በሳምንቱ መጀመርያ ላይ እንደሰማነውም ኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት ትውጣ የሚለው ሰነድ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፈርመዋል፡፡ ይህ ገደብ በመጪው ጥር ወር ላይ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡
በውጭ ያሉ የሕወሓት ቡድን አባላት የሸረቡት ሴራ እንዳይሳካ ኢትዮጵያውያን በጋራም ሆነ በተናጠል ጥረቶች አድርገዋል፡፡
ከአገር በተዘረፈ ሀብት የተገዙ ወትዋቾች ምኞታቸው የተሳካ ቢመስልም፣ የአሜሪካ ውሳኔ ዓለማችን ያለችበትን አሳዛኝ ጊዜ የሚነግረንም ነው፡፡ ምዕራባውያንም በሐሰት ትርክት ላይ ተመርኩዘው የሚወስኑት ፍርደ ገምድል ውሳኔ ምን ያህል ፈር የለቀቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የአሜሪካ ውሳኔ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ይላኩ የነበሩ በአብዛኛው የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶች ከቀረጥ ነፃ እንዳይገቡ ክልከላ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ግን ኩባንያዎቻችን ምርቶቻቸውን ቀረጥ ከፍለው ወደ አሜሪካ የሚልኩበት ዕድል ተዘጋ ማለት አይደለም፡፡
ቀረጥ ከፍለን ምርቱን ማቅረብ እንችላለን፡፡ ይህ ባይሳካልን እንኳን ለአሜሪካ ገበያ መቅረብ የቻሉ በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶች በዓለም ላይ ሌላ ገዥ ያጣሉ ተብሎ አይታሰብምና ዓይናችንን ከፍተን አማራጭ ገበያ ማፈላለጉ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ምርቶቹ ለአገር ውስጥ ገበያም በጥሩ ዋጋ ሊሸጡ የሚችሉ መሆናቸውም ታሳቢ ሲደረግ አማራጮች እንዳሉን በማሰብ ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ በተገኙ አማራጮች መሄድ ይገባል፡፡ ከሠራንና ከጣርን ደግሞ ለአሜሪካ ይቀርብ የነበረውን ምርት ለሌላ አገር ማቅረብ ይቻላል፡፡
የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያ ምርቶች ያለ ቀረጥ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ውሳኔ ሲያሳልፉ ይብዛም ይነስም ኢትዮጵያ መጎዳቷ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ ከአጎዋ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችን አንፃር ከአምስት በመቶ ያልበለጠ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ለነገሩ ብዙም መቆዘም ያለብን አይመስለኝም፡፡
ዕድሉን ባናጣ መልካም ቢሆንም፣ እንዲህ ዓይነት የገበያ ዕድሎች ወትሮም እጅ መጠምዘዣ እንደሆኑ ታስበው የተቀመጡ ነበርና ጊዜው ደርሶ ሲተገበር መደንገጥ አይኖርብንም፡፡ እንዲሁም ምንም ነገር ከአገር በላይ ክብር ስለሌለ አማራጭ ገበያ ለማፈላለግ ዓይናችንን እንድንገልጥ የሚያስችል ነው፡፡
ስለዚህ የዕገዳውን ጉዳት ለመቀነስ ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ መሥራት ጊዜ የሚሰጠው አይሆንም፡፡
የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ አንዱ ችግር ለመዘናገት የገበያ መዳረሻዎቻችን ቁጥር የተወሰኑ መሆናቸውና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶቻችን አሁንም እሴት ያልታከለባቸው ጥሬ የግብርና ምርቶች ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በተለይ የውጭ ንግዳችን አጠገባችን ያለውን የአፍሪካን ገበያ ያላየ መሆኑም ክፍተት ነውና ይህን በመገንዘብ አማራጭ ገበያ ፍለጋው በሁሉም አቅጣጫ ሊሆን ይገባል፡፡
ሌላው ችግር ምርቶቻችንን ወደ ዓለም ገበያ ለመቀላቀል የሚያስችል ጠንካራ ፖሊሲ ካለመኖሩም በላይ ምርቶቻችን በሚገባ የሚያስተዋውቅ ጉልበት ማጣታችን ነው፡፡
የአሜሪካ ውሳኔ ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳን ነው ከተባለ ደግሞ መታሰብ ያለበት የወጪ ንግድ ምርቶቻችን በአግባቡ የማስተዋወቅ ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆን አለበት፡፡
ወደ አሜሪካ ቀረጥ ሳይቀረጥባቸው እንዳይገቡ የተከለከሉ ምርቶቻችንንም ሌሎች የማይረከቡበት ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ ገበያ ላይ የታዩት ምርቶች ጥራት ተቀባይነት ያላቸው ስለሆነ እነዚህን ምርቶች በሌሎች አገሮች ገበያዎች ውስጥ እንድናገኛቸው ከተፈለገ በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ የገበያ ቦታዎችን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም የወጪ ንግዳችንን ጉዳይ አሁንም በደንብ ልንሠራበት የሚገባ ነው፡፡ ያለንበት ወቅትም በተለመደው መንገድ ቡናና ሰሊጥ በጥሬው እየላክን የምንቀጥልበት አይደለም፡፡ በተለየ መንገድ እሴት ጨምሮ መላክን የምናበረታታበትና አብዝቶ ማምረትን ወሳኝ ጉዳይ አድርገን የምንቀሳቀስበት ነው፡፡
ዛሬ የአጎዋን ዕድል አጣን ብለን የጮህንበት ምክንያት የወጪ ንግድ ግብይታችን ኋላ ቀርነትና እንዲህ ቢያጋጥመን በዚህ መንገድ እንወጣለን ብለን አማራጭ ቀድሞ ካለማስቀመጣችን ነው፡፡
አማራጮች ቢኖሩን አሜሪካም ያልተደረገን አደረጋችሁ ብላ አጎዋን አርጩሜ ባላደረገችብን ነበር፡፡ ይህንን የእኛም ስንፍና ያመጣው መሆኑን አምነን መማሪያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከአጎዋ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ስናሰላውም ያን ያህል ኢኮኖሚውን የሚያናጋ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ይህ ማለት ግን ጠቃሚያችን አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ይህንን ዕድል በተፈለገው መንገድ ተጠቅመንበታል ተብሎ ሒሳብ እንሥራ ካልንም አጥጋቢ መልስ የለንም፡፡
ስለዚህ ይህ ዕድል ባይቀርብን ጥሩ ቢሆንም የሚያዛልቀን አለመሆኑን አስበንና በተለይ ደግሞ የተደረገብንም የአገር ሉዓላዊነታችንን በመጋፋት ጭምር በመሆኑ መታገዱም መፈቃዱም እንደ አገር ሲታሰብ ቆራጥ መሆን አለብን፡፡
ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታም እንዲህ ካሉ ነገሮች ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ከየአቅጣጫው እየመጣብን ያለውን ጫና ለመቋቋም በግልጽና በጋራ እንደ ዜና አገራችን ካለችበት ችግር ለማውጣት አቅማችን የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ይጠይቃል፡፡
የተደማመሩ ጫናዎች የሚያሳርፉት ተፅዕኖዎችን ከማሰብ በላይ መፍትሔው ምን መሆን አለበት? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መትጋት ለዚህም መመካከርና በአንድነት መቆም ያስፈልገናል፡፡
ምልከታችንን አስፍተን የጋራ ጠላታችንን ለመፋለም የምናሳየውን ወኔ ያህል ችግሮቻችንንም በተመሳሳይ መወጣት አለብን፡፡ አንድነት ኃይል ነው የሚባለውም ኃይል በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በመተባበርና በመተጋገዝ አብሮ መራድ በተናጠል የሚገጥመንን ጥቃት ለመከላከል ስለሚያስችለን ነው፡፡ ስለዚህ ከጦርነቱ ባሻገር ሊገጥሙን የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመሻገር የምንችለው ቀውሶቹን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የበለጠ ውጤታማ የምንሆንበትን መንገድ መቀየስ ሲያስችለን ነው፡፡ ይህ ችግር የሚወልደው መፍትሔ ደግሞ ወቅታዊውን ችግር ብቻ ሳይሆን መጪውንም ጊዜ ታሳቢ ያደረገና ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን ይገባል፡፡
አማራጮች ይስፉ የተሻሉ የሚባሉ ዕድሎችን የሚያመላክቱ ሐሳቦች ቀርበው በትብብር አገርንም ኢኮኖሚውንም እንታደግ፡፡