Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ጨረታ አወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2014/15 ዓ.ም. የሰብል ዘመን የሚቀርብ ከ20.1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም ግልጽ ጨረታ ማውጣቱን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኮርፖሬሽኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ሦስት ወራት የሚያደርጋቸው የዝግጅት ሥራዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ኮርፖሬሽኑ ለሥልጠና፣ ለእርሻ መሣሪያዎች ዝግጅት፣ ለመስኖ ማስፋፋት፣ ለምርጥ ዘር ምርት አቅርቦትናሜካናይዜሽን ማዕከል ማስፋፊያ፣ ለአፈር ማዳበሪያና ለምርት ማከማቻ መጋዘን ግንባታና ለምርት ስብሰባ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከሚያከነውናቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የአፈር ማዳበሪያን ግዥን በግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ መፈጸም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ኮርፖሬሽኑ በጥቅምት ወር መጨረሻ ለ25 ቀናት ክፍት የሆነ ዓለም አቀፍ ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ጨረታው የፋይናንስ የቴክኒክ ሰነድ ግምገማ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ተግባር እንደተገባዳደ ወደ ግብርና ሚኒስቴር ተልኮ እንደሚፀድቅ አቶ ጋሻው አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ 18.1 ሚሊየን ኩንታል እንደነበር ያስታወቁት አቶ ጋሻው፣ ዘንድሮ የቀረበው ፍላጎት የሁለት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለበት እንደሆነ አስረድተዋው፣ ይህም ፍላጎት የሚዘጋጀው በግብርና ሚኒስቴር አማካይነት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዓመቱ መጨረሻ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት እንዳቀደ ተገልጿል፡፡ ይህም ከኦፕሬሽን ገቢ፣ ዕጣንና ሙጫ ወደ ውጭ በመላክ ከሚገኝ ገቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አቶ ጋሻው እንዳስታወቁት የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የልማት ድርጅት በመሆኑ ከውጭ አምጥቶ የሚያቀርባቸውን ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶች ያለ ምንም ትርፍ ለገበሬው ያከፋፍላል ብለው፣ ይህ የሆነው አንድም የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ለማሳደግ በሌላ በኩል ደግሞ የግብርና ምጣኔ ሀብቱን ለማሳደግ በሚል  እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ለምርት ዘመኑ ከውጭ አገር የተገዙ አግሮ ኬሚካሎችም ለተጠቃሚዎች በመሠራጨት ላይ እንደሚገኙ ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ፣ ምርት ለማሰባሰብና የመስኖ እርሻ ለማዘጋጀት እንዲቻል የእርሻ መሣሪያዎች ማለትም ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች፣ ዶዘሮችና የዘር ማበጠሪያ ማሽኖች በክረምት ወራት ተጠግነው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በተጨማሪም አሜሪካ ከሚገኘው ኦርጋኒክስ ኢንተርናሽናል ኤልኤልሲ ድርጅት (Organix International LLC) ጋር በመተባበር ‹‹ባዮጎልድ›› የተባለ ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና ወደፊት በአገር ውስጥ በጋራ ማልማት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ማዳበሪያ ምርትን በጥራት ለማምረት ከማስቻሉም ባሻገር፣ ለአገሪቱ የግብርና ኤክስቴንሽን አማራጭ ሆኖ እንደሚቀርብ ተነግሯል፡፡

በተለይ ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያው ምን ያህል ጥሩ ግብዓት ነው? የሚለውን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተለይም የሆርቲካልቸር ምርቶችን በናሙና በመምረጥ ጥናት ያደረገበት ሲሆን፣ የተገኘውን የጥናት ውጤት መቸረት በማድረግ ኮርፖሬሽኑ ጊቤ በሚገኘው የእርሻ ማሳ ላይ በስንዴና በበቆሎ ሰብሎች ላይ ለመተግበር ዝግጅት ተደርጓል፡፡

አቶ ጋሻው እንዳስታወቁት በቻግኒና በጊቤ ነባር እርሻ ጣቢያዎች ለዘር ዝግጅት የሚውል መስኖ እርሻ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችልቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል፡፡ ለሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚውሉ እንደ ትራክተሮች፣ ማረሻዎችና ተጨማሪ የእርሻ መሣሪያዎች ከእነ መለዋወጫቸው በገዥ እንዲሟሉ እየተደረገ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንዳስታወቀውኧ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለምርጥ ዘር ብዜት 1,500 ክታር መሬት የተገኘ ሲሆን፣ጋምቤላ ክልል ሁለት ዞኖች እስከ 5,000 ክታር መሬት ለኮርፖሬሽኑ ለመስጠት የክልሉ መንግሥት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይም በቦንጋ ከተማግብርና ግብዓት አቅርቦትና ሜካናይዜሽን ማዕከል ግንባታ ለማስጀመር የኮንትራክተሮች መረጣ በመከናወን ላይ ነው፡፡

የግንባታ ዲዛይናቸው የተጠናቀቀ ሦስት የአፈር ማዳበሪያና የምርት ማከማቻ መጋዘኖችን በአዳማ፣ ሞጆና ኮምቦልቻ ከተሞች ለመገንባት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ጋሻው፣ በተጨማሪም በነባርና በአዳዲስ የእርሻ ጣቢያዎች ለምርት መሰብሰብ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ እንደ ማሳያ በጊቤ እርሻ ጣቢያ ከዝግጅት ምዕራፍ ወቅት ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለውን የበቆሎ ምርት መሰብሰቢያና መፈልፈያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሹ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም በሞሮኮ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ኦሲፒ (OCP) እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተደረሰው የጋራ ማልማት ስምምነት (Joint Development Agreement) መሠረት፣ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን  ከኢትዮጵያ መንግሥት 50 በመቶ ድርሻ ውስጥ አሥር በመቶውን እንዳገኘ አቶ ጋሻው አስታውቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በትግራይ ክልል ሽሬ፣ መቀሌና አክሱም የግብርና ጣቢያዎች እንዳለው ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውስጥ የሽሬና መቀሌዎቹ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንደሆኑና አክሱም ግን የሚገኘው የግብርና ጣቢያ ነው ብለዋል፡፡ በመቀሌ በ2014  የበጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ ባለው የዘር ማባዣ መሬት ላይ 30,000 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማባዛት ታቅዶ እንደነበር ያስታወቁት አቶ ጋሻው፣ ክልሉ ግጭት ውስጥ ስላለ ይህንን ማሳካት እንዳልተቻለና በዚህ ወቅት የዘር ምርቱ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙት ጣቢያዎቹ፣ ቅርንጫፎቹ፣ መጋዘኖቹ፣ መኪናዎችና ንብረቶች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ የደረሰባቸው ዝርፊያና ውድመት ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ እንደተቸገረ ተገልጿል፡፡ በኮምቦልቻም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለና ምን ያህል ጉዳት ደርሷል የሚለው ተጣርቶ እንደሚቀርብ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች