Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው 11 ቋሚ ኮሚቴዎችን አዋቀረ

ፓርላማው 11 ቋሚ ኮሚቴዎችን አዋቀረ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በቀድሞው ምክር ቤት አሥር የነበረውን የቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ወደ 11 ከፍ በማድረግ እንደ አዲስ አዋቀረ፡፡

ፓርላማው የምክር ቤቱን ቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት፣ ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በ15 ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው ምክር ቤት በቋሚ ኮሚቴ ውስጥ የምክር ቤት አባላት ቁጥር እስከ 45 የሚደርስ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ አደረጃጀት ከዘጠኝ እስከ 13 አባላት እንዲይዝ ተደርጎ ሲዋቀር፣ በቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚካተቱ አባላት ቁጥር ማነስ ከምክር ቤቱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

መሐመድ አብዶ (ፕሮፌሰር) የተባሉ የምክር ቤት አባል በህንድ፣ በቱርክ፣ በናይጄሪያ፣ በእስራኤልና በሌሎች አገሮች የሚገኙ የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችን አወቃቀርና አደረጃጀት በመጥቀስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በሥራ ላይ ካለው የአስፈጻሚ አካላት ቁጥር አንፃር የተዋቀሩት የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀትና በውስጣቸው የሚይዙት አባላት ብዛት ዝቅተኛ መሆኑን፣ ይህም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን አደጋች ሊያደርገው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

 

በፓርላማው ውስጥ ያለው የሰው ኃይል በትምህርትና በልምድ የዳበረ በመሆኑ የአስፈጻሚውን  የዕለት ተዕለት ክንውን በሚገባ ለመገምገም የአደረጃጀቱም ሆነ የአባላቱ ቁጥሩ ከፍ ብሎ እንዲደራጅ ጠይቀዋል፡፡

አቶ እሸቱ ገብረ ማርያም የተባሉ የምክር ቤት አባል አዲሱ አደረጃጀት፣ ከአጠቃላይ 547 የፓርላማ አባላት ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆኑትን ከቋሚ ኮሚቴ አባልነት ውጪ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

 በአዲሱ አወቃቀር መሠረት በ11 ቋሚ ኮሚቴ ሊካተቱ የሚችሉት የምክር ቤት አባላት ከ140 የሚበልጡ አይሆንም ሲሉ አክለዋል፡፡

ሌላ የምክር ቤት አባል ፓርላማው ቢያንስ ከ100 በላይ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ተወካዮች እያሉ ቁጥሩን ማሳነስ በተለያዩ ሙያዎች ተደግፎ ሥራን ለማከናወንና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያስቸግራል ብለዋል፡፡

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተዋቀረው የአስፈጻሚ አካል  ብዛት 22 ሲሆን፣ ፓርላማው ያደራጃቸው 11 ቋሚ ኮሚቴዎች እያንዳንዳቸው ቢያንስ የሁለት ሚኒስቴሮችን የሥራ እንቅስቃሴ ክትትል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከተወቀሩት ‹‹ቋሚ ኮሚቴዎች ኃላፊነቶች ውስጥ ለተቃዋሚዎችም የተሰጡ ቦታዎች ሲኖሩ፣ ለአብነትም የመንግሥት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን የአብን ፓርቲ ተወካይ አቶ ክርስቲያን ታደለ በሰብሳቢነት እንዲመሩት ተደርጓል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የቋሚ ኮሚቴዎች የአባላት ቁጥር እንዲቀንስ የተደረገበት ምክንያት በዋናነት የሰው ኃይልን ከሀብት ጋር አቀናጅቶና አናቦ ለመሄድና ተቀራራቢ ኃላፊነት ያላቸውን አስፈጻሚ ተቋማት በአንድ ላይ ክትትል ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በቀድሞው የፓርላማ ዘመን እስከ 45 የምክር ቤት አባላት በአንድ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ በመካተታቸው፣ ተቋማትን ለመገምገም በሚሄዱበት ወቅት ድግግሞሽ የበዛበት ሥራ ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለአብነትም በስብሰባና በግምገማ ወቅት ‹‹እገሌ እንዳለው›› በማለት የተደጋገሙ ሐሳቦች አዘውትረው ይነሱ እንደነበር፣ ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ በሚጠበቀው የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት እንዳስፈላጊነቱ የአባላትን ቁጥር በየጊዜው መጨመር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...