Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትተጫዋቾች በ‹‹ሃይማኖታዊ መልዕክት›› ምክንያት ቅጣት ተላለፈባቸው

ተጫዋቾች በ‹‹ሃይማኖታዊ መልዕክት›› ምክንያት ቅጣት ተላለፈባቸው

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በሦስተኛው ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ላይ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ ተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ምክንያት የተባለው ደግሞ ተጫዋቾች በጨዋታ ላይ ሃይማኖታዊ መልዕክት አሳይተዋል በሚል እንደሆነ በቅጣት ውሳኔው ላይ ተመላክቷል፡፡

ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው መልዕክት አስተላልፈዋል ተብለው የዲሲፕሊን ውሳኔ ከተላለፈባቸው ተጫዋቾች መካከል፣ የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ተጨዋች የሆነው ናትናኤል ገብረ ጊዮርጊስ አንዱ ሲሆን፣ ተጨዋቹ በሦስተኛው ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 4 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ፣ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ከዋናው መለያ ውስጥ ባለው መለያ ላይ ያሳየውን መልዕክት ተከትሎ በቀረበበት ሪፖርት መሠረት የ3,000 ብር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ተጨዋች የሆነው ፍፁም ጥላሁን፣ ቡድኑ መከላከያን 3 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ፣ ደስታውን ከውስጥ በለበሰው መለያ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው መልዕክት በማሳየቱ እንደ ፋሲል ከተማው ተጫዋች ተመሳሳይ የ3,000 ብር ቅጣት የተላለፈበት መሆኑ የውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ይፋ አድርጓል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ በርካቶች ቅጣቱን ያሳለፈው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደሆነ በማድረግ ተጫዋቾቹ ላይ የጣለው ቅጣት ትክክል እንዳልሆነ እየገለጹ ይገኛል፡፡

በዚህ ጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ ውሳኔው ሙሉ በሙሉ ፌዴሬሽኑን እንደማይመለከት፣ በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ ሲታይ ግን ከግንዛቤ እጥረት የመጣ እንደመሆኑ አክሲዮን ማኅበሩ ተገቢውን መረጃ ለስፖርት ቤተሰቡ ሊያስተላልፍ የሚገባው ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስፖርቱ ጋር ተያይዞ የተደነገጉ መመርያና ደንቦች፣ ስፖርቱ የቆዳ ቀለምን ጨምሮ ከማናቸውም ፓለቲካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ፍፁም የፀዳ መሆን እንዳለበትም ቢደነግግም፣ ከተፈጻሚነቱ ጋር ተያይዞ በሁሉም የዓለም ጫፍ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ በተለይም በታላላቅ አገሮች በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ጫና የሚደረግባቸው አትሌቶች የዓለም አቀፉን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በማድረግ ከለላ ሲደረግላቸው ብዙም አይስተዋልም፡፡

ክፍተቱን ተከትሎ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ እንዲሁም በሌሎችም ስፖርቶች አትሌቶች ፖለቲካዊ ይሁን ሃይማኖታዊ መልዕክቶች በተለያዩ መድረኮች ሲያሳዩ፣ ሲስተላልፉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን ታላላቅ አትሌቶችም ይህንኑ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ዕውን ሲያደርጉት ታይቷል፡፡

በተያያዘ ዜና የውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብና የሲዳማ ቡና ክለብ ኃላፊዎች አቶ ኡቴሳ ኡጋሞና አዲሱ ቃሚሶ፣ በጨዋታ መሃል ‹‹የውኃ መጠጫ ፕላስቲክ ወርውረዋል፣ ድርጊቱም የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ነው፤›› በሚል እያንዳንዳቸው የ25 ሺሕ ብር ቅጣት ውሳኔ መጣሉን ይፋ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለነበረበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተቋርጦ የሰነበተው ፕሪሚየር ሊግ እሑድ ይጀመራል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...