Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጉሙዝ ታጣቂዎች በመተከል ዞን በፈጸሙት ጥቃት ንፁኃንን መግደላቸውና ማገታቸው ተሰማ

የጉሙዝ ታጣቂዎች በመተከል ዞን በፈጸሙት ጥቃት ንፁኃንን መግደላቸውና ማገታቸው ተሰማ

ቀን:

በአማኑኤል ይልቃል

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ከእሑድ ጥቅምት 21 እስከ ረዕቡ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ውስጥ የጉሙዝ ታጣቂዎች በንፁኃን ላይ በከፈቱት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም አራት ሰዎች መታገታቸውን የዞኑ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡

ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ቻግኒ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ተሽከርካሪዎች ካር የተባለ ኬላ ለመድረስ 200 ሜትር ገደማ ርቀት ሲቀራቸው ጥቃት እንደተከፈተባቸው፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተሽከርካሪዎቹ ላይ በተከፈተው ጥቃት ሦስት ሰዎች እንደቆሰሉ፣ አንድ የሚኒባስ ረዳት የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ባህር ዳር ከተማ ለሕክምና መላኩ ተገልጿል፡፡

ሰኞ ዕለትም እንዲሁ በቡለን ወረዳ አንድ የዞኑ ነዋሪ ግድያ እንደተፈጸመበት ተሰምቷል፡፡ የወረዳው ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግድያው የተፈጸመው አዘም በተባለች ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ግድያ የተፈጸመበት ግለሰብ በመጥረቢያ ባላ ሲቆርጥ ድምፅ የሰሙ ታጣቂዎች፣ በተኮሷቸው ሦስት ጥይቶች የግለሰቡን ሕይወት መቅጠፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በበኩላቸው፣ ሰኞ ዕለት ግድያው የተፈጸመው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ በሆነ ታዳጊ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመተከል ዞን ለተከታታይ ቀናት በታጣቂዎች ከተፈጸመ ጥቃት በኋላ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ግለሰቦች በድባጤ ወረዳ መገደላቸው ተሰምቷል፡፡

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የቤተሰብ አባላት ከድባጤ ወረዳ ወደ ቻግኒ መውጫ በባለ ሦስት እግር መኪና (ባጃጅ) እየተጓዙ ነበር፡፡ የቤተሰብ አባላቱ አውራ ጎዳና ካምፕ የተባለ አካባቢ ሲደርሱ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተውባቸዋል፡፡ በዚህም አባትና ሁለት ልጆቻቸው መገደላቸውን የቡለን ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ማክሰኞ ዕለት የተገደሉት የአንድ ቤተሰብ አባላት ቁጥር አራት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ረቡዕ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ ታጣቂዎች ሁለት ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡ ታጣቂዎቹ በፈጸሟቸው ጥቃቶች ነዋሪዎች መገደላቸውን፣  መቁሰላቸውንና መታገታቸውን በበርበር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ነዋሪው ገለጻ፣ ነዋሪዎች በጭነት ተሽከርካሪ ከፓርዜት ወደ ድባጤ ሲጓዙ ማንደን የተባለ ቀበሌ ሲደርሱ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተውባቸዋል፡፡ በጥቃቱም ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ሦስት ሰዎች ቆስለዋል፡፡ አራት ሰዎች ደግሞ መታገታቸውና የገቡበት አለመታወቁን ነዋሪው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ረዕቡ ዕለት ረፋድ ላይ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች ውስጥ ከአንዱ ጋር ዝምድና እንዳላቸው የበርበር ቀበሌ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ሌላው ጥቃት የተፈጸመው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ነው ተብሏል፡፡ ታጣቂዎቹ በፓርዜት የሚገኙ አርሶ አደሮች ንብረት የሆኑ ከ100 በላይ ከብቶችን እየነዱ መውሰዳቸውን፣ የአካባቢው አርሶ አደሮችም ከብቶቻቸውን ለማስመለስ ሲከተሉ ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪው ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎቹ በእነዚህ ቀናት በዞኑ ግድያና ጥቃት በነዋሪዎች ላይ የተፈጸመው በጉሙዝ ታጣቂዎች መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ጥቃቶቹ መፈጸማቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አብዮት፣ ‹‹ቁጥሮች የመረጃ ስህተት ሊያመጡ ይችላሉ፤›› በማለት በጥቃቶቹ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

እሑድ ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ስለተፈጸመው ጥቃት ሲያስረዱ፣ ታጣቂዎቹ በተሽከርካሪዎች ላይ ትንኮሳ ለማድረስ መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች በቅርበት ስለነበሩ እግር በእግር ተከትለው ዕርምጃ መውሰድ ተችሏል ብለዋል፡፡

አቶ አብዮት ረዕቡ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተም፣ ‹‹እጀባ በሚያስፈልግበት አካባቢ ያለ እጀባ የተንቀሳቀሱ አካላት ነበሩ፡፡ በአካባቢው በቅርበት የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን በመገንዘብ ጥቃት ሊያደርሱ ችለዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በሚገኘው መተከል ዞን በተደጋጋሚ ግድያ፣ የጅምላ ጭፍጨፋና መፈናቀል ሲፈጸም እንደቆየ ገልጸው፣ ‹‹የጉሙዝ ሽፍታ›› ብለው የጠሩት ታጣቂ ኃይል ጥቃት የፈጸመው ‹‹የሕወሓት ኃይሎች ቦታዎቹን ተቆጣጥሯል›› የሚል ፕሮፖጋንዳ ሲሰማ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ኃላፊው በአጭር ጊዜ ውስጥ በዞኑ ፀጥታን ለማስፈንና ነዋሪዎችም ወደ ልማት ሥራ እንዲዞሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ በተለይም ግድያ የተፈጸመበት የመተከል ዞን ማኅበረሰብ ‹የያዘውን መሣሪያ ይዞ› ከፀጥታ አካላት ጋር መተባበር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው በዞኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ተሰማርተዋል ብለው፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የአካባቢው ሚሊሻዎችም የፀጥታ ኃይሉ አካል መሆናቸው በእነዚህ ኃይሎች ጥምረት ውጤት ማምጣት ተችሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በፀጥታ ኃይሎቹ ቅንጅት በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ውስጥ የሚገኙና ታጣቂዎቹ የሚጠቀሙባቸውን ካምፖች ማፍረስ መቻሉን አቶ አብዮት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ቅንጅት የተነሳ ድባጤ፣ ቡለን፣ ማንዱራና ዳንጉር ወረዳዎችን ጨምሮ በስድስት ወረዳዎች ውጤታማ የሆኑ የኦፕሬሽን ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ አብዮት የፀጥታ አካላቱ ቅንጅት ውጤታማ መሆኑን ይግለጹ እንጂ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፀጥታ አካላት ላይም ቅሬታ ይነሳል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመንግሥት ኃይሎች በመተከል ዞን ድባጤና ቡለን ወረዳዎች የብሔርና የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት በማድረግ በዜጎች ላይ እስራት እየፈጸሙ ነው ሲል ወቀሳ አቅርቧል፡፡

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) የፓርቲያቸው አባልና ደጋፊ የሆኑ አምስት ሰዎች መታሰራቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አንዱዓለም አቶምሳና ሙለታ ረጋሳ የተባሉ የፓርቲው የድባጤ ወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎች ታስረዋል ከተባሉት የፓርቲው አባላት መካከል ናቸው ብለዋል፡፡

በክልሉ ያሉ ባለሥልጣንና የፀጥታ አካላት ዜጎችን እንደ ወታደራዊ ካምፕ ባሉ ከመደበኛ ማረሚያና ማረፊያ ቤቶች ውጪ በሆኑ ቦታዎች እያሰሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ የሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ግን ይኼንን ወቀሳ ውድቅ አድርገዋል፡፡ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በጥፋታቸው መጠን ሊጠየቁና ሊታሰሩ እንደሚችሉ ገልጸው፣ የታሰሩት ሰዎች የፓርቲ አባል ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን በተመለከተ ግን ከፓርቲው በጽሑፍ የቀረበልን ጥያቄም ሆነ አቤቱታ የለም ብለዋል፡፡

ኃላፊው ማንም ሰው ሲያዝ ሕግ በሚያውቃቸው ቦታዎች ነው የሚጠየቀው ካሉ በኋላ፣ ባልተገቡ ቦታዎች ሰዎች ታስረዋል ለሚለው ግን፣ ‹‹ይኼንን ያደረገ አካል የለም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...