ጎበዝ ዘንድሮ የገጠመን ፈተና ከባድና ውስብስብ ቢሆንም፣ በማስተዋልና በተረጋጋ ሁኔታ ነገሮችን ማጤን ከቻልን እንደምንወጣው አልጠራጠርም፡፡ ዋናው የሚያስፈልገው ነገር አርቆ ማሰብና ራስን በሚገባ መግዛት ነው፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ሆነን የሚባለውን ሁሉ ሳናገናዝብ የምናግበሰብስ ከሆንን መጫወቻ ነው የምንሆነው፡፡ ስለዚህም ረጋ ብለን እየተከናወኑ ያሉ ነገሮችን በፅሞና እንከታተል፡፡ ከስሜታዊነት ነፃ ሆነን በምክንያታዊነት ማሰብ ስንጀምር እየተቀመሩልን ያሉ ተንኮሎች በሙሉ በቀላሉ ይገቡናል፡፡ በቀደም ዕለት ከመስቀል አደባባይ ሠልፍ ወደ ቤቴ ስመለስ መጀመርያ ያደረግኩት ነገር፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለዋልንበት የሚሊዮኖች ሠልፍ ምን እንደሚሉ መስማት ነበር፡፡ እነሱ ግን የሕወሓት ታጣቂዎች ሊይዟት እየገሰገሱባት ባለችው አዲስ አበባ፣ አሥር ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ ወጥተው ነበር ሲሉ በሕይወቴ የማላውቀው ዓይነት ሳቅ ነበር ያንፈራፈረኝ፡፡
እኛ ሕወሓትንና ኦነግ-ሸኔን ያወገዝንበትን፣ ለአገራችን ህልውና ለሚዋደቁ ጀግኖች ድጋፋችንን ያሳየንበትንና ምዕራባውያንና ተላላኪ ሚዲያዎቻቸውን አደብ ግዙ ያልንበትን የሚያስተጋባ ድምፃችንን አፍነው የተለመደውን፣ ‹‹በቅርብ ርቀት የተከበበችው አዲስ›› አበባ እያሉ ሲዘፍኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነው አንቅሬ የተፋዋቸው፡፡ ከዚህ ቀደምም ቢሆን በከፍተኛ ጥርጣሬ ዘገባዎቻቸውን ብከታተልም፣ እንደ በቀደም ዕለት ግን አስጠልተውኝ አያውቁም ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ ሁሌም ቢሆን በዓለም ላይ እንደ አማራጭ የሚታዩትን አርቲ፣ ቲአርቲና እንደ ግሎባል ኔትወርክ የመሳሰሉ የእነ ሲኤንኤን፣ የእነ ቢቢሲና አልጄዚራን ጭምብል የሚገነጥሉ ሚዲያዎች እከታተላለሁ፡፡ ዓለምን በዚህ መንገድ ካልቃኘናት እነ ሲኤንኤን የአሜሪካና የሸሪኮቿ መጫወቻ ስለሆኑ፣ መረጃዎችን እያዛቡ ውሸት ሲግቱን ነው የሚኖሩት፡፡ በኢትዮጵያ ላይም በውሸት ናዳ የተነሱት አሜሪካና መሰሎቿ ለምን በእጅ አዙር ቅኝ አንገዛችሁም ስላሉ ብቻ ነው፡፡ ኮርፖሬት ሚዲያዎቹ ዋና ሥራቸው ከእነ ሲአይኤ ባልተናነሰ ጠላት የተባለን አገር ለማፍረስ ውሸት መፈብረክ ነው፡፡ ለካ ዶናልድ ትራምፕ ወዶ አይደለም ‹‹ፌክ ኒውስ›› ሲላቸው የነበረው፡፡ ወገኖቼ ከዚህ በኋላ ተነቃቅተናል በማለት የሚሠሩትን እግር በእግር እየተከታተሉ ማጋለጥ ነው የሚያዋጣው፡፡ እስቲ ይህንን ሰሞነኛ ጉድ አንብቡ፡፡
‹‹ዘ ግሬይ ዞን ኒውስ›› የሚባል ሚዲያ ረዳት አዘጋጅ የሆነው ቤንጃሚን ኖርተን፣ 173,800 ተከታዮች ባሉት የትዊተር ገጹ ያሳፈረው ዜና ቀልቤን ስለሳበው እናንተም ተጋሩ፡፡ ይህ ጋዜጠኛ በእንግሊዝኛና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ለሚሠራው ሚዲያ ዘገባ ለማዘጋጀት ኒካራጓ ተገኝቷል፡፡ እዚያ የሄደበት ምክንያትም ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ምርጫ ለመዘገብ ነበር፡፡ የኒካራጓ ምርጫ ውጤት እንደተሰማ የአሜሪካን ጨምሮ የምዕራባውያን በርካታ ሚዲያዎች ምርጫውን ሲያብጠለጥሉ ነበር የከረሙት፡፡ ዋናው ምክንያታቸው ደግሞ ዝነኛው ዳንኤል ኦርቴጋ ምርጫውን ለአራተኛ ጊዜ ማሸነፋቸው ነበር፡፡ ኦርቴጋ በመላው ዓለም ከአርባ ምናምን ዓመታት በላይ የሚታወቁት ኮሙዩኒስት በመሆናቸው ነው፡፡ አሜሪካ ደግሞ ኮሙዩኒስት የሚባል ነገር መስማት አትወድም፡፡ ሚዲያዎቹ ደግሞ አሜሪካ የማትወደው ኃይል ላይ ጃስ ይባላሉ፡፡
ሆዜ ዳንኤል ኦርቴጋ ሳቬርዳ ‹‹ሳንዳኒስታ ናሽናል ሊበሬሽን ፍሮንት›› በመባል በደቡብ አሜሪካ ዝነኛ የሆነው ፓርቲ መሪ ሲሆኑ፣ አገራቸውን ከአምባገነኑ የሶሞዛ አገዛዝ በትጥቅ ትግል በመገርሰስ እንደ ኩባ መሰል አገር በደቡብ አሜሪካ ለመገንባት ጥረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ ምክንያት ዕቅዳቸው ሙሉ በሙሉ ባይሳካም፣ በኒካራጓውያን ልብ ውስጥ ነበሩና በፖለቲካው ውስጥ ወጥረው በመሳተፋቸው በተደጋጋሚ ሊመረጡ ችለዋል፡፡ ኦርቴጋ ለአሜሪካና ለምዕራባውያኑ የተመቹ ስላልሆኑ እንደ ጠላት ነው የሚታዩት፡፡ በምርጫው ካሸነፉ በኋላ ግን የምዕራባውያን ሚዲያዎች በተለይ የአሜሪካን ትንፋሽ ተከትለው ኒካራጓንና መሪዎቿን እያብጠለጠሉ ነው፡፡ ቀንና ሌሊት የምርጫውን ተዓማኒነት ከል ለማልበስ ተረባርበዋል፡፡ ጋዜጠኛው ግን ሌላ ታሪክ ይነግረናል፡፡
ጋዜጠኛ ኖርተን አራት የምርጫ ማዕከላትን ጎብኝቶ ከመራጮች ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አጭር ቪዲዮ ከጽሑፉ ጋር አያይዟል፡፡ ‹‹የኒካራጓን ምርጫ አስመልክቶ በእነዚህ ኮርፖሬት ሚዲያዎች እጅግ በጣም በርካታ የውሸት ዜናዎች እየተፈበረኩ ነው፡፡ ምርጫው ተዓማኒነት እንዳያገኝ በሐሰተኛ ዜናዎቻቸው ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ እኔ ባየሁዋቸው አራት የምርጫ ማዕከላት በርካታ መራጮች ድምፃቸውን በተቀላጠፈና ግልጽ በሆነ መንገድ ሲሰጡ አይቻለሁ፡፡ አታምኑኝም? እንግዲያውስ ቃለ መጠይቅ ያደረግኩላቸውን ሰዎች የሚሉትን ተመልከቱ፤›› በማለት ቪዲዮውን ጋብዟል፡፡ ቃለ መጠይቅ የተደረጉ ሰዎች ያለ ምንም ፍራቻ በልበ ሙሉነት ድምፃቸውን መስጠታቸውንና መደሰታቸውን ሲናገሩ ይታያሉ፡፡
ይህ ጋዜጠኛ በተጨማሪም የተለያዩ ፎቶዎችን በማሳየት የታዘበውን ይናገራል፡፡ ‹‹እነዚህን ፎቶዎች ከተለያዩ የምርጫ ጣቢዎች ያነሳኋቸው ናቸው፡፡ ከፎቶዎቹ እንደምታዩት በርካቶች ድምፃቸውን እየሰጡ ነው፡፡ የምርጫ ሒደቱ ግልጽና በሚገባ የተደራጀ ነው፡፡ የምርጫ ጣቢያዎቹ በሰዎች የተሞሉ ቢሆኑም፣ መራጮች ግን በፍጥነት እየገቡ እየመረጡ ወደ ቤታቸው እየሄዱ ነው፡፡ በግልጽና በፈጣን አሠራር ነበር ሒደቱ ሲከናወን የነበረው…›› ብሎ ጋዜጠኛው በዓይኑ አይቶ በምሥል ያስቀረውን ለትዊተር ገጽ ተከታዮቹ አጋርቷል፡፡ ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎቸ ጥረቱን አድንቀው የምዕራባውያን ሚዲያዎች በማስረጃ ያልተደገፈ ማደንቆር አውግዘዋል፡፡ ምዕራባውያን ሚዲያዎች ከተመዘገቡ መራጮች 70 በመቶ አልመረጡም ያሉበትን ምርጫ ብዙዎችን ከማስገረም አልፎ ያበሳጨ ነበር፡፡ ምንጭ ሳይጠቅሱ በውሸት የሚለፈልፉትን የምዕራብ ሚዲያዎች ጋዜጠኛ ኖርተን በማጋለጡም ተመሥግኖበታል፡፡ እነ ሲኤንኤን ግን እንዲህ የተከበሩ ሳይሆኑ ውርደት ቀለባቸው ስለሆነ፣ የአሜሪካ ጠላት አለ በተባለበት ቦታ ያላዩትንና ያልሰሙትን እየዋሹ አገር ለመበተን ይቅበዘበዛሉ፡፡ እነዚህ ውሸታሞች ገና ብዙ አስገራሚ የውሸት ወሬዎችን ስለሚያሠራጩ፣ ነቃ ብለን ተጨባጩን ሁኔታ እንገንዘብ፡፡ በፍፁም መታለል የለብንም፡፡ ጎበዝ ከዚህ በኋላ ቀልድ ስለሌለ ወጥረን እነሱን ማጋለጥና ይህንን ከባድ ጊዜ ለማለፍ በአንድነት እንሠለፍ፡፡ አገራችንን ለመታደግ የሚያዋጣው ይኼ ብቻ ነው፡፡
(ዋሲሁን አበጋዝ፣ ከአስኮ)