ሊገባደድ የሁለት ወራት ዕድሜ በቀረው የአውሮፓውያኑ 2021 በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ካቀደው ገንዘብ የ 1.3 ቢሊዮን ዶላር እጥረት እንዳጋጠመው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ማክሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዋና አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ሲያደርጉት የነበረውን የአራት ቀናት ጉብኝት መጠናቀቅ አስመልክቶ ድርጅቱ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ እ.ኤ.አ. 2021 ለሰብዓዊ ዕርዳታ ለማግኘት ከታሰበው 1.3 ቢሊዮን ዶላር እጥረት ስላጋጠመ ለበርካታ ዜጎች ዕርዳታ ማቅረብ አልቻለም፡፡
ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በ2021፣ 606 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ ክልል ማቅረብ እንደቻለ፣ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ 474 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረሱን ገልጿል፡፡
ቢሮው በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ካለው አገራዊ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት አንፃር በጣም አነስተኛ ነው፡፡
ዋና አስተባባሪውን ጠቅሶ የወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን፣ የተፈናቃዮች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን ዕርዳታ ለማግኘት እንደከበዳቸው ጠቁሟል፡፡
ጦርነት ውስጥ የገቡት ሁለቱ አካላት ለዜጎች ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲደርስና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከሥቃይ እንዲወጡ ግጭት እንዲያቆሙ በማሳሰብ፣ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የተጀመረውን የመፍትሔ ሐሳብ ተመድ እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡
እንደ ድርጅቱ መግለጫ በኢትዮጵያ በጦርነት፣ በድርቅ፣ በበረሃ አንበጣ፣ በጎርፍና መሰል ችግሮች ወደ ሃያ ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ዕርዳታ ሲያስፈልጋቸው፣ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ምክንያት ዕርዳታ የሚጠብቁ ናቸው፡፡