Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትቢሊዮኖች የፈሰሰባቸው ስታዲየሞች ግንባታ

ቢሊዮኖች የፈሰሰባቸው ስታዲየሞች ግንባታ

ቀን:

ግንባታቸው በ1998 የተጀመረ 13 ስታዲየሞች 7.3 ቢሊዮን ብር ወጥቶባቸዋል

ግንባታቸውን በአሥር ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ 14 ቢሊዮን ብር ተበጅቷል

አራት አዲስ ስታዲየሞችን ለመገንባት 20 ቢሊዮን ብር ተበጅቷል

- Advertisement -

በስፖርቱ ዓለም ረብጣ ገንዘብ ከሚፈስባቸው ተግባራት መካከል የስታዲየም ግንባታ ተጠቃሽ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲቃረቡ ስታዲየሞች ሲገነቡ ወይም ሲታደሱ ይስተዋላል፡፡

ግንባታዎቹ ዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር ሳይቀር አካተው የዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ደረጃን አሟልተው ይገነባሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 ደቡብ አፍሪካ፣ በ2014 የብራዚሉና በ2018 የሩሲያ ዓለም ዋንጫዎች፣ የነበሩትን ስታዲየሞች ለማደስ እንዲሁም ተጨማሪ ስታዲየሞች ለመገንባት በቢሊዮን ዶላሮች አፍስሰዋል፡፡

በአራት ዓመት አንዴ ለሚመጣው የኦሊምፒክ ጨዋታም እንዲሁ ከፍተኛ  ወጪ ተደርጎላቸው የሚታደሱት ታድሰው፣ እንደ አዲስ የሚገነቡትም ተገንብተው ለውድድር ክፍት ይሆናሉ፡፡ ታዲያ አገሮች ለእነዚህ ስታዲየሞች ግንባታና ዕድሳት ካላቸው ዓመታዊ ገቢ ላይ ቆንጥረው ሲያወጡ፣ በስፖርቱ እንዴት አትርፈው ኢኮኖሚያቸው ማሰደግ እንደሚችሉ አስልተው ነው፡፡

አሜሪካ በርካታ ቅንጡ ስታዲየሞች በመገንባት በቀዳሚነት ትቀመጣለች፡፡ ለቅርጫት ኳስና ለእግር ኳስ እንዲሁም ለሌሎች ውድድሮች የገነባቻቸው ስታዲየሞች ቀላል የሚባሉ አይደለም፡፡

ከስፖርት ኢንቨስትመንትና ስታዲየም ግንባታዎች ጋር በተያያዘ በቀረቡት ጥናቶች መሠረት፣ አራት ዋና ዋና ጥቅሞች እንዳላቸው ያስቀምጣል፡፡ አንደኛው ግንባታው ማከናወን የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሁለተኛው ግንባታው ተጠናቆ በስታዲየሞ ከሚታደመው ሰው የሚገኘው ገቢ፣ በስታዲየሙ ዙሪያ ላለው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድልን ያሰፋል፡፡ ሦስተኛው የስታዲየሙ ባለቤት የሆነው ቡድን ተመልካችና ቱሪስትን በመሳብ ሌላ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ሲያስችል፣ በመጨረሻም ስታዲየሙ በመገንባቱ ብቻ ተጨማሪ የሆነ ገቢ በመኖሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ከማምጣቱም በላይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡

በቅርቡ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማሰናዳት የቻለችው ኬንያ፣ በማደግ ላይ ካሉ አገሮች በስፖርት መሠረተ ልማት ጥሩ ጀማሬ ላይ እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኬንያ የወጣቶቹን ሻምፒዮና አቀላጥፋ ማዘጋጀቷን ተከትሎ፣ በቀጣይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማሰናዳት ጥያቄ አቅርባለች፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ አንድም የካፍንም ሆነ የፊፋን ደረጃ የሚያሟላ ስታዲየም በማጣቷ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስደተኛ ለመሆን ተገዷል፡፡ በዚህም ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና አቻው ጋር ለመጫወት የደቡብ አፍሪካ ስታዲየም ለመጠቀም ተገዷል፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆነው ‹‹አንድ ለእናቱ›› ሆኖ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሲያስተናግድ የነበረው የባህር ዳር ስታዲየም በካፍ መታገዱን ተከትሎ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ ስታዲየሞችና የግንባታ ሁኔታ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስታዲየም ጉዳይ ‹‹ከአቅሜ በላይ ነው›› ብሎ ከተናገር ሰነባብቷል፡፡ በዚህም ሒደት ውስጥ የአዲስ አበባ ስታዲየም ታግዶ፣ የባህር ዳር ስታዲየም ብቻ የተወሰኑ ጨዋታዎች ሲያስተናግድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በቅርቡ ካፍ ደረጃውን አልጠበቀም ብሎ አግዶታል፡፡

በኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ የ13 ስታዲየሞች ግንባታቸው/ ዕድሳታቸው ተጀምሯል፡፡ እነሱም የባህር ዳር፣ መቀለ፣ ሐዋሳ፣ ሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ነቀምቴ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ አበበ ቢቂላና አዲስ አበባ ስታዲየሞች ናቸው፡፡

በአዲስ አባባ እየተገነባ ያለውን አደይ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ በክልል በተለያዩ ከተሞች ለሚገነቡት ስታድየሞች መንግሥት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ በጅቷል፡፡ ሆኖም ግንባታቸው ከ80 በላይ እንደሆነ ሪፖርት ቢቀርብም፣ ያልተጠናቀቁና የክንውን አፈጻጸማቸው ከሚቀርቡት ቁጥራዊ መረጃዎች ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡

በአንፃሩ በሒደት ይሻሻላሉ ተብሎ የካፍን አዎንታ አግኝተው የነበሩ ስታዲየሞች የሜዳቸው ሳር ለጨዋታ የማይሆንና ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ እንዲነሳና በአዲስ እንዲተካ ታዟል፡፡ ምንም እንኳን ስታዲየሞቹ ተጠናቀዋል ቢባልም፣ ሁሉም ግንባታዎች የጥራት ችግር እንዳለባቸው ይነገራል፡፡

ባህር ዳር ስታዲየም

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወጪ ሲገነባ የቆየው የባህር ዳር ስታዲየም ግንባታ የተጀመረው በ2002 ዓ.ም. ነው፡፡ 45 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም አለው የተባለው ስታዲየሙ ‹‹መቶ በመቶ እንደተጠናቀቀ›› የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሪፖርት ያመለክታል፡፡ የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ 2.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ እስካሁን 616,155,035 ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በቀጣይ አሥር ዓመት የበጀት ፍላጎት ሁለት ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል፡፡ ስታዲየሙ መቶ በመቶ ተጠናቋል ቢባልም፣ ከወራት በፊት ካፍ በርካታ ጉዳዮች እንደሚጎሉትና የተተከለው ሳር እንኳን ደረጃውን የጠበቀ እንዳልሆነ ገልጾ፣ ዳግም ተነቅሎ ሌላ የሳር ዘር እንዲተከልበት የሚል ትዕዛዝ ስጥቷል፡፡ 

ሐዋሳ ስታዲየም

የሐዋሳ ስታዲየም በ2004 ዓ.ም. በወቅቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት ግንባታው በጀመረ፡፡ 42 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየሙ፣ ከ96 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቀ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡ ወጪው በክልሉ መንግሥት የተሸፈነ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ 2.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን እስካሁን 763,381,622 ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በቀጣይ አሥር ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ 1.8 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡

ስለ ሐዋሳ ስታዲየም በቁጥር የተነገረውና ያለበት ሁኔታ ግን የሚጣጣም አይደለም፡፡ የስታዲየሙ መጠናቀቅ ከተገለጸ በኋላ የተወሰኑ አኅጉር አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ ቢችልም፣ ሜዳው በዝናብ ወቅት ውኃ በማዘሉ ማጫወት ባለመቻሉ ሳሩ እንዲነቀልና ተስማሚ የሆነ ሳር መተካት እንዳለበት ቀደም ሲል ታዟል፡፡

ከትዕዛዙ በኋላ ግን ዳግም ዞር ብሎ ያየው አካል ባለመኖሩ፣ እስካሁን ለበዓላትና ለፖለቲካ ጉዳዮች መሰብሰቢያነት ባለፈ አገልግሎት ሊሰጥ አልቻለም፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ውኃ ራሱ በበቂ ሆኔታ ባለማግኘቱ ሳሩ አሸዋማ መልክ ይዟል፡፡

ሰመራ ስታዲየም

የአፋር ክልል በ2008 ዓ.ም. ግንባታውን የጀመረው ሰመራ ስታዲየም 40 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም አለው፡፡ በሪፖርቱ መሠረት 88 በመቶ መጠናቀቁን ተጠቅሷል፡፡ ለፕሮጀክቱ እስካሁን 583 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በቀጣይ አሥር ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 217 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ ይኼም ስታዲየም የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከተከበረበት በኋላ ሕዝባዊ ሥነ ሥርዓቶች ከማዘጋጀት ባሻገር በተለይ ለእግር ኳስ ጨዋታ ደረጃ የሚመጥን አቋም ላይ እንዳይደለ ይነገራል፡፡

ጅግጅጋ ስታዲየም

የጅግጅጋ ስታዲየም በ2008 ዓ.ም. ግንባታው የጀመረ ሲሆን፣ 50 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም አለው፡፡ የፕሮጀክቱ በጀት 1.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣  እስካሁን 283 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ይኼም ስታዲየም ከሕዝባዊ በዓላት አገልግሎት ወጪ ሲሰጥ አልታየም፡፡

ነቀምቴ ስታዲየም  

የነቀምቴ ስታዲየም ግንባታ የጀመረው በ2002 ዓ.ም. ሲሆን፣ 45 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም አለው፡፡ ፕሮጀክቱ 99.9 በመቶ መጠናቀቁን በሪፖርቱ የቀረበ ሲሆን፣ 880 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡ እስካሁን 700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ለወንበር ገጠማ ደግሞ 180 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡

ስለ ስታዲየሞቹ ግንባታ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

ምንም እንኳን ስታዲየሞቹ በቁጥራዊ ሪፖርት የተጋነኑ ቢሆንም፣ መሬት ላይ ሲታዩ ግን ውድድር የማስተናገድ አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡ ሪፖርተር ከላይ የተዘረዘሩትን ስታዲየሞች እንደ ምሳሌ ጠቀሳቸው እንጂ፣ የድሬዳዋ፣ ሐረሪ፣ ጋምቤላ እንዲሁም አሶሳ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፡፡ ነባሩን የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት ጨምሮ አዲስ ለሚገነቡት የአዳማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ የደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ድሬዳዋ ስታዲየሞች የተመደበላቸው በጀት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

ከስታዲየሞቹ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግንባታዎቹ ከጨረታ ጀምሮ እስከ ጥራታቸው ድረስ ችግር እንዳለባቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው እነዚህ ስታዲየሞች ዓለም አቀፉ ስፖርት አወዳዳሪ አካል (ፊፋ፣ ካፍ) የሚጠይቃቸውን መሠረታዊ ግባዓቶች ለማሟላት የሚያስችል ቁመና ላይ አለመሆናቸው ይነገራል፡፡

አቶ ዳንኤል አሰፋ የጂዳው ኮንሰልቲንግ አርክቴክትና ኢንጂነር በአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ አካል ለመሆን ጨረታውን መሳተፍ ከቻሉ ተቋማት አንዱ እንደነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነቡ ላሉት ስታዲየሞች የጨረታ ሒደት ክፍተት እንዳለበት ያነሳሉ፡፡

‹‹ገና ከግንባታው ጥንስስ ጀምሮ ጨረታው ሕጋዊ የሆነ አካሄድን ያልተከተለና ለአንድ ተቋራጭ ብቻ በጥቅም ትስስር የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶቹ ስታዲየሞች ስህተቶቻቸው ተመሳሳይ ናቸው፤›› በማለት አቶ ዳንኤል ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው በዘርፉ ልምድ ያላቸው ባለሙያው (ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም) ስታዲየሞቹ በጥራትና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ አለመገንባታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ስታዲየሞቹ አንደ አዲስ መሠራት ይገባቸዋል በማለት አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

‹‹አብዛኞቹ ስታዲየሞቹ በተመሳሳይ ተቋራጭ በመገንባታቸው የጥራታቸው ጉዳይም ተመሳሳይ ያደርገዋል፡፡ እነዚህ ስታዲየሞች ድጋሚ ካልተገነቡ ችግራቸው የሚፈታ አይመስልም፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን  ያክላሉ፡፡

ለዚህም ምክንያቱ  የስታዲየሞቹ ዲዛይን ሰፋፊና የካፍን መሥፈርት ለማሟላት አመቺ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ የሚገልጹት አርክቴክት አቶ ተሰማ ደምሴ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ተሰማ አስተያየት ከሆነ፣ ግንባታው ሲጀመር ዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተቀመጠለት፣ ተጠንቶ የተቀመጠ መሥፈርት የሌለውና ግንባታውን አጥንቶ ለመሥራት የሚያስችል ምቹ ሆኔታዎች የሌሉበት እንደነበር ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

‹‹ሙስና አንደኛው ችግር ቢሆንም ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ግንባታ የሚያደርግ የለም፡፡ ገንዘብ ብቻ ስለሚከፈላቸው ግንባታውን በደፈናው ሲጀምሩ ነው የሚስተዋለው፤›› በማለት አቶ ተሰማ የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ፡፡

አቶ ተሰማ አክለውም በአገሪቷ ያለው የምሕንድስና ሙያና ትምህርት ዳግም መጤን ይኖርበታል ይላሉ፡፡ ምክንያቱም የተገነቡት ስታዲየሞች የአገሪቷ ምሕንድስና ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ እንደሆነ ያክላሉ፡፡

‹‹የተገነቡት ስታዲየሞች ዳግም መገንባት ባይችሉ እንኳን ዲዛይናቸው ታይቶ፣ ምክንያቶች ቀርበውና ማሻሻያ ተደርጎባቸው ለወጣቶች ማዘውተሪያ መሆን የሚችሉበት መንገድ መፈጠር አለበት፤›› በማለት የመፍትሔ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስፖርቱ የነቃ ተሳትፎ (በተለይ በአትሌቲክሱ) እንዳላት ይታወቃል፡፡ ሆኖም ኬንያና የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማሰናዳት ከአውሮፓ አገሮች ጋር መፎካከርን ከተያያዙት ሰነባብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብትና አቅም መጠቀም ተስኗት የሊግ ውድድር እንኳን ለማስተናገድ በዩኒቨርሲቲ ስታዲየሞች  ለማከናወን ተገዳለች፡፡

በቀጣይ ሊገነቡ ለታሰቡት ስታዲየሞች ገንዘብ ከማውጣት ባሻገር ግንባታቸው ዓለም አቀፍ ልኬትን የጠበቁ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ጥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...