Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በርካታ ኩባንያዎች የሚሳተፉባቸው ንግድ ትርዒቶች ነገ ይከፈታሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ትርዒቶችን በቋሚነትና በተደራጀ ሁኔታ ከሚያሰናዱ ተቋማት ውስጥ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ምክር ቤቱ በዓመት ለአራት ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ ዓለም አቀፍ ቋሚ ንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለይ አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በርካታ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በማሳተፍ ወደ ሃያ ዓመት የሚቆጠር ዕድሜ ያለው ነው፡፡  

ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን እዚህ በቋሚነት ሲያዘጋጇቸው የነበሩ የንግድ ትርዒቶችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳያዘጋጅ ቀርቷል፡፡

የንግድ ትርዒቶቹን መልሶ ለማስጀመር በወሰነው መሠረት ነገ ኅዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም. 13ኛውን ዓለም አቀፍ እርሻና የምግብ፣ እንዲሁም አራተኛውን የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ የንግድ ትርዒቶች በማጣመር ይከፍታል፡፡

ከኅዳር 2 እስከ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚቆዩት የንግድ ትርዒቶች ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ ንግድ ምክር ቤቱ የሚዘጋጃቸው ንግድ ትርዒቶች ናቸው፡፡ ንግድ ትርዒቶቹ ‹‹ኮሜርሻል አግሪካልቸር ፎር ፉድ ሰስተነብሊቲ ኢን ኢትዮጵያ›› እና ‹‹ኮምፕቴቲቭነስ ኢን ማኑፋክቸሪንግ›› በሚሉ የሚካሄዱ እንደሆነም ንግድ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡  

እነዚህን የንግድ ትርዒቶች በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በንግድ ትርዒቶቹ ወደ 160 የሚሆኑ ኩባንያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 100 የሚሆኑት በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ፣ 60ዎቹ ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ከእነዚህ ሁለት የንግድ ትርዒቶች ጎን ለጎን በመስቀል አደባባይ መስክ ላይ ለንግድ ምክር ቤቱ የመጀመርያው የሚሆን የአውቶሞቲቭ ንግድ ትርዒት የተሰናዳ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በአውቶሞቲቭ የንግድ ትርዒቱ 20 ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

 በሦስቱ ዘርፎች የሚሳተፉ ኩባንያዎች 180 እንደሚደርሱ ከዋና ፀሐፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከኮቪድ-19 በኋላ የተዘጋጁት ንግድ ትርዒቶች ላይ ለመጀመርያ ጊዜ አንድም የውጭ አገር ኩባንያ የማይሳተፍበት ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የንግድ ትርዒት ለመጀመርያ ጊዜ የውጭ አገር ኩባንያዎች የማይገኙበት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህም የሆነው ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሥጋትና በቅርቡም በወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት እንሳተፋለን ብለው ማረጋገጫ የሰጡ ኩባንያዎች ተሳትፏቸውን በመሰረዛቸውን ነው፡፡

በዋናነት ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቸ በኢትዮጵያ ላይ እያሠራጯቸው ያሉት ዘገባዎች ፍላጎት የነበራቸውን የውጭ አገር ኩባንያዎች ሥጋት ያሳደረባቸው በመሆኑ በዘንድሮው የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ እንዳይኖር አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ፈታኝ ቢሆንም፣ እንደ ምክር ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት በማሳደጉ ረገድ ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ከዚሁ አንፃር ሥራችንን እንሠራለን ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የውጭ ኩባንያዎች ባይኖሩም ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ በአገር ውስጥ ኩባንያዎችም ቢሆን የምናካሂዳቸውን የንግድ ትርዒቶች ሳናቋርጥ እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለይ ግብርናንና ማኑፋክቸሪንግን በተመለከት የንግድ ትርዒቶች ላይ በአነስተኛ ደረጃ ከ30 ያላነሱ የውጭ አገር ኩባንያዎች ይሳተፉበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በሚያዘጋጀው ትልቁ የአዲስ ቻምበር የንግድ ትርዒት ላይ በትንሹ ከ27 አገሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ግን የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እያሳረፉ ያለው ጫና ቢኖርም፣ ዓላማውን ለማሳካት አስፈላጊውን ጥረት የሚያደረግ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚካሄዱ የንግድ ትርዒቶች ላይ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ እንዲኖር ሚዲያዎቹ የሚያሠራጩት ዘገባ ትክክል አለመሆኑን በማስረዳት አስፈላጊውን ሥራ እንደሚሠሩ ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮው የንግድ ትርዒቶች እንደሚሳተፉ አሳውቀው ከሰረዙት መካከል የዱባይና የጣሊያን ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች