Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለት ሳምንታት በተደረጉ የእሑድ ገበያዎች ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ግብይቶች መፈጸማቸው ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ እየተባባሰ የመጣውን የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ለማቃለል በማሰብ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደረጉት የእሑድ ገበያ አማራጮች፣ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ግብይቶች መፈጸማቸው ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የግብይት ዳይሬክተር ወ/ሮ ደብሪቱ ለዓለም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በሁለቱ እሑዶች የተደረጉት ግብይቶች መጠን በገንዘብ ሲሰላ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡  

ለመጀመርያ ጊዜ በአምስት የተመረጡ አካባቢዎች በተደረገው የእሑድ ገበያ የተደረገው ግብይት ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር ያስታወቁት ዳይሬክተሯ፣ በሁለተኛው ዙር እሑድ ደግሞ የተፈጸመው ግብይት ከ7.6 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የእሑድ ገበያ መስፋፋት ምርትን በተመጣጠነ ዋጋ የማቅረብ ጥቅም ብቻ ያለው እንዳልሆነ የገለጹት ወ/ሮ ደብሪቱ፣ የአቅርቦቱን መሻሻል የሚመለከቱት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ሳይወዱ በግድ ምርቶችን በተመጣጠነ ዋጋ የሚያቀርቡበት ዕድል አንደሚፈጠር አስረድተዋል፡፡

አሥር ያህል የሸማች ኅብረት ሥራ ዩኒየኖች በእሑድ ገበያ የግብይት እንቅስቃሴ እየተሳተፉ ሲሆኑ፣ እነዚህ ዩኒየኖች በሥራቸው ላሉ መሠረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለግብይቱ አስፈላጊ ምርቶችን የሚያስገቡና የሚያቀርቡ ናቸው ተብሏል፡፡ ከሌሎች አምራች የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች ጋር ትስስር የሚፈጥሩት ዩኒየኖቹ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ 148 የሚደርሱ መሠረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 62 የሚሆነት በእሑድ ገበያ ተሳታፊ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ሁሉንም ማኅበራት ለማሳተፍ የማይቻለው አንድም ሁሉም የመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቶችን በእኩል አቅምና የትራንስፖርት አቅርቦት መጠን ለማቅረብ ባላቸው የዓቅም ውስንነት እንደሆነ ያስታወቁት ወ/ሮ ደብሪቱ፣ በተጨማሪም በቂ የሆነ ምርት ላይኖራቸው ይችላል የሚለው ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በቀጣይ ሁሉም መሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በሚገኙበት አካባቢ ምርቶችን እንዲያቀርቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በየወረዳው የሚገኙ የኅብረት ሥራ ሱቆች አማካይነት ምርቶች እንደሚሸጡ ጠቁመዋል፡፡

በእሑድ ገበያ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ለተጠቃሚውና  ለነዋሪው ጥሩ አማራጭ ሆኗል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ቀደም የገበያ አማራጩ ሲጀመር በወር አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ እንዲደረግ ቢታቀደም፣ የሰውን አቀባበልና ፍላጎት መሠረት በማድረግ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በየክልሉ ከሚገኙ  የአምራች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር ምርቶች ለሸማቹ እንዲቀርቡ እየተደረጉ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ከታወቁ ነጋዴዎችና ከአምራችና አስመጪ ኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲሁ በመነጋገር ምርቶች መቅረባቸው ታውቋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ደብሪቱ ገለጻ፣ በቀረበው የገበያ አማራጭ በምርቶች ላይ ከሁለት ብር እስከ ሦስት መቶ ብር የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ታይቷል፡፡ በተለይም ጤፍ የቀረበበት ዋጋ በመደበኛው ገበያ ላይ ካለው ዋጋ ሰፊ ልዩነት የታየበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ቀይ ጤፍ በእሑድ ገበያ ኪሎው በ37 እና 38 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ በመደበኛው ገበያ ለገበያ የሚቀርብበት ዋጋ 40 እና 41 ብር ነው፡፡ ይህም በሁለቱ ገበያዎች መካከል በኩንታል 300 ብር የሚደርስ ልዩነት እንዳለ ያሳያል ተብሏል፡፡

ሠርገኛ ጤፍ ሸማች ማኅበራት ኪሎውን 40 እና 41 ብር እንደሚሸጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ነጋዴውን የሚሸጥበት ዋጋ ከ44 ብር በላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከምንጃር አካባቢ ‹‹ከሰም›› በሚባል የአምራች ኅብረት ሥራ ዩኒየን የቀረበው ማኛ ጤፍ ኪሎው 46.50 ብር እንደሚሸጥ የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ተመሳሳይ የሆነው ምርት በመደበኛ ወፍጮ ቤቶች ከ54 እስከ 56 ብር እንደሚሸጥ ገልጸዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለኅብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ አገልግሎት አቅራቢነታቸው ታምኖበት፣ በከተማዋ የሚደረጉ የኢኮኖሚ አሻጥርና የምግብ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት የ500 ሚሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ብድር ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች መስጠቱን ያስታወሱት ወ/ሮ ደብሪቱ፣ ይህንን የተፈቀደ ብድር ዩኒየኖቹ ወስደው በዋናነት ለሰብል እህሎች ግ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት አሥር የሚደርሱ ኅብረት ሥራ ዩኒየኖቹ በነፍስ ወከፍ ከተፈቀደው 500 ሚሊዮን ብር፣ 50 ሚሊዮን ብር በሁለት ዙር እንደወሰዱ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ተዘዋዋሪ ብድሩ የሚመለስበት ጊዜ ስለደረስ ገንዘብ ቶሎ ተመልሶ ሥራ ላይ እንዲውል ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኤጀንሲው የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተለቀቀውን የተዘዋዋሪ ብድር በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ ጥሩ ሥራዎችን እየሠራ ነው ያሉት ወ/ሮ ደብሪቱ፣ የከተማ አስተዳደሩም የተዘዋዋሪ ብድር ድጋፉን እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች