የሥልጣን ዘመናቸው በተጠናቀቀ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የቦርድ ፕሬዚዳንትና አመራሮች በሕገወጥ መንገድ ከማኅበሩ አባልነት መታገዳቸውን በመቃወም፣ በማኅበሩ በላይ ክስ መሥርተው ለስድስት ዓመታት ያህል ተከራክረው በማሸነፋቸው መታገዳቸውና መሰናበታቸው ሕገወጥ መሆኑ ተገልጾ ተፈረደላቸው፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የእነ አቶ አብነት ገብረ መስቀል የሥልጣን ዘመን በ2006 ዓ.ም. ያበቃ መሆኑን በመግለጽ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና ውይይት ተደርጎ ምርጫ እንዲካሄድ፣ የማኅበሩ አባላት እነ አቶ ዳንኤል ካሳ እሸቴ ጥያቄ በማቅረባቸው አለመግባባቶች እንደተፈጠሩ፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ያደረጓቸው የክርክር ሒደቶች ያሳያሉ፡፡
የማኅበሩ አመራሮች ግንቦት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራትና ውይይት በማድረግ፣ ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. አሁን የፍርድ ባለመብት የሆኑትን አቶ ዳንኤል ካሳን ጨምሮ አራት የማኅበሩን አባላት ከማኅበሩ አባልነት ማገዳቸውንም የክርክር ሰነዶቹ ያመለክታሉ፡፡ የስፖርት ማኅበሩ የቦርድ አመራሮች በእነ አቶ ዳንኤል ላይ ዕገዳ የጣሉት የማኅበሩን ውጤቶች እንደሚያንኳስሱ፣ የሐሰት መረጃዎችን በኅትመትና በኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያሠራጩ፣ የክለቡንና የአመራሩን ስም እንደሚያጠፉ በመግለጽ መሆኑንም ሰነዶቹ ይገልጻሉ፡፡
ምንም እንኳን ሦስቱ የማኅበሩ አባላት ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ፍላጎት ባይኖራቸውም ሕጋዊ ጥያቄዎችን በማንሳታቸውና የስፖርት ማኅበሩን ቀጣይ ህልውና አስመልክቶ አስተያየቶችን በመስጠታቸው ከማኅበሩ መታገዳቸው ከሕግ አግባብ ውጭ እንደሆነና የመብት ጥሰት መሆኑን መረዳታቸውን በማመን ወደ ፍርድ ቤት ያመሩት አቶ ዳንኤል ካሳ መሆናቸውን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም አቶ ዳንኤል ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክስ አቅርበዋል፡፡ የተለያዩ ማስረጃዎችን አቅርበው የተከራከሩ ቢሆንም፣ የፍርድ ባለቤት የሆነው (ያሸነፈው) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር መሆኑንም ሰነዶቹ ይገልጻሉ፡፡
መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ከስፖርት ማኅበሩ የተሰናበቱት አቶ ዳንኤል፣ ክርክሩን እንደ አዲስ ከሁለቱ ዓመት ቆይታ በኋላ ታኅሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት በይግባኝ አቅርበዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ይግባኝ የጠየቁት ለሥር ፍርድ ቤት የስፖርት ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ የጠራበት ሒደት ስብሰባውን ያካሄደበትንና እሳቸውንና ሌሎች አባላትን ከስፖርት ማኅበርተኝነት ያሰናበተበት ሒደቶች፣ በበርካታ የሕግ ግድፈቶች በተሞላበት ሁኔታ መሆኑን በመግለጽ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻርላቸው መሆኑን ሰነዶቹ ያሳያሉ፡፡
የስፖርት ማኅበሩ ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበው መቃወሚያና መከራከሪያ ሐሳቦች በማስረጃ ያልተደገፉና ከእውነት የራቁ መሆናቸው ቢታወቅም፣ ፍርድ ቤቱ ያንን በማለፍ የተፈረደባቸው መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መሆኑንም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግም ሆነ የማስረጃ መሠረት የሌለውና መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን በመጥቀስ ውሳኔው እንዲሻርላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት (ከፍተኛው ፍርድ ቤት) የይግባኝ አቤቱታውን ተቀብሎና የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ተመልክቶ ‹‹ያስቀርባል›› በማለት የስፖርት ማኅበሩ አስተያየት እንዲሰጥበት አድርጓል፡፡ ከሳሽ አቶ ዳንኤልም የመልስ መልስ እንዲሰጡ በማድረግ መዝገቡን መርምሯል፡፡
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይገባኙን ሲመረምር ስፖርት ማኅበሩ ጉባዔውን ያካሄደውና ውሳኔውን ያስተላለፈው ምልዓተ ጉባዔው ተሟልቶ ነው ወይም ሳይሟላ፣ ከሳሽ አቶ ዳንኤልን ከማኅበሩ አባልነት ያሰናበተው በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብን ተላልፈው ተገኝተው ነው? በመገናኛ ብዙኃን ያስተላለፏቸው መረጃዎች መተዳደሪያ ደንቡን ጥሰዋል? እና ሌሎችንም ጭብጦች ይዞ መሆኑን ፍርዱ ያሳያል፡፡
በያዘው ጭብጥ መሠረት ስፖርት ማኅበሩ የማኅበሩን አባላት ቁጥር 13,000 እና 10,000 በማለት ገልጾ እያለ በክርክር ሒደቱ 2,522 አባላት እንዳሉ፣ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ 1,461 ተገኝተው 1,325 አባላት ከሳሽና ሌሎች አባላት በሰጡት ድጋፍ ከአባልነት እንዲታገዱ ማድረጉን ገልጿል፡፡ አቶ ዳንኤል በመገናኛ ብዙኃን ሰጡ የተባለው መረጃም የስፖርቱንም ሆነ የአመራሩን ስም የሚያጠፋ ሳይሆን፣ የክለቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን መሆን እንዳለበት የሚገልጽ መሆኑን በፍርዱ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም አቶ ዳንኤል ከማኅበር አባልነታቸው የተሰናበቱት በተሳሳተና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሻሩን ገልጾ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡