በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ፣ እንዲሁም በአሸባሪነት የተፈረጁትን ሕወሓትና ኦነግሸኔን፣የውጭ አገራትና ሚዲያዎቻቸውን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓም ከንጋት አንድ ሰዓት ጀምሮ ተካሄደ።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በተለይ ሰሞኑን ፍፁም ሀሰት የሆኑ መረጃዎችንና “አዲስ አበባ በአሸባሪው ቡድን ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ተከባለች” በማለት የዘገቡትን የውጭ አገራት የመገናኛ ብዙኃንን አጥብቀው የሚተቹ ፣በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተፃፉ የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል።ከሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናትና ከተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮች ጋር በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ “አዲስ አበባ ተከባለች” የሚለውን የሲኤን ኤን ዘገባን በሚመለከት ባደረጉት ንግግር፣” አዎ አዲስ አበባ ከተማ በብርቅየና የቁርጥ ቀን ልጆቿ እንዲሁም በልማቷ ተከባለች”በማለት ለሀሰተኛ ዘገባው ምላሽ ሰጥተዋል።ሰልፉም በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።