና ለምልጃ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አገር ሰላም ስታጣ አይዞሽ አለን የሚሉትን ያህል፣ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት የሚነሱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? ነገራችን ሁሉ ግራና ቀኝ ሲረግጥ እንዲህም እንሆናለን ለማለት ነው፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!

   ለሕዝብ አገልግሎት መስጠትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ነው እየተባለ ይለፈፋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር እጅግ አታካች መሆኑ ነው የሚታየኝ። ባሻዬ አንዳንዴ ለእንቅስቃሴ በሚል ሰበብ እንጨት ካልፈለጥኩ ይላሉ፡፡ ታዲያ ምሁሩ ልጃቸው እንቢ ብሎ ሙጥኝ ሲላቸው፣ ‹‹ወይ አትሠራ… ወይ አታሠራ…›› ይሉታል፡፡ ቅኔያቸው ይገባዋል፡፡ ‹‹ኃላፊነትህን በአግባቡ ተወጣ…›› ለማለት እንደፈለጉ ይገባዋል። ‹‹ወድጄ ነው?›› ይላል። እንደ ጎረምሳ አፍንጫውን ነፍቶ፣ ‹‹እባካችሁ በኃላፊነት ስሜት ሥራችንን እንሥራ ሲባል ሁሉም ተቀምጦ መተቸት እንጂ መቼ ለሥራ ይነሳል…›› ብሎ፣ ‹‹ታዲያ እኔ ብቻዬን ምን ላድርግ?›› ይላቸዋል፡፡ ባሻዬም፣ ‹‹አላሠራን አሉ በማለት ከማላዘን እንዴት እንደሚሠራ በተግባር አሳይቶ ማሳፈር ሲገባ፣ ሰበብ ላይ እየተንጠላጠሉ አገርን ማስበላት ዘመን ያለፈበት ፋሽን ነው…›› እያሉ ይናደዳሉ፡፡ የሚወራው ሌላ የሚደረገው ሌላ እንደሚባለው ነገሩ ሁሉ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ይሆንባቸዋል። እሳቸውን ቱግ ብለው ሲናገሩ እኔና ልጃቸው በኃፍረት እናቀረቅራለን፡፡ ኃፍረት እኮ አንገት ያስደፋል፡፡ ምንም የማይመስላቸው ቢኖሩም እኛ ግን እናፍራለን፡፡ ይሉኝታ በሉት!

ይገርማችኋል የመብራትና የውኃም ጉዳይ ያዝ መለስ ከሆነ ከረምረም እያለ ነው። መብራቱስ በይደር የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ነው ቢባል ለውኃ መቆራረጥ ደግሞ ምን ይሆን ምክንያቱ? ባሻዬ በጀሪካን ውኃ እያስላኩ ማስመጣት ስልችት ብሏቸው፣ ‹‹እኔ ምለው አንበርብር? የባይ ግድብ  እንጂ በገንዘብ መዋጮ የሚሠራው ውኃውንም ለግድቡ እያዋጣን ነው እንዴ?” እያሉ ሲያስቁኝ ይውላሉ:: ወዲያው ማንጠግቦሽ ትዝ ትለኛለች። በዚያ መቃተቷ ላይ ውኃ ቀድታ ስትሸከም በዓይነ ህሊናዬ ትታየኛለች። ‹‹የአምባሰል ዝንጀሮ ሲሄድ አጎንብሶ፣ ሲመለስ ቀና አለ የልቡን አድርሶ…›› እያልኩ በሸክም ቁርጥ ያለ ወገቧን አቅፌ ላሳርፈው ወደ ቤቴ ላጥ እላለሁ። ባይሆን የባልና የሚስት ጨዋታ አይወደድ እንጂ የሸቀጥ ዋጋ መናርን እየረሳነው ነው፡፡ ‹‹ሰይጣንም ሲለመድ ወዳጅ ይሆናል›› የሚል ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ምን ያድርገው? ‹‹ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን›› እየተባለ አድጎ ነው፡፡ የእኛም ነገር እንዲህ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› የሚባለው ግን እንዳይረሳ አደራ እላለሁ፡፡ ለምድርና ለሰማይ የከበደ ነገር ሲገጥመን ያልፋል ነው የሚባለው፡፡ ነገር ማለፉ ዕውን የሚሆነው በሀቅ ሲታጀብ መልካም ነው፡፡ እርግጥ ነው ከባድ ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ነገር ግን ይህም ያልፋል ብለን ብንግባባ መልካም ነው፡፡ ይህም ያልፋል! መልካም ሰንበት!

 

 

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት