Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉወርጅዎች እነ ማን ናቸው?

ወርጅዎች እነ ማን ናቸው?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በዚሁ ጋዜጣ ሰኔ 8 እና 15 ቀን 2013 (13 June 2021 & 20 June 2021) ዕትም ‹‹አዲስ የታሪክ ዳሰሳ በስልጤዎች ዙሪያ›› በሚል ርዕስ ለንባብ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በዚህም ርዕስ ስልጤ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር ከሚገኙት ዞኖች አንዱ እንደሆነ ተጠቅሶ ይህም ዞን በበፊት ጉራጌ እየተባለ ሲጠራ ወይም ከጉራጌ ጋር ተደምሮ ሲጠራ እንደነበር ጠቅሶ ስለስልጤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ስለስልጤዎች ታሪክ፣ አፈ ታሪክና ወደ ፊት ትኩረት ሊሰጥባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች፣ ስልጢዎች ወይም ስልጤዎች እነማን ናቸው? የስልጢ/ስልጤ ማለት ትርጉም ምንድነው? ወረባ/ወራቤ ማለትስ? ወደ ስልጢ ስለመጡ የሐረሪ ወይዛዝርት (ጊስቲዎች) በአጭሩም ቢሆን ቀርቧል፡፡ መስከረም 9 ቀን 2014 (19 September 2021) ደግሞ ‹‹የገራድና ገራድነት ታሪክ በኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ በሰሜናዊው የአገራችን ክፍል በተለይ በጎንደር በጎጃም፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በሸዋ፣ (አማራ፣ ትግራይ፣ አገው) ልዑላዊ፣ ወታደራዊ፣ ኦፊሴላዊና የሲቪል ማዕረጎች እንዳሉ ተጠቅሶ  በሐረር፣ በሱማሊ፣ በስልጢ፣ በሐድያና በሌሎችም አካባቢዎች ‹ገራድ የሚል› ማዕረግ መኖሩና ስለገራድነትም ሰፊ ትንታኔ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ያኔ በቀረቡት ጽሑፎች ረጋዶች እነ ማን ናቸው? ስልጢዎችስ? ብለን ጠይቀን መልስ እንዳገኘነው ሁሉ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ደግሞ ‹‹ወርጅዎች እነማን ናቸው?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ይደረጋል፡፡

በዚህ ጥናታዊ ጽሐፍ ስለ ወርጅዎች እነማንነት፣ ስለወርጅ ዓውዳዊ ትርጉም፣ ስለወርጅ ሕዝብ መኖሪያ፣ የወርጅ ሕዝብ በሸዋ ሱልጣኔትናሸዋ ሰለሞናዊው ክርሲቲያናዊ ሥርወ መንግሥት፣ እንዲሁም በኢፋት ሱልጣኔት ስለነበረው ሚና፣ ስለትግሬ ወርጅ ቋንቋ መሞትና ቋንቋዎች ሲሞቱ የሚከሰቱ ችግሮች ምን እንደሚሆን፣ ቋንቋ እንዳይሞት ማድረግ ምን መደረግ እንዳለበትና ቋንቋን ከሞት ማዳን መመለስ ይቻል እንደሆነ፣ ወርጅዎች ቋንቋቸው ቢሞትም ባህላቸው እንዳልሞተና ወደፊት እንደምን ማንነታቸውን ጠብቀው ሊኖሩ እንደሚችሉ ይተነናል፡፡

- Advertisement -

የወርጅ ዓውዳዊ ትርጉም

አንሳይክሎፒዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኘው ወርጅ የሚለው የጎሳ አባላት ስም በመጀመሪያ ሰፍሮ የምናገኘው በሸዋ ታሪክ በተለይም በ13ኛው ክፍለ ዘመን በተጻፈ ሙአለ ዜና ውስጥ ሲሆን በዚህ ሙዓለ ዜና ቸሩሊ አማራ ገዥዎች በ1128 በወርጅዎች ላይ የሰነዘሩት ጥቃት እንዳልተሳካላቸው ይጠቅሳል (Enrico Cerulli 1941: 18)፡፡ ወርጂን ከዓረብኛ አጠራሩ ጋር በማያያዝ ‹‹ወርጅህ›› በማለት የሚጠራው ኢንሪኮ ቸሩሊ በ1932 እና በ1941 ለኅትመት ባበቃው የምርምር ሥራው እንደጠቀሰው ‹‹ከ10ኛው እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን በሸዋ ሱልጣኔት ውስጥ ይገኝ የነበረ ሕዝብ ሲሆን ፒ. ማርሳኒ ደግሞ በ1332 በሥልጣን ላይ ስለነበሩት አፄ አምደ ጽዩን መንግሥት ከሚተርከው በግዕዝ የተጻፈ ሙዓለ ዜና በመውሰድ ‹‹ወርጅህ›› ይለዋል (P. Marrassini, 1993, p. 54)፡፡ ጀምስ ኪዊሪን (James Quirin) በኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ (2010 p. 1145) ካሰፈሩት ጽሑፍ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ መረጃዎች  ወርግህ፣ መርግህ፣ ወርጂህ ተብሎ እንደተጠቀሰ እንገነዘባለን፡፡

በዚህም መሠረት ዛሬ ወርጂ ተብሎ የሚጠራው ሕዝብ ‹‹ወርጅህ፣ ወርግህ፣ መርግህ፣›› ተብሎ በተለያዩ ጸሐፊያን እንደተገለጠ እንረዳለን፡፡ ወርጂ ከፊቱ ቅጽል ተጨምሮበት ‹‹ትግሪ ወርጂ›› ተብሎም ይጠራል፡፡ ትግሪ ወርጅ የተባለበትን ምክንያትንም የተለያዩ መረጃዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ወደፊት በዝርዝር የምንመለከታቸው መረጃዎች እንደሚሉት ጥንታዊ ወርጅዎች ቋንቋቸው ከትግርኛ ጋር ይመሳሰል ስለነበር ከትግራይ ወይም ከኤርትራ የመጡ ትግርኛ ተናጋሪ ነጋዴዎች ናቸው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ‹‹የለም ትግሪ የሚለው ቃል ቲጃሪ ማለትም ነጋዴ ከሚለው የዓረብኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ትግሪ ወርጂ ወይም ቲጃሪ ወርጅ ማለት ወርጅ ነጋዴ ወይም የወርጅ ነጋዴ ነው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ቲጃሪ›› የሚለው የዓረብኛ ቃል (ዓረቦች ‹ገ› የሚል ፊደል ስለሌላቸው ‹‹ትግሪ›› ተብሎ ሲነገር የነበረው በፊደላቸው ‹‹ትጅሪ›› ብለው እንደጻፉት ቀጥሎም ትርጉም ሲፈልጉለት በማጠጋጋት ‹‹ትጃሪ›› ከሚል የዓረብኛ ቃል የተወሰደ ነው ቢሉ የሚገርም አይደለም፡፡ ሰዎች አርጎባን ሲተረጉሙ በማጠጋጋት ‹‹ዓረብ ገባ›› እንዳሉት ማለት ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ትግሪም ይሁን ትግሪ የሚል ከፊቱ ገላጭ ቅጽ ኖረውም አልኖረውም ‹‹ወርጅ›› የሚባል ሕዝብ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ ከተጀመረበት ከዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ህልውናውን ጠብቆ መኖሩን የሚከልል ከቶ አይደለም፡፡ ወርጅዎች ጥንትም ነበሩ፣ ዛሬም እንዲሁ፡፡

የወርጅ ሕዝብ አሠፋፈር

በመሠረቱ የወርጅ ሕዝብ ለብቻው ሳይሆን ከአዳል፣ ከሐርላ፣ ከኦሮሞ፣ ከጋፋት፣ ከወራባ፣ ከሐድያ ወዘተ ሕዝብ ጋር የኖረ ሕዝብ ሲሆን በሸዋ፣ በኢፋት፣ በአሊዩ አምባ፣ በአዋሽ ቆላማ ሥፍራዎች፣ በወጅ፣ ወዘተ ተሠራጭቶ እንደሚገኝ ቀደም ሲል የተጠቀሱትና ወደፊትም በአግባቡ የሚገለጹ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በጀምስ ኪዊሪን (James Quirin) በኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ሰፍሮ እንደምናገኘው ወርጅዎች በምሥራቅ አዋሽ ወንዝ ሜዳማ ሥፍራዎች አካባቢ ከብቶችና ግመሎችን እያረቡ ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎች መሆናቸውን ጠቅሶ የአፄ አምደ ጽዮን ዜና ሙዓል ዘጋቢ ወርጃዎችና ገበል የተባሉ ጎሳዎች በተጠቀሰው ቆላማ ሥፍራ ይኖሩ እንደነበሩ አስፍሯል፡፡ ዜና ሙዓሉ አፄ ዓምደ ጽዮን የሸዋ ግዛት ድንበራቸውን በማስፋፋት ላይ በነበሩበት ጊዜም ከወርጅዎች ጋር መዋጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል እንደተገለጸው የወርጅ ሕዝብ ሰፍሮ ይኖር የነበረው በሸዋ፣ በኢፋት፣ በአሊዩ አምባ፣ በአዋሽ ቆላማ ሥፍራዎች፣ በወጅ ነው፡፡ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩና ከኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች መረጃ ሰብስበው የታሪክ ጽሑፍ ያሰባሰቡ እንደኢብን ሰይድ አል መቕሪቢን፣ ኢብን ፈድለሏህ አል-ዑማሪን፣ አል መርዙቂን፣ ኢብን ኻልዱንንና አል-ቃልቃሻንዲን ያሉ ዓረቦች እንደሚሉት በዚህም የመኖሪያ ሥፍራ የሚገኝ ነዋሪ ከዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስልምናን ተቀብሎ የሚኖር ነበር፡፡ ስለሆነም ይህን እውነታ በጥቅሉ መቀበል ወይም በጥቅሉ መቃወም ሳይሆን፣ በመጀመሪያ በመኽዙማዊያን ከሚመራው የሸዋ ሱልጣኔት ቀጥሎም ከይፋት ሱልጣኔት፣ ግዛት ውስጥ ይገኝ እንደሆን መፈለግ ይኖርብናል፡፡ በዚህም መሠረት፣ የተጠቀሱት ሱልጣኔቶች ግዛት አንድ ጊዜ ሲሰፋ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሲጠብ እንደነበር ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ ለምሳሌ የሸዋ ሱልጣኔት እስከ ዛሬው ምዕራብና ደቡብ ሸዋ ሊዘረጋ ሲችል የኢፋት ሱልጣኔት በስተምስራቅ ወደ አፋርና ባሌ ወይም ወደ ድሮው ሀረርጌ ሊሰፋ ይችላል፡፡ ስለሆነም ስለወርጅ ሕዝብ ታሪክ ስናጠና እነዚህን ግዛቶች መፈተሸ ይኖርብናል፡፡ 

ሀ. የሸዋ ሱልጣኔትና የሸዋ ሰለሞናዊው ክርሲቲያናዊ ሥርወ መንግሥት

የመኽዙማዊ ሱልጣኔት ሥርወ መንግሥት ወይም ሸዋ ሱልጣኔት እየተባለ የሚጠራው በአሁኒቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ወለሌ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ማለትም በሐርላ ግዛት ውስጥ ከሚገኘው ከሐረርጌ በስተሰሜን የሚገኝ ኢስላማዊ ግዛት ነው፡፡ የመኽዙማዊ ሥርወ መንግሥት የአክሱም ሥርወ መንግሥት መወገድን ተከትሎ እንደመንግሥት ብቅ ያለ ሲሆን በዚህም ሥርወ መንግሥት እንደ ጨለንቆ፣ ባቲ፣ ድሬዳዋ አጠገብ ባለው ሐርላና ላንጋኖ አጠገብ በሚገኘው ሙኔሳ ተብሎ የሚጠራውን ግዛት ያጠቃልላል፡፡

ምንም እንኳን አንዳንድ መረጃዎች መኽዙማዊ ሥርወ መንግሥት በ896 እንደተመሠረተ ቢጠቁሙም ከ12ኛው ክፍለ ዘመን በፊት እምነታቸውን ወደ ኢስላም ስለመለወጣቸው የሚያመለክት የሙዓለ ዜና መረጃ የለም፡፡ ይህም ሆኖ በ1108 ‹‹ጋብህ›› ተብለው የሚጠሩ ጎሳዎች እስልምናን መቀበላቸውንን እነዚህም ጎሳዎች የአርጎባዎች ቅድመ አያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ትሪሚንግሃም ግምቱን አስፍሯል፡፡ በ14ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽም በሰሜን አዋሽ በተለይም በዘብርና ምድረ ዘጋ (ከአሁኗ መርሐቤቴ ደቡብ) ገበል ወይም ወርጂ (ትግሪ ወርጅ)፣ ተጉለትና መንዝ ያኔ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ የሸዋ ሱልጣኔት ዜና ሙዓል እንደሚተርከው በ1128 አማራዎች ከሸዋ ታራራማ ሥፍራዎች ወደ አዋሽ ሸለቆ በመሄድ ከወርጅዎች ጋር መኖር ጀመሩ፡፡ ወርጅዎችም ያኔ በተጠቀሰው ሥፍራ የሚኖሩ ከብት አርቢዎች ነበሩ፡፡

እስካሁን ድረስ የሸዋ ሱልጣኔትና የሸዋ ሰለሞናዊው ክርሲቲያናዊ ሥርወ መንግሥት በተቀራራቢ ዘመን በአካባቢ እንደነበሩ ይልቁንም የሸዋው ሱልጣኔት ሰፊ ግዛት እንደነበረውና በኃይልም የበላይነት እንደነበረው ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይልቁንም በሸዋ ሱልጣኔት ከነበሩት ጎሳዎች ወርጅዎች ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው የአፄ አምደ ጽዮን ሙዓለ ዜና ያመለክታል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሸዋ ሰለሞናዊው ክርሲቲያናዊ ሥርወ መንግሥት በ13ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ይኩኖ አምላክ አማካይነት የበላይነቱ ገኖ ከመውጣቱ በፊት ከዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ሥር እንደነበረንና የዛጉዌ ሥርወ መንግሥትም በሸዋ ሱልጣኔት፣ በአዳል ሱልጣኔት፣ በኢፋት ሱልጣኔት ወደ ባህር ወደቦች ይደረግ የነበረውን ጉዞ እንደገታበት፣ በዚህም ምክንያት መንግሥቱ እንደተዳከመ፣ በመዳከሙም የሸዋ ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሥልጣኑን እንደወሰደበት እንገነዘባለን፡፡

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ያሪክ ሰነዶች የሸዋ ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የመሠረቱት ኃይሎች የአክሱም መንግሥት ሲሸነፍ ወደ ሸዋ የመጡ መሆናቸውንና እነዚህም ሰለሞናውያን ኃይላቸውን አጠናክረው የዛጉዌ ሥር መንግሥትን እንዳሸነፉ ይገልጣሉ፡፡ ለእነዚህም የታሪክ ጸሐፊዎች መሠረታቸው ክርስትና ከሰሜን ኢትዮጵያ እስከ ሸዋ ድረስ እንደተስፋፋ የሚያመለክቱ መረጃዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ደብረ አሰቦ ገዳም (ደብረ ሊባኖስ) ሚኤሶ አካባቢ ወይም ምሥራቅ አዋሽ በ13ኛው ክፍለ ዘመን መቆርቆሩን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደ አርጎባ፣ ጋፋት፣ ወራባ፣ ሐረሪ ያሉት የኅብረተሰቡ ክፍሎች እንደ ዳሞት፣ አንጎት፣ ወለቃ፣ ጋይንት፣ መርሐ ቤቴ ሰሜዋ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሆኑትም ከዚህ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ ወርጅም ከሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ጋር ሊመደብ እንደሚችል የሚያመለክቱ ወደ ፊት የምንመለከታው ፍንጮች አሉ፡፡ ሆኖም እንደ ጋፋት፣ ዛይ ወይም ላቂ ሕዝብ ሁሉ የእነሱም ቋንቋ ጠፍቷል፡፡

የሸዋ ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ከአፄ ይኩኖ አምላክ (1270) እስከ አፄ ገላውዲዎስ ግዛቱን ከሸዋ ባሻገር ሲያስፋፋ የሸዋ ሱልጣኔትን እንዳዳከመው እርግጥ ሲሆን፣ አፄ ዘርአ ያዕቆብ መናገሻ ከተማቸውን አሁን ‹‹ደብረ ብርሃን›› እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ ላይ ሲቆረቁሩ፣ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የአቡነ ዜና ማርቆሱ ደብረ ብሥራት፣ በ15ኘው ክፍለ ዘመን ደብረ ምጥማቅ ቤተ ክርስቲያ፣ በዝቋላ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስና ሌሎችም ገዳማትና ደብራት ሲመሠረቱ ክርስትና በአካባቢው የበላይነትን እያገኘ እንደመጣ ይታወቃል፡፡ የበላይነት እያገኘ በመምጣቱም አንፃራዊ በሆነ መልኩ ሲታይ እንደ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ሲና፣ በረራ፣ መናገሻ፣ የረር፣ እንጦጦ ያሉት የተመሠረቱትና ያደጉት በከፍተኛ ፍጥነት ነው፡፡

የእነዚህ ከተሞች መቆርቆርም በግብርናና በቤተክህነት ተወስነው ይኖሩ የነበሩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ፊታቸውን ወደ ንግድ ለማዞር አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይልቁንም እንደ ወርጂ፣ አርጎባ፣ ወራባ፣ ሃድያና የመሳሰሉት በአመዛኙ በንግድ ሥራ ላይ ኑሯቸውን የመሠረቱ ጎሳዎች ይኖሩባቸው የነበሩ ግዛቶችን እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ማለትም እስከ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልቓዚ ወደ ሥልጣን መምጣት ድረስ ለመቆጣጠር በመቻላቸው ከፍተኛ ሀብት ለማካበት ችለው ነበር፡፡ ለምሳሌ ወራባ በኢማም አሕመድ ኢብራሂም ስትያዝ አፄ ልብነ ድንግል ምን ያህል እንደቆጫቸው ዓረብ ፈቂህ ‹‹ፉቱሑል ሐበሽ በተሰኘው መጽሐፉ አስፍሯል፡፡ የዚህ መጽሐፍ አዘጋጅም የስልጤዎችን ታሪክ በጻፈበት ሥራው በሰፊው አስፍሯል፡፡

አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የግራኝ አሕመድ ወረራ›› በሚል ርእስ በ1968 ባሳተሙት መጽሐፍ ‹‹በዚህ ሰዓት በአንጎት የሚገኙት አፄ ልብነ ድንግል የወረባን በእስላሞቹ መያዝ ሲሰሙ በጣም አዝነው ይህች አገር ገነት ስለሆነች ያጣናት እንደሆነ ዘውዳችን ኃይላችንም መጥፋቱ ነው፡፡ ስለዚህ ሂድ ተከላከል ብለው በፊት የዚሁ ወረዳ ሹም ለነበረው ለራስ ነቢያት ነግረውት ነቢያት ጦር ይዞ ከአንጎት ወደ ወረባ መጣ፡፡ እንደመጣም ሕዝቡን ሰብስቦ እስላሞቹም ካገራችሁ ለማባረር ከንጉሡ ተልኬ መጠቻለሁና እርዱኝ ብሎ መልዕክተኛ ለየባላገሩ ቢያስለፍፍ ባላገሩ መልዕክተኛውን ሰድቦ አሳፍሮ መለሰው…›› በማለት አስፍረዋል፡፡

የሸዋ ሥርወ መንግሥት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን በኦሮሞ መስፋፋት ዘመን ቢዳከምም ከ19ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ እየተጠናከረ በመምጣቱ ግዛቱን ከአራቱም አቅጣጫ አስፋፋ፡፡ በተለይም እንደ ወርጅ፣ ወራባ፣ አርጎባ፣ ሀላባ ሀድያ ያሉ ሱልጣኔቶች በመዳከማቸው የሚጫንባቸውን ግብር ከመክፈል በስተቀር ሌላ አማራጭ መንገድ አልነበራቸውም፡፡ የሸዋ ሥርወ መንግሥት በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እየተጠናከረ ሲመጣ ለሥርዓቱ አንገዛም ያሉትን በጦር እያንበረከከ፣ ሥጋት ሆነው ሲያገኛቸውም ከመኖሪያቸው እያፈናቀለ ወደ ሌላ ቦታ ያሰፍራቸው ነበር፡፡ የወርጅ አዛውንት እንደሚናገሩት ከአሊዩ አምባ፣ ከደብረ ብርሃን፣ ከሰኖ፣ ከሰበታ፣ ወዘተ አካባቢ የነበሩትን ወርጅዎች ጠራርጎ በማውጣት ወደ ምዕራብ ሸዋ አሰፈራቸው፡፡

ለ. የኢፋት ሱልጣኔት

በወላስማ ሥርወ መንግሥት የተመሠረተው የኢፋት ሱልጣኔት ከሸዋ ሱልጣኔት ቀጥሎ የመጣ ሲሆን፣ ይህም ሥርወ መንግሥት የተመሠረተው የሸዋ ሱልጣኔት በሸዋ አፄዎች ሥርወ መንግሥት ከተዳከመ በኋላ መሆኑ ኤንሪኮ ቸሩሊ በ1943 ለንባብ ባቀረበው ጥናታዊ ጽሑፉ (ገጽ 248) ይገልጻል፡፡ አሕመድ ሀሰን ዑመር-ዴኒስ ኖስነተሲን (Ahmed Hassen Omer–Denis Nosnitsin) በኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፕካ ውስጥ ኢብን ሰይድ አል መቕሪቢን፣ ኢብን ፈድለሏህ አል-ዑማሪን፣ አል መርዙቂን፣ ኢብን ኻልዱንንና አል-ቃልቃሻንዲን ጠቅሰው እንዳሰፈሩት የኢፋት ወላስማዊ ሥርወ መንግሥት የተመሠረተው በ1285 እንደሆነና ጸሐፍቱም በየበኩላቸው ሰፋ ያለ መረጃ መጻፋቸውን ገልጸዋል፡፡ አሕመድ ሀሰን ዑመር-ዴኒስ ኖስነተሲን የተጠቀሱት ጸሐፊዎች ያሰፈሩትን መረጃ በመያዝ የኢፋት ሥርወ መንግሥት ከሰሜን ምሥራቅ ሸዋ እስከ ምሥራቅ ዘይላዕ ድረስ እንደነበር ያብራራሉ፡፡ ጸሐፍቱ በተለይ የኢፋት ሥርወ መንግሥትን ከገበርቲ፣ ገባራ፣ ገበርት ተብለውም እንደሚጠሩ መረጃዎቹን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህም ‹‹ጀበርቲዎች ናቸው›› ብለው ይገልጿቸዋል፡፡

ምንም እንኳን ወርጅዎች በ12ኛውና በ13ኛው ክፍለ ዘመን ቀደም ሲል በተጠቀሰው በምሥራቅ አዋሽ ሸለቆ አካባቢና በዓሊዩ አምባ መኖራቸው በአፄ አምደ ጽዮን ዜና ሙዓል የተጠቀሰ ቢሆንም በ16ኝው ክፍለ ዘመን በተጻፈው በፉቱሑል ሐበሽ ውስጥ ሰፍሮ አናገኘውም፡፡ ሆኖም በ19ኛው ክፍለ ዘመን በመላው ሸዋ በንግዱ ዘርፍ የበላይነቱን ይዘው እንደነበርና እስከ ጊቤ ሥርወ መንግሥት ግዛት ድረስ ይነግዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነዚህ በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ የወርጅ ነጋዴዎችም ከ1840-1870 በነበረው ጊዜ በአካባቢው እስልምናን እንዳስፋፉ ትሪሚንግሃም ይገልጻል (Trimingham Islam in Ethiopia 199):: ይህ በዚህ እንዳለ፣ በአዲስ አበባ ዙርያ የሚገኙ ወርጅዎች ከሐረር እንደመጡ ይናገራሉ፡፡ በጣም አክራሪ ሙስሊሞች መሆናቸው የሚነገርላቸው ወርጅዎች ኦሮሞች በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች እየተጓዙ እንደሚሠሩ ሞንዶን-ቪዳሌት (Mondon-Vidailhet) ጠቅሶ ወርጅዎች በአንድ ቦታ ረግተው ከሚነግዱት ‹‹ከትግሪዎች›› የተለዩ መሆናቸውን በጥናቱ አስፍሯል፡፡ ሞንዶን-ቪዳሌት ከዚህም በተጨማሪ ትግሪዎች ወርጅዎች አፍካላዎች የሚያርዱትን እንደማይበሉም በጥናቱ አስፍሯል (Mondon-Vidailhet 1900:170)፡፡ ሆነም ቀረ በደቡብ አዲስ አበባ የሚኖሩ ወርጅዎች ከጉራጌዎች ጋር እየኖሩ እስልምናን እንዳስፋፉ (ዶር) መርእድ ወልደ አረጋይና ትሪሚንግሃም ይገልጣሉ (Merid Wolde Aregay 1974: 270; TrIslam 186)፡፡ ሆኖም በጀበርቲዎችና በአፍካላ ጎሳዎ መካከል ያለው ዝምድና ግልጽ ባይሆንም አፍካላዎች ቀድመው ወደ ሸዋ ግዛት እንደመጡና ጀበርቲዎች እንደተከተሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የትግሪ ወርጅ ቋንቋ

ለአንድ ማኅበረሰብ ትንታኔ የሥነ ልሳን ትንታኔ አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁንና ትግሪ ወርጅዎች ቋንቋቸውን ስለረሱ አሁን በአብዛኛው የሚናገሩት ኦሮሚኛና አማርኛ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሐረሰቦች ተቋም የጥናት መዛግብት እንደሚያመላክቱት (1992:13) ቋንቋቸው የዓረብኛና የጀበርቲ ቅልቅል እንደነበር የትግሪ ወርጂ አገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ ሸማግሌዎቹ እንደሚሉት አማራ ከሰሜን፣ ኦሮሞ ከደቡብ የበላይነቱን ሲይዙ ግን ወርጃዎች የእነሱን ቋንቋ ለመናገርና የራሳቸውን ለመርሳት ተገደዱ፡፡ አንዱ አስረጅ ‹‹ኦሮሞዎችና አማሮች መጥተው መሬታችንን ወሰዱ፣ እኛ ደግሞ ቋንቋቸውን ወሰድን›› በማለት የተናገሩት ይህን እውነታ ያንፀባርቃል፡፡ በእርግጥ ከታሪክ ምዕራፎች እንደምንረዳው አማርኛ ቋንቋ የመንግሥትን ቢሮክራሲን ተጠቅሞ የበላይነት ስለነበረው የአማርኛ ዓለም አመለካከት፣ ባህል፣ ልማድና ክርስቲያን እንዲሆኑ ማጥመቅ አማራ ላልሆነው ሕዝብ ሁሉ ቅድመ ሁኔታ ነበር (Kruyow 1994:232)፡፡

ስለሆነም እንደተጠቀሰው ትግሪ ወርጅዎች በረዥም ጊዜ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖማያና ፖለቲካዊ የበላይነት ምክንያት ቋንቋ ህልውና አክትሟል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ቋንቋ ዝርዝር ውስጥ የትግሪ ዎርጅ ቋንቋ ተካቶና መለያ ቁጥር ተሰጥቶት አይገኝም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከብሔረሰቡ መካከል አንድ እንኳን ቋንቋውን የሚናገር የለም፡፡ ስለዚህም ‹‹አንድ ጎሳ እንዴት ያለ ቋንቋ ሊኖር ይችላል?›› ብሎ ለሚጠይቅ ካልሆነ በስተቀር፣ በአሁኑ ጊዜ የትግሬ ወርጅ ቋንቋ ነበረው ብሎ ማመን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሆኖም፣ ትግሪ ወርጅዎች አንድም ኦሮሚኛ ወይም አማርኛ የሚናገሩ ሆነው ሳለ ለምንድነው ከሁለቱ የአንዱ ብሔረሰብ አባል ሆነው የማይታዩት? አስረጂዎች ‹‹እኛ አማርኛ ወይም ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ልንሆን እንችላለን፣ ነገር ግን የሁለቱም ብሔረሰቦች አባላት አይደለንም፡፡ ስለዚህም አማራ ወይም ኦሮሞ ሆነን ሳንሆን ትግሪ ወርጅ ሆነን መታወቅ እንፈልጋለን፤›› ይላሉ፡፡

በመሠረቱ እንኳን ‹‹ወርጅ›› ተብሎ የሚታወቅ አንድ ሙሉ ጎሳ የአንድ ቀበሌ ሕዝብ ወይም አንድም ሰው ቢሆን ‹‹እኔ የዚህ ብሔረሰብ አባል አይደለሁም›› ካለ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ በሌላ አገር እኮ የራሱን ቋንቋ የሚናገር አንድ አዛውንት ብቻ ተገኝቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የራሱ ቋንቋ ስለሌለው ብቻ ማንነቱን ሊያጣ አይገባም፡፡ ቋንቋ እርስ በርስ ለመግባቢያነት የሚያገልግል መሣሪያ እንጂ ማንነት መለወጫ አይደለም፡፡ ቋንቋ ይፈጠራል፣ ያድጋል፣ ይለወጣል፣ በመጨረሻም ህልውናው ያበቃል፡፡ ይህም ሆኖ ትግሪ ወርጅዎች የራሳቸው ቋንቋ ሳይኖራቸው ማንነታቸውን ጠብቀው ኖሩ? የሚለው ጥያቄ መመለስ ይኖርበታል፡፡ ወርጅዎች በአሁኑ ጊዜ በብዛት ከሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ውስጥም ሰበታ በተለይም ሀውሳ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ዳለቲ፣ ዓለም ገና፣ ፉሪ ተራራና አዲስ አበባ ከተማ ናቸው፡፡

የወርጅዎች ቋንቋ ለምን ሞተ?

ስለወርጅዎች ቋንቋ መሞት ለማወቅ በዓለማችን ስለጠፉት ቋንቋዎች  በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዓለማችን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች የጠፉ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት 30 ዓመታትም 6,000 ያህል ምናልባትም ከዚያ በላይ ቁጥር የሚኖራቸው ቋንቋዎች ሊጠፉ እንደሚችሉ፣ በ2,100 ደግሞ የዓለም ሕዝብ በብዛት ከሚናገራቸው ከዋና ዋናዎቹ  በግማሽ ጠፍተው ጥቂት ብቻ እንደሚቀሩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ቋንቋዎች ከሚጠፉባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው የራሱ የሆነ ቋንቋ ያለው ማኅበረሰብ ሌላ ቋንቋ ያለውን ማኅበረሰብ በጦርነት አሸንፎ ለብዙ ጊዜ በመያዝና ቋንቋውን ቀስ በቀስ በማዳከም በመጨረሻም በራሱ ቋንቋ እንዲተካ ሲያደርግ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ሲኖረው በኢኮኖሚ ዕድገቱ ከፍተኛ የሆነ አገር ከሌሎች አገሮች ጋር በሚመሠርተው የንግድ ግንኙነት ቋንቋውንና ባህሉን ይዞ በመሄድ በየደረሰበት ስለሚያስፋፋ ሊሆን ይችል፡፡ ሦስተኛው በተደጋጋሚ ሊደርስ በሚችል ርሃብ ወይም በጦርነት ምክንያት አካባቢያቸው ለቀው ሌላ ቋንቋና ከፍተኛ ቁጥር ካለው ሕዝብ ጋር መኖር ሲጀምሩ ቋንቋቸውን እየተው የዚያን ሕዝብ ቋንቋ መናገር ስለሚጀምሩ ቋንቋቸው ሊሞት ይችላል፡፡ አራተኛውና ወቅታዊ ምክንያቱ ሰዎች ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይልቅ አንድን ብሔረሰብ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲናገሩ ግፊት መደረጉ ነው፡፡ ይልቁንም ይህንኑ ብሔራዊ ቋንቋ አለመናገር እንዳለመሰልጠን መቆጠሩ የሥራ ቋንቋ በሁሉም ክልሎች በዚያው ቋንቋ እንዲነገር መደረጉ ለአንድ ሕዝብ ቋንቋ መዳከም አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

በዚህም መሠረት ቀደም ሲሉ በተጠቀሱትና ወደፊትም ጥናትን በመመርኮዝ በሚደረስባቸው እውነታዎች የወርጅዎች ቋንቋ በተለያዩ መሠረታዊ ምክንያቶች እንደጠፋ እንገነዘባለን፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ከአዋሽ በስተምሥራቅ ይኖር የነበረው የወርጅ ሕዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ገኖ በወጣውና ግዛቱን ባስፋፋው የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋውን እየለወጠ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሆነ፡፡ በደብረ ብርሃን ማለትም በምሥራቅ ሸዋ፣ በይፋት ተራራማ ሥፍራዎች ይኖር የነበረው የወርጅ ሕዝብም እንደ አርጎባዎችና እንደስልጢዎች እራሱን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ሲከላከል ከቆዬ በኋላ ለስልጣን አስጊ ናቸው የተባሉ ወርጅዎች በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከመኖሪያቸው በግዳጅ ተነስተው ዛሬ በሚገኙበት በምዕራብ ሸዋ እንዲሰፍሩ እንደተደረገ በዕድሜያቸው የገፉ አዛውንት ያስረዳሉ፡፡ በመደረጉም በይፋት የቀሩት ጥቂት ወርጅዎች ቀስ በቀስ ቋንቋቸው ወደ አማርኛ ሲለወጥ በሸኖ፣ በሰበታ፣ በምራብ አዲስ አበባ ዙሪያ፣ በዓለም ገና፣ በፉሪ አካባቢ ያሉት ቋንቋቸው ወደ ኦሮምኛ ተቀየረ፡፡ በዚህም መሠረት ዛሬ ወርጅዎች ባህላቸውን ባይተውም ቋንቋቸውን ግን አጥተዋል፡፡

ቋንቋዎች ሲሞቱ የሚከሰቱ ችግሮች

የአንድ ሕዝብ ቋንቋ ሲሞት በርካታ ችግሮ አሉ፡፡ አንደኛው በራስ ቋንቋ መናገር አለመቻል ነው፡፡ ባለመቻሉም የግል መንፈሳዊ ኩራት አይኖርም፣ የግል ምስጢር እንኳን መናገር አይቻልም፡፡ በቋንቋው ሲነጋገሩ ራሳቸውን የሚገልጹበት ስሜት በሌላ ቋንቋ ሲናገሩ ያን ስሜት ላያስተላልፉ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ ወሎዬ ወይም ጎንደሬ በዓይኑም፣ በእጁም ወይም በትከሻው ስሜቱን እየገለጸ ‹‹ኧረ ወይኔ! አንተ ምንሆነህ ነው?›› የሚል ቢሆንና ይህን ስሜት በሌላ ቋንቋ ግለጽ ቢባል ምን ያህል እንደሚያስቸግር በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በ1970ዎቹ የደርግ የለውጥ ሐዋሪያት በየክፍለ ሀገሩ እየዞሩ ለስለአብዮቱ ሲያስረዱ አንዱ የለውጥ ሐዋርያ አርሲ አሰላ ይመደባል፡፡ በዚህ ጊዜ ስለአብዮቱ በአስተርጓሚው አማካኝነት ማብራሪያ ሲሰጥ በመካከሉ ‹‹ቢሆንም ቅሉ›› የሚል ይጨምርበታል፡፡ አስተርጓሚውም ‹‹ሀተኡመሌ ቡቄ›› በማለት ተርጉሞ በወቅቱ የነበሩ ምሁራንን አስቋቸዋል፡፡ ተሰብሳቢውም ምን ሊባል እንደተፈለገ ሳይረዳው ቀርቷል፡፡ ይህም የሚያመለክተው አንድ ቋንቋ ያካተተውን ባህላዊ እሴት የያዘው የሌላውን ላይዝ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ይህንን በሌላ ምሳሌ እንመልከተው፡፡ ህንዶች እንግሊዘኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው ይናገሩታል፡፡ ሆኖም አካላዊ እንቅስቃሴያቸው ከእንግሊዛውያኑ የተለየ ነው፡፡

እርግጥ ነው የኦሮሞ ሕዝብ የወርጅ ሕዝብን በቋንቋው እንዳይናገር አልከለከለውም፡፡ የኦሮሞ ባህል አሳታፊ እንጅ አግላይ ባለመሆኑ እንዲቀላቀል እንጂ እንዲነጠል አያደርገውም፡፡ እንዲሁም በግብርና ላይ የተመሠረተው ሕይወቱ በንግድ የተሠማራውን የወርጅን ሕይወት ሊያስገድድ ስለማይችል ተጽፅኖ አላደረሰበትም፡፡ ሆኖም በብዛቱ ዋጠው፡፡ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱ እንደማግኔት ወደ ራሱ እየሳበ አስገባው፡፡ የሚያቀርበውን ዕቃ በቋንቋው እየገዛና እየለወጠ፣ የሚያመርተው ሰብልና ፍራፍሬ በቋንቋው እየሸጠና እየለወጠ፣ ሴት ልጆቹን እየሰጠ.. ቋንቋውን አስተማረ፡፡ ጥንታዊ ሁኔታዎችን ስንመለከተውም፣ ሕይወት እንጂ አማራው ሕዝብ  ‹‹የወርጅ ሕዝብ ሆይ፣ ከዛሬ ጀምሮ ቋንቋህን ትተህ አማርኛ ተናጋሪ ትሆናለህ›› ብሎ አላስገደደውም፡፡ ነገር ግን አካባቢውን ለቆ ወደ ከተማ ሲገባና የንግድ ሥራውን ሲያከናውን አማርኛ ተናጋሪ እንዲሆን አደረገው፡፡ የቁጥሩ አነስተኛነትም በዚህ ረገድ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ቋንቋ እንዳይሞት ማድረግ ወይም ከሞት ማዳን ይቻላል ወይ?

ይህም ሆኖ ቋንቋ በተጠቀሱና ባልተጠቀሱ ምክንያቶች የሚሞት ከሆነ የሚቀጥለው ጥያቄ ‹‹እንዳይሞትስ ማድረግ ይቻላል ወይ?›› የሚለው ይሆናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት የሞቱትን ሳይሆን እየሞቱ ያሉትን ቋንቋዎች ከሞት መታደግ እንኳን ባይቻል በጽሑፍና መድምፅ ጠብቆ ማቆየት ይቻላል፡፡ ይህም በመሞት ያሉትን ማለትም የተናጋሪያቸው ቁጥር እየመነመነ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሕዝብን ቋንቋንና ከቋንቋቸው የተያያዘ ባህላቸውንም በመዝገበ ቃላት ጽፎና በድምፅና በምሥል ቀርፆ በማስቀመጥ ከጥፋት ማዳን ይቻላል፡፡ ጨርሶ የሞቱትን ለማስነሳት ግን እጅግ እሩቅ መንገድ መጓዝ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሞተውን የወርጅዎች ቋንቋ ለመፈለግ አሁን ሠፍረው በሚገኙባቸው ሥፍራዎች የሚነገረው የኦሮምኛ ቋንቋ በሌሎች አካባቢዎች ከሚነገረው ቋንቋ፣ በሚጨምራቸው እንግዳ ቃላት፣ በሰዋስዋዊ ሥርዓት፣ ዘዬ ወዘተ የተለዬ ቢሆን እነዚያ የተጨመሩ እንግዳ ቃላት፣ ሰዋስዋዊ ሥርዓትና ዘዬ ከየት እንደተገኙ በመመርመር፣ ከአርጎብኛ፣ ከስልጢኛ፣ ከሐረሪኛ ጋር ይመሳሰሉ እንደሆነ በመፈተሽ፣ በባህላዊ ሥርዓቶቻቸው ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቃላት ለምሳሌ በሠርግ፣ በሐዘን፣ በሃይማኖታዊ በዓላት፣ በአምልኮ ዝግጅቶች መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡

ወርጅዎች ቋንቋቸው ቢሞትም ባህላቸው አልሞተም

የወርጅ ሕዝብ ቋንቋው ቢያንስ በታሪክ ከተመዘገበው በ16ኛው ክፍለ ዘመን እስካሁን ድረስ ስሙን ከባህሉ ጋር ጠብቆ ይገኛል፡፡ ይህም ባህሉ ከኢስላማዊ ባህል ጋር በጥብቅ የተገናኘ ነው፡፡ ስለሆነም ጋብቻውም ሆነ ሐዘኑ፣ እንዲሁም ልዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸው በኢስላማዊ መንገድ ይፈጸማል፡፡ የወርጂ ሕዝብ ህልውና ተጠብቆ እንዲቆይ፣ የትግሪ ወርጂ ወጣቶች ገና በአፍላ ዕድሜያቸው ማንነታቸውን ለማወቅ የሚያስችላቸው ሁኔታ ዘመናዊና በሠለጠነ መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ስለወርጂ ማንነት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ የልማቷ አጋሮች እንዲሆኑ ማስቻል፣ ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞች ጸሐፊዎችና የኪነ ጥበብ ሰዎች የትግሬ ወርጂ ሕዝብ ተጉዘው መረጃ ከማጠናቀራቸው በፊት ከመጽሐፉ አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኙ በመርዳት መሠረታዊ ዓላማውን ማራመድ፣ ወጣት ተማሪዎች የትግሪ ወርጂ በሚመለከት ለሚጽፉት መረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ከወደፊቱ ትውልድ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የትግሪ ወርጂ  ሕዝብ ማንነቱን ጠብቆ ለመቆየት ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ የሕዝቡ ባህላዊ ማዕከል ማቋቋምሆን ይችላል፡፡ በመጨረሻም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የወርጅ ሕዝብ ታሪክ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል መጠናትና መታወቅ ያለበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እያጠናው መሆኑን እየገለጸ ተጨማሪ መረጃ አለን የሚሉ ከታች በተጠቀሰው የኢሜይል አድራሻ እንዲልኩለት በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...