የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ85.1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የአዲስ አበባ ኃይል ማስተላለፊያና ማሠራጫ መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት፣ በሚያዝያ ወር ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማክሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሪፖተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በኤሌክትሪክ ማሠራጫ መስመሮች እርጅና ምክንያት የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር ለመቅረፍና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ የትራንስሚሽንና የሥርጭት (ዲስትሪቢዩሽን) መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግ በ85.1 ሚሊዮን ዶላር በጀት በአዲስ አበባና 50 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር ለመቅረፍ፣ የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ማስፈጸሚያ ከተመደበው ወጪ 60.64 ሚሊዮን ዶላር ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ እንዲሁም ቀሪውን 24.46 ሚሊዮን ዶላር ከጃፓን መንግሥት የተገኘ ብድር ነው፡፡
ይህ በቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኩፕመንት ቴክኖሎጂ (CET) እና ቻይና ‹‹ናሽል ሄቪ ማሽነሪ ኮርፖሬሽን›› (CHMC) በተባሉ የቻይና ሥራ ተቋራጮች እየተከናወነ ያለ ፕሮጀክት፣ በአዲስ አበባና በአካባቢው ያለውን የዲስትሪቢዩሽ ኔትወርክ በማደስና አቅሙንም በማሳደግ በከተሞቹ የሚኖረውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጥራት ያለውና አስተማማኝ የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ግንባታው በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያስታወቀ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት 35 በመቶ አፈጻጸም ደረጃ ላይ የደረሰው ይህ ፕሮጀክት 625 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታና 266 የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮች ተከላን ያካተተ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ የመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ስርቆት በሐዋሳ ዲስትሪክትና አካባቢው መፈጸሙን አስታወቋል፡፡ በተቋሙ የደቡብ ሪጅን የሕግ አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዲሳ ስንታቸው እንዳስታወቁት፣ በሪጅኑ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ4.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ስርቆት ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ስርቆቱ የተፈጸመባቸው የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ ሽቦና ተሸካሚ ምሰሶዎች እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተለይም በደቡብ ክልል በሚገኙት ወላይታ፣ ከምባታና ጠምባሮ ዞኖች፣ እንዲሁም በሲዳማ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ችግሩ በስፋት እንደሚታይ ተጠቁሟል፡፡
ከተጠቀሱት ቦታዎች በተለይም ከቢሻን ጉራቻ እስከ ሐዋሳ አየር ማረፊያ ድረስ የሚዘልቅ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር ስርቆት ሳቢያ፣ በአካባቢዎቹ በዚህ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በጉምሩክ ኮሚሽን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ሻሸመኔ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ግምታቸው ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ 28 ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ ጥቅል ሽቦዎች መያዛቸው ገልጾ፣ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለመከላከል ማኅበረሰቡ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡