የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለዜጎች ለማዳረስ እንዲሁም የፍትሕ አስተዳደር እንዲቀላጠፍ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡
ብሔራዊ መታወቂያም እንዲሁ የብሔራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅና በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ ያለው ሚና ጉልህ ነው፡፡
ለዚሁ አፅንኦት ሰጥቶ በ2010 ዓ.ም. የወጣው የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 ማሻሻያ ተደርጎለታል፡፡ ማሻሻያው አብዛኛው ትኩረት ያደረገው በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማለትም ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ ፍቺ ላይ ቢሆንም በብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባና አሰጣጥ ላይ መሆን አለባቸው ያላቸውን ጉዳዮች አካቷል፡፡
መታወቂያም የአገሮችን ብሔራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ዜጎችን ዜጋ ካልሆኑ ነዋሪዎች ለመለየትና በዜግነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማጥቅሞች ማለትም መንጃ ፈቃድ፣ ፓስፖርትና ሌሎችም መለያዎችን ለማውጣት እንዲሁም የተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንዲችሉ የሚሰጥ ነው፡፡ ታዲያ ለየግለሰቦች የሚሰጠው መታወቂያ የባለመታወቂያውን ማንነት የሚገልጽ መረጃ ይይዛል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው መታወቂያ ላይ የባለመታወቂያው ሙሉ ስም፣ የእናት ስም፣ የትውልድ ዘመንና ቦታ፣ ፆታ፣ ስልክና ብሔር፣ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን የያዘ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎች ምዝገባና የመታወቂያ አሰጣጥ መመርያ ቁጥር 3/2010 በማሻሻል በተለይም ከ2013 ወዲህ በብዛት መሰጠት የጀመረውና ከፊት ለፊትና ከጀርባ የባለመታወቂያውን መረጃ የያዘው አዲሱ መታወቂያ ደግሞ ብሔር፣ የትውልድ ቦታና የእናት ስምን አውጥቶ የደም ዓይነት እንዲታከልበት አድርጓል፡፡
የእናት ስም ከመታወቂያው ላይ መውጣቱም አገልግሎት አሳጣጥ ላይ መስተጓጎል እየፈጠረ መሆኑን በጉዳዩ ያነጋገርናቸው አገልግሎት ፈላጊዎች ነግረውናል፡፡
ውክልና ለመስጠት ካዛንችስ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የተገኙት አገልግሎት ፈላጊ እንደነገሩን፣ የእናትና የአባታቸውን ንብረት ወንድማቸው እንዲያስተዳድሩላቸው ውክልና ለመስጠት የጀመሩት ሒደት የተስተጓጎለው በአዲሱ መታወቂያቸው ላይ የእናታቸው ስም ባለመኖሩ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ መታወቂያ ካገኙበት ወረዳ ሔደው የእናታቸውን ስም የሚገልጽ ማረጋገጫ እንዲያመጡ ተጠይቀዋል፡፡
ሌላው አስተያየት የሰጡን ተገልጋይ ደግሞ፣ ለልጃቸው የመሥሪያ ቤት ዋስ ለመሆን ፈልገው በተጓተተ አሠራር ውስጥ ማለፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ልጃቸው መታወቂያ ላይ የእናት ስም ባለመኖሩ እናት ነኝ ብለው የሄዱት እናትም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የአገልግሎት ፈላጊው እናት ስለመሆናቸው ልጃቸው ከወረዳው ሄዶ ማረጋገጫ ማምጣት እንዳለበት ተነግሯቸው በዚሁ አግባብ ጉዳያቸውን ጨርሰዋል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ለሕክምናና ኢንሹራንስ ቤተሰብን ጨምሮ ለሚገቡ ድርጅቶች የቤተሰብ መረጃ ሲሞላ ከዚህ ቀደም እናትና አባት ከመታወቂያ ላይ ታይቶ ይሞላ የነበረው አሁን ላይ የእናት ስም መታወቂያ ላይ ባለመኖሩ ማረጋገጫ ከየወረዳው ማምጣት ይጠይቃል፡፡
ማጭበርበርን ጨምሮ የተለያዩ ሥጋቶችን ይቀንሳል በሚል በመልካም ጎኑ የሚጠቀሰው አዲሱ ዲጂታል መታወቂያ፣ የባለመታወቂያውን የእናት ስም አለማካተቱ የሥራ መጓተቶችን እየፈጠረ መሆኑንም ሪፖርተርም ታዝቧል፡፡
በአዲሱ ዲጂታል መታወቂያ ላይ የእናት ስም አለመካተቱን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያ አቶ አዶናይ ሰይፉ አንተንይስጠኝ እንደሚሉት፣ በፊት የነበረው መታወቂያ ላይ የባለመታወቂያው የእናት ስም ነበር፡፡ በአዋጅ 760/2004 አንቀጽ 57 ላይ ‹‹ለብሔራዊ መታወቂያ ስለመመዝገብ›› በሚለው ሥር ሙሉ ስም ከነአያት፣ ልዩ ምልክት፣ የወላጆች ሙሉ ስምና ዜግነት፣ የትውልድ ቦታና ቀን፣ ፆታና የጋብቻ ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ይይዛል፡፡
‹‹ብሔራዊ መታወቂያ ስለመስጠት›› የሚለው አንቀጽ 58 ላይ መታወቂያው ምን መያዝ እንዳለበት በሚገልጸው ሥር በአንቀጽ 57 የተካተተው የወላጆች ሙሉ ስምና ዜግነት የሚለው ሙሉ ስም ከነአያት በሚለው ተጠቅሶ፣ የእናት ስም የሚለው አልተካተተም፡፡
በአንቀጽ 57 ላይ ያለው ወደ መታወቂያው ሲወርድ፣ መታወቂያው የሚይዘው መረጃ ይበዛል በሚል እሳቤ ቀርቶ ሊሆን እንደሚችል የገመቱት አቶ አዶናይ፣ የባለመታወቂያው የእናት ስም መኖር እንደነበረበትና ወሳኝ ስለመሆኑ ያሰምሩበታል፡፡
ምክንያቱም በተለይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በአገልግሎት ፈላጊው ዘንድ በመታወቂያ ላይ የባለመታወቂያ እናት ስም ባለመካተቱ ብቻ በርካታ መስተጓጎሎች ይፈጠራሉና፡፡
ከባንክ አዲስ ደብተር ለማውጣት፣ ከኢሚግሬሽን ፓስፖርት፣ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣትና በሌሎች በርካታ ተቋማት የእናት ስም ይጠየቃል የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ መታወቂያ ላይ በግለሰቦች የእናት ስም ባልተካተተበት ሁኔታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የባለመታወቂያውን ቃል አምነው ሊሠሩ የሚችሉበት አኳኋን ስለማይኖር መታወቂያውን ከሰጠው አካል አረጋግጦ እንዲመጣ ማድረጋቸው ግድ ይሆናል፡፡
ይህ ደግሞ መታወቂያ የሰጠው አካል በአንቀጽ 47 መሠረት የመዘገበውን መረጃ አውጥቶ እንዲያይ አንዳንዴም ምስክር እንዲጠይቅ ያደርጋል፡፡ ይህ በበርካታ ዜጎች እየቀረበ ያለ ቅሬታ ነው፡፡
እንደ አቶ አዶናይ፣ ይህ ከሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር ክፍተት እየፈጠረ ነው፡፡ ለአገልግሎት ፈላጊው ብቻ ሳይሆን ሰጪው አካል ላይም ተደራራቢ ሥራ የሚፈጥር ነው፡፡ መታወቂያ በወረዳ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑና ወረዳ ደግሞ አብዛኛው ሥራ የሚከናወንበት ስለሆነ የጊዜ፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ብክነት ያስከትላል፡፡ የሥራ ጫናንም ይፈጥራል፡፡
የውጭ ተሞክሮን በተመለከተ ‹‹ፕራይቬሲ ፐብሊክ ኢንተርናሽናል››ን ጠቅሰው አቶ አዶናይ እንዳሉት፣ ከ110 አገሮች በላይ የመታወቂያ ሕግ አላቸው፡፡ ከአፍሪካ ደግሞ የኤርትራ፣ አንጎላና ቦትስዋና የመታወቂያ ዝርዝር መረጃ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡
ነገር ግን የውጭ ተሞክሮ ሳይታይም የበፊቱን የኢትዮጵያን አሠራር በማየት የባለመታወቂያ የእናት ስም መኖሩ ከነበረው ጠቀሜታና ጥሩ ተሞክሮ ተነስቶ አካቶ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡
ለምሳሌ የአውሮፓ ሲታይ የዜጎች መረጃ በመረጃ ቋት ስላለና ተቋማት ያንን አይተው ማረጋገጥ የሚችሉበት የኔትወርክ ሥርዓት ስለተዘረጋ፣ መታወቂያ የያዘ ሰው ድንበር እስከ ማቋረጥ ሊገለገልበት ይችላል፡፡ የእናት ስም ባይመዘገብ እንኳን ተቋማት ከመረጃ ቋቱ ላይ ስለግለሰቧ/ቡ ሙሉ መረጃ ስለሚያገኙ ለእነሱ ይህ ችግር አይሆንም፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግን የመንግሥትና የግል እንዲሁም የመንግሥትና የመንግሥት ተቋማት እርስ በርስ በቴክኖሎጂና በመረጃ አያያዝ የተሳሰሩ አለመሆናቸው ችግሩን ያጎላዋል፡፡ ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው ደግሞ የኔትወርክ ትስስር በመፍጠር ነው፡፡ ይህ እስከሚሳካ ግን ከዚህ በኋላ የሚሰጡ መታወቂያዎች ላይ የእናት ስም የሚለው ቢገባ፣ ከዚህ በፊት ያሳደሱ ደግሞ ወደፊት ሲያሳድሱ የእናት ስም እንዲካተት ቢደረግ ችግሩን መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡
መታወቂያ ሰጪ አካል አዋጁን ጠቅሶ ‹‹የእናት ስም ይካተት አይልም›› ቢል እንኳን የሕግ ክፍተቱን አይቶ፣ የተገልጋዮችን ችግር ተገንዝቦ ማሻሻል ይቻላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሥልጣን ለተሰጠው አካል መብት ተሰጥቷል፡፡
‹‹ሕግ ሁሉን ነገር ሊይዝ አይችልም›› ያሉት አቶ አዶናይ፣ ችግሮችና ክፍተቶች ወደፊት ሊመጡ ይችላሉ ብሎ እንደሚያስገባ፣ ክፍተቶች ሲገኙበት ማሻሻያ እንደሚደረግባትም ይጠቁማሉ፡፡
በመሆኑም በሕግ ማሻሻያ ላይ በአንቀጽ 57 የተቀመጠው የባለመታወቂያው ወላጆች ሙሉ ስምና ዜግነት የሚለውን እንደመነሻ ወስዶ የእናት ስምን በማስገባት ማሻሻል ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ መታወቂያው የባለመታወቂያውን የእናት ስም ባለመያዙ የሚከተሉ ብዙ የአሠራር ክፍተቶችንና ጉድለቶችን ይሞላል፣ እንግልትና ብክነትን ያስቀራል፡፡
ሪፖርተር እንደታዘበው በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የባንክ ደብተር የሚያወጡ ግለሰቦች የእናትን ሙሉ ስም ጨምሮ ዝርዝር መረጃ እንዲያካትቱ ያዛል፡፡ ይህ ደግሞ ከደብተር አውጭው የታደሰ መታወቂያ የሚቀዳ ነው፡፡ በባንክ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ ጉዳይ፣ ውክልና እና ሌሎችም አገልግሎቶች የአገልግሎት ፈላጊውን የእናት ስም ጨምሮ ሙሉ መረጃ ይፈልጋሉ፡፡ ከአዲሱ መታወቂያ ጋር ተያይዞ ችግሮች መታየት በመጀመራቸው የሚመለከተው የመንግሥት አካል ማሻሻያ አድርጎ እንዲያስተካክለው ምክረ ሐሳባቸውን የሰጡን በችግሩ ውስጥ ያለፉ አንድ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የመረጃ ዘርፍ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ዮናስ ዓለማየሁ እንዳሉት፣ በ2011 ዓ.ም. መታወቂያው ወደተግባር ከመለወጡ በፊት በረቂቅ ይዘቱ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ መታወቂያው ምን ምን ይዞ ይውጣ የሚለው አንዱ ትኩረት የተሰጠው መወያያ ነበር፡፡ በወቅቱ ከነበረው ውይይት በበፊቱ መታወቂያ የነበረው የእናት ስም ይውጣ አይውጣ የሚለው አንዱ ነበር፡፡
በወቅቱም መመዘኛ የነበረው ምን ያክል ተቋማት የእናት ስም መረጃ አስገዳጅና አስፈላጊ ነው ብለው ለሥራቸው ይጠይቃሉ የሚለው ነበር፡፡ ባንኮች፣ ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት አስተያየት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ በወቅቱም ብዙም አስፈላጊ አይደለም የሚል ግብረ መልስ ነበር የተገኘው፡፡
‹‹መነሻችን የእናት ስም መታወቂያ ላይ መቀመጡ ትክክል አይደለም የሚለው ሳይሆን የእናት ስም መታወቂያ ላይ ቢሰፍር ምን ያህል ተቋማት አገልግሎት ሲሰጡ ይህን ይጠይቃሉ የሚለው ነበር›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ የመታወቂያ መረጃ ይዘት ሁሉን ነገር ሊይዝ እንደማይችልና መገደብ አለበት ከሚለው በመነሳት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ሰው መረጃ ተሟልቶ በመረጃ ቋት ያለመስፈሩና ከተቋማት ጋርም በኔትወርክ የተሳሰረ መረጃ ባለመኖሩ እንጂ አሁን መታወቂያው ላይ የተዘረዘሩ በርካታ መረጃዎችም አያስፈልጉም ነበር ያሉት አቶ ዮናስ፣ በወቅቱ ውይይት ሲደረግ የእናት ስም ቢወጣ የሚለው ድምዳሜ ላይ የተደረሰው የእናትን ስም የሚጠይቁ ተቋማት በጣም ውስን ሆነው በመገኘታቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የእናትነት አገልግሎት ይሰጠን ብለው የሚጠይቁ አገልግሎቱን የሚያገኙ መሆናቸውን፣ በመታወቂያ ላይ ባይሰፍርም አጠቃላይ በምዝገባ ሒደቱ መካተቱን አንስተዋል፡፡
ይህ የሥራ መጓተት አይፈጥርም ወይ? በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የባንክ ደብተር ለማግኘት የእናት ስም የሚጠየቅ መሆኑንና በባንክ ብቻ ሳይሆን፣ ውርስ፣ ውክልናና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚጠየቅ መሆኑን ያነሳንላቸው አቶ ዮናስ፣ መታወቂያ ላይ ያለው መረጃ ሊሻሻል የሚችል እንጂ ዝግ አለመሆኑን፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ በወረዳዎች ላይ ሰፊ ጫና የሚፈጥር ጥያቄ አለመኖሩን ነገር ግን አዳዲስ መመርያዎች ሲመጡ የእናት ስም መኖርን የሚጠይቁ ፍላጎቶች ከመጡ ጉዳዩን መልሰው እንደሚያዩ ገልጸዋል፡፡
የመታወቂያ ጠቀሜታ አገልግሎት ማሳለጥና ሰዎች ማንነታቸውን ገልጸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን እንዲያገኙ ማስቻል በመሆኑ ሲስተማቸውን ጭምር ለተቋማት ክፍት ለማድረግ፣ ተቋማትም መታወቂያውን አይተው እዚያው ማረጋገጥ የሚችሉበትን አሠራር ለመዘርጋት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በአዲስ አበባ 700 ሺሕ ያህል ሰዎች ዲጂታል መታወቂያ መያዛቸውን፣ ይህንን ከተቋማት ጋር በማያያዝ አሠራሮችን ለማቀላጠፍ እንደሚሠራም አክለዋል፡