Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ መንግሥትና የሕወሓት አመራሮች ችግር ፖለቲካዊ መሆኑንና መፍትሄውም ፖለቲካዊ እንደሆነ መረዳታቸውን...

የኢትዮጵያ መንግሥትና የሕወሓት አመራሮች ችግር ፖለቲካዊ መሆኑንና መፍትሄውም ፖለቲካዊ እንደሆነ መረዳታቸውን ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ተናገሩ

ቀን:

በግጭቱ የሚሳተፉ አካላት ከወሰናቸው ውጪ ያሰማሩትን ጦር እንዲያስወጡ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል

መንግሥት ለሕወሓት የጦር መሣሪያ የሚያቀርቡ የውጭ አካላት መኖራቸውን ለፀጥታው ምክር ቤት አስታውቋል

የኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮችና የሕወሓትን አመራሮች በተናጠል አነጋግረው ፣በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን አሳሳቢ ግጭት ችግር ፖለቲካዊ መሆኑንና መፍትሄውም ፖለቲካዊ  እንደሆነ መረዳታቸውን  የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ተናገሩ።

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ይህንን የተናገሩት፣ ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2014 .. ምሽት ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ላይ ለመከረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት እያደረጉ ያሉትን የሰላም ጥረት የተመለከተ ገለጻ ሲሰጡ ነው።

የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካዩ ኦባሳንጆ እንደተናገሩት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (/) እና ከኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሣህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር የሰላም ተልዕኳቸውን በተመለከተ መምከራቸውንና ባለፈው እሑድ ጥቅምት 28 ቀን ደግሞ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በመገኘት ከክልሉ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ መንግሥት ከሚገኙ አመራሮች፣ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር ትርጉም ያለው ውይይት ማድረጋቸውንና በመቀሌ ተገኝተውም ይህንኑ መከወናቸውን የገለጹት ኦባሳንጆ፣ ‹‹ሁለቱም ወገኖች ወደ ግጭት ያስገባቸው የፖለቲካ ልዩነት እንደሆነና ልዩነታቸውም በፖለቲካዊ ውይይት መፍትሔ ማግኘት ይችላል ብለው እንደሚያምኑ በተናጠል ገልጸውልኛል፤›› ብለዋል።

ይህ እምነታቸውም ችግሩን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ዕድል እንደከፈተ የተናገሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ፣ ይህንን ዕድል ለመጠቀም ሁሉም ዓለም አቀፍ ባለድርሻ እንድ ሆኖ በመተባበር ዕድሉን መጠቀምና ግጭቱ ማስቆም እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ እንደሚገባው አስረድተዋል።

‹‹ነገር ግን የተከፈተው ዕድል ትንሽና ያለው ጊዜም በጣም አጭር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፤ብለዋል።

‹‹በመሆኑም የፀጥታ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሊሰጥና ሊያበረታታ ይገባል፤›› ያሉት ኦባሳንጆ አክለውም፣ ‹‹ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ያለቅድመ ሁኔታና ጊዜ ሳይሰጡ አጠቃላይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የፀጥታ ምክርቤቱ ጥሪ ማቅረብ ይኖርበታል፤›› ሲሉ አሳስበዋል።

በቀጣዮቹ ቀናትም ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በማቅናት በተለይም ከአማራና ከአፋር ክልል አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ አስታውቀዋል። ወደየአገሪቱ ክልሎች በመጓዝ ከክልል አመራሮች ጋር ውይይት የሚያደርጉበት ምክንያት የሁሉንም ባለድርሻዎች ሐሳብ አንድ ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

‹‹ይህንን የማደርገው የሁሉንም ባለድርሻዎች ሐሳብ ለማስታረቅና ከክልሎቹ የአስተዳደር ወሰን ውጪ በሚገኙ አካባቢዎች የተሰማሩ የጦር ኃይሎቻቸውን እንዲያስወጡ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ዕርዳታ በፍጥነትና ያለገደብ ለተረጂዎች መቅረብ እንዲችል ለማድረግ ነው፤ብለዋል።

በተያዘው ሳምንት መገባደጃም ሁለቱን ጉዳዮች ማለትም ከአስተዳደር ክልላቸው ውጪ እንዲሰማሩ የተደረጉ የጦር ኃይሎች ለማስወጣትና ያልተገደብ ሰብዓዊ ዕርዳታ በፍጥነት ለማቅረብ ወደሚያስችል ተጨባጭ መዳረሻ ለመድረስ ይቻላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በዚህ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውይይት ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) የሕወሓት ኃይል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባ በመውጋት የፈጸመው የአገር ክህደት ሳያንስ ይህ ቡድን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምፁን ሰጥቶ ያስቀመጠውን የፌዴራል መንግሥት በኃይል ለማንሳት እየጣረ መሆኑን ተናግረዋል።

‹‹የወንጀል ቡድን›› ሲሉ የጠሩት የሕወሓት ኃይል ከፈጸመው ክህደት አልፎ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ ጦርነቱን ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት ያገኘው በውጭ ኃይሎችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሚያደርጉለት ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ ተበረታቶ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወትሮም ቢሆን ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ዝግጁ እንደነበርና አሁንም ለሰላማዊ መፍትሔ እንደሚሠራ ታዬ (አምባሳደር) አስረድተዋል።

‹‹ለዚህ ቡድን ከሞራል ድጋፍ ባሻገር የሳተላይት የግንኙነት መሣሪያዎችን፣ የጦር መሣሪያና ተዋጊ ጭምር በማቅረብ እየደገፉ ያሉ የውጭ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፤›› ብለዋል።

የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ወይይት በተካሄደ በማግሥቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አጭር መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው የፌዴራል መንግሥት ኢትዮጵያ የገጠማትን ጊዜያዊ ችግር ለመፍታትና የጀመረውን የማሻሻያ ሥራዎች ለማከናወን ከኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የሕወሓት አመራሮች ለተለያዩ የውጭ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች በሰጡት አስተያየት፣ በትግራይ ክልል ላይ የተጣሉ ዕቀባዎች በቅድሚያ ከተነሱ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...