Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ይቻላል!

በጦርነቱ ምክንያት ተስፋ የሚያስቆርጡ ውስብስብ ችግሮች ቢኖሩም፣ ፈተናውን በመሻገር መልካም አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል፡፡ በተደጋጋሚ ከሚነሱ የኢትዮጵያ ፀጋዎች መካከል አንዱ ከ110 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ከሚገመተው ሕዝብ ውስጥ፣ ከ70 በመቶ በላይ የሆኑት ወጣቶችና ታዳጊዎች መሆናቸው ነው፡፡ ይህንን የሚያህል አፍላ ኃይል ይዞ የኢትዮጵያን ለምና ጠፍ መሬቶች በማልማት፣ በአፍሪካ ቁጥር አንድ የምግብ አምራች ለመሆን የሚያዳግት ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ከገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውኃ ሀብት በተጨማሪ፣ ክረምት ከበጋ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የሚያስገኙ ተስማሚ የአየር ፀባዮች አሉዋት፡፡ በእንስሳት ሀብት በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ የምትሠለፍ ሲሆን፣ ሀብቷን በሚገባ ከተጠቀመችበት እንኳንስ ለአፍሪካ ለዓለም ገበያ መትረፍ ትችላለች፡፡ የውኃ አካላት በሚገባ ከተሠራባቸው በዓሳ ሀብት ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት አያዳግትም፡፡ ምድሪቱ የታቀፈቻቸው ለቁጥር የሚያታክቱ ማዕድናት፣ ኢትዮጵያን በዘርፉ ቁንጮ ሊያደርጓት እንደሚችሉ መጠራጠር አይገባም፡፡ በቱሪዝም መስክ ደግሞ ከሚዳሰሱና ከረቂቅ ቅርሶች በተጨማሪ በርካታ አስደማሚ መስህቦች አሉ፡፡ ይህንን የፈተና ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ብሔራዊ ንቅናቄ መፍጠር ይገባል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በተለይ ከምዕራባውያን ኃይሎች እየተሰነዘረባቸው ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊያስደነግጣቸውና ተስፋ ሊያስቆርጣቸው አይገባም፡፡ ይልቁንም የሌሎች አገሮችን ልምዶች በመቅሰምና ጫናውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር፣ ታላቁን የልማትና የዕድገት ጉዞ ለመጀመር ታጥቀው መነሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዓለማችን ብዙ አገሮች ከነበሩበት የድህነት ማጥ ውስጥ ታግለው የወጡት፣ ፈተና ባጋጠማቸው ጊዜ ዜጎቻቸው ኃይላቸውን አስተባብረው ለአንድ ዓለማ መሠለፍ በመቻላቸው ነው፡፡ የብዙዎቹ አገሮች ልምድ ሲወሳም በፈተና ጊዜ ከመራብ አልፈው፣ የሕይወት መስዋዕትነት የሚያስከፍል ጀብዱ መፈጸማቸው አይዘነጋም፡፡ ቻይና ያለፈችበት ፈተና አሁን ለደረሰችበት ስኬት የተጫወተው ሚና ግንባር ቀደም ምሳሌ ነው፡፡ በአሜሪካ በምድር፣ በየብስና በባህር በቦምብ የታረሰችው ቬትናም ያለፈችበት ውጣ ውረድና አሁን የደረሰችበት ደረጃ የሚናገረው አለው፡፡ ከጀልባ መቆሚያነት የዘለለ ፋይዳ ባልነበራት ትንሿ ሲንጋፖር ውስጥ የተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላስገኘላት ጥቅምና ክብር በምሳሌነት ይወሳል፡፡ ደቡብ ኮሪያ ከፍርስራሽ ውስጥ ወጥታ አሁን የደረሰችበት ሌላው ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከተሠራባት የገጠማትን ፈተና ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ትችላለች፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር የሚስተዋል አሳዛኝ ድርጊት ነበር፡፡ አንዱ የገነባውን ሌላው ለማፍረስ የሚያጠፋው ጊዜና ሀብት በጣም የሚያስቆጭ ነበር፡፡ ከበፊቱ መልካሙን አስቀርቶ የማይጠቅመውን ለማስወገድ በጥናት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ መውሰድ እየተቻለ፣ ኢትዮጵያን እያደር ወደ ቁልቁለት የሚያንደረድር ድርጊት ነበር የሚፈጸመው፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧ፣ እንዲሁም ከተሞች በሚያስገርም ሁኔታ መስፋፋታቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል፡፡ እርግጥ ነው በኢኮኖሚው ላይ የመጠን ለውጥ መኖሩ ባይካድም፣ ለአብዛኛው አርሶ አደርና ሠርቶ አደር ሕዝብ የተረፈው ምንድነው ሲባል መልሱ ዕዳ ነው፡፡ ጥቂቶች እሴት ሳይጨምሩ ሚሊየነር የሆኑበት የንፋስ አመጣሽ ሀብት አግበስባሽነት ጥያቄ ሲነሳበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከመሬት፣ ከባንክ ብድር፣ ከውጭ ምንዛሪና ከቀረጥ ነፃ ዕድል ተጠቃሚነት አኳያ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች ይህን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ አድሎአዊ በሆነ መንገድ ይመራ የነበረው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ መላውን ሕዝብ በማደህየት እንዳይኖር እንዳይሞት በሰመመን መርፌ ነበር የሚያኖረው፡፡ ይህ አድሏዊነትና ፍፁም ነውረኝነት የተፀናወተው ድርጊት በቁጠባ ቤቶች ዕጣ ድልድል፣ ኢፍትሐዊ በሆነ የንግድ ውድድርና በበርካታ ብልሹ አሠራሮች የተጥለቀለቀ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

ኢትዮጵያ ከእንዲህ ዓይነቱ መረን የለቀቀ ጎዳና ውስጥ ወጥታ እኩልነት የሰፈነበት የሥራ ዕድልና ተጠቃሚነት እንዲኖር፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ያስፈልጓታል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተፈጥረው፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖርበት የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ከፖለቲካ ተቀጥላነት ተላቀው በነፃነት የሚሠሩበት ዓውድ እንዲፈጠር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ተቋማቱ በጥናት የታገዘ መሠረታዊ ለውጥ ተካሂዶባቸው፣ ብቁ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ማግኘት አለባቸው፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ላይ አተኩረው የሚሠሩ ተቋማት በከፍተኛ ጥንካሬ ሲደራጁ፣ ኢትዮጵያ ወደ ሀብት ማማ የምታደርገውን ጉዞ ያግዛሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋፅኦ ሊኖራቸው የሚገቡ ተቋማትን ማጠናከር ባለመቻሉ፣ ሚናቸውን በሌሎች አካላት ተቀምተው ተሽመድምደው ነው የኖሩት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መሠረታዊ ችግር ተቀርፎ ተቋማቱ ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ሲችሉ፣ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ የሚታዩ መሰናክሎች በቀላሉ ይወገዳሉ፡፡ ተቋማቱ ሲጠናከሩና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሲደረግ፣ ከዚህ ቀደም ያመለጡ ዕድሎችን በማግኘት ታሪክ መሥራት ይቻላል፡፡ ድህነት ታሪክ የሚሆነው በሥራ እንጂ በእርግማን ስላልሆነ፣ ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና ለማላቀቅና አጋጣሚውን ለመጠቀም ጊዜው አሁን መሆን አለበት፡፡

ብዙዎቹ የአገሪቱ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት አይፈልጉም፡፡ በቀላሉ ሀብት የሚገኝበት የአስመጪነት ሥራ እያለ ኢንዱስትሪ ውስጥ መሰማራት አዋጭ አይደለም ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በስንት ድካም የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ የምታባክነው፣ አገር ውስጥ በቀላሉ ተመርተው ገበያ ውስጥ መገኘት ለሚኖርባቸው ሸቀጣ ሸቀጦች ነው፡፡ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ወተትና ሌሎች ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገባት ይልቅ እዚህ ማምረት የሚከብድበት ምክንያት የለም፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰው ኃይል፣ መሬት፣ ውኃ፣ የእንስሳት ሀብትና ሌሎች ፀጋዎች በሞሉባት አገር ውስጥ የሚያዋጣው አስመጪነት ሳይሆን አምራችነት ነው፡፡ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የኢንቨስትመንት ከባቢውን ማሻሻል የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ለምሳሌ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲያተኩሩ ማነቃቂያዎችንና ማበረታቻዎችን ለመስጠት ፖሊሲዎችን መከለስ ያስፈልጋል፡፡ አላሠራ የሚሉ ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች የሚወገዱት በጠንካራና አስተማማኝ ውሳኔ ነው፡፡ ይህም የመንግሥትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የንግዱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ የባህሪ ለውጥ በማድረግ፣ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃደኝነት ማሳየት ይኖርበታል፡፡ አየር በአየር ንግድ ላይ ብቻ እያተኮሩ ጥቅምን ማሳደድ አገር ያደኸያል፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና የምትሻገረው ዘመናዊ የንግድና የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ ሲኖራት ነው፡፡

ጦርነት የአንድን አገር ዜጎች ሕይወትና ንብረት ብቻ ሳይሆን የሚነጥቀው፣ ኢኮኖሚውን በማሽመድመድ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያም ከገባችበት ጦርነት በፍጥነት ተላቃ ፊቷን ወደ ልማት ማዞር አለባት፡፡ ወርቅና ለም አፈር ላይ ተቀምጦ መራብና መለመን ስለሚያሳፍር፣ በተፈጥሮ የተለገሱ ፀጋዎችን በመጠቀም ከጠኔ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሥራ ባህል ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ በሥራ ላይ የማዋል ልማድን በመቀየር እጥፍ ለመሥራት ራስን ማሳመን ይገባል፡፡ ለዕረፍትና ለመዝናናት የሚባክን ጊዜ እንዳይኖር የሚያደርግ የሥራ ባህል ለመፍጠር የሚቻለው፣ ሰፊ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊፈጥር የሚችል በዕውቀት የሚደገፍ ጥናት ሲደረግ ነው፡፡ ንቅናቄው በተለመደው መፈክርና የአንድ ሰሞን ሁካታ ተጠልፎ እንዳይወድቅ፣ በሥራ ዓለም ያሉ ዜጎች በሙሉ የባህሪ ለውጥ የሚያደርጉባቸው መድረኮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ለጦርነት በአንድ መንፈስ እንደሚሰማራ ሠራዊት ለአንድ የጋራ ዓላማ መሠለፍ የግድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ወጣት ልጆቿንና የተፈጥሮ በረከቶችን ይዛ በረሃብ መቆራመድ የለባትም፡፡ ምዕራባውያን በማዕቀብ ሊያሽመደምዷት ሲያሴሩ፣ ልጆቿ ሸብረክ እንዳይሉ ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ መነቃቃት መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ብሔራዊ መነቃቃት በአግባቡ ከተመራ ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና ወደ መልካም አጋጣሚ መለወጥ አያቅታትም! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...