Tuesday, July 23, 2024

በችግር ጊዜ የሚያዋጣው የዜጎችን ዕምቅ አቅም መጠቀም ነው!

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ በተጨማሪ፣ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የዕውቀትና የልምድ ባለቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች አገራቸውን በሁሉም መስኮች ለማገልገል የሚያስችል ዕምቅ አቅም ስላላቸው፣ ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና ለመገላገል በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚባክኑ ውድ ሀብቶች መካከል አንዱ ዕውቀት ነው፡፡ የበርካታ ዕውቀት ባለቤቶች ወደ ጎን እየተገፉ ኢትዮጵያ የደረሰባት መከራ አይረሳም፡፡ አሁንም ይህ ችግር ተንሰራፍቶ ይታያል፡፡ አገራቸውን ያለ ምንም ክፍያ ለማገዝ የሚፈልጉ ወገኖች ዕውቀታችንና ልምዳችንን ተጠቀሙ ብለው ለመንግሥት አቤት ሲሉ የሚሰማቸው የለም፡፡ ቢሮክራሲው ውስጥ የተሰገሰገው ለአገር ደንታ የሌለው ኃይል ሥራውን የሚያጣ ይመስል፣ የዕውቀትና የልምድ ባለፀጋዎችን እየገፋ ኢትዮጵያ ከመጠን በላይ ተጎድታለች፡፡ የአገሪቱ ዲፕሎማሲ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲጠቃ ልምድ ያላቸው ሰዎች አይፈለጉም፡፡ ኢኮኖሚው በዋጋ ንረት ሲመታ መፍትሔ ማቅረብ የሚችሉ ባለሙያዎችን ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም፡፡ ውትድርናን ጨምሮ በሌሎች በርካታ መስኮች አገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ወገኖች ገሸሽ እየተደረጉ፣ ለአገራቸው ማበርከት የሚችሉት አስተዋፅኦ እንደ ጉም በኖ ቀርቷል፡፡ አሁን ጊዜው ቢረፍድም ‹‹ከመቅረት መዘግየት ይሻላል›› እንዲሉ፣ ለአገራቸው የሚጠቅም ዕምቅ አቅም ያላቸውን ዜጎች ማሰባሰብ ጠቃሚ ነው፣ ያዋጣልም፡፡

አገር ጦርነት ውስጥ ሆና ከውስጥም ከውጭም ጫናው ሲበረታ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲና በማኅበራዊ መስኮች በርካታ መሰናክሎች ማጋጠማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችንም ሆነ ማስፈራሪያዎችን በፅናት መመከት የምትችለው፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ፈጣንና እንደ ወቅቱ ሁኔታ ሊያገልግሉ የሚችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እየተራዘመ ሲሄድ ሊያስከትለው የሚችለው ተፅዕኖ ከባድ ስለሆነ፣ ጦርነቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡ የጦርነት ማጠናቀቂያ ዘዴዎች በርካታ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያዊያንን ዕምቅ አቅም መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖችም የሚያዋጣውን መፍትሔ ማመላከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጦርነት ሲራዘም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያዳክማል፣ ለልማት መዋል ያለበትን የሰው ኃይልና መዋዕለ ንዋይ ያባክናል፣ ከግብርና በተጨማሪ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ሊገኙ የሚችሉ ምርቶችንና አገልግሎቶችን መጠን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፣ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ያደርቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ብልኃት መፍጠር የሚችል ጠንካራና አርቆ አስተዋይ አመራር ያስፈልጋል፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በዲፕሎማሲው መስኮች ሊኖሩ የሚችሉ ተፅኖዎችን ለመመከት ብቻ መረባረብ ሳይሆን፣ ከተፈጠሩት ተግዳሮቶች ጭምር ለመጠቀም ብልኃተኛ መሆን የግድ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ወገኖችን ዕምቅ አቅም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

‹‹ችግር የብልኃት እናት ናት›› እንደሚባለው በምዕራባውያን ሊጣሉ የሚችሉ ማዕቀቦችን ታሳቢ በማድረግ፣ ከዕለት የፍጆታ ምርቶች ጀምሮ ሌሎችን ጭምር አገር ውስጥ ለማምረት የፖሊሲ አማራጮችን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ከውጭ የሚገቡ አብዛኞቹን ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን ለማስመጣት እንደ በፊቱ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አዳጋች ስለሚሆን፣ በእንዲህ ዓይነት ሒደት ውስጥ ያለፉ ሌሎች አገሮችን ልምድ በመቅሰም መላ መፈለግ በየዘርፉ ያሉ ልሂቃንና ባለሙያዎች ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡ ሽንኩርትን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ ከጎረቤት አገር የማስመጣት ወደር የሌለው ስንፍና በፍጥነት ተወግዶ፣ ሌላው ቢቀር በስንዴና በዘይት ራስን መቻል ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡ ከከተማ እስከ ገጠር በጓሮ እርሻ የሚመረቱ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና የመሳሰሉ ምርቶች ገበያዎችን መሙላት አለባቸው፡፡ ጤፍና የተለያዩ የጥራጥሬ ምርቶች በሰፊው ተመርተው ገበያውን ማጥገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዝናብ ጠባቂ በሆነው የመኸር እርሻ ብቻ ሳይሆን፣ የመስኖ እርሻ በከፍተኛ መጠን ተስፋፍቶ ከፅኑ የምግብ እጥረት መገላገል ያስፈልጋል፡፡ ሰፊ ለም መሬትና ከፍተኛ የውኃ ሀብት ከተስማሚ የአየር ፀባዮች ጋር የታደለች አገር፣ ወጣቶቿን አንቀሳቅሳ በምግብ የተትረፈረፈች እንድትሆን የሚመለከታቸው አካላት የኢትዮጵያዊያንን ዕምቅ አቅም ሥራ ላይ ያውሉ፡፡

ብልኃት የሚገኘው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፍለጋ ሲኖር ነው፡፡ ዕውቀት ሲባል ደግሞ ከየትም የተቃረመ ጥራዝ ነጠቅነት ሳይሆን፣ ጥራት ባለው ትምህርት ውስጥ ታልፎ ለምርምር የተዘጋጀ አዕምሮ መቀዳጀት ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት የሰረፀ ዕውቀት ከአካባቢ ጀምሮ ዓለምን እያዳረሰ በርካታ ልምዶችን ይቀምራል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ቅርቃር ውስጥ እንድትወጣ ለማገዝ ፈቃደኛ የሆኑ፣ በዕውቀትም ሆነ በልምድ የካበተ ተሞክሮ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሞልተዋል፡፡ የእነዚህን ወገኖች ዕምቅ ዕውቀትና ልምድ ለመጠቀም የግድ ቢሮ መስጠት አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን በትምህርታቸውና በሥራቸው ያካበቱትን ልምድ ለመጠቀም መድረኩን ማመቻቸት ይቻላል፡፡ በአማካሪነትም ሆነ በአሠልጣኝነት ጭምር በመጠቀም ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣም ብልኃት መቅሰም ይቻላል፡፡ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በሕክምና፣ በዲፕሎማሲ፣ በውትድርናም ሆነ በሌሎች መስኮች ሊገኝ የሚችለው ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ብልኃት ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ይህንን ዕምቅ አቅም እንደ አልባሌ ዕቃ የትም በመጣል መጎዳት ለኢትዮጵያ ኪሳራ ነው፡፡ የመንግሥት አመራሮችም ሆኑ ሌሎች ይህንን ጉዳይ ያጢኑት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ ምልከታዎች በመንግሥት እንዲከናወኑ ተብለው በተበታተነ መንገድ ምክረ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚደገፍ ቢሆንም፣ ከምክረ ሐሳቦቹ ባልተናነሰ ከትምህርትና ከልምድ የተገኙ ድጋፎች ግን ያስፈልጋሉ፡፡ ሁሉንም ነገር አንድ ወገን ላይ ጭኖ ለውጥ መጠበቅ ስለማይቻል፣ ከሚቀርቡት ሐሳቦች ባልተናነሰ በተግባር ሊታይ የሚችል ድጋፍ ለማድረግ መነሳት ይጠቅማል፡፡ ‹‹ጨለማ ላይ ከማፍጠጥ ቁራጭ ሻማ መለኮስ›› እንዲሉ፣ ሰጥቶ ለመቀበል የሚያስችሉ የሐሳብ ልውውጦች በተግባራዊ ድጋፍ ሊታጀቡ ይገባል፡፡ እዚህች ታሪካዊት አገር ውስጥ ዕውቀትና ጥንካሬ ቢኖሩም፣ ለተግባራዊ ለውጥ ካልማሰኑ ግን ውጤቱ ኃይል ማባከን ይሆናል፡፡ አሁን ቀዳሚው ጉዳይ ሕዝብን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያቀራርቡ፣ ለአገሩ ልማትና ዴሞክራሲ ተዋናይ እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን ማመቻቸትና ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ማውጣት መቅደም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እናት እንድትሆን የሚያግዙ ፍሬ ነገሮች ላይ ማተኮር ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተሞክረው ፍሬ ያላፈሩት ጽንፈኝነት፣ ጥላቻ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና ፍሬ ከርሲ ነገሮች ለኢትዮጵያ አይጠቅሙም፡፡ ብልኃትና አመክንዮ ላይ የተመሠረተ አሠራር ማስፈን የሚቻለው ዕምቅ አቅምን በመጠቀም ነው፡፡

አሁን ወሳኙ ሥራ መሆን ያለበት የኢትዮጵያዊያንን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም ፈጣንና አስተማማኝ ፖሊሲ መቅረፅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ሕገወጥ ድርጊቶችን ማምከን ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መሳተፍ በሕግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል መተማመን እንዲፈጠር፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ መብቶች በተግባር ሥራ ላይ እንዲውሉ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዳይጣሱ፣ ፓርላማው አስፈጻሚውን አካል በሚገባ እንዲቆጣጠር፣ የዳኝነት አካሉ በነፃነት እየሠራ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ አስፈጻሚው አካል በከፍተኛ ትጋትና ብቃት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው የጋራ ጉዳዮች ተሳታፊ የመሆን መብታቸው እንዲከበር፣ ከማንነት ብዝኃነት በተጨማሪ የሐሳብ ብዝኃነት ተግባራዊ ዕውቅና እንዲሰጠው፣ በጠላትነት የሚያፈራርጁ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ ወዘተ ከልብ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያንም በያሉበት ከተሰማሩበት የሥራ መስክ አስተዋፅኦ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ስኬታማ ሆና ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትሸጋገር ዕገዛ ያድርጉ፡፡ የሚያዋጣው የኢትዮጵያዊያንን ዕምቅ አቅም መጠቀም ነውና!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...