Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአሁኑ ተግዳሮትና የፌዴራል ሥርዓቱ የሚሻው ሕክምና!

የአሁኑ ተግዳሮትና የፌዴራል ሥርዓቱ የሚሻው ሕክምና!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ኤሌኖር ሩዝቬልት ‹‹ትናንት ታሪክ ነው፣ ነገ ደግሞ ሚስጥር፣ ዛሬ ግን ስጦታ ነው›› ይላል፡፡ ለዚህም ነው ማንም ሰው መኖርን ግድ የሚለው፡፡ የታላቋን አሜሪካ ተጠቃሽ ቀደምት መሪ አባባል ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስናመጣው ትናንትስ እንደ ምንም ተደርጎ የታለፈ ታሪክ ሆነ? እንዴት የዛሬን ስጦታነትም ሆነ የነገን ሚስጥራዊ ተስፋነት አደብዝዘን እንቀብራለን ብሎ መቆጨት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ቁጭት የአገርም የሕዝብም መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ብዙዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮች በፊውዳላዊና ወታደራዊ አገዛዞች ዘመናትን ከማሳለፏ ባሻገር ጦርነት፣ ድህነትና ኋላቀርነት ገጽታዎቿ ሆነው ነበር የቆዩት፡፡ እነዚህ እውነታዎች ደግሞ ከታሪካዊነቷና ከጥንታዊነቷ በላይ በነፃነት ከመኖሯ ጋር የሚጋጩ የታሪካችን ክፋዮች ሆነው ዘልቀዋል፡፡ አረሩም መረሩም እነዚያ ታሪኮቻችን ናቸው፡፡ ጥሩ የሚሆነው ዛሬና ነገ ጥፋቶችን ላለመድገምና የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለማስቀጠል ተግባብተን መሥራት ስንችል ነበር፡፡

ሌላው ቀርቶ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የተከናወኑ በጎም፣ ክፉም ድርጊቶች ታሪክ ከመሆን አያመልጡም፡፡ ትናንት ለጥቂቶች የፖለቲካ ትርፍ ሲባል በተካሄደ አሉታዊ ቅስቀሳና የተዛባ ትርክት ምክንያት፣ እንዴት አንድ ትውልድ እየተዳማና እርስ በርሱ እየተፋጀ ለመቀጠል ይችላል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና በተለይ አማራ በተባለው ሕዝብ ላይ የተነጣጠረው የጥላቻ ቀስትና የጠባቦች ፍላፃ መቆሚያው መቼ ነው?

በእርግጥ ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የተከተለችው ፌዴራላዊ ሥርዓት በአብዛኛው ዘውግ ተኮርና የማንነት አከላለል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዜጎች የግል መብት በላይ ብሔረሰቦች እንደ ቡድን ያላቸው መብትም አድጎና ተለይቶ መቀመጡ ልዩነትን በማበርታት ረገድ ድርሻ ነበረው፡፡ ያም ሆኖ የጠራ መግባባት የተፈጠረበት ባይሆንም፣ አዲስ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዞ ተጀማምሮ ታይቷል፡፡

በዚህም በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ለዘመናት የኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና እምነታቸውን ማራመድ፣ ማስተዋወቅና ማስፋፋት ሲችሉ፣ በሌላ በኩል በራሳቸው ቋንቋ መማርና መዳኘት መቻላቸውን፣ ባልተማከለ አስተዳዳር በመመራታቸውም የተሻለ ልማት እየገኙ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአርብቶ አደሩና በአብዛኛው ታዳጊ ክልል የተመዘገቡ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊና የመሠረተ ልማት ውጤቶች እንደ ቀላል ሊታዩ አይችሉም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ኢፍትሐዊነቱና ሙስናው ሳንካ እንደነበረ ባይካድም፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ግን እየተከተልነው ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በታሪካዊ ቅራኔዎች ላይ የተመሠረተ፣ ጎሳና ማንነትን አልፋና ኦሜጋ በማድረግ አገራዊ ኅብረትና አንድነቱን የደፈቀ፣ ዴሞክራሲያዊነት አጅቦት ባለመቆየቱም ባልተመለሱ በርካታ ፍላጎቶች የሚላጋ መሆኑ ዳፋው ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪውም ትውልድ የሚተርፍ እየመሰለ መጥቷል፡፡ ከሁሉ በላይ ብሔረሰቦች ከዜጎች በላይ መብት ኖሯቸው ክልሎችን በባለቤትነት በመያዝ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ እንዲፈጠርባቸው እያደረጉ ያሉት፡፡ ነገሩ ከሕወሓት/ኦነግ ሸኔ አደገኛ አካሄድ በኋላ እንኳን ከወዲሁ ካልታረመም ድግሱ የፍጅት እንዳይሆን ያሳስባል፡፡

በመሠረቱ እንኳን ገና ለጋ ተሞክሮ ባለንና በተዛባ ቅኝት ፌዴራሊዝምን በጀመርነው ሕዝቦች ዘንድ ቀርቶ፣ በየትኛውም አገር ቢሆን ፌዴራሊዝምና ርዕዮተ ዓለም (አይዲኦሎጂ) የሚምታቱበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ነገሩን ከሥሩ ለመመርመር ጊዜም ሆነ ፍላጎት የሌለው ሰው ወይም ቡድን ደግሞ ፌዴራሊዝም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ‹‹ርዕዮተ ዓለም›› ከሚለው የአመለካከት ሒደት ጋር ያመሳቅለዋል፣ ወይም ሆን ብሎ ያጋጨዋል፡፡ ነገሩን በዕውቀትና በእውነት መመዘንና ወደ ውጤት መቀየር ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢታሰብም ነባራዊው ሁኔታ ሊያስተናግደው የማይችለውን አሀዳዊነት እንደ ማስፈራሪያ በመቁጠርና ፌዴራሊዝምን የልዩነት መቆስቆሻ ፍልጥ የማድረግ ዝንባሌ አየሩን እየሞላው ይገኛል፡፡ በተለይ በሕወሓትና በኦነግ ሸኔ ጀሌዎች አስተባባሪነት እየነደደ ያለው የነፍጥ ተቃውሞ፣ መነጋገርንና ሰላማዊ ትግልን የሚደፍቅ አገርን የሚረብሽ ብቻ ሳይሆን፣ ከተጀመረው መንገድም ሙሉ በሙሉ የሚያስወጣ መሆኑ በገቢር ታይቷል፡፡

ሕዝብን እንደ ሞኝ መቁጠር የሚያምራቸው በተዛባ መንገድ ሊነግዱበት ይሞክሩ እንጂ፣ ፌዴራሊዝም ርዕዮተ ዓለም አይደለም፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አደረጃጀት ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች በፌዴራል ደረጃ ዕውቅና ያለው መንግሥት የሚመሠርቱበትና በዚያም መንግሥት የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው፡፡ የአገሩን ሰማይና ምድር የሚጠብቀውም ሆነ የሚወክለውም በጋራና በአብላጫ ድምፅ የሚገነባው የፌዴራሉ መንግሥት ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ አባል የሆነ እያንዳንዱ ክልል ደግሞ በማዕከላዊው ፌዴራል መንግሥት መርሆዎች ላይ ተመሥርቶ እንደ የራሱ ልዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች የሚያደራጅበት ሥርዓት ነው፡፡ በእዚያ ላይም አንድ የጋራ አገርና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሚገነባበት ነው እንጂ፣ በእኛ አገር በአጉራ ዘለልነት እንደታየው (በተለይ በትግራይ ገዥዎች) ሁሉም የራሱን ጦር እየሰበቀና አገር ላፍርስ እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚባልበት አይደለም፡፡

የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ዓላማ በብዝኃነት ውስጥ አንድነትን፣ ልማትንና ዕድገትን፣ በዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም አሠራር አማካይነት ማምጣት መሆኑም ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ብዝኃነት ያላቸውን ሕዝቦች አንድ ለማድረግ ከዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የተሻለ ሥርዓት የለም የሚባለውም ከዚሁ እውነታ በመነሳት ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን በእኛ አገር ከተለያየ አገርነት የተሰባሰቡ ክልሎች ይመስል ቅራኔና ልዩነት ማቀጣጠልን ወያኔ በቀደደው ቦይ ለማስቀጠል የሚመኙ ትንሽ አልሆኑም፡፡

ዜጎች በዘርና በጎሳ እየተቧደኑ የሚባሉና አንዱ ሌላውን እያጠቃ የሚተራመሱበት ሳይሆን፣ ሁሉም ሕዝቦች በኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሕይወት ውስጥ በጋራ የመሳተፍ፣ እኩል ዕድል የሚያገኙበት ዴሞክራሲያዊነትን ይበልጥ ለማራመድ የሚረዳ ሥርዓት ነው፡፡ ያለ ጥርጥር የሥልጣን ክፍፍልን ለማረጋጋጥ እንደሚረዳም መናገር አይከብድም፡፡ ይህን ነው የዛሬዎቹ ፌዴራሊስት ተብዬዎች መረዳት የተሳናቸው፡፡ በአፋጣኝ መስተካከል አለበት፡፡

ይህንን እውነታ ከእኛ አገር አንፃር ስንመለከተው ምንም እንኳን ለዘመናት አብረው የኖሩ ብሔረሰቦች ቢኖሩም፣ ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር የተሟላ ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሐዊ ልማትን ለማምጣት ፌዴራላዊ ሥርዓት መገንባታቸው መልካም ዕርምጃ ነበር፡፡ አሁን እየታየ ያለው የትርምስና የግጭት መንስዔ ሥርዓቱ እንደሆነ ከማስመሰል፣ የግጭትና የጦርነት መንገድን ዘግቶ በሰላማዊ መንገድ መነጋገር ይበልጥ ጠቃሚ ነበር፡፡ ለወደፊቱም ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ይኼው አካሄድ ነው፡፡

አሁን አሁን በተጨባጭ እንደምንመለከተው በዚህች አገር ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ የተሻለ ዕድል እየተፈጠረና መንግሥታዊ ሆደ ሰፊነት እየታየም፣ በየጊዜው ለሚነሱ የብሔር ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች መነሻዎቹ ግልጽ እየሆኑ ነው፡፡ ይኼውም ከዚህ ቀደም በመሸፋፋን እንደሚባለው የአፈጻጸም ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ሕገ መንግሥቱ ወይም የፌዴራል ሥርዓቱ እሴቶች አለመሻሻልና በጥናት ላይ የተመሠረተ አሳታፊ ዕርምቶች ባለመደረጋቸው ሥጋት አጥልቷል፡፡ ያለ ይሉኝታ በድፍረትና በቅንነት ወደ መነጋገር ካልተገባም ከትናንት የተሻለ ዛሬን ማረጋገጥ መክበዱ አይቀሬ ነው፡፡ ቅድሚያ ግን ሰላምንና የአገር ህልውናን ማረጋገጥ መቅደም እንዳለበት ጥርጥር የለውም፡፡

በተለይ ሕወሓትና መሰሎቹ ለተራ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል የአገር ህልውናንም ሆነ የሕዝብ አንድነትን ለመናድ የሚሞክሩበትን አካሄድ የሚያበረታታውን ክፍተትና የሕግጋቱን ጉድለት መፈተሽ ግድ የሚል ሆኗል፡፡ ትውልዱም በየዋህነት ወይም በግብዝነት፣ በስህተት ወይም በሌላ ሥውር ዓላማ ሰበብ የፌዴራሊዝሙን ይዘት በማዛባት ወደ ሌላ ግብ ለመምራት የሚጎትቱትን ፅንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች የሚያርምበት ስክነት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ምሁራንና ሕዝቡም ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

እርግጥ ነው አሁን የተጀመረውን የጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መሠረት ያለው ፌዴራሊዝም ለመናድ ጠላት የሆነው ኃይል በዝቷል፡፡ በዋናነት ከአናሳ ቋት የወጣው ሕወሓት አክራሪ ብሔርተኞችን አሰባስቦ በሰላም አይሉት በጦርነትና በግብረ ሽበራ አገር ማናጋት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ለዚህም ነው ከለውጥ በኋላም ቢሆን በሕዝቦች መካከል ፀንቶ የቆየውን የአብሮ የመኖር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሁኔታዎችን የማፈራረስ ዓላማ ያላቸው ወገኖች አገር እያተራመሱ የሚገኙት፡፡

በተለይ ኦሮሚያ በተባለው ሰፊና አቃፊ ሲባል በኖረ ክልል ውስጥ ፅንፈኞች በሚያካሂዱት አስከፊ ቅስቀሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ብቻ (አንዴ ሳይሆን ተደጋግሞ) እየተገደሉ ነው፡፡ ሺዎችም ሀብት ንብረታቸው እየወደመ ለዕርዳታ ከመጋለጣቸው ባሻገር፣ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበትን (የጌዴኦ ያስታውሷል) ጭካኔ ማየት ተችሏል፡፡ ሕወሓት ራሱ በቀጥታ በተሳተፈበት ማይካድራ፣ አድርቃይና አፋርን የመሳሰሉ ቦታዎች ንፁኃን ተፈጅተውባቸዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ያለውን እውነትም ዓለም ጭምር የሚያውቀው ነው፡፡

በመሠረቱ ምንም ያህል ስለአብሮነትና ነባር እሴቶች ብንነጋገር፣ አንዱ ብሔር የራሱን ክልል ብቻ ይዞ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ በሩን ዘግቶ ‹‹አትድረሱብኝ›› የሚል አቋም እንዲኖረው ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ተጨማሪ ዕድል ከተሰጣቸው፣ ድርጊታቸው ጥፋት ብቻ ነው፡፡ የቀደሙ አገዛዞችን ክፍተት (ያውም በተጋነነ ትርክት እያዛቡ በመተንተን)፣ በምንም መለኪያ ከኃጢያቱ ጋር ግንኙነት በሌለው ትውልድ ላይ ለማወራረድ መቅበዝበዝ ምን የሚሉት ዝቅጠትና ዕብደት ይሆን ብሎ በድፍረት መነጋገር ካልተቻለ፣ ከፊት ያለውን ገደል አደገኛ ያደርገዋል፡፡ አስፈሪነቱም እንደ ቀላል ሊታይ አይገባም፡፡

እውነት ለመናገር እንኳንስ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር ወይም ሲዳማና ደቡብ ይቅርና በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ባልሆኑ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሥጋት ሥርዓታዊ ማስተካከያ ሊበጅለት የግድ ነው፡፡ አንዳንዴ በሌሎች ላይ የሚከሰተው ሰቆቃና ጥቃት ምንም እንኳን የብዙኃኑ አገር ወዳድ ኦሮሞ መገለጫ ነው ባይባልም፣ አመለካካቱ የሚመነጨው ከአክራሪው ብሔርተኛ የፖለቲካ ሥምሪት ብቻ ሳይሆን፣ ከራሱ ከዘውግ ፌዴራሊዝሙ አተገባበርም ነው ብሎ ደፍሮ አለመናገር ውድቀትን እንደማስቀጠል የሚቆጠር ነው፡፡

በተለይ የተዛባው አስተሳሳብ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ በተወሸቀ ጥገኛ የሚራመድ መሆኑ የአደጋውን ክብደት ያሳያል፡፡ ስለሆነም ጁንታው አበቃላትም፣ ተንኮታኩቶ በዋሻው ቀጠለም፣ ልዩ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ የፌዴራሊዝሙን ሕገ መንግሥታዊ እውነታዎች መፈተሽና ማስተካከል መሆን አለበት፡፡ በመተማመንና በድፍረት፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት ክልል መሆን ምንም እንኳን ሕጋዊ መብት ቢሆንም፣ የሕዝብ ሀብትን በክልል ሕዝብ ሥልጣን ይዞ ለመቀራመትም ሆነ አጥርን ከልሎ በብሔር ዋሻ ለመወሸቅ ያለው የልሂቃን ፍላጎት፣ አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር ተጣምሮ የጋራ ክልል ለመመሥረት እንኳን እየገደበ እንደሚገኝ እንደ ኦሮሞ፣ ቅማንት፣ አገውና መሰል ሕዝቦች በሚገኙባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የነበረውን ውጥረት እናስታውሳለን፡፡ አከላለልን ለብሔር የሚሰጠው ኋላቀርና ጥገኛ አስተሳሰብ እስከ መቼ ሊገፋ ይችላል የሚለው አስጨናቂ ጉዳይ ነው፡፡

እስካሁን በኢትዮጵያ በጉድለት የታየው የተዛባ የፖለቲካ አቋም የፌዴራሊዝሙ ትርጓሜና አሠራር ከርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ጋር ያጋጫል፡፡ ፌዴራሊዝም የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ነው ብለን ስናበቃ፣ ዘረኝነት ግን ርዕዮተ ዓለም መሆኑን ለምን ችላ እንላለን? ይህ አገር የሚያፈራርስ አስተሳሰብ በማንኛውም መንገድ ካልተቀጨ ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካው ዓይነት የዘር ጥላቻ (Xenophobia) ወይም እንደ ሩዋንዳዊያን ወደ እርስ በርስ መባላት ሊገፋን እንደሚችል ጁንታውና አጋሮቹ እየፈጸሙት ባለው ደባ በገሃድ ታይቷል፡፡ በሕዝቡ ጨዋነት ተገታ እንጂ፡፡

በእርግጥ አሁን ለሚታዩት ችግሮች መባባስ በሕገ መንግሥቱ አተገባበር ላይ ሆደ ሰፊነት ያጡ መሪዎችና ፖለቲከኞች የፈጠሩት ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ፅንፈኛ አክቲቪስቶች፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፖለቲከኞችና መቀመጫቸውን አሽሽተው የሕዝቡን መከራ የማይጋሩ ዳያስፖራዎች በዋነኛነት የሚንቀሳቀሱበት ሒደት እንዳለም ይታወቃል፡፡ እስካሁን እንደሚታየው የዘውግ ፌዴራሊዝሙን የተለጠጠ መንደርተኛ ዕሳቤ በማቀንቀን በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ተወሽቀው የሁከቱና የፀጥታ ችግር ስፖንሰሮች የሆኑ ጥገኞች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ይኼው በገባንበት መራር ጦርነት ውስጥም ሳይቀር አሻጥሩ እየታየ ነውና፡፡

ይህን አጨቃጫቂ ፌዴራላዊና ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ እንዲቀጥል የሚፈልገው ወገን ማን እንደሆነ በግልጽ ተለይቷል፡፡ ሕዝብ አንቅሮ የተፋው ሕወሓትና አጋሮቹ አገር ፈርሳም ብትሆን ምኞታችን ይሳካል ብለው ባልተገባ መንገድ ይህን ሁሉ ጥፋት እያደረሱ ያሉት፣ ትናንት የዚህ ሕገ መንግሥት ዋና ጠበቃ ነን ሲሉ የነበሩት ናቸው፡፡ ያን ሲሉ የነበሩት ግን ለእነሱ ብቻ እስከጠቀመ ድረስ ብቻ ነበር፡፡

አገራዊ ቀውስና ውድመት እያስከተለ ያለውን ጦርነት ቀድሞ እንደለኮሰ ብዙዎች የሚከሱት ሕወሓት ከአማራና አፋር ሕዝቦች ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ጠቡ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመከላከያውን የሰሜን ዕዝ በሌሊት ሲያጠቃ ከመላው አገሪቱ የተሰባሰቡ ልጆችን በመጨፍጨፍ ነበር፡፡ በሁሉም ግንባሮች የአገርን ሉዓላዊነት ለመከላከል እየተፋለመ ያለው ሠራዊትም ከየአቅጣጫው የተሰባሰበና የአገሩን ዓርማ ያነሳ ነው፡፡ በምንም መለኪያ ቢሆን የአገር ሀብት ውድመትና ዳግም ጦርነት የሚሻ ወገን አለ ብሎ መናገርም አይቻልም፡፡ ታዲያ ማን ነው ሕወሓትን አይዞህ ሊለው የሚችለው፡፡

በመሠረቱ ከሦስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ሕገ መንግሥቱን ሳይነካ ባለበት የቀጠለ፣ ፋታ በማጣቱ እንጂ የተለየ ማሻሻያዎችን በመውሰድ ዘላቂ ለውጥ ለማንበር የሚሞክር ነበር፡፡ እውነት ለመናገር ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ጋርም ሆነ ብሔርተኛ ከሚባለው አስተሳሰብ ጋርም የተቆራረጠ መስመር ነው ሊባል የሚችል አልነበረም፡፡ ግን እንቅፋቱና እየገጠመው ያለው ፈተና አገር እስከ መናድም የሚገፋ መሆኑ ብዙዎችን ማሳዘኑ አይካድም፡፡

ለውጡ በችግር ውስጥም እያለፈ የወሰዳቸው አንዳንድ ጅምሮች የፌዴራሊዝሙን መጠናከር እንጂ መጨፍለቅ የሚያሳዩም አልነበሩም፡፡ ለአብነት ያህል ከዴሞክራሲ ምኅዳሩ መስፋት ባሻገር በፌዴራሊዝሙ አተገባበርም ቢሆን የተሻለ ጀምር እየታየበት ያለ ለመሆኑ፣ የሲዳማ ሕዝብን የዘመናት የክልልነት ጥያቄ የመለሰበት አግባብ ይጠቀሳል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ፣ ከሞላ ጎደል አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ የተባለው ምርጫ፣ ልዩነትን ለማካተት የሞከረው የመንግሥት ምሥረታና መሰል ተግባራትም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 መንግሥት ከዚህ ቀደም የዜጎች የጎን ውጋት የነበሩትን ፍትሐዊ የልማት ሥርጭትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ቆርጦ የተነሳበት ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ አንድነትን መልሶ ለመገንባት እየተጋም ነበር፡፡ በየአካባቢው እየጎላ የመጣውን መገፋፋት ለመግታት ላይ ታች የሚልበት ጊዜም ነበር፡፡ የፌዴራሊዝም ጠበቃ መስለው ነጣጣይና በተቃርኖ የሞላውን ሕገ መንግሥት ለማስቀጠል የሚሹ ኃይሎች ናቸው ወደ ጦርነት የከተቱን፡፡

በእርግጥ አሁን ጦርነቱ ያደረሰውን ጥፋት አድርሶ፣ ብዙዎች ሞተውበት፣ አካላቸው ጎድሎ፣ ሚሊኖችን አፈናቅሎና ብዙ ሀብትና ንብረት በልቶ ወደ መቋጫው ምዕራፍ የሚደርስ መስሏል፡፡ በቀጣይ ግን መንግሥት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ፖለቲከኞችና ሕዝቡ የሰላምና የፀጥታ ሥራን ለማጠናከር ብሎም የሴረኞችን አደገኛ ዝንባሌ ለማክሸፍ የሚረባረብበት ሥርዓት መፈጠር አለበት፡፡ የሒደቱን አደናቃፊ ሕግጋትና አስተሳሰቦች በጋራ የማረሙ ጉዳይም ለነገ የሚባል አይሆንም፡፡

እንደ አገር ዜጎችን ያሳተፈ አገራዊ ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራና ለሰላም ዘብ መቆም ብቻ ሳይሆን፣ በፌዴራሊዝም ስም በጥላቻ ትርክትና በቂም በቀል ፖለቲካ የተሳከረውን ልሂቅም ወደ ማረም መገባት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን ዕውን በማድረግ የመላው ብሔር ብሔረሰቦችን መብት ይበልጥ ማረጋገጥና አገርን ለመጪው ትውልድ ጠብቆ ማስተላለፍ የሚቻለው፡፡ በእርግጠኝነት ግን የፅንፈኞች መንገድ ከከባድ ኪሳራ በኋላም ቢሆን ፉርሽ ይሆናል፡፡

በእርግጥ አሁን አገር የምትገኝበት ሁኔታ የሞት ሽረት ትግል የሚካሄድበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ስለደኅንነቱና ወጥቶ መግባቱ እንጂ ስለሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያና ሪፎርም ሊያስብ አይችልም፡፡ መንግሥት ቢዘገይም ችግሮቹን በዘዴና በብልኃት፣ በትዕግሥትና በማስተዋል ይዞ ለመራመድ ከመጓጓት ወጥቶ አገር ለማዳን መረባረቡ ሕዝብ ከጎኑ እንዲቆም የሚያደርገው ነው፡፡ በቀጣይም የአገሪቱን ህልውና፣ የሕዝቡን ሕይወትና ንብረት፣ የፌዴራል ሥርዓቱን መጠበቅና በብዙ የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ዘላቂነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡

መንግሥት ይህን ወደር የሌለው ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ያውቃል ተብሎ ይገመታል፡፡ ጠላት ባላቸው ኃይሎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ ጥርሱን ነክሶ እየሠራ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ የአገረ መንግሥት ግንባታ እንቅፋትና የውዝግብ በሮች የሆኑ ችግሮችን ከሥር ከመሠረታቸው ለመፍታትም ደጋግሞ መመርመርን የሚዘነጋው አይሆንም፡፡ የተጀመረው የፌዴራሊዝም ጉዞ የሚታከምበትና ይበልጥ የሚጠናከርበትን መንገድን መሻትንም እንዲሁ፡፡ ለዚህ ግን ከትናንት ታሪክ እየተማሩ፣ የነገ ሚስጥርነት እያጤኑ፣ የዛሬን ስጦታነት ዕውን ማድረግ ይገባል፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...