Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትትግልና ተጋድሎ ላይ ስለሆንን ገና ብዙ ይቀረናል

ትግልና ተጋድሎ ላይ ስለሆንን ገና ብዙ ይቀረናል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዓመት በሞላው፣ አሳሳቢነቱ እያደር እየበረታና እየፀና በመጣው፣ ዴሞክራሲን የማደላደልን፣ ገለልተኛ በሆነ ዓምደ መንግሥት ላይ ዴሞክራሲያዊ ትድድርን የመገንባት የለውጥና የሽግግር ተግባርን፣ አገርን ከማዳን ግዳጅና አደራ ጋር ባገጣጠመው በኢትየጵያ ጉዳይና አጀንዳ ውስጥ ይህ አሁን የያዝነው የኖቬምር ወርም ሌላ ወር ነው፡፡ ወይስ የኖቬምበር ወር ዝም ብሎ ሌላ ወር አይደለም ነው የሚባለው? ወሩን የተለየ ወር ነው፣ አምሳያ የሌለው ወር ነው፣ ዝም ብሎ ተራ ወር፣ እንደ ሌሎች ወሮች አይደለም ለማለት ምንድነው የሚባለው? አማርኛው ይህን ያህል አስቸጋሪና ‹‹ውብ›› ነው፡፡

የአማርኛ ነገር ከተነሳ አማርኛችን፣ የሥራ ቋንቋችን፣ የእሱ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት በብዙ አማርኛ ተናጋሪ ባልሆኑ፣ በራሳቸው ቋንቋና በውጭ አገር ቋንቋ በሚናገሩ ሚዲያዎች፣ ባለሥልጣናት ዘንድ በሰፊ የሚመራበት ‹‹መዘዝ››ና ጠንቅ ያለው ክስና ውንጀላ ጎትቶብናል፡፡ ለዚህ ዓይነት ክስና ውንጀላ ዳርጎናል፡፡ እኔ የቋንቋ ሊቅ ቀርቶ የቋንቋ ተማሪ አይደለሁም፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ የኢትዮጵያን ‹‹የከፍተኛ ትምህርት›› የማስተማሪያ ቋንቋን በዚያው በትምህርት ቤት ቆይታዬ በንባብ ውስጥ (እንግሊዝኛን) እችላለሁ ብሎ ‹‹CV››ዬ ላይ ጭምር ከማስመዘግበው በላይ፣ ከአማርኛ ውጪ ሌላ ቋንቋ አላውቅም፡፡ ስለዚህም ይህንን እግረ መንገድ፣ በነገራችን ላይ፣ ነገርን ነገር አንስቶት የመጣ ጉዳይ ላይ አስተያየት የምሰጠው ጉዳዩን ለቋንቋ ምሁራን በጥያቄ መልክ፣ በ‹‹እባካችሁ አስረዱን›› ዓይነት አቤቱታና ልመና ለመምራትና ለማቅረብ እንጂ፣ የማውቀው ነገር በጭራሽ የለም፡፡ እንዲያው በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አስገብቼ እግረ መንገዴን የማክለው ‹‹ማብራሪያ›› ቢጤ ነገር ቀደም ሲል የጠቀስኩትን ክስና ውንጀላ ለማስታወቅ እንጂ፣ የእንቆቅልሹን ትርጉምና ማብራሪያ ለመስጠት አይደለም፡፡ ይልቁንም ደግሜ ደጋግሜ የማሳምነው ‹‹ተማሪ ነኝ አልገባኝም፣ የምታውቁ አስረዱኝ!›› እያልኩ፣ የጨነቀው የጠበበው ሰው ሆኜ ነው፡፡

በአጭሩ ወደ እዚህ እግረ መንገዳዊ ጉዳይ ልመለስ፡፡ ኢትዮጵያችን ፖለቲካ ውስጥ የተለያየ አቋምና አመለካከት ይዞ እሱንም በይፋ አውጥቶ ገልጾ ተነጋግሮ፣ ቂም ሳይዙ መለያየት፣ ለጥላቻ ፖለቲካ ሳይዳረጉ በወዳጃነት፣ በጓደኝነት፣ በባልንጀራነት ተመልሶ መገናኘት የተለመደ አይደለም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለውጥና ሽግግሩ ከጀመረ በኋላ፣ የፖለቲካ ፀበኝነትን ለማዳከም፣ የጠላትነት ፖለቲካን ለመገላገል፣ የፖለቲካ ቡድኖች በጠላትነት መፈራረጃቸው እንዲሟሽሽ ለማድረግ፣ በጭፍን ጥላቻና ቅዋሜ ውስጥ መንፈላሰስ የፈቀደውን ፖለቲካዊ መሬት ለማጥበብ የሚደረገው ትግል ከተጀመረ፣ ኋላም ጥቃትና ክህደት ከደረሰበት በኋላ (የሌላውን ቋንቋ ጉዳይ አላውቅም) በአማርኛ መናገር፣ የአማርኛ ቋንቋን አቅምና ሀብት በሙሉ መጠቀም አለመግባባትን የሚፈጥር፣ በክፉ ነገር የሚያስጠረጥር፣ የሚያስከስስ፣ የሚያወነጃጅል አደገኛ የፈንጂ አካባቢ እንደ መግባት የሚቆጠር ሆኖ አረፈው፡፡ ‹‹የጥላቻ ንግግር›› ወይም ‹‹ሄት ስፒች›› የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ‹‹የሥራ ላይ/ውስጥ አደጋ/ሕመም›› ወይም ‹‹Occupational Diseases/Hazard›› ሆነ፡፡

የቋንቋ ባለሙያዎች ሲነግሩን እንደምንሰማው በግዑዝ ነገሮችና በእንስሳት ተምሳሌት አማካይነት ሐሳብን መግለጽ በመላው ዓለም ቋንቋዎች የተመለደ ነው፡፡ አገራችን ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር በእሳት መጫወት እየሆነ መጣ፡፡ እንዴት እንደ ተጀመረ ባላውቅም በተለይም ከ‹‹ቀን ጅብ›› ንግግር ወዲህ እንዲህ ያለ ንግግር ‹‹አደገኛ›› እየሆነ መጣ፡፡ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተደረገ ዝግጅት ግጥሟን በ(ቀጥታ) ቴሌቪዥን ያሰማች አንዲት ወጣት ገጣሚን፣ የጥላቻ ፖለቲካችን ‹‹አዋረደችን›› ብሎ ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ አወገዛት፡፡

መሰንበቻችንንም በተለይም በጦርነቱ አንድ ዓመት መዳረሻ ዝክር አካባቢ ኮርፖሬት ሚዲያው በሙሉ ማለት ይቻላል የጠቅላይ ሚነስትሩን ‹‹ጠላቶቻችንን በቆፈሩት ጉድጓድ እንቀብራለን›› ንግግርን፣ የጥላቻ ንግግር ራሱ ‹‹ማነሳሳት›› በአካሉና በዛቱ አድርገው አቀረቡት፡፡ ‹‹በቆፈሩት ጉድጓድ መቀበር አይቀርም›› የሚል ተራ ተረት ባለበት አገር፣ በቆፈሩት ጉድጓድ ይቀበራሉ ማለት፣ ‹‹ከሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው›› በጭራሽ ተለይቶ በማይታይበት አገርና ቋንቋ፣ የትምህርትና የዕድሜ ደረጃ ሳይለይ እነዚህን ተረቶችና ምሳሌዎች (በቆፈሩት ጉድጓድ መቀበር አይቀርም፣ ፌንጣ ብትቆጣ እግሯን ጥላ ሄደች፣ ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ) ለተማሪዎቻችን በምናስተምርበት አገር፣ ለምን ይህ ንግግርና አባባል የእነዚህ ሚዲያዎች ‹‹ጮማ›› ወሬ ሆነ? አይገባኝም፣ አልገባኝም፡፡ ምሁራንና ባለሙያዎች ያስረዱናል የምለውም ይህንኑ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የፌስቡክ ኩባንያ ራሱ ‹‹አሉባልታ ወይም ክስ ወይም ጥቆማ ሰምቶ፣ ጥቆማም ክስም የቀረበበትን ‹‹ደንበኛ›› መልስ መስማት ሳያስፈልገውና በሌለበት ውሳኔ ሰጥቶ ያነሳውና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ነው የተባለው ፖስት፣ በሲኤንኤኗ ቤኪ አንደርሰንና በእኛዋ ቢልለኔ ሥዩም መካከል በተደረገው (ያልተስተካከለ የአዛዥና የታዛዥ ዓይነት ሜዳ ላይ) ግብግብ እንደሰማሁትና እንዳየሁት፣ ‹‹We will bury this enemy with our blood and bones and make the glory of Ethiopia high again.›› የሚለው ነው፡፡ 

በእኔ ግምት (አንተ ምን አግብቶህ፣ በማታውቀው ጉዳይ ትዘባርቃለህ ቢባል ተገቢ መሆኑን እንደማውቅ መንደርደሪያ አድርጌ) አማርኛ ሲበዛ ፊሊጣዊ አነጋገር የተትረፈረፈበት ቋንቋ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህንንም አሁንም የምናረገው ሲሉ የሰማሁትን ነው፡፡ ባለሁለት ቅጽ የአማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት (ልዩ/የተለየ መዝገብ ቃላት) በ1990 (እ.ኤ.አ.) ያዘጋጁት እንዲሚሉት፣ አማርኛ እጅግ በጣም ሲበዛ የአነጋገር ፈሊጥ ያየለበት ቋንቋ ነው፡፡ ‹‹Amharic is a highly idiomatic language›› ይላሉ፡፡ የመዝገበ ቃላቱ አዘጋጆች ይህንንም ያብራራሉ፣ በምሳሌም ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሞተሩ አርዳችሁ ተቀቡኝ እንጂ አልነሳም አለ›› ይባላል፡፡ ምን ማለት ነው? ይህንን ለማስረዳት ምን ያህል መከራ እንደሚዩ/የእንግሊዝኛው ማብራሪያ ራሱ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ እንዳለ ላቅርበው፣ ‹‹The motor absolutely refused to start (lit. slaughter me, – besmear yourselves with me E.I.P. My blood] but I will not start.››

በዚህ መዝገበ ቃላት ውስጥ የተካተቱትን ቃላትና ሐረግ ለመፍታት፣ ለማስረዳት ስለታየው ‹‹መከራ›› ከላይ ጠቆም አድርጌያለሁ፡፡ አማርኛ ለማያውቅ ሰው፣ አማርኛ አውቆም አማርኛ መነጋገሪያው፣ ቋንቋው፣ ማሰቢያው ሆኖም አማርኛን ለማያውቅ ሰው ‹‹የቀን ጅብ››፣ በቆፈሩት ጉድጓድ መቅበር ነገር ለምን ከሁሉም በላይ፣ ከእኛ ከአገር ቤቶቹ አብዛኞቹ ይልቅ የውጭ ሰዎችን አንጫጫ? ለምን እንዲህ ያለ አባባል የከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ንድፍ (ብሉ ፕሪንት) ተደርጎ ተወሰደ? ወይስ ልንዋጋው የሚገባ ‹‹የዘፈን ዳር ዳሩ›› ነው? ጥያቄ ያቀረብኩላቸው የቋንቋ፣ ወዘተ ባለሙያዎች ቢያንስ ቢያንስ አደራ ይመስለኛል፡፡

ወደ ጉዳዬ ልመለስ፡፡ ኖቬምበር ያው ዝም ብሎ ሌላ ተራ ወር ነው? ወይስ ሌላ የተለየ ወር የነገር መነሻ የተደረገ ጥያቄ ነው፡፡ ኖቬምበር ወር ከጥቅምት 22 ቀን እስከ ኅደር 22 ድረስ የሚዘረጋው የአንድ ወር ጊዜ ነው፡፡ ኖቬምበር ማለት ‹‹ችግር›› ውስጥ የገባሁት ብዙዎቹ የምናያቸውና ያጋጠሙን ጉዳዮች በዚህ ወር ልዩ ገጠመኞች በመሆናቸው (ወይም ስለተባሉ) ነው፡፡

አስቀድሜ የማነሳው በወሩ መጀመርያ ላይ ኖቬምበር 4 (በእኛ ጥቅምት 24) ‹‹የተከበረው››ን ቀን ነው፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር፣ መላው የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ የሚባለውና ሚዲያዎቻቸው ያከበሩት ግን ዓብይ አህመድ በትግራይ [አማፂያን] ላይ ጦርነት ያዘዙበት ቀን፣ ስለዚህም ጦርነቱ የተጀመረበት ቀን አድርገው ነው፡፡ መላው ሚዲያ በኢትዮጵያ ላይ አብሮ፣ ውሸት ተናግሮ እንዲህ ቢልም የኢትዮጵያ ሀቅ፣ በዚያን ዕለት የተፈጸመው ጥቃት፣ ክህደትና ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት አደጋ ላይ የመጣል ሴራ ግን እዚህ ሁሉ የውሸት ወሬና አስረሽ ምቺው ውስጥ ተደብቆ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ በዚያን ቀን የሆነችውን፣ የደረሰባትን ወረራ፣ ጥቃትና ክህደት ሆንኩኝ ብላ በዓለም ሸንጎ የተናገረችውን ግን ወደፊት አንድ ቀን የሳማንታ ፓወር፣ ወይም የሱዛን ራይስ፣ ወይም የብሊንከን፣ ወይም የባይደን የልጅ ልጅ ልጆች ሥልጣን ይዘው ከወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ጋር ሲነጋገሩ፣ በ2021 እና በ21ኛው ምዕተ ዓመት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የዋለችውን ግፍ፣ የሠራችውን በደል፣ ሴራ አውስተው በጉዳቸው ሲያፍሩና ሲሸማቀቁ እስክንሰማ ድረስ አንጠብቅም፡፡ የካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ዩኤንዲፒ ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ የላኩት ማስታወሻ ዛሬም ዘለዓለምም የሚታወሰው እውነቱን በመግለጽ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱም የድበቃ ሴራ የተሠራበት በመሆኑ ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናዥ (Tibor Nagy) ከዚህ ቀደምም በተለያየ አጋጣሚ የሰጡትን ምስክርነት ደጋግመው በማስረዳት፣ ለፍራንስ 24 ጦርነቱን የጀመረው ሕወሓት ነው ብለው አረጋግጠዋል፡፡ ጦርነቱን የጀመረው ሕወሓት ነው ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹Much like the American civil war was started by the South Carolina militia attacking Fort Sumter›› ነው ያሉት፡፡

ዓብይ አህመድ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት ብቻ፣ ‹‹ከመሬት ተነስተው››፣ ዝም ብለው፣ ጦር ጥራ ብለው በወሰዱት ዕርምጃ ጦርነቱ መነሳቱን፣ አንድ ዓመቱንም ‹‹ማክበሩን›› ያላንዳች ዓውድ፣ ያላንዳች የጀርባ ታሪክ በወሩ መጀመርያ ሳምንት በመደበኛም፣ በተለይ በተሠራ ልዩ ፕሮግራምም በኢትዮጵያ ላይ ያበሩትና የተባበሩት ሁሉ ሌላው ቀርቶ ከላይ የጠቀስናቸውን ዓይነት የዩኤንዲፒ አስተዳዳሪና የአሜሪካ ባለሥልጣን ቲቦር ናዥ እንደ እነዚህ ያሉ ምስክርነቶች መኖራቸውን እንኳን እግረ መንገዳቸውን አይገልጹም፡፡ ወይም ውሸት፣ ሐሰት፣ ቅጥፈት መሆናቸውን አረጋገጥን ብለው ተራ የሙያ ሥራ ግዴታቸውን አይወጡም፡፡

ይህንን ከሚያደርጉትና ሙያ አድርገው ከሚኮሩት መካከል አንዱና በጣም የሚገርመው አልጄዚራ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ አልጄዚራ ከምድረ ኮርፖሬት ሚዲያ መካከል ነጥዬ ያወጣሁትና መታዘብ ውስጥ የገባሁት 25ኛ ዓመቱን ሲያብር ይህን ጠልቼ ተነሳሁ፣ የኮርፖሬት ሚዲያውን መረን የለቀቀ ኃፍረት የለሽ ተግባር ለማጋለጥ መጣሁ፣ ‹‹the opinion and the other opinion›› ብዬ የውሸት፣ የአድሏዊነትና የወገንተኛነትን መቃብር ፈንቅዬ ወጣሁ ስለሚል ነው፡፡ ከዝንጀሮ ቆንጆ ምንን ያማርጣል ብዬ ብልስ? ‹‹ይገባቸው›› ይሆን? አልጄዚራን ለይቼ የታለ ‹‹ሞቶ››ህ የምለውም ለዚህ ነው፡፡

አልጄዚራን ጨምሮ ሁሉም ‹‹የዝንጀሮ ቆንጆዎች›› የተረባረቡበት፣ ከአንድ ጭቃ ተጠፍጥፈው የተሠሩበትንና ከአንድ ባህር የተቀዱበትን ማንም ከማንም የማይሻል መሆኑን ደግሞ እንደገና ያረጋጡበት ሌላም ምሳሌ አለ፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጠዋት ከቤቴ ወደ ሥራ የወጣሁት፣ ረቡዕ ምሽትና በተለይም ወደ እኩለ ሌሊት አካባቢና ከዚያም በኋላ የሲኤንኤንን ድንገተኛና የተራዘመ፣ ‹‹አማፂያን የአዲስ አበባን አካባቢ ከበዋል›› የሚል ዜና እየሰማሁ፣ ጆሮዬ ነው ወይስ እነሱ ዕውን ይህን እየተናገሩ ነው? እያወሩ ነው? እያልኩ፣ ከብዙ ጊዜ በኋላና ከነጋ በኋላ ጠዋትም ይህንን ማለታቸውን፣ ማውራታቸውን ወሬ አድርገው ማቅረባቸውን፣ እንዲያውም ‹‹ምንጫ››ቸው ዲፕማሲያዊ ምንጭ መሆኑን አረጋግጬ ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡

በወሬው፣ በዜናው ላይ የተገለጸውን ኹነት (አዲስ አበባ መከበቡን) ሳይሆን ወሬውን ራሱን ‹‹በህልሜ ነው በዕውኔ›› ብዬ የተጠራጠርኩት ከሌሎች መካከል እኔም የምኖረው አዲስ አበባ ጫፍ፣ አዲስ አበባ ጠርዝ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚያን ዕለት ሲኤንኤን የቀደሰው ዜና ጀምሮ የምሰማቸው ‹‹የዓለም አቀፍ›› ሚዲያ ሁሉ አዝማች ‹‹ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ ያሉት/የተጠጉት አማፅያን›› የሚል ሆነ፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውና የተወካዮች ምክር ቤትም አዋጅ ቁጥር 1204 አድርጎ ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ ላይ ያሉትን ተቃዋሚዎች ለመግታት የወጣ ተብሎ ዜና ተሠራበት፡፡ ከረቡዕ ምሽት ጀምሮ ሐሙስ ጠዋት ድረስ የአዲስ አበባ ዙሪያ ጥምጥም በተቃዋሚዎች መከበቡን ከሁነኛ ዲፕሎማተክ ‹‹ምንጮች›› አግኝቶ ሲያሸብረን ያደረገው ሲኤንኤን፣ ሐሙስ ቀን ላይ አማፂያን የደረሱበትን ቦታ ወደ ገብረ ጉራቻ ለወጠው፡፡ ‹‹ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ ላይ ያሉ አማፂያን›› እንቅስቃሴ ግን የአገር  የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መግባት ምክንያት ሆኖ መወራቱ ቀጠለ፡፡

ከሁነኛ ምንጭ (Reliable Source – በነገራችን ላይ ሲኤንኤን ‹‹ሪሊየብል ሪሶርስ› የሚባል ፕሮግራም አለው) የተገኘው የአዲስ አበባ ዙሪያ ጥምጥም የመከበብ ዜና ግን ብቻውን ቆሞ አልቀረም፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ የዜጎቹና የሠራተኞቹ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ ጭምር እየሆነ መጣ፡፡ እንዲያውም በዓለም ደረጃ በተወራ፣ መጀመርያ ፎረን ፖሊሲ፣ ቀጥሎም እነ ሲኤንኤን ተቀባብለውና ይበልጥ ‹‹እየቆፈርን፣ ተጨማሪ እያገኘን አረጋግጠን›› እሉ እንደ ዘገቡት አሜሪካ የዲፕሎማቶቿን፣ የዜጎቿንና የሌሎችንም ኢትዮጵያውያን ከአገር/ከኢትዮጵያ በሰላም ለቅቆ መውጣት የሚያረጋግጥ፣ የሚያደራጅና የሚያግዝ ታስክ ፎርስ (ግብረ ኃይል) መቋቋሙ ከፍተኛ የደኅንነት መረጃ ተደርጎ ተዘገበ፡፡ ‹‹ደረጃ አራት የጉዞ ማስጠንቀቂያ››ም ሆነ፡፡ ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሚፈልገውን ‹‹ሕዝብ›› ከትርምስ ለማዳን፣ ምናልባትም ነሐሴ ወር ላይ ካቡል አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰውን ዓይነት ችግር፣ ከችግር ይልቅ ውርደት ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል ዜናም ሆነ ‹‹እንቅስቃሴ›› በየሚዲው ቢራገብም፣ እነሆ እግዜር ይመስገን ቦሌ ኤርፖርት ስትጨነቅ ስትጠበብ አላየንም፡፡ ሁሉም መንገዶች ‹‹ወደ ቦሌ የሚወስዱ›› አልሆኑም፡፡

በምንሰማውና በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው የጦርነት ትጋት (War Effort) አካል በሆነው ‹‹ዜና›› መሠረት በፍጥነት በመገስገስ ላይ ያሉት የአዲስ አበባን መንገድ ጭምር ይዘው እየመጡ ያሉ አማፂያን ብቻ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ እኩል ምናልባት በባሰ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እየዘቀጠ ነው፡፡ ‹‹The situation quickly deteriorates›› የሚለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ነው፡፡   

ኖቬምበር የጀመረው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ከኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የጋራ የምርመራ ቡድን አጥንቶ ባቀረበው የጥቅምት 24 ቀን 2014 (ኖምበርን 3) ሪፖርት ዜናና በይዘቱም ጭምር ነው፡፡ በጣም በጉጉት ሲጠበቅ የቆየ ሪፖርት ነው፡፡ ‹‹ሲጠበቅ የቆየ›› ሲባል ብዙ ጊዜ ወሰደ፣ ‹‹እሺ ነገ›› ውስጥ ገባ፣ በቀጠሮ ሲራዘም ቆየ ማለት እንዳይመስልብኝ በከፍተኛ አጽንኦት መግለጽ ይገባኛል፡፡ ይህ በጭራሽ አልሆነም፡፡ ሲጠበቅ የቆየ የተባለበት ምክንያት ‹‹ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ›› የሚባለውም የተለያዩ የዚህ ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ ዓይነት አቦዳደኖችም፣ በነፍስ ወከፍ መንግሥታት ዘንድም ጭምር ያለ ልዩነት የኢትዮጵያው ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ ምርመራውን ለማድረግ መስማመታቸውን ተቀብለውና መርቀው፣ ውጤቱንም የሚጠብቁ መሆናቸውን አንድ ላይ ገጥመው ይፋዊ መግለጫ መስጠታቸውን ለማመልከት ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ራሱ በአፕሪል 22 ፕሬስ ስቴትመንት በደስታ ተቀብሎታል፡፡ ተቃውሞስ አላጋጠመውም ወይ ከተባለ በይፋ ዋነኛውና ምናልባትም ብቸኛው ተቃዋሚ፣ አሁንም ድኅረ ሪፖርት ጭምር ሕወሓት ብቻ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የራሱ የመንግሥቱ አካል ነው ብቻ ሳይሆን፣ የኢሰመኮን ኮሚሽነር ራሳቸውን በግል ጭምር በመቃወም ሕወሓት የምርመራውን ገለልተኝነት አላምንም ብሎ ተቃውሟል፡፡     

ከምርመራ ውጤቱ በኋላስ? እዚህ ጽሑፍ ውስጥ እኔ ስለይዘቱ አላወራም፡፡ ስለይዘቱም አልመሰክርም፡፡ ይህንን ከማድረግ ፈንታ ሪፖርቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ‹‹ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ›› የሚባለው በአጠቃላይ፣ የተለያዩና ጉዳይዩ ይመለከተናል ብለው በቅርብና በጥብቅ ሲከታተሉ፣ እንዲያውም ከሪፖርቱ ውጤት በፊት በየአጋጣሚው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሪፖርቱን ቀድመው ብይን ሲሰጡ ስሞታውን፣ ሐሜቱን፣ ውንጀላውን፣ ስም መስጠቱን፣ መፈረጁን ራሱን የክሱ ማስረጃና ውሳኔም ጭምር አድርገው ሲፈርጁ የነበሩት ሁሉ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ድኅረ ሪፖርት የሰጠውን ይፋዊ ምላሽ በአጭሩ ማቅረብ ከሁሉም ነገር ይገለግላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በዕለቱና ወዲያውኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት የሰጠው መልስ በገዛ ራሱ በዚህም ዓይነት ጨለማ፣ ‹‹ኖቬምበር›› ወርና ሁኔታም ውስጥ ቢሆን ኢትዮጵያ፣ ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች የመንግሥት ‹‹አያያዝ››ና ደንታ ወደ ሻል ያለ ዓለም መንቀሳቀሱን ወይም መላወሱን የሚሳይ ነው፡፡ የመንግሥት ምላሽ በሪፖርቱ ላይ የማይስማማባቸው ጉዳዮች መኖሩን ገልጾ የሪፖርቱን ባለሙያዊነት አድንቆ፣ ለሪፖርቱ ዓላማና መደምደሚያም እንደሚገዛ አስታውቆ መልስ መስጠቱ በአገራችን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ታሪክ ውስጥ የሚመዘገብ ብርቅና ድንቅ ነገር ነው፡፡ ተራና የዘወትር የሥራ ተግባርና ግዳጅ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርቱን በ‹‹ጉጉት›› ሲጠብቅ የነበረው ዓለም አቀፋዊው ማኅበረሰብም ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገበት ቀን አንስቶ እስከ ኖቬምበር 6 (ጥቅምት 27) ድረስ ባሉት ቀናት፣ አካትቶና አጠናቆ አስተያየቱንና ምላሹን ሰጥቷል፡፡ አንዳቸውም ክፉ ነገር አልተናገሩበትም፡፡ በተለያዩ መድረኮች በሴኪዩሪቲ ካውንስል የመጨረሻ ስብሰባ ጭምር ስለጋራ ሪፖርቱ የተለያየ አስተያየት ሲሰጥ የሰማን ቢሆንም፣ እቃወመዋለሁ ያለ አንድም ‹‹ጎበዝ›› ወይም ‹‹የጎበዝ አለቃ›› አላየንም፡፡ የሁለቱ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት የጋራ ሪፖርት ዋነኛው ዓላማና ግብ በአጠቃለይ እውነቱን ማውጣት፣ ሳይጠየቁ መቅረትን መከላከከል፣ ወዘተ ቢሆንም፣ በዚህ ሪፖርት ውስጥ እኔ በበኩሌ ያየሁት እንዲህ ባለ የአገር የፈተናና የበረታ የትግል ወቅትም ውስጥ ቢሆን ለውጡና ሽግግሩ፣ በአጠቃላይ ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ጨርሶ አለመክሸፉን የሚሳዩ ምስክርነቶችና ድሎች አደባባይ ወጥተው መታየታቸው ነው፡፡ ከአንድ ፓርቲ የበላይነት መዳፍ የመውጣት ሒደትን ለውጥ ብሎ የተነሳውን ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታን ኢትዮጵያን እውነትም ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የማድረግ ቅድመ ሁኔታ ነው ብሎ ዴሞክራሲን የማደላደል ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ንቅናቄ ፍሬ እያስመዘገበ ዓይተናል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ እንኳን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የመሰለ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ መቃን ውስጥ ሠልፍ ይዞ፣ አደራ ተቀብሎ (ለዚያውም አደራውን ራሱ አመንጭቶ) እውነቱን ለዓለምም ለራሱ መንግሥትም ጭምር በድፍረትና በነፃ መናገር የሚችል ተቋም መገንባት ችለናል፡፡ በዚህ ትግልና ሒደት ውስጥ አንካሳነት ቢኖር ኖሮ፣ ኖቬምበር 8 (ጥቅምት 29) ለተሰበሰበውና ኢትዮጵያን አጀንዳው ላደረገው የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ በ‹‹አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ›› ሕግ ዓለም ምን እንሆን ነበር?  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...