- ዋሊያዎቹ ነገ በጆሃንስበርግ ጋናን ያስተናግዳሉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በነበረበት የማሟያ ጨዋታ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀደም ሲል በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት የሚቀጥል መሆኑ የሊጉ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ፡፡
ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደነገገውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ ‹የሊጉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?› በሚል ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች ነበሩ፡፡
በጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሊጉ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ፣ ይኼንን አስተያየት እስከሰጡበት ድረስ ጉዳዩን የተመለከተ፣ ከሚመለከተው አካል ምንም ዓይነት የደረሳቸው መመርያ የለም፡፡ በመሆኑም ፕሪሚየር ሊጉ ቀደም ሲል በወጣለት ፕሮግራም መሠረት በዚያው በሐዋሳ የሚቀጥል ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡
ከጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲካሄድ የሰነበተው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ብሔራዊ ቡድኑ ለነበረበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመርሐ ግብር ማሟያ ጨዋታ ምክንያት ሊጉ እስከ ኅዳር 15 ቀን ድረስ እንደሚቋረጥ መነገሩ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ብሔራዊ ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራ ሲሆን፣ በነገው ዕለት ከጋና አቻው ጋር ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል ዋሊያዎቹ ኅዳር 2 ቀን ከጋና ጋር በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ ላይ ከተጫወቱ በኋላ፣ በዚያው ወደ ዚምባቡዌ አቅንተው የመጨረሻውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ኅዳር 5 ቀን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡