Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የትርፍ ምጣኔ ከዕጥፍ በላይ ማደጉ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ዓ.ም. የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አገኛለሁ ብሎ ካቀደው ገቢ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ገቢ ማግኘቱንና የትርፍ ምጣኔውንም ከዕጥፍ በላይ ማሳደጉ ተገለጸ፡፡

በባንኩ ታሪክ በአንድ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ከፍተኛ የሆነ ትርፍና ገቢ የተመዘገበበት ተደርጎ በተወሰደው በዘንድሮው የሩብ ዓመት አፈጻጸም፣ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 6.8 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ መቻሉን ከባንኩና ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች የይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኤጀንሲው እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ካቀደው በላይ 146 በመቶ አፈጻጸም የተመዘገበበት ነው፡፡ እንዲሁም በገቢ ደረጃም በሩብ ዓመቱ ያገኘው ገቢ ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ 148 በመቶ አፈጻጸም የታየበት ነው፡፡

የሩብ ዓመቱ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይም ከፍተኛ የሆነ ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነ የሚያመለክተው ባንኩ፣ በ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ገቢ 3.1 ቢሊዮን እንደነበር አስታውሷል፡፡

የዘንድሮ የሩብ ዓመት ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ3.5 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

ከኤጀንሲው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዕቅዱ በታች ውጤት ያስመዘገበው በውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ነው፡፡ ባንኩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ዝቅተኛና በተፈለገው ልክ ያልተጓዘ ስለመሆኑ ሲገልጽ የነበረ ሲሆን፣ በዘንድሮው የመጀመርያ ሩብ ዓመትም ያቀደውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻለም፡፡

ባንኩ በሩብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ አቅዶ የነበረው 707.9 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ማሳካት የቻለው 613.4 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አንፃር የዕቅዱን 87 በመቶ ያሳካ መሆኑን ያሳያል፡፡

ነገር ግን የሩብ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ11 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን መረጃው ያመለክታል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2013 ዓ.ም. በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አትርፎ የነበረው 3.1 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ በ2014 ዓ.ም. የመጀመርያው ሩብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ እጅግ ከፍተኛ ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ የትርፍ መጠኑ ከቀዳሚው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከዕጥፍ በላይ ወይም ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዕድገት የተገኘበት እንደሆነ ከወጣው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ኤጀንሲ የ2013 ዓ.ም. የመጀመርያው የሩብ ዓመት የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማትን አፈጻጸም ሪፖርት ባደረገበት ወቅት፣ በኤጀንሲው ሥር የሚገኙ ሦስቱ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በጥቅል ከታክስ በፊት አትርፈውት የነበረው የገንዘብ መጠን 3.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር መጥቀሱ ይታወሳል፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2014 ዓ.ም. የመጀመርያው ሩብ ዓመት ትርፍ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ የባንኩ አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ ያደገበት ምክንያት በተመለከተ ኤጀንሲው የሰጠው ማብራሪያ ባይኖርም፣ በኢንዱስትሪም ደረጃ በዚህን ያህል የትርፍም ሆነ የገቢ ዕድገት የተመዘገበበት ጊዜ እንደሌለ ግን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ2013 ዓ.ም. የመጀመርያው ሩብ ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገኛለሁ ያለውን ገቢም ሆነ የትርፍ መጠን በዕቅዱ ልክ ያሳካ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን ይህንን ታሪክ በተለየ ሁኔታ ቀይሮ ውጤቱን ከዕጥፍ በላይ ማሳደግ ችሏል፡፡

የዘንድሮ አፈጻጸሙን በዚህን ያህል ደረጃ ማሳደጉን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም፣ የዘንድሮ የሩብ ዓመት ትርፉ በባንኩ ከፍተኛ የሚባል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የባንክ ገበያ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ በመጓዝ ላይ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2013 ዓ.ም. ሙሉ የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 20.3 ቢሊዮን ብር አትርፎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡         

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች