Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከአገር ህልውና የሚቀድም ምንም ነገር የለም!

የአገር ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ወሳኝ ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ኢትዮጵያ የታሪኳ የተለያዩ ገጾች እንደሚያሳዩት፣ በበርካታ መከራዎች እየተፈተነች ነው እዚህ ደረጃ የደረሰችው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ጋር ከተደረጉ በርካታ ጦርነቶች በተጨማሪ፣ በየዘመኑ በተነሱ ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ተደጋጋሚ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት የተገበረባቸው በርካታ ዓውደ ውጊያዎች የታሪክ መዛግብት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ወዲህም ከሶማሊያ ወራሪዎች፣ እንዲሁም ከኤርትራና ከትግራይ አማፂዎች ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ከመካሄዳቸውም በላይ፣ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በባድመ ምክንያት ከመቶ ሺሕ በላይ ሰዎች የሞቱበትና ከፍተኛ ውድመት ያደረሰ ጦርነት ከኤርትራ ጋር መደረጉ አይረሳም፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት አንፃራዊ የሚባል ሰላም የሰፈነ ቢመስልም፣ አገዛዙ የኢትዮጵያዊያንን መብቶች በመደፍጠጡና በፀረ ዴሞክራሲ ባህሪው ምክንያት ባደረሰው አደጋ ሳቢያ መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ተቀስቅሶበት የሥርዓት ለውጥ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህ ለውጥ ግን በተመቻቸ ጎዳና ላይ ሳይሆን በርካታ ወጀቦች ውስጥ በማለፉ በሰው ልጆች ላይ ከደረሰው ሞትና ውድመት በተጨማሪ፣ አገሪቱን ለአንድ ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ በመክተት ህልውናዋን እየተፈታተነ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ህልውና ማስቀደም ከተቻለ ሁሉም ችግሮች በየተራ ይቃለላሉ፡፡

ጦርነቱ በአገር ህልውና ላይ የደቀነው አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ በመሆኑ፣ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ዜጎች ትኩረታቸው በሙሉ የአገር ደኅንነት ላይ እንዲሆን አድርጓል፡፡ አገር የአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ ሆና መንግሥት ሙሉ ጊዜውን አገር ለመከላከል ባዋለበት በዚህ ጊዜ፣ ዜጎች በበኩላቸው አገራቸው ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ በተቻለ መጠን ከሐሰተኛ ወሬዎችና ከፕሮፓጋንዳዎች ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከቁጥጥር በላይ የሆነ መፈናቀል ከቻለባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ራስንና አካባቢን ተደራጅቶ ከመጠበቅ ይልቅ በሐሰተኛ ወሬ መፈታት በመበርከቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም በውጭ የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖችና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር የሚወጡ መረጃዎች ዋነኛ ትኩረታቸው፣ ሕዝብ እንዳይረጋጋ በማድረግ በፍርኃት ማርበድበድ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መንግሥት ለሕዝብ የተጣሩ መረጃዎችን በፍጥነት የማድረስ ኃላፊነቱን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎችን የጦርነት ቀጣና አድርጎ ሕዝብን የማስበርገግ የሥነ ልቦና ጦርነት ሊገታ የሚችለው፣ መንግሥት በልዩ ትኩረት ፈጣንና ትኩስ አስተማማኝ መረጃዎችን ሲያቀርብ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

የፕሮፓጋንዳውን ዘመቻ በሰፊው ከሚመሩት መካከል፣ በተለይ ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው የውጭ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ለተለያዩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ዓላማ ስኬት የሥነ ልቦና ጦርነት የሚያካሂዱ ግለሰቦች፣ በየቀኑ ያለ መታከት በርካታ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ በቀላሉ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የተራዘመ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አሉታዊ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ያሉ የውጭ ኃይሎች፣ እነዚህን ግለሰቦች ለሥነ ልቦና ጦርነት እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡ ብዙዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሳተፉ ወገኖች በተቻላቸው መጠን ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር ቢተናነቁም፣ የምዕራባውያን መደበኛ ሚዲያዎች እነሱን ሁነኛ ምንጭ እያደረጉ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከመደበኛው ውጊያ ባልተናነሰ የሥነ ልቦና ጦርነቱ ሊያደርስ ለሚችለው ጉዳት ልዩ ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልገው፡፡ ከመንግሥት በተጨማሪ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች፣ ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ የተለየ ትኩረት በመስጠት ፕሮፓጋንዳውን መመከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገር በጦርነት እየወደመች፣ ሕዝባችን እየሞተና እየተፈናቀለ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ ሰላም ለማስፈን በርካታ አማራጮች እንዳሉ ቢታወቅም፣ አሁን መቅደም ያለበት ግን የአገር ህልውና ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና ሲሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ማለት አለባቸው፡፡ አገር ከማንኛውም ፓርቲና ግለሰብ በላይ ናት፡፡ የአገር ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ መቅደም ያለበት፣ የማንም ጉዳይ ከአገር በላይ ስላልሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖባት በልማት መገስገስ የምትችለው፣ ልጆቿ ያለ ምንም ስስት ያላቸውን ሁሉ ሲያበረክቱላት ነው፡፡ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ራሳቸውን ከአገር በላይ አሳብጠው ሲቀርቡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት ሊያገኙ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ጉዳዮች ልዩነት ቢኖራቸውም፣ ለጋራ አገራቸው ሲሉ ግን አንድነት ፈጥረው የተጋረጡ ችግሮችን ማስወገድ አለባቸው፡፡ ከአገር በላይ የሆነ ልዩነት ተፈጥሮ መከፋፈል ስለማይኖርባቸው፣ ለአገራቸው ዘለቄታዊ ሰላምና ዕድገት ሲሉ መተባበር ግዴታቸው መሆን አለበት፡፡ አገር ከሌለች ሥልጣንም ሆነ ይዞት የሚመጣው ጥቅም ዋጋ የለውም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከቋንቋና ከሌሎች ልዩነቶች በላይ የምታስተሳስራቸው አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ አገር ባለቤት መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ እንደ አያትና ቅድመ አያቶቻቸው የዓድዋንና የሌሎች ታላላቅ ጦርነቶች ዓይነት ድሎችን በተለያዩ መስኮች ማስመዝገብ አያቅታቸውም፡፡ አገራቸውን ከምንም ነገር በላይ ማስቀደም ከቻሉ ይህ ችግር ማለፉ አይቀርም፡፡ አገርን መውደድ በቃላት ብቻ የሚነገር ሳይሆን ላብና ደም ጭምር የሚከፈልበት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በወሬ መፈታት አይገባም፡፡

ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ወገኖቻቸውን ከመደገፍ ባለፈ፣ እርስ በርስ በመተዛዘንና በመረዳዳት ይህንን ከባድ ጊዜ ለማሳለፍ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን በተለያዩ ማዕቀቦች ቀስፈው ለመያዝ በተነሱበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያዊያን ሊጎድል የሚችለውን አቅርቦት በአገር ውስጥ ለማሟላት የሚያስችሉ ዘዴዎችን በመቀየስና ለተግባራዊነታቸውም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በማዋጣት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላትም አጋጣሚውን ትርፍ ለማጋበሻነት ለመጠቀም ከመቀበዝበዝ ይልቅ፣ ወገኖቻቸው እንዳይጎዱ የዜግነት ግዴታቸውን በኪሳራ ጭምር ለመወጣት መቁረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ የንግድ ክህሎታቸውን በመጠቀም ለሕዝቡ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እንዳይቋረጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት ይወጡ፡፡ የመንግሥት አገልግሎት መስጫዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትጋት በማሳየት የወገን አለኝታ መሆናቸውን ያሳዩ፡፡ ከዚህ ቀደም የሚታወቁትን ውስብስብና አሰልቺ አሠራሮች ወደ ጎን በማድረግ፣ ለአገልግሎት ፈላጊዎች ፈጣንና አስተማማኝ ይሁኑ፡፡ የመንግሥት አመራሮች በዚህ ወሳኝ ጊዜ ሕዝብ የሚፈልግባቸውን አመራር ይስጡ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሥነ ልቦና ጦርነት ተከፍቶ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ የለባቸውም፡፡ ከአገር ህልውና ምንም የሚቀድም ነገር ስለሌለ ለሕዝብ አስተማማኝ መረጃ እንዲደርሱ በማድረግ፣ እንዲሁም አለመረጋጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ክፍተቶችን በመድፈን ኃላፊነታቸውን በተግባር ይወጡ፡፡

በዚህ ፈታኝ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ከብረት በጠነከረ ዲሲፕሊን በመታገዝ ለሕግ የበላይነት መከበር፣ ሥርዓተ አልበኝነትና ሕገወጥነት እንዳይኖር፣ ሐሰተኛ ወሬዎችና ፕሮፓጋንዳዎች መደናገር እንዳይፈጥሩና የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት የሚያቃውሱ አፍራሽ ድርጊቶችን በጋራ ለመመከት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር ስለሌለ አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ በመስጠት በገንዘብ፣ በጉልበትና በሞራል የአገር ደኅንነት ለማስጠበቅ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ያልፋሉ አገር ግን በትውልዶች ቅብብሎሽ ትቀጥላለች፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ተወግዶ አስተማማኝና ዘለቄታዊ ሰላም ማስፈን የሚቻለው፣ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና በአንድነት ሲቆሙ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ፍላጎትና ዓላማ ለአገር ህልውና አይበጅም፡፡ አገር ፀንታ መቆም የምትችለው ልጆቿ ከልዩነቶቻቸው በላይ አንድ የሚያደርጓቸው፣ ዘመናትን የተሻገሩ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ስላሉዋቸው እንደሆነ በአፅንኦት ሊታወስ ይገባል፡፡ እነዚህ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲቀባበሉ እዚህ የደረሱት፣ በትውልዶች በተከፈለ መስዋዕትነት እንደሆነም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ልጆቿ መስዋዕትነት ነው የዘመናት ፈተናዎችን ተሻግራ እዚህ የደረሰችው፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ ህልውና የሚቀድም ምንም ነገር የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...