Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኅብረት ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከ731 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን መሰብሰቡን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅብረት ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የ2013 ሒሳብ ዓመት ከሁለቱም የመድን ዘርፎች ከ731.3 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን መሰብሰቡንና በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ከ169.9 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ካፒታሉን በእጥፍ ለማሳደግ ያቀረበው ሐሳብ ደግሞ ይተላለፍ ተባለ፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ ሐሙስ ኅዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከሰበሰበው ጠቅላላ የዓረቦን መጠን ውስጥ 660 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ ነው፡፡

ሕይወት ነክ ካልሆነው የሰበሰበው ዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የተባለ አፈጻጸም ያስመዘገበው በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው ዓረቦን መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሙሉዓለም ብርሃኔ ባቀረቡት ሪፖርታቸው ላይ እንደገለጹትም፣ በሒሳብ ዓመቱ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የሰበሰበው የዓረቦን መጠን 71.3 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የዓረቦን ገቢ ከ2012 የሒሳብ ዓመት ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ56 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱም የመድን ዘርፎች ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ኩባንያው 731.3 ሚሊዮን ብር ገቢ ያስገኘለት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ የዓረቦን ገቢ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ22.4 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት ነው፡፡

በ2012 የሒሳብ ዓመት ከሁለቱም የመድን ዘርፎች የተሰባሰበው የዓረቦን መጠን 597.4 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የ2013 ገቢው ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ የታየበት እንደሆነ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተትሏል፡፡

የካሳ ክፍያን በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት የካሳ ክፍያ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡

የቦርዱ ሊቀመንበር በሪፖርታቸው እንደጠቆሙት፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ሕይወት ነክ ባልሆነው የመድን ዘርፍ አጠቃላይ የተከፈለው የካሳ ክፍያ በ2012 ዓ.ም. ከነበረው 56 በመቶ በ2013 ወደ 61 በመቶ አድጓል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ በካሳ ክፍያ ያዋለው ወጪም 288.2 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡

የኩባንያው የካሳ ክፍያ ምጣኔ በዚህ ያህል ደረጃ ለማደጉ በዋናነት የተጠቀሰው የተሽከርካሪ አደጋ መብዛትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ነው፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን በ15 በመቶ በመጨመር 169.9 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የተጣራ የትርፍ መጠኑ ደግሞ 145.1 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ አመልክቷል፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ ከኦፕሬሽን ሥራ ገቢው ባሻገር ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እያገኘ ስላለው ገቢም ተነግሯል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩም ‹‹ኩባንያችን በሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት የአራት ሕንፃዎች ባለቤት ለመሆን የቻለ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ የኪራይ ገቢ ያገኘ ከመሆኑም ባሻገር ለኪራይ ክፍያ ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለማዳን ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡

ከተለያዩ ኢንቨስት ካደረገባቸው ዘርፎች ያገኘነውን ገቢ በተመለከተም ከኅብረት ባንክ አክሲዮን ማኅበርና ከኢትዮጵያ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር ካሉት ኢንቨስትመንቶች የትርፍ ድርሻ ያገኘ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ከሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ካሉት አክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡

የኅብረት ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታል 473 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ እደደረሰ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት 501 ባለአክሲዮን የያዘው ኅብረት ባንክ 434 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ 54 ቅርንጫፉና አገናኝ ቢሮዎች አሉት፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በሐሙሱ ጠቅላላ ጉባዔው ካፒታሉን በእጥፍ ለማሳደግ ያቀረበውን ሐሳብ ባለአክሲዮኖች ለቀጣይ ዓመት ይተላለፍ በማለት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

በዕለቱ ከኢንሹራንሱ የዳይሬክተሮች ቦርድ በቀረበ ሐሳብ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ብር ወደ አንድ ቢሊዮን ብር እንዲያድግ የሚል ነበር፡፡

የሥራ አመራር ቦርዱ ካፒታሉን ለማሳደግ ያቀረበው ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የብር ምንዛሪ አቅም እየቀነሰ በመምጣቱና አሁን ያለው የኩባንያው ካፒታል ከውጭ ምንዛሪ ተመን አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱን ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የኩባንያው የዓረቦን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱና ወደ ጠለፋ መድን ዋስትና የሚሰጥ ወይም በኩባንያው አቅም የሚያስቀረው የሽፋን መጠን ዕድገት ጋር የተመጣጠነ የካፒታል አቅም እንዲኖረው ለማስቻል ካፒታሉን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብሎ ስላመነ ነበር፡፡

ኩባንያው ትርፋማነቱን ከፍ ለማድረግና የኢንቨስትመንቱን ውጤት ለማረጋገጥ እንዲችል፣ በቦሌ መድኃኔዓለም 1,000 ካሬ ሜትር፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 8,000 ካሬ ሜትር፣ ለተጎዱ መኪናዎች ማቆያ ቦታ መግዛትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል የተጠየቁ ቦታዎች ላይ ግንባታዎችን ለማከናወን በዝግጅት ላይ ስለሆነ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የካፒታሉ ማደግ ያስፈልጋል የሚልም እምነት በመያዝም ነበር፡፡

ሆኖም አብዛኛው ባለአክሲዮን ሐሳቡን ለከርሞ እንምከርበት በማለት የካፒታሉን መጠኑ በ500 ሚሊዮን ብር ይቀጥል ብሏል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀል ይዞት የተነሳው የካፒታል መጠን 8.6 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች