Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሎላት›› ሁለገቡ የዲራሼ የትንፋሽ መሣሪያ

‹‹ሎላት›› ሁለገቡ የዲራሼ የትንፋሽ መሣሪያ

ቀን:

በደቡብ ኢትዮጵያ በጋርዱላ አካባቢ የሚገኘው የዲራሼ ማኅበረሰብ ለት ባሉት ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቹና ጨዋታዎቹ ታዋቂ ነው፡፡

የሙዚቃ መሣሪያዎቹ የትንፋስ፣ የክር እና የምት ተብለው በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ከዘጠኙ የትንፋሽ መሣሪያዎች አንዱ ‹‹ሎላት›› ይሰኛል፡፡ አቶ ፍሬው ተስፋዬ ኦዳይቴ፣ ‹‹ፊላና ሌሎች ሙዚቃዊ ጥበባት በጋርዱላ ዲራሼ፣›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ከተመለከቷቸው አንዱ ሎላት ነው፡፡

እንደ አቶ ፍሬው ማብራሪያ፣ ዘመን ከማይሽራቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች አንዱ የሆነው ሎላት የሚሠራው ከሳላ ቀንድ ወይም ከአጋም እንጨት ነው፡፡ ሎላታ ከተዘጋጀ በኋላ በቅቤ ታሽቶ ጭስ ባለበት ቆጥ (ቅሻይት) ይቀመጥና እንዲወዛ ይደረጋል፡፡ ከፍየል ፂም አካባቢ በሚገኝ ቆዳና ፀጉር እንዲሁም በተለያዩ ጌጣጌጦች ሎላታን ማስዋብ የተለመደ ነው፡፡

ቁመቱ በአማካይ እስከ 40 ሳንቲ ሜትር የሚረዝመው ሎላት መሣሪያው በሁለቱም ጫፍ ቀዳዳ ያለው ሲሆን፣ ቀዳዳው በአንዱ ወገን ሰፋ ብሎ በሌላው በኩል በጣም ቀጭን ነው፡፡ አነፋፉም በሰፊው በኩል የሚከናወን ቢሆንም በቀጭኑ በኩል በጣት ያዝ ለቀቅ እየተደረገ ልዩ ልዩ ድምፅ እንዲሰጥ ተደርጎ ይነፋል፡፡ ከቆዳ የሚሠራ ማንጠልጠያም ይበጅለታል፡፡

‹‹ሎላት ከማኅበረሰቡ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ይልቅ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውልና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በተለይም ከእርሻ ሥራ ጋር ተያያዥነት ያለው ነው፤›› የሚሉት ደራሲው፣ እያንዳንዱ ቤተሰብና መንደር የየራሱን የሎላት ድምፆች ለይቶ እንደሚያውቅ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ምንጊዜም ንጋት ላይ ሎላት ሲነፋ የመጀመርያው መልዕክት ጥሪና ተዘጋጁ ማለትን ይወክላል፡፡ በጋራ በእርሻ ሥራ ወይም አደን የሚሰማሩ ሰዎች ለሥራ ሲወጡ በሎላት ይጠራራሉ፡፡ ከእርሻ ሥራ መልስ ወደ መኖሪያ መንደር ሲቃረቡም በሰላም ተመልሰናል፣ የሚበላና የሚጠጣ ይዘጋጅ የሚለውን መልዕክት በሎላት ያስተላልፋሉ፡፡››

በአቶ ፍሬው ማብራሪያ፣ በዲራሼዎቹ ዘንድ እጀግ ተወዳጅ የሆነውና የብዙዎችን ቀልብ የሚገዛው ፊላ ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፡፡ ፊላ ሙዚቃም፣ ዳንስም፣ የሙዚቃ መሣሪያም ነው፡፡ የፊላን በውዝዋዜና በሙዚቃ የታጀበ ክዋኔን ለመፈጸም የተለያዩ ቡድኖች ጥሪ የሚቀርብላቸው በሎላት ነው፡፡

‹‹ሎላት ለቡድን ጥሪ አገልግሎት ሲውል የየራሱ ትርጉም አለው፣ በማለዳ ሁለት ጊዜ ከተነፋ ንቁ ተነሱ የሚል መልዕክት አለው፡፡ በመቀጠል አራት ጊዜ ከተነፋ ተዘጋጁ ማለት ሲሆን፣ በመጨረሻ ስድስት ጊዜ ሲነፋ ጉዞ ጀምረናል የሚለውን መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ በሎላታ ተጠራርተው ወደ እርሻ ወይም ሌላ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች ሲመለሱና ወደ መንደር ሲቃረቡ በሚነፉት ሎላታ በሰላም መመለሳቸው ይታወቃል፡፡››

ሁለገቡ አገልጋይ

ሎላት ጨዋታን የማድመቅና በሥራ ላይ ወይም በጉዞ ላይ ያሉ ሰዎችን ለማበረታታት ያገለግላል፡፡ የበዓል፣ የለቅሶ ወይም ማንኛውም ጭፈራ ጨዋታ በደመቀ ሁኔታ ሲከናወን ሎላት ይነፋል፡፡ የሎላት መነፋት የጨዋታው ድምቀት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ከማሳየቱም በላይ ድምቀቱ እየጨመረ እንዲሄድ የሚያበረታታ ነው ሲሉም ይገልጹታል፡፡ በፊላ ጨዋታ ወቅት ሎላት በስፋት አገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፣ ተገልብጦ በቀጭኑ ቀዳዳ በኩል ሲነፋ ግን ልዩ ድምፅ ስለሚሰጥ የፊላ ጨዋታ ቆሞ ወደ ሌላኛው ትዕይንት (ፋስካ/ላይታ) እንሻገር የሚል መልዕክትን ያስረዳል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች በዝማሬ ድምቀት ውስጥ ሎላት መስማት እየተለመደ መምጣቱን ደራሲው ያወሳሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...