Tuesday, July 23, 2024

በሰው ዘር ላይ ወንጀል መፈጸሙን ያመላከተው የተቋማቱ ሪፖርት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዮናስ አማረ

በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥምረት ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ የሆነው ሰሞነኛው የትግራይ ጦርነት ሪፖርት የሁነቶችን ቅደም ተከተል ሲያስቀምጥ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ መከላከያ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ለጦርነቱ መጀመር መነሻ እንደሆነ ይጠቅሰዋል፡፡ ከዚያች ዕለት ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ በትግራይ ክልል ጦርነቱ በቀጠለበት ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በጥልቀት የሚያቀርበው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ቀደም ከሚሰሙ መረጃዎች በተለየ ብዙ ግኝቶችን አስነብቧል፡፡ በማይካድራ፣ መቀሌ፣ ሁመራ፣ ተምቤን፣ አክሱም፣ ሽሬና በሌሎችም የትግራይ አካባቢዎች የተደረጉ ምርመራዎችን፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ጭምር የተደረጉ ምርመራዎችን ሪፖርቱ ማካተቱ ግኝቱን ሰፊ እንዳደረገው ነው የሪፖርቱ ባለቤቶች የሚያስረዱት፡፡   

በትግራይ ‹‹ከዚህ ግጭት መጀመር በኋላ ብዙ ምስቅልቅሎች ደርሰዋል›› ይላል ሪፖርቱ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ይሰሙ የነበሩ በተቃርኖ የተሞሉ መካሰሶችና ውንጀላዎችን ለማጥራት የሚሞክረው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ቀደም ይወጡ ከነበሩ መረጃዎች በተለየ ሁሉንም የጦር ተፋላሚ ኃይሎችን ተጠያቂ ያደረገ ነበር፡፡ በትግራይ የኤርትራ ሠራዊት ወደ ጦርነቱ መግባቱ እንዲሁም ፈጸመ ተብሎ ሲነገር የቆየው ውንጀላ ጉዳይ በዚህ ሪፖርት ተብራርቶ ቀርቧል፡፡ ሕወሓትና የሕወሓት ደጋፊ የሆኑ ኃይሎች ፈጽመዋል የሚባለው ወንጀሎችም ቢሆን በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ‹‹ሕግ ማስከበር›› ያለውን የትግራይ ጦርነት ሲካፈል አደረሰው የሚባለው የመብት ጥሰትም በዚህ ሪፖርት ተካቶ ይገኛል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይልና ከአማራ ክልል የተነሱ ፋኖዎች አደረሱት የሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትም በአዲሱ ሪፖርት ራሱን ችሎ ቀርቧል፡፡

የትግራይ ጦርነት ተፋፍሞ ይካሄድ በነበረበት ከሰኔ ወር አስቀድሞ ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥትና ደጋፊዎቹ በሚባሉት የአማራ ክልል ኃይላትና የኤርትራ ሠራዊት ላይ ይሰማ የነበረው ክስ ከረር ያለ ነበር፡፡ ከሕወሓት ወገን ይደመጥ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ ተጠቅሞ ትግራይን ለመቅጣት ይሞክራል›› የሚለው ውንጀላ በተለይ በምዕራባዊያን መንግሥታትና በሚዲያዎቻቸው ጎልቶ ሲስተጋባ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን በሰብዓዊ ወንጀሎችና በዘር ማጥፋት ጭምር በዓለም አቀፍ አደባባይ ለማስጠየቅ ከሚዲያ ክስ ባለፈ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ጭምር ብዙ ጥረቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በትግራይ ለደረሰው ምሥቅልቅል ከምዕራባዊያን ከባዱን ጫና ቢቀበልም፣ ነገር ግን በአሜሪካኖቹ የቪዛ ማዕቀብ ተቀጪ የሆኑት ሁሉም ተፋላሚ ኃይላት ነበሩ፡፡ አሜሪካ የትግራይ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲባባስ ምክንያት ሆነዋል ባለቻቸው በሕወሓት፣ በአማራ ክልል፣ በፌደራል መንግሥትና በኤርትራ ጦር ባለሥልጣናት ላይ በጅምላ የቪዛ ማዕቀብ እስከመጣል ደርሳም ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ጫናው እየበረታና ግፊቱ እያየለ በሄደበት ወቅት ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይ ጉዳይ ተጣርቶለት እንዲቀርብ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኩል ግፊት በማድረጉ የሪፖርቱ ጥናት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዲካፈል በማድረግ ከአውሮፓዊያኑ ከግንቦት 16 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ በጋራ ግብረ ኃይል ጥናቱ ሲካሄድ የከረመው ይህ የትግራይ ጦርነት ሪፖርት፣ ከረዥም ጊዜ ጥበቃ በኋላ ነበር ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ለዓለም ይፋ የሆነው፡፡

ሪፖርቱ ስለትግራይ ጦርነት ትክክለኛ የነበረውን ሁኔታ ገላጭ መሆኑ፣ ሪፖርቱን ያቀረበው ጥምር ግብረ ኃይል በሸራተን ሆቴል በሰጠው መግለጫ ላይ አመልክቷል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቅርንጫፍ ኃላፊ ማርሴል አኮፖጎ ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ‹‹በትግራይ ጦርነት ከባዱን ዋጋ የከፈሉትና እየከፈሉም ያሉትም ሲቪሎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የጥቃቱ ሰለባዎች የደረሰባቸውን መከራ ምንነት ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ሀቁን ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ የቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለስም ይሻሉ፤›› በማለት ነበር ማርሴል አክፖግ ከምንም በላይ ሪፖርቱ ያለውን ፋይዳ ያስረዱት፡፡

ይህ ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በትግራይ ጦርነት የደረሰውን ሁኔታ በግልጽና ገለልተኛ በሆነ መንገድ እውነቱን ለማሳየት መቅረቡን ያስረዱት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶክተር) በበኩላቸው ‹‹አሉ የተባሉ መረጃዎችን ጥራት ባለው ባለሙያ ጥራት ባለው መንገድ ለማሰባሰብና ጥራት ያለው ሪፖርት ለማቅረብ›› እንደተሞከረ አስረድተዋል፡፡ ሕወሓት በግልጽ ለተቋማቸው የተአማኒነት ዕውቅና በመንፈግ በሪፖርቱ ላይ አስተያየትም ሆነ ግምገማ ለማድረግ እንደማይፈልግ እንደገለጸ ያስረዱት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ከዚያ በተረፈ ግን የኢትዮጵያ መንግሥትና የሚመለከታቸውን ሁሉ ባማከለ መንገድ ሪፖርቱ ግብዓታቸውን ወስዶ መቅረቡን አስቀምጠዋል፡፡

የሪፖርቱ ጥምር ግብረ ኃይል የሪፖርቱን አዘገጃጀት በተመለከተ ሸራተን ሆቴል ተደርጎ በነበረው ሪፖርቱን ይፋ የማድረግ ሥነ ሥርዓት ላይ ተዓማኒነቱን አጉልቶ ነው ያስቀመጠው፡፡ ሪፖርቱ በማንም ጫና ወይም ግፊትና ጣልቃ ገብነት ሳይሆን በገለልተኝነት ከፍ ባለ አጠናንና በበቁ ባለሙያዎች መቅረቡ በዚሁ ጊዜ ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡

ሪፖርቱ ከመቅረቡ በፊት በተለያዩ ወገኖች ይሰማ የነበረው አስተያየት ወደ አንዱ ያደላል በሚል ግብረ መልስ ሲፈተን መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የተለያዩ አካላት እንደየፍላጎታቸውና እንደየዝንባሌያቸው ከጦር ተፋላሚ ኃይላቱ በመምረጥ ሲወነጅሉም ይታዩ ነበር፡፡ ይህ ሪፖርት ‹‹በትግራይ ጦርነት ዋነኛ አጥፊው አካል እከሌ ነው›› ሳይል በተቻለ መጠን ለሁሉም ወገኖች የተመጣጠነ ጥፋትን ይሰጣል፡፡

ሪፖርቱ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከመቁጠርና በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፎ ከማቅረብ ባለፈም፣ አጥፊ በሆኑ አካላት ላይ ተጨማሪ የወንጀል ማጣራትም ሆነ ክስ የመመሥረት ሒደት ለማስጀመር ዕድል እንዲፈጠር መንገድ ይጠርጋል በማለት ነው የጥናቱ ቡድን ይፋ ያደረገው፡፡ ይህ ሪፖርት በጦርነቱ ተሳታፊ በነበሩ አካላት ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ ምልከታ ሚዛን ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የንጹኃን ተጎጂዎች ጉዳት ሜዳ ላይ ያለተጠያቂነት እንዳይቀር የሚረዳ ወሳኝ ሰነድ መሆኑም ነው የተብራራው፡፡

ሪፖርቱ ሲቀርብ ይህ ሁሉ ቢባልም ነገር ግን ሪፖርቱ መቅረቡን ተከትሎ የተሰሙ አስተያየቶች ይህን የሚያንፀባርቁ ሆነው አልተገኙም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ሪፖርቱን ወዲያው ነበር ያጣጣለው፡፡ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል መግለጫ ያወጣው የአስመራ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለን (ዶ/ር) ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ ኮሚሽነሩን በኤርትራ ጠልነት የከሰሰው የኤርትራ መንግሥት፣ ሪፖርቱንም የተምታታና ያልተጨበጠ መረጃ ይዞ የቀረበ ነው በማለት አጣጥሎታል፡፡

ሪፖርቱ ብዙ ጉድለቶች ያሉት ቢሆኑም ከነችግሮቹ እንደሚቀበሉት የተናገሩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ላይ ሲካሄድ የቆየውን የተዛባ ዓለም አቀፍ ውንጀላ ለማረም እንደሚያግዝ ተስፋ ጥለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ይህ ሪፖርት በኢትዮጵያ ላይ የተንሸዋረረ ዕይታ ያላቸው ወገኖችን እንደሚያስተካክልና ስለትግራይ ጦርነት የተጨበጠ መረጃ እንደሚያቀርብ ነበር የገለጹት፡፡

ይህን ሪፖርት ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖራቸው ቀጣይ ግንኙነት ወሳኝ ግብዓት ይሆናል ብለው ሲጠብቁ የቆዩ ወገኖች ነበሩ፡፡ በተለይ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታትና አሜሪካ በዚህ ሪፖርት መቅረብ ላይ ብዙ ፍላጎት እንዳሳደሩ ሲዘገብ ነበር የከረመው፡፡ ይህ ተጨማሪ ግምገማና ጥናት ሊደረግበት ይገባል በሚል ሐረግ ተደግፎ የቀረበ የትግራይ ጦርነትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሪፖርት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኩል ያገኘው ትኩረትና መነጋገሪያነትም ቀላል አልነበረም፡፡ 

የጥናቱ ዋና መመዘኛዎች ደግሞ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕጎች፣ የስደተኞች ሕጎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕጎች ናቸው፡፡

ሪፖርቱ ይፋ ሲሆን እንደተገለጸው፣ ከሆነ በትግራይ ጦርነት ሲቪሎችን የጥቃት ዒላማ ማድረግ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ሕፃናትን ለጉዳት ማጋለጥን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡

በትግራይ ጦርነት የዓለምና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕጎች ተጥሰዋል፡፡ በትግራይ ጦርነት የጦርነት ሕጎችም ተጥሰዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጦርነት ከሰብዓዊ ወንጀሎች ውጪ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለመገኘቱ ተነግሯል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በቀድሞ ጊዜ በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር በጦርነት ሕግ አማካሪነት ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህም ቢሆን ከ17 ላላነሱ ጊዜያት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ቀርበው ስለጦርነት ሕጎችና ስለሰብዓዊ ወንጀሎች ትንተና ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ስለዚሁ ጦርነት በቅርበት እንደመከታተላቸውና በሕግ ዘርፍ ካካበቱት ሰፊ ልምድ ተመርኩዘው የሪፖርቱን አጠቃላይ ድባብ አስተያየት እንዲሰጡበት ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል፡፡

የዘር ማጥፋት አልተፈጸመም የሚለው የሪፖርቱ ግኝት ለአገሪቱ ጠቃሚ ጎን ቢኖረውም ነገር ግን በአንዳንድ ምክንያቶች እንደማይቀበሉት አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ፡፡ በማይካድራ ምንድን ነበር የተፈጸመው? አንድን ዘር ለይቶ መግደልና ማጥቃት አልነበረም ወይ? ሲሉም የሕግ ባለሙያው ይጠይቃሉ፡፡ በአክሱም የኤርትራ ጦር አደረሰው የተባለውን ጥቃትም የሚያነሱት የሕግ ባለሙያው፣ በከተማዋ ከትግራይ ተወላጅ ውጪ ብዙም ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ የዘር ማጥፋት ላይባል ይችላል፡፡ ነገር ግን ማይካድራ አካባቢ ብዙ ብሔሮች ይኖሩ ነበር፡፡ መርጦ አማሮችን ብቻ መግደል በዚህ ረገድ ‹‹የዘር ማጥፋት ተብሎ አለመታየቱ አስገራሚ ነው›› በማለትም ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

በጥናቱ 269 የሚጠጉ ተጎጂ ዜጎችን በሚስጥር ቃለመጠይቅ መደረጋቸውን፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና አመራሮች ጋር ጥልቅ ውይይት መካሄዱንና በመስክ ምልከታ የተገኙ ማስረጃዎች ተካቶ ሪፖርቱ መጠናቀሩ ተመልክቷል፡፡ የዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ኢሰመኮ ጥምር ሪፖርት በማይካድራ ሳምሪ የተባለው ቡድን 200 ሲቪል አማራዎችን መግደሉን፣ በአክሱም የኤርትራ ጦር 100 ሲቪሎችን መግደሉን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመቀሌ ባካሄደው ጥቃት 29 ሲቪሎች ለሞት መዳረጋቸውን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች በጦርነቱ ተካፋይ በሆኑ ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ቁጥራቸውንና ቀናቸውን በመጥቀስ ጭምር ይዘረዝራል፡፡

ጥምር የጥናት ቡድኑ ያወጣው ሪፖርት ግኝት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ ጦር፣ የሕወሓት ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይልን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃዎች በጦርነቱ የተካፈሉ ወገኖች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን ያትታል፡፡

ሆኖም ይህን በተመለከተ ለዘብ ያለ ግኝት ሪፖርቱ ይዞ መውጣቱን የጠቀሱት የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ሪፖርቱ ከባድ ጥፋት ፈጻሚውን ደፍሮ ለመወንጀል አለመቻሉን ያስቀምጡታል፡፡

ከመደበኛ የጦር ሠራዊት ኃይሎች ውጪም በሁሉም ጎራ የተሠለፉ የሚሊሻ፣ ሳምሪ፣ ፋኖና ሌሎች ኢመደበኛ ኃይሎችም በሰብዓዊ ወንጀል መፈጸም በሪፖርቱ ተዘርዝረዋል፡፡ ሪፖርቱ ጥፋትን ማከፋፈሉና ከግራም ከቀኝም አመዛዛኝ የሆነ ግኝት ማምጣቱ በጎ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የወንጀል ዋና ተጠያቂ ኃይሎችን ደፍሮ አለማቅረቡ እንደ አንድ የሪፖርቱ ድክመት ሆኖ እንደሚታያቸው ነው የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ለሪፖርተር የተናገሩት፡፡

በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ የሚባሉትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንጀሎች ፍርድ ቤታ (ICC) ማቋቋሚያ ላይ የተቀመጡት አራት ድንጋጌዎች አሉ፡፡ አንዱ የዘር ማጥፋት ሲሆን፣ ሁለተኛው በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ ሦስተኛው የጦር ወንጀልና የስደተኞች ጎች ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ አቶ ሰለሞን፡፡ በእነዚህ መሥፈርቶችም ሆነ በሌሎች ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ ባሉ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ጥናቱ በመመርኮዝ ጠዘር ማጥፋት አለማግኘቱን ማረጋገጡንም ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሲቪሎች ተገድለዋል፣ ቤት ንብረታቸው ወድሟል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሕፃናትም በጦርነቱ ተጎድተዋል ብሎ ሪፖርቱ መዘርዘሩን የሚያስረዱት የሕግ ባለሙያው ይህም ቢሆን ቀላል የሚባል የወንጀል ድርጊት አለመሆኑን ነው ከሕግ ሙያቸው አንፃር አቶ ሰለሞን ያስረዱት፡፡

ሪፖርቱ ለስለስ ያለ ይመስላል፡፡ ዝም ብሎ ይህ ተፈጸመ፣ ይህ ሆነ የማለት ነገር ይታይበታል፡፡ ሁሉንም ወገን አንዱን ከሌላው ብዙም ሳያበላልጥ ጥፋተኛ ከማድረግ በዘለለ ደፍሮ የጎላ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚውን አያስቀምጥም፡፡ በማለት የግል እይታቸውንም አቶ ሰለሞን ያክላሉ፡፡

ሪፖርቱ በቀረበ ወቅት የጥናት ቡድኑ የጥፋቱ ምንጭ የሚባለውን አካል ተጠያቂ ማድረግ ላይ እንዳላተኮረ መነገሩን ያነሳንላቸው አቶ ሰለሞን ጥናቱ ይህን ጉዳይ አልሸፍንም ካለ የማስቀመጥ ግዴታ እንደሌለበት ነግረውናል፡፡

የሪፖርቱን ግኝት ባቀረቡ ወቅት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሪፖርት ዋና ዓላማ ለጦርነቱ ዋና መነሻ የሆነውን ኃይል ተጠያቂ ማድረግ ወይም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ደረጃ ማውጣት አለመሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ሪፖርቱ ገለልተኛና ጥራት ያለው ተዓማኒ መረጃ መያዙን አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ከሪፖርቱ አስቀድሞ የራሳቸውን ትንበያ በመከተል ስለጦርነቱ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያወጡ አገሮችም ሆነ አካላት በዚህ ሪፖርት ይታረማሉ ብለው እንደሚጠብቁ ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡

ይህ ሪፖርት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስተካከል ያግዛል የሚለውን ግምት ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) ብቻ ሳይሆን የሕግ ባለሙያው አቶ ሰለሞንም ተጋርተውታል፡፡

ዳንኤል (ዶ/ር) ተዓማኒነት ባለው የአጠናን መንገድ ተዓማኒ የሆኑ መረጃዎችን ይዞ የቀረበ ያሉት ይህ ሪፖርት በትግራይ ጦርነት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበሩ አገሮችንም ሆነ ተቋማት አቋም ለማስቀየር መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው አቶ ሰለሞንም ቢሆን ኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት አደረሰች የሰብዓዊ ረድኤትን ለጦርነት በመጠቀም ወንጀል ፈጸመች እያሉ የሚከሷት ሁሉ በዚህ ሪፖርት አመለካከታቸው ሊሻሻል ይችላል ብለው እንደሚገምቱ ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -