የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን እንዲሰለፉ ጥሪ አቀረበ።
ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀረበው ዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2014 ዓም በካፒታል ሆቴል በሃገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ ነው።
በክልል ከተሞችና ከተማ አስተዳደሮች እየተጠራ ያለውንና ነገ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓም በመስቀል አደባባይ የተጠራውን “የክተት ዘመቻ” እንደሚደግፍና ሚሊዮኖች የሰልፉ አካል ይሆናሉ የሚል ግምት እንዳለው አስታውቋል።
የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ እየተደረገ ባለው ዘመቻ ከጦር ሀይሉ ጎን እንዲሰለፉ የጠየቀ ሲሆን፣ በመላው ሀገሪቱ የክተት አዋጅ እንዲደረግ ምክርቤቱ ጥያቄ እንዳቀረበም ተገልጿል።
ምክር ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ በትላንትናው እለት በአሜሪካ የተደረገውን የዘጠኝ ፓርቲዎች ጥምረትም አውግዟል። ጥምረቱ የስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤትን ያጣጣለ ነው ሲልም ወቅሷል።
ምክር ቤቱ በውግያ መሀል የሚደረጉ አሻጥሮች እንዳሉ ጠቁሞ፣ መንግስት ውስጡን እንዲፈትሽ ጠይቋል።